አብሮ የማደግ ዘመኑን የሚዋጅ ራዕይ

የቀይ ባሕር አካባቢ ከፍተኛ የዓለም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚደረግበት፣ በርካታ መርከቦች በስዊዝ ካናልና በባብኤል ማንዴብ ሸርጦች የሚተላለፉበት ሀገራት ትኩረት ሰጥተውት ፀጥታው የተረጋጋ እንዲሆን የሚሠሩበት፣ የአካባቢው ሀገራት በባሕር መተላለፊያው ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ የሚፈልጉበት ዓለም አቀፍ መተላለፊያ ነው ::

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በቀይ ባሕር ላይ ይዞታ የነበራትና ቀይ ባሕርንም ስታዝበት የኖረች ሀገር ነች:: 1ሺ800 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን የቀይ ባሕር ይዞታ በቁጥጥሯ ስራ ያኖረችና ለወጭና ገቢ እቃዎች ሁለት ወደቦች የምታስተዳድር ሀገር ነበረች:: ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ውጪ ቀይ ባሕርንም ከኢትዮጵያ ውጭ ማሰብ አይቻልም ነበር:: የኢትዮጵያን ማደግ በማይፈልጉ ኃይላት ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እንድትርቅ ተደርጓል:: ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ምንም ድርሻ እንዳልነበራት ሆን ተብሎ በተሰራጨው ትርክት ሀገሪቱ እና ቀይ ባሕር ተቆራርጠው ላለፉት ሦስት አስርተ ዓመታት ኖረዋል::

የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆን በሕዝቦቿ ላይ ሊፈጥር ከሚችለው የሥነልቦና ተፅዕኖ ባሻገር ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ፈጥሯል፤ እየፈጠረም ነው። የኢትዮጵያን ክብርና ዝና ዝቅ ከማድረግ ባሻገር የልብ ስብራት ይዞ መጥቷል:: ለበርካታ መሠረተ ልማቶችና ድሕነትን ለመሻገር ሊውል የሚችል ከ1ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ ለወደብ ለማዋል ተገድዳለች:: ይህም የሸቀጦች ዋጋ እንዲንርና የኑሮ ውድነትም እንዲባባስ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል::

በኢትዮጵያ አዲስ የመንግሥት ለውጥ ከመጣ ጀምሮ በትኩረት ከሠራባቸውና ለውጥ ካመጣባቸው ጉዳዮች ይኸው የባሕር በር ጥያቄ አንዱ ነው:: መንግሥት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለዘመናት ቁጭት ፈጥሮ የነበረውን የባሕር በር ጥያቄ በመመለስና ስብራትን በመጠገን ታሪካዊ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል:: ላለፉት ሦስት አስርተ ዓመታት ያህል ፈርሶ የቆየውን የባሕር ኃይል እንደገና በማደራጀት ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል እንዲኖራት አድርጓል::

ከዚሁ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ ከ33 ዓመታት በኋላ የባሕር በር የምታገኝበት አማራጭ በማፈላለግ ተስፋ ሰጭ መንገድ ላይ ይገኛል:: ሰሞኑን ከሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር የሚገኝበትን መግባቢያ ሰነድ (Memorandum of understanding) መፈራረሙም የዚሁ ተጨባጭ እውነታ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው ::

ይህ የመግባቢያ ሰነድ ሲተገበር አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣና ኢትዮጵያም በቀጣናው ላይ አለኝ የምትለውን የባለቤትነት ጥያቄ መልስ እንዲገኝ በር የሚከፍት እንደሆነ ይታመናል:: ቀጣናዊ ሰላምን በማስፈን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተረጋጋ እንዲሆን አስተዋፅዖው ከፍያለ ነው::

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠው ለጎረቤት አገሮች ነው:: በተለይም ለቀጣናዊ ግንኙነት ከፍያለ ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጠበቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲኖራት መልካም አጋጣሚዎችን የሚያሰፋ ነው::

የኢትዮጵያ ልማት በአስተማማኝ መሠረት የሚቆመው የኢትዮጵያ የውስጥ ሠላምና መረጋጋት ሲረጋገጥ እንደሆነ እና ይኸው ሰላምና መረጋጋት የሚጸናው ደግሞ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሰላማዊ ግንኙነትን አጽንቶ ማስቀጠል ሲቻል ነው:: ይህንን ታሳቢ በማድረግ በወዳጅነት እና ከዚህ በሚመነጭ አብሮ በማደግ በጎ ህሊና የተቃኘ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ጀምራለች::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ ከሚጎበኟቸውና ትኩረት ከሚሰጧቸው ሀገራት መካከል ግንባር ቀደሞቹ የጎረቤት ሀገራት ናቸው:: ለዚሁ ማሳያ የሚሆነው፤ ወደ ሥልጣን በመጡ በጥቂት ቀናት ውስጥ የመጀመሪያ የውጭ ጉዟቸውን ያደረጉት ወደ ጎረቤት ሀገር ጅቡቲ ነው::

ጅቡቲ ለኢትዮጵያ 95 በመቶ የወደብ አገልግሎት የምትሰጥ መሆንዋ፤ ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚው መስክ ከፍተኛ ትስስር ያላቸው ከመሆናቸው አንጻር ከጎረቤት ሀገራት ጅቡቲን ማስቀደማቸው ተገቢ ነበር ማለት ይቻላል:: ከዚያም በመቀጠል ያቀኑት ወደ ሱዳን ነው። በዚያም በቀውስ ውስጥ የነበረችውን ሀገር ወደ ተሻለ መረጋጋት የሚወስድ የአስታራቂነት ሚና ተጫውታለች:: በመቀጠልም ለ20 ዓመታት ያህል በጦርነት ስጋት ውስጥ የቆዩትን ኢትዮጵያንና ኤርትራን በማስታረቅና ግንኙታቸውንም ወደ ተሻለ ደረጃ በማድረስ ቀጣናዊ ዲፕሎማሲው ወደ ከፍታ እንዲሸጋገር የመሪነቱን ሚና ተጫውተዋል::

ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ብሎም በአፍሪካ ደረጃ ሠላም አስጠባቂ ኃይል ሆና የበርካታ የጎረቤት ሀገራትን ሠላም ለማስጠበቅ ብዙ ዋጋ ከፍላለች:: በሶማሊያና በሱዳን በርካታ የኢትዮጵያ ወታደሮች የሀገራቱን ሠላም ለማስከበር የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ላይ ይገኛሉ:: ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እንደገለጹትም የሶማሊያን ሕዝብ ሠላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሕይወታቸውን ገብረዋል::

ከዚሁ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትስስሮሽ በሚፈጥሩ የጋራ በሆኑ የባቡር፣ የመንገድና የወደብ ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ የነቃ ተሳትፎ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ለቀጣናው የኃይል አቅርቦት ዋና ምንጭ በመሆን ትልቅ አስተዋፅዖ እያደረገች መሆኑም ጎልቶ እየተነሳ ነው:: ስንዴንም ለጎረቤት ሀገራት ጭምር ኤክስፖርት በማድረግ ያመረተችውን በማቃመስ ላይ ትገኛለች::

ከህዳሴ ግድብ እና ከግልገል ግቤ ሦስት የምታመነጨውን ኃይል ለጅቡቲ፤ ለኬኒያ፤ ለሱዳንና ለደቡብ ሱዳን በመላክ ለቀጣናው ሀገሮች ዘላቂ የሆነ ታዳሽ ኃይል በማቅረብ ላይ ትገኛለች:: ለጅቡቲም የመጠጥ ውኃ በማቅረብ ጭምር ለቀጣናዊ ትስስሮሽ ጉልህ አስተዋፅዖ እያደረገች ነው:: ከሰሞኑ ለጅቡቲ ሕዝብ በቀን ስትልከው የነበረውን 5ሺ ኪዩቢክ ሊትር ውሃ ወደ 100 ሺ ኪዩቢክ ሊትር በማሳደግ አጋርነቷን በተግባር አረጋግጣለች ::

ብዙዎች እንደሚስማሙበት፤ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ያላቸውን የተፈጥሮ ፀጋዎች አቀናጅተው መንቀሳቀስ ከቻሉ፤ ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅም ሆነው መውጣት ይቻላሉ። ዘላቂ ሠላም እና ዳቦ ለቸገረው የአካባቢው ሕዝብ የተሻሉ ነገዎችን በቀላሉ መፍጠር እንደሚችሉም ይታመናል::

የኢትዮጵያ አስተማማኝ እና ቀልጣፋ የወደብ አገልግሎትና የባሕር በር ለማግኘት እያቀረበ ያለው ጥያቄና ጥያቄው የተገዛበት አስተሳሰብ ይህንን እውነታ በተጨባጭ መሬት ለማውረድ ትልቅ አቅም ነው። ይህን ጥያቄ በበጎ ሕሊና መቀበል ነገ ላይ የሚመጣው ትሩፋት የቀጣናውን ሀገራት ሕዝቦች ነገዎች ብሩህ ማድረግ የሚያስችል ነው ።

እሳቤው ለቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች ሊኖረው ከሚችለው ስትራቴጂክ ፋይዳ አንጻር፤ አንዳንድ ጎረቤት ሀገራት፤ በተለይም ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ጉዳዩን ከአቅሙ በላይ በማስጮህ እየሄደችበት ያለው መንገድ ተገቢ ያልሆነ፤ የሀገራቱን ሕዝቦች ለረጅም ዘመናት የቆየ ወንድማማችነት የሚመጥን አይደለም ።

ሶማሊያ ላለፉት ረጅም ዓመታት፤ ባለመረጋጋትና በግጭት ውስጥ ብዙ ዋጋ እየከፈለች የምትኖር ሀገር ነች:: በእነዚህ የችግር/የመከራ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያውያን ከሶማሊያ ሕዝብ ጎን በመቆም የሕይወት መስዋዕትነት የጠየቁ አስቸጋሪ ግዳጆችን ተወጥተዋል::

ቀደም ባለው ጊዜ ‘AMISOM’ አሁን ደግሞ ‘AT­MIS’ እየተባለ በሚጠራው የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ሠላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ፤ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሠላም ጉልህ አስተዋፅዖ ስታደርግ ቆይታለች:: በዚህ ተልዕኮም አብዛኛውን የሶማሊያ መሬት በመሸፈንና ከጥቃት በመከላከል የሶማሊያ ሕዝብ በሠላም ወጥቶ እንዲገባ፤ የሶማሊያ መንግሥትም ተረጋግቶ መንግሥታዊ ሥራዎችን እንዲያከናውን በማድረግ ላይ ትገኛለች::

የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት ከመንግሥት ግንኙነት ባለፈ በጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የተሳሰረ ነው:: የሀገራቱ ሕዝቦች ዕጣ ፈንታም ተመሳሳይነት ያለው፤ አብሮ ማደግንና ተደማምጦ መጓዝን የሚጠይቅ ነው:: ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን አሁን ላይ አብሮ ለማደግ፤ ተደማምጦ ለመጓዝ ያቀረቡት ጥሪ የፍጻሜው ጅማሪ ተደርጎ የሚወሰድ ነው::

የኢትዮጵያ መንግሥት አማራጭ የወደብና የባሕር በር ጥያቄ የቀረበው በአካባቢው ላሉ ወዳጅ ሀገራት ነው። ለጥያቄው እስካሁን ምላሽ የሰጠችው ሶማሊ ላንድ ብትሆንም ዕድሉን ለመጠቀም የሶማሊያ መንግሥት ጨምሮ ሌሎች የአካባቢው ሀገራም በሩ ክፍት ነው ።

በርካታ አማራጮችን በማማተር ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግሥት የጋራ ተጠቃሚነትን መርሕ በመንተራስ ከሶማሊላንድ ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል:: ይህ ስምምነት ደግሞ ከወዲሁ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል:: በታዋቂ ሰዎች፤ በዲፕሎማቶችና በፖለቲከኞች ጭምር ተገቢነቱ እየተነገረ ነው::

በኢትዮጵያ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር ቲቦር ናዥ፤ ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የደረሱበት ሥምምነት ዘመን ተሻጋሪ ግንኙነት በመመሥረት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በር ይከፍታል ሲሉ ተናግረዋል:: አምባሳደር፤ ከሶማሊላንድ ክሮኒክል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፡- ኢትዮጵያ የወደብ አስፈላጊነትን በተመለከተ ከወራት በፊት ይፋ ያደረገችው ሐሳብ ጎረቤት ሀገራትን ተጠቃሚ ከማድረግ ያለፈ ምንም ጉዳት እንደሌለው አስረድተዋል።

የሀገራቱ ሥምምነት፡- መሠረተ ልማቶችን በጋራ ለማስፋፋት፣ የኢኮኖሚ ትስስርን ለማሳደግ፣ ሠላምና መረጋጋትን እውን ለማድረግ ብሎም የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን፤ ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የደረሱበት ሥምምነት በርካታ ደረጃዎችን ያለፈና በደንብ የታሰበበት እንደሆነ በመጥቀስ በቀጣይም አብረው ሊሠሩባቸው የሚችሉ በርካታ ስምምነቶች ሊፈጸሙ እንደሚችሉም ጠቅሰዋል።

ሥምምነቱ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን በእጅጉ ሊደግፍላት የሚችል፣ የባሕር በር የሚያስገኝ እንደሆነ፤ ለሶማሊላንድም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥና ለበርካታ ዜጎቿ ሠፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በጋራ እንዲሠሩ በር የሚከፍት መሆኑንም አመልክተዋል።

በተመሳሳይም በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ነው ሲሉ በሣህል ቀጠና የቀድሞ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛና የአትላንቲክ ካውንስል የፖለቲካ ጉዳዮች ተመራማሪ አምባሳደር ጄ ፒተር ፋም ለቢቢሲ ተናግረዋል። አምባሳደሩ፤ በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት÷ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ብዛትና የመልማት አቅም እንዲሁም ከወደብ ኪራይ ዋጋ ውድነት አንጻር በጅቡቲ ወደቦች ላይ ብቻ ጥገኛ ሆና መቀጠል እንደማትችል ከተገነዘበች ቆይታለች ያሉት ልዩ መልዕክተኛው፤ ስምምነቱ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን ነባራዊ ሁኔታዎች ያገናዘበ፣ በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ መሆኑንም አስረድተዋል። የቀጣናውን አካባቢ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ሊያሻሽል የሚችል መሆኑን ተናግረዋል::

በፈረንጆቹ በ1960ዎቹ በርካታ ሀገራት ሶማሊላንድን በነፃና ሉዓላዊት ሀገርነት እውቅና ሰጥተዋት የነበረ መሆኑን አስታውሰው ÷ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ከሶማሊያ ግዛት ጋር እንድትቀላቀል ተደርጓል፤ ከዚያድ ባሬ አስተዳደር መፈራረስ በኋላ ሶማሊላንድ የራሷ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች በማድረግ የራሷን አስተዳደር መሥርታ ከ30 ዓመታት በላይ መቆየቷንም አስታውሰዋል።

ከኢትዮጵያ ባሻገር ሌሎች ሀገራትም በሶማሊላንድ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ነው፤ ለአብነትም የእንግሊዝ ኩባንያዎች ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ዱባይ ፖርትስ ኩባንያ ጋር በመሆን ቢሊዮን ዶላሮችን በማውጣት በበርበራ ወደብ ልማት ላይ እየተሳተፉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You