አልባሷን ጨምሮ የአንገቷ፣ የእጇ፣ የእግሯ፣ በግንባሯ ላይ ሳይቀር የተጠቀመቻቸው ጌጣጌጦች በጨሌ ያሸበረቁ ናቸው:: የጥበብ ሥራው ያስደንቃል:: በተለያየ የጨሌ ቀለማት የተዋበው አልባስ ከእንስሳት ቆዳ የተዘጋጀው ነው:: በተለያየ የአፈር ቀለም አይነቶችም ፊትና የተለያየ የሰውነት ክፍልን ማስዋብም በደቡብ ምዕራብ በና ፀማይ አካባቢ የተለመደ ነው:: እንዲህ ባለው መዋቢያ፣ ጌጣጌጥና የባሕል አልባሳት ተውባ ያገኘናት አሎ ላሌ የጥቁር ቆንጆ፣ ጥርሶችዋ እንደ ወተት የነጡ ቁመተ ለግላጋ ናት::
ወይዘሮ አሎ ላሌ ከወገቧ በታች በጨሌ ያጌጡ ሦስት የፍየል ቆዳዎች ነበር የለበሰችው:: አንዱ ቆዳ ቃሺ፣ ሁለተኛው ደግሞ ኮረባ፣ ሦስተኛው ቡዳአይስ በሚል በአካባቢው ይጠራል:: ፍየሉም ለአልባሱ በተሰጠው ስያሜ ቅደም ተከተል መሠረት ነው እርድ የሚከናወነው:: አልባሱም ሆነ ጌጣጌጦቹ የእርስዋ የእጅ ጥበብ ውጤቶች ናቸው:: ቆዳውን ፍቃና አለስልሳ ነው ያዘጋጀችው::
በሌላ ሰው ማሠራት በአካባቢው አልተለመደም:: ለገበያም አይቀርብም:: ሁሉም እንደፍላጎቱና እንደምር ጫው ሠርቶ ነው የሚጠቀመው:: ስለተሠራው ጌጣጌጥ የጓደኛ ምክር መጠየቅ ግን የተለመደ ነው::
የሚዘጋጁት አብዛኞቹ አልባሳት ከጉልበት በላይ አጠር ያሉ ናቸው:: በከተማው ሚኒስከርት እንደሚባለው አይነት፤ ወይዘሮ አሎ እንዳጋጣሚ ዘመናዊውን ልብስ ቀላቅላ ለብሳ ነው እንጂ ከወገብ በላይ ሰውነት አይሸፈንም:: የአካባቢው ባሕል ነው:: ዘወትርም የሚለበሰው በዚህ መልኩ ነው::
አሁን ላይ ግን የጨሌ ዋጋ መጨመር አቅማቸውን እየተፈታተነው ነው ትላለች ወይዘሮ አሎ:: ጨሌውን ነጋዴዎች ከኬኒያ ሀገር ገዝተው የሚያቀርቡትን ነው የሚጠቀሙት:: በጨሌ ዋጋ መወደድ ምክንያትና የኢኮኖሚ አቅምም ለመፍጠር በተለይ ደግሞ ወደ አካባቢው የሚሄዱ ቱሪስቶች የባሕል አልባሱንም ሆነ ጌጣጌጦቹን የተለያዩ የአካባቢው መገለጫ የሆኑ የባሕል ቁሶች ለመግዛት ፍላጎት ሲያሳዩ ወይዘሮ አሎ ፍላጎታቸውን ለማሟላት እርስዋም ገቢ ለማግኘት እየሠራች ወደ ገበያ ለመውጣት ሞክራ ነበር:: ገበያ ላይ ማውጣት በአካባቢው ያልተለመደና እንደነውርም የሚታይ በመሆኑ በፖሊስ በቁጥጥር ሥራ ውላ እንደነበር አስታውሳለች::
የገበያ ክልከላው ግን አልቀጠለም:: አንዲት የአካባቢው ሴት ከሚመለከታቸው የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመምከር ከብዙ ትግል በኋላ ለስኬት ማብቃት በመቻሏ ሴቶች ተደራጅተው የአካባቢያቸውን ባሕል የሚያንፀባርቁ የእጅ ጥበብ ውጤቶችን ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበት እድል ተፈጠረ::
ወይዘሮ አሎ ቀድሞም ፍላጎቱ ስለነበራት ፍቃድ በማግኘቷ ደስታዋ ወደር አልነበረውም:: ከእርስዋ ጋር ስድስት ሆነው በመደራጀት ነበር ወደ ሥራው የገባችው:: ላለፉት 17 ዓመታትም የእጅ ጥበብ ሥራ ውጤታቸውን ለገበያ በማቅረብ ላይ ነች:: ሥራውን እንደጀመሩ ጥሩ ገበያም እንደነበረው ወይዘሮ አሎ ትገልጻለች::
በተለይ ለጉብኝት ወደ አካባቢው የሚሄዱ የውጭ ሀገር ዜጎች ናቸው በብዛት የሚገዟቸው:: የተሻለ ገቢም የሚያገኙት የውጭ ዜጎች ሲገዟቸው ነው::
ወይዘሮ አሎ እንደምትለው፤ ኑሮአቸው የተመሠረተው በግብርናና በከፊል አርብቶአደር በመሆኑ ምርት ደርሶ ለገበያ ቀርቦ ገንዘብ እስኪገኝ ለገበያ የሚያቀርቡት የእጅ ጥበብ ውጤቶቻቸው ከፍተኛ የኑሮ ድጎማ ያደርጉላቸዋል:: ቤታቸው እንዳይጎድልና ለልጆቻቸውም አስፈላጊ ነገሮችን ለማሟላት ረድቷቸዋል::
ሥራው ኑሮአቸውን ለመደጎም አቅም የፈጠረላቸው ቢሆንም፤ ሥራውና ገቢው ግን የተመጣጠነ አይደለም:: በእጅ የሚሠራ በመሆኑ ለሥራ የሚጠቀሙበት መርፌ ጥንቃቄ ካልተደረገ ጣቶችን ይጎዳል:: ዓይንም ያደክማል:: በመሆኑም ከባድ ነው:: የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸው ገበያ አግኝተው የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ ሥራቸውን አይቶ የተለያየ ድጋፍ የሚያደርግላቸው አካል አለመኖሩም የጠበቁትን ያህል ጥቅም እንዳያገኙ አድርጓቸዋል::
በዚህ የተነሳም አራቱ የማኅበር አባላቶቻቸው አብረዋቸው ሊቀጥሉ አልቻሉም:: የተቀሩት ሁለቱም ቢሆኑ የቤተሰብ ኃላፊ በመሆናቸው ቤት በመምራት ሙሉ ጊዜያቸውን ለገበያ ለሚያውሉት ሥራ እየሰጡ አይደለም:: ውጤታማ ለመሆን እንደሥራ ይዞ ማስቀጠል ያስፈልጋል::
ወይዘሮ አሎ ስለአካባቢያቸው የትዳር ሁኔታ በተለይም ጎጂ ልማዳዊ ከሆኑ ድርጊቶች ጋር በተያያዘ እንድትነግረን ጥያቄ ባቀረብንላት ጊዜ በተለይም ከጋብቻ ጋር የተያያዘውን ‹ኡ› በማለት ነበር የጫናውን ከባድነት ለመግለጽ የሞከረችው:: በአካባቢው ላይ በተለያየ አካላት፤ ትምህርት እየተሰጠም ሊለወጥና ሊቀረፍ ያልቻለ ነገር ብላ ያነሳችው በሴቷ ላይ የሚደርሰው ጫና ከፍተኛ መኖሩን በማንሳት ነው::
እርስዋ እንዳለችው ሴት ልጅ የነገ ዕጣ ፈንታዋ ሳይታወቅ በጥቆማ በሚመጣ ባል ትዳራለች:: የወደፊት ባሏ አምባር ያደርግላታል:: አምባር ማድረግ ባይችል የከብት እበት ይቀባታል:: ልጅቷ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የእከሌ ሚስት ተብላ እየተጠራች ከቤተሰብዋ ጋር ሆና እንድታድግ ይሆናል:: ወደ ባሏ ቤት የምትሄደው እንደሁኔታው ቢሆንም ከ13 ዓመቷ ጀምሮ ግን ይጠበቃል::
ወይዘሮ አሎም በዚህ ዕጣ ፈንታ ውስጥ ነው ያለፈችው:: የ12 አመት ታዳጊ ሆና ነበር ያገባቸው:: ስድስት ልጆች ወልዳለች:: ወይዘሮ ላሌ ገና በመውለድ እድሜ ክልል ውስጥ በመሆኗ መውለዱ ሊቀጥል ይችላል:: ከባሕሉ ውጭ መሆን ስላልቻለች እንጂ ከተማ ውስጥ የመኖር እድሉን አግኝታ ነበር:: እራስዋን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአካባቢውን ልጃገረዶች ካለእድሜያቸው እንዳይዳሩ መታደግ ትችል ነበር:: ከቤተሰብና ከባሕል ውጭ ለመሆን ድፍረቱን አላገኘችም:: አባቷ በሕይወት አለመኖራቸው ደግሞ የበለጠ አቅም እንዳይኖራት አደረጋት:: የአሁኑ ባሏ ጠልፎ ነበር የወሰዳት::
ወደ ትዳር ከገባች በኋላ ስለነበረው ሁኔታም በተለይም ከፍቅር ጋር የተያያዘውን ጉዳይም ‹‹ምን ታረጊዋለሽ ወደድሽም ጠላሽም አንዴ ገብተሽበታል:: እማንስ ጋር ሄደሽ አቤት ትያለሽ፤ ወንዱ ነው መብት ያለው::›› ነበር ያለችው::
ወይዘሮ አሎ ልጆችዋ እርስዋ ባለፈችበት መንገድ እንዳያልፉ፤ እርስዋ ያጣችውን የትምህርት እድል እነርሱም እንዳይገጥማቸው፤ የትምህርት እድልም እንዲያገኙ በግሏ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነች ነው ያጫወተችን:: ሁለት ልጆችዋም በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ በማገልገል ላይ እንደሆኑ፣ አንደኛውም የፖሊስ አባል መሆኑን፣ ከአንዲት ሕፃን በስተቀር የተቀሩት ልጆችም በተለያየ የትምህርት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አጫውታናለች::
በበና እና አካባቢው በሴቷ ፍላጎት ላይ ያልተመሠረተ ያለእድሜ ጋብቻ ትልቁ ፈተና ቢሆንም፤ የቤት ውስጥ የሥራ ጫናውም ቢሆን ከዚህ ያልተናነሰ ነው:: ማልዳ ከመኝታዋ ተነስታ ከበረት ውስጥ ከብቶችን በማውጣት ታሰማራለች:: ለአባወራውና ለልጆች ምግብ ለማዘጋጀት ማጀት ትገባለች፤ የማጀቱ ሥራ እንዳለቀ ደግሞ ውሃ ለመቅዳት ከመኖሪያዋ አካባቢ ርቃ ትሄዳለች፤ በእርሻ ሥራ ወቅት ደግሞ ወደ ማሳ በመሄድ በጉልጓሎ፣ በማረም፣ የእርሻ ሥራ ታግዛለች:: ለበና ሴት የመኝታ ሰዓት ካልሆነ እረፍት የሚባለው ቅንጦት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል:: ይሄ የእለት ተእለት ተግባሯ ነው:: አባወራው ከቤቱ ውጭ ለቀናት የሚያሳድረው ነገር ቢገጥመው የከብቱን፣ የቤቱንና የልጆቹን ጉዳይ ለሚስቱ ጥሎ ጉዳዩን ፈጽሞ ነው የሚመለሰው::
ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ሴቷን ተጠቂ ከሚያደርጉ አንዱ የሴት ልጅ ግርዛት ነው:: በዚህ በኩል በበና እና ሐመር እንደስጋት እንደማይነሳ ነው ወይዘሮ አሎ የገለጸችልን:: በአካበቢው በጣም ዘግናኝ የሆነው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ሕጻናትን መግደል ነው:: አንዲት ሴት ከጋብቻ ውጭ ፀንሳ ቀርቶ አግብታ ከትዳር አጋሯ እንኳን የፀነሰችው ልጅ የሚገደልበት ሁኔታ ልማድ ሆኖ እስከ ዛሬ ይፈጸማል:: ወይዘሮ አሎ እንደነገረችን፤ አንዲት ሴት አግብታ ከመፀነሷ በፊት የወር አበባ ማየት አለባት::
የወር አበባ ከማየቷ በፊት ከፀነሰች ደግሞ ለባሏ ማሳወቅ፣ ባለቤቷ ደግሞ ሁኔታውን ለሀገር ሽማግሌዎች መንገር ይኖርበታል:: ባሕሉ ስለሚያዝ መፈጸም ግድ ነው:: የተፀነሰው ልጅ እስኪወለድ ጠብቃ እንዲገደል የምታደርግ የምትከታተል ሴት በመኖርዋ ልጁ በምንም ሁኔታ እንዲያድግ አይደረግም:: ጠብቃ ይሄን የምትፈጽመዋ ሴት ደግሞ የቅርብ ዝምድና ያላት ናት:: አክስትም ልትሆን ትችላለች::
ከዚሁ ጋር ሌላው በባሕሉ መፈጸም ያለበት ደግሞ ጋብቻው እንደተፈጸመ በመጠጥ መልክ የተዘጋጀ ነገር ሴቷ መውሰድ ይጠበቅባታል:: ወንዱ ከማግባቱ በፊት ከከብት መዝለል ይጠበቅበታል:: ከከብት የሚያዘልለው በአካባቢው ዳሪ ተብሎ ይጠራል:: ያገባች ሴት እዚህ ዳሪ ቤት ሄዳ እዛው በማደር ነው በዳሪው የተዘጋጀውን የሚጠጣ ነገር የምትወስደው:: በባሕሉ መሠረት ከቅጠላቅጠልና ሥራስር የተዘጋጀውን እንድትጠጣ የሚደረገው ሌሎች ሰዎች ከመኝታቸው ሳይነሱና የምትጠጣበትም እቃ ሌሎች ሳይነኩት መሆን አለበት:: ከዚያ ዕቃ ውስጥም በእጇ ላይ እየተደረገላት ነው የምትጠጣው:: እጇ ላይ እያደረገች የምታጠጣት ዳሪ የተባለችው ሴት እቃውን መሬት ላይ ጥላ እንድትረግጠው ታደርጋታለች:: እቃውን ረግጣ ከሰበረችው ልጅ ተፈጥሯል ተብሎ ይታሰባል:: ይሄ ሳይደረግም ልጅ ከተፀነሰ እንዲያድግ እድል አይሰጠውም::
ዕጣ ፈንታው ሞት ነው:: እናትም የዘጠኝ ወር ድካሟ ከንቱ ነው የሚሆነው:: የበና ፀማይ ሴት ኑሮ ጥሩ ነው የሚባለው ብዙ ከብቶች ያሉት ባል ማግባቷ ብቻ ነው::
ላሌ ቀልጠፍ ያለች ሴት ሆና ነው ያገኘናት:: በቋንቋም በአማርኛ ነው የተግባባነው:: ግን ትምህርት አልተማረችም:: ምክንያቱን ጠየቅናት፤ ቃቆ የምትባል ከተማ ላይ እንደተወለደችና እድገቷም እዛ በመሆኑ ቋንቋም ለመማር እድሉን እንዳገኘች ነው ያጫወተችን:: እርስዋ እንዳለችው ትምህርት መማር እየፈለገች ግን አባቷ ባለመፍቀዳቸው አልተማረችም::
በአካባቢው ላይ ያለው የባሕል ተፅዕኖ፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት፣ ትምህርት የማግኘት ሁኔታና ሌሎችም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች አሁንም እንደቀድሞው እንደቀጠለ ባይሆንም ጨርሶ ባለመቀረፉ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ ወይዘሮ አሎ ትናገራለች:: መሻሻልን ለማምጣት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአካባቢው አስተዳደርና ሌሎችም እያደረጉ ያለው እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑንና ቀጣይ ትውልድም ጥሩ ነገር ይገጥመዋል ብላ ተስፋ አድርጋለች::
ወይዘሮ አሎ እንዲህ ስለአካባቢዋ ያጫወተችን በቅርቡ 19ኛው የአርብቶአደሮች ቀን ‹‹አርብቶአደርነት የምሥራቅ አፍሪካ ኅብረቀለም›› በሚል መሪ ቃል በመዲናችን አዲስአበባ ከተማ ላይ በተዘጋጀበት ወቅት ነው:: ወይዘሮ አሎ በዚህ መርሐግብር ላይ መሳተፏ ካስደሰታት ነገር አንዱ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ አርብቶአደሮች የአካባቢያቸውን ልማት፣ ባሕል፣ ቋንቋ በሚያሳይ መልኩ ዝግጅት አድርገው ይዘውት መምጣታቸው፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ከተለያየ አካባቢ የመጡ ሰዎች በአንድ አዳራሽ ውስጥ በመደናነቅ፣ ሰላምታ በመለዋወጥ፣ አንድነትና አብሮነታቸውን ማየት መቻሏ እንደሆነ ነው የገለጸችው::
‹‹ኢትዮጵያውያን ለካ ፍቅራቸው እንዲህ የበዛ ነው እንድል ነው ያደረገኝ›› የምትለው ወይዘሮ አሎ በሚሊኒየም አዳራሽ ውስጥ በተዘጋጀው መርሐግብር ያየችው የኢትዮጵያውያን አንድነት እንዲቀጥል ምኞትዋ ነው:: እንዲህ አንድነት ያለው ማኅበረሰብ እርስ በርስ መገናኘት ከመፋቀር ውጭ ጥላቻ ፈጽሞ ሊኖር እንደማይችል ነው የተናገረችው:: ለሀገር ሰላምም በጎ ተመኝታለች::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም