ሰላም ናፍቆን እንዳይቀር! በአዲስ አቅጣጫ የተዘጉ  የሰላም ደጆቻችንን እንክፈት

የሰላም ጥያቄ ከሕልውና ጥያቄ ጋር እኩል ዋጋ ያለው ነው፡፡ የሰው ልጅ ሕልውናውን በተለያዩ መንገዶች ሊያረጋግጥ ይችላል፤ እንደሰላም ግን የመኖር ዋስትና የሚረጋገጥበት አጋጣሚ የለም። እንደ ሀገር ሰላም ባጣንባቸው የጦርነት ዓመታት ውስጥ የደረሰብንን የሕይወት መጥፋትና የአካል መጉደል እናውቀዋለን፡፡ ማኅበራዊና ስነልቦናዊ ጫናው እንዳለ ሆኖ ብዙ ነገራችንን በመንጠቅ ለአዲስና ለማይለመድ የሕይወት ተግዳሮት የሚዳርግ የሕይወት ፈተና ነው፡፡

የሰላም እጦት መቆሚያ የለውም፡፡ ሰላም ሀገር የሚሰራ፣ ትውልድ የሚያቆም የአንድነትና የመጽናት ምሳሌ እንደሆነ የሚጠፋው አይኖርም፡፡ በተቃራኒው የሰላም እጦት ደግሞ መቆሚያ የሌለው፣ ከታሪክ ጋር አብሮ የሚዘከር፣ ከትውልድ ጋር አብሮ የሚተላለፍ የበቀልና የቂም የመገፋፋትም አረንቋ ነው፡፡ ለዚህ ምሳሌ እንዲሆነን በሀገራችን በተለያየ ጊዜ የተነሱትን ግጭቶች እና ይዘዋቸው የመጡትን መዘዝ ማስታወሱ ይበቃል፡፡

በሰፋና በገዘፈ አብሮነት ውስጥ እኔነትን አስርጸን በተዛነፈ ትርክት በውንብድና የቆምነው ትላንት ላይ በተነገረን ውደ ዛሬ ባመጣነው የሀሰት ትርክት ነው፡፡ የወንድማማችነት ግፊያ ማንንም ፊተኛ እንደማያደርግ ሲነገረን ያደግን ነን፡፡ ‹ወንድሙን ታግሎ የጣለ ጀግና አይባልም› እየተባልን ቂምና በቀልን በሚሽር የአብሮነት መንፈስ የመጣን ነን፡፡ ኢትዮጵያ በሌለችበት የከረረ የብሄር እሳቤ ጨቅይተን አደበዘዝነው እንጂ ስርዐቶቻችን ከየትኛውም ሕገመንግስት በላይ በአብሮነት አዋህደው ያኖሩን ነበሩ፡፡

ከመነሻችን ጀምሮ ኢትዮጵያዊነት ከማንነት ገዝፎ የታየበት የታሪክ ስርዐት አልነበረንም፡፡ በአብሮነት የረገጥነው ሰርጠ ዳና ኢትዮጵያዊነትን ኩሎ ፍቅርን ያተመ እንደሆነ ታሪክ ማገላበጡ ብቻ በቂ ነው፡፡ በየትኛውም ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አውድ ፊት ሀገር ቀድማ እኛ ስንከተል ዛሬን ያየን ሕዝቦች ነን፡፡ ይሄን በመሰለው ብዙሀነት ጸንሶ በወለደው የአብሮነትና የመተሳሰብ ባሕልና ስርዐት ዘመን አሳልፈናል፡፡

አሁናዊ ትርምሳችን ከስልጣኔ ሳይሆን ከስይጥንና ስለመመንጨቱ አንድ ጊዜ ማሰቡ ብቻ በቂ ነው። ስልጣኔ ሰላም ተኮር አስተሳሰቦችን በማራመድ እና ተነጋግሮ በመግባባት የሚያምን የአካላዊና የአእምሮአዊ ስብጥር እንደሆነ ከገባን ቢቆይም ለሰላም ዋጋ ስንከፍል ግን እንብዛም አንታይም፡፡ እዚም እዛም የተፈጠሩ አለመግባባቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የእኛ እጆች አሉበት፡፡ ችግሮቻችን እኛ የፈጠርናቸው ስለሆኑ ነው ማስቆም ያልተቻለው፡፡

