ለቱሪዝም ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት በተግባር ቁመና

በአስር ዓመቱ ብሔራዊ የልማት እቅድ ትኩረት ከተሰጣቸው የምጣኔ ሃብት ምሰሶዎች መካከል አንዱ የቱሪዝም ዘርፉ ነው። ኢትዮጵያ በቱሪዝም ያላት ከፍተኛ አቅም ሲታሰብ ለዘርፉ ልማት ትኩረት መስጠቷ የሚያስገርም አይሆንም። ጠቃሚው ቁም ነገር ለዘርፉ ልማት የተሰጠው ትኩረት በተግባር የሚተረጎምበት አሠራር ነው።

ቱሪዝም ዘመናዊ፣ የተቀናጁ፣ በእውቀት ላይ የተመሠረቱ እንዲሁም ትጋትን የሚሹ አሠራሮችን ይፈልጋል። አስተማማኝ ሠላም፣ በዘርፉ በቂ እውቀትና ልምድ ያለው ባለሙያ እና ቀልጣፋ የመሠረተ ልማት አገልግሎት የቱሪዝም እድገት ምሰሶዎች ናቸው። በሀገር አቀፍ ደረጃ ለቱሪዝም የተሰጠው ትኩረት እነዚህን ግብዓቶች ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይገባል።

እንደሚታወቀው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (COVID-19) እና በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተፈጠሩ የፀጥታ መደፍረስ ችግሮች በሀገሪቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድረው እንደነበር ይታወሳል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የጎብኚዎችን እንቅስቃሴ በመገደብ፣ በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማትንና ግለሰቦችን ከሥራ ውጭ በማድረግ ዓይነተ ብዙ ግለሰባዊና ተቋማዊ ምስቅልቅሎች እንዲፈጠሩ አድርጓል።

የቱሪዝም ዘርፉ በወረርሽኙ እየተፈተነ በነበረበት ወቅት የተከሰቱት ግጭቶች (በተለይም የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት) ደግሞ የዘርፉን ችግር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርገውበት ነበር። ወረርሽኙም ሆነ ጦርነቱ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ እንቅፋት ከመሆናቸው በተጨማሪ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች እንቅስቃሴም ገቷል።

በእነዚህ ፈተናዎች ምክንያትም የቱሪዝም ዘርፉ ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት የሚያበረክተው አስተዋፅዖ በእጅጉ ተቀዛቅዞ ቆይቷል። ለአብነት ያህል ‹‹ኮቪድ-19›› ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ከጥቂት ወራት በኋላ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ 98 በመቶ ኪሳራ ውስጥ መግባቱን የኢትዮጵያ ሆቴል ባለሙያዎች ማኅበር ገልፆ ነበር።

በሌላ በኩል ጦርነቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲቋረጥ ከማድረጉ በተጨማሪ፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት እንዲወድሙም ምክንያት ሆኗል። በጦርነቱ የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ፣ በርካታ የቱሪዝም አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ ሙዚየሞችና ሌሎች የታሪክና የባህል ሀብቶች ወድመዋል፤ ተዘርፈዋል። ይህም ሀገሪቱ በተለይ ከውጭ ጎብኚዎች ማግኘት የሚገባትን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ አሳጥቷታል።

በኮሮና ቫይረስ እና በሠላም እጦት ችግሮች ክፉኛ ተፈትኖ የቆየው የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ በአሁኑ ወቅት ካጋጠሙት ፈተናዎች ለመውጣት በትልቅ ትግል ላይ ይገኛል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት መቀነስ እና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥትና በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት የቱሪዝም ዘርፉ እንዲነቃቃ አድርገዋል።

ለጉብኝትና ለሥራ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የውጭ ሀገራት ዜጎችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ቁጥር ጨምሯል። ዘርፉን ለማነቃቃት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከብሔራዊ በዓላት ጋር ተያያዥ ተደርገው የተተገበሩ እቅዶች የጎብኚዎች ፍሰት እንዲጨምር በጎ አስተዋፅዖ አበርክተዋል።

በአጠቃላይ በሥራ እድል ፈጠራና በውጭ ምንዛሪ ግኝት ሀገራዊ ምጣኔ ሀብቱን የሚደግፈው ይህ ዘርፍ፣ ሀገሪቱ በዘርፉ ካላት አቅም አንፃር በሀገራዊ ምጣኔ ሀብቱ ላይ ያለው ሚና የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም እድገቱ መሻሻል እያሳየ ይገኛል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት የተገነቡና ለመገንባት በእቅድ የተያዙ የ‹‹ገበታ ለሸገር››፣ ‹‹ገበታ ለሀገር›› እና ‹‹ገበታ ለትውልድ›› ፕሮጀክቶች ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከቱ ይገኛሉ።

እነዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ በላቀ ትጋትና በከፍተኛ ጥራት ተገንብተው የተጠናቀቁ ታሪክን፣ የአካባቢ ነባራዊ ሁኔታዎችንና የወደፊት ራዕይን አስተሳስረው የያዙ ማራኪ የቱሪስት መናኸሪያዎች፣ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥሉት ብዙ ዓመታት ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ አቅም ሆነው ይኖራሉ። እነዚህ ለሀገር በጎ ገፅታ የሚያላብሱ የቱሪስት መናኸሪያዎች የታሰበላቸውን ዓላማ እንዲያሳኩ ሠላም የማስፈን፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል የማፍራት እና መሠረተ-ልማቶችን የማሟላት ተግባራት ከፍተኛ ትኩረት ሊያገኙ ይገባል።

ቱሪዝም ሠላምን በእጅጉ የሚሻ ዘርፍ በመሆኑ ሠላምን በማስፈን የቱሪስቶች ፍሰት በቋሚነት እንዲጨምር እንዲሁም የወደሙ የቱሪዝም ተቋማት መልሰው እንዲገነቡ በማድረግ የቱሪዝም ዘርፉ ያሳየውን መነቃቃትና እድገት ቋሚ/ዘላቂ ማድረግ ያስፈልጋል።

በሠለጠነ የሰው ኃይል የማይመራ የቱሪዝም ዘርፍ ስኬታማ ሊሆን እንደማይችል በመገንዘብ ዘርፉን በብቃት ሊመሩና ሊያስተዳድሩ የሚችሉ በቂ እውቀትና ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎችንና አመራሮችን መመደብ ይገባል።

መሠረተ-ልማቶች ያልተሟሉላቸው የቱሪስት መዳረሻዎች የተሟላ የቱሪዝም አገልግሎትን ማቅረብ እንደማይችሉ በመረዳት ሀብትን አቀናጅቶ በመጠቀም የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን ማሟላት አስፈላጊ ተግባር ነው። በአጠቃላይ ወቅታዊ ሁኔታዎች (የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መቀነስ፣ የሠላም ስምምነቱ፣ … ወዘተ የፈጠሯቸውን መልካም አጋጣሚዎች በሚገባ በመጠቀም በተደራራቢ ፈተናዎች የተጎዳውን የቱሪዝሙን ዘርፍ ማነቃቃት ይገባል።

በተለይም እንደ ሀገር እምቅ የቱሪዝም አቅም ኖሯቸው ተገቢውን ትኩረት ያላገኙ በርካታ መንደሮች በመለየት፣ በማልማትና በማስተዋወቅ፣ ለዘርፉ ተጨማሪ አቅም የሚሆኑበትን እድል መፍጠር ተገቢ ነው። የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መንደር ተብለው የተመረጡት ወንጪ፣ ጮቄ (ሙሉ ኢኮ ሎጅ) እና ሌጲስ የየአካባቢያቸውን ማኅበረሰቦች ባሕል ጠብቀው የቱሪስቶች ቀልብ ይበልጥ ይስቡ ዘንድ፣ አካባቢዎቹ ጥበቃ ሊደረግላቸውና መሠረተ ልማት ሊሟላላቸው ይገባል። ወንጪ በ‹‹ገበታ ለሀገር›› ፕሮጀክት ማራኪ የቱሪስት መዳረሻ ሆኖ ግንባታው በመጠናቀቁ ቀን ወጥቶለታል፤ ለሌሎቹ መንደሮችም ተመሳሳይ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።

ከዚህ በተጨማሪም ለቱሪዝሙ ዘርፍ መነቃቃት እድል የሚፈጥሩ ተጨማሪ መልካም አጋጣሚዎችን በብቃት መጠቀምም ይገባል። በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ደማቅ በሆኑ ሥርዓቶች ታጅበው የሚከወኑ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ኹነቶች የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡና ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ገቢ የሚያስገኙ በመሆናቸው ለቱሪዝሙ ዘርፍ መነቃቃት እድል ይፈጥራሉ። መሰል ክዋኔዎችን በስፋት በማስተዋወቅና ባሕልና ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ በማከናወን ለቱሪዝሙ ዘርፍ ማነቃቂያ ማድረግ ያስፈልጋል።

በተደራራቢ ችግሮች ምክንያት ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች የገጠሙት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ከገጠመው ችግር እንዲወጣ አስቸኳይ የማገገሚያ ሥራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር በጦርነት/ግጭት ምክንያት ጉዳት ያስተናገደውን ማኅበረሰብ በማነቃቃት የማኅበረሰቡ እንቅስቃሴ በፍጥነት እንዲያገግም ማድረግ፣ የወደሙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መልሶ ማልማት፣ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ማበረታታት፣ በቀጣይም የቱሪዝም ዘርፉ የኢንሹራንስ አገልግሎት እንዲኖረው ማድረግ … ያስፈልጋል። በአጠቃላይ ለቱሪዝም ዘርፍ የተሰጠው ብሔራዊ ትኩረት፣ ውጤት እንዲያስገኝ የታቀደውን ለውጥ እውን ማድረግ በሚያስችል የተግባር ቁመና መተርጎም አለበት!።

ወንድይራድ ሰይፈሚካኤል

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You