ከችግር ፈጣሪነት ተላቀን ለሰላም የሚሆን የሞራል ልዕልና ስንገነባ ነው ተነጋግረን የምንግባባውም ሆነ ተግባብተን የጋራ ስርዐት የምናቆመው፡፡ መልካም አንደበት ብዙ ሕይወትን ማዳን እንደሚችል፤ ነውረኛ አንደበት የብዙ ጥፋት ምንጭ መሆኑ አይቀርም፡፡ አሁን አሁን በአፎቻችን ሀገር ስለማዳን፣ ትውልድ አንድ ስለማድረግ ከመናገር ይልቅ፤ ድምጽ ማጉያ በጨበጥን ቁጥር የሚቀናን ስለሌላው ክፉ ማውራት እየሆነ መጥቷል፡፡ መድረክ ፊት በቆምን ቁጥር ሌላው የሌለበትን የብቻ ዓለም በመፍጠር ራስወዳድነትን የምንሰብክ ሆኗል፡፡ ይሄን መሰሉ ያልተገራ አካሄድ ለሀገራችን ሰላም እጦት ተጨማሪ ቤንዚል ሆኖ ትውልዱን እየበላው ነው፡፡

ከዛሬ ወደነገ የሚሻገር ለዘላቂ ሰላምና አብሮነት መሰረት የሚሆን የእርቅና የተግባቦት አቅጣጫ ያስፈልገናልም፡፡ ፈረንጆች ‹ከፍጥነት አቅጣጫ ይበልጣል› ይላሉ፡፡ ልብ ብለን ካስተዋልን አብዛኞቹን ሀገራዊ ተግዳሮቶቻችንን ከዚህ እውነታ ጋር ማያያዝ ይቻላል፡፡ ለማደግ፣ ለመሰልጠን ብሎም ከድህነት ለመውጣት ጽኖ የሆነ መሻት አለን፡፡

ከተረጂነት ለመውጣት፣ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ጎን ለመቆም እቅድና ስትራቴጂ ተነድፎ እንቅስቃሴ ላይ ነን፡፡ በትምህርቱ፣ በጤናው፣ በግብርናው፣ በኢንዱስትሪው አመርቂ ውጤት ለማምጣት እንቅልፍ አጥተናል፡፡ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በዲፖሎማሲው፣ በማኅበራዊ ህይወታችን ከትላንት የተሻለ እምርታን ለማየት ትጋታችን ከፍተኛ ነው፡፡ ግን የአቅጣጫ ለውጥ አላደረግንም፡፡ ዛሬም የምንሄደው በትላንቱ ነባር አቅጣጫ ነው፡፡

”ከፍጥነት አቅጣጫ ይበልጣል ”ሲባል ልክ ባልሆነ አቅጣጫ ላይ ልክ የሆነ ውጤት አይገኝም ማለት ነው፡፡ ወቅታዊም ሆነ ነባር ችግሮቻችን የአቅጣጫ ለውጥ ባለማድረግ የመጡ መጥተውም አልሄድ ያሉ ናቸው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን በትምህርት ስርዐታችን ላይ እያየነው ያለውን ተዐምራዊ ለውጥ ነው፡፡ የትምህርት ስርዐታችን ምን ይመስል እንደነበረ መናገሩ ለቀባሪ ማርዳት ያህል ነው፡፡ ባልተስተካከለና ባልዘመነ አንድ አይነት አቅጣጫ ላይ አንድ አይነት ተማሪዎችን ስናፈራ መቆየታችንም የቅርብ ጊዜ ትስውታ ነው፡፡

በዚህም ከነበርንበት ሳንቀሳቀስ ለበርካታ ዓመታት በአንድ አይነት ሁኔታ ውስጥ ነበርን። በቅርብ በተደረገ የአቅጣጫ ለውጥ ግን አዲስ ስርዐትን እያየን እንገኛለን፡፡ የትምህርት ስርዐቱ ምንም የተለየ ነገር አላደረገም ያደረገው የአቅጣጫ ለውጥ ነው፡፡ በአቅጣጫ ለውጡም ብዙ ተስፋ የሚጣልበት ነገር እያየነው ነው፡፡ የነበረውን ሽሮ ወዳላየነውና ወዳልሞከርነው አዲስ አቅጣጫ ኃይሉን አድርጎ ለውጥ ተኮር በሆነ ትግበራ ላይ ነው፡፡

ከነበርንበት አንድ እርምጃ ፈቀቅ ለማለት ከፍጥነት ይልቅ የአቅጣጫ ለውጥ ወሳኝ ነው፡፡ በአንድ አይነት አስተሳሰብ፣ በአንድ አይነት አረዳድ እንደሀገርም ሆነ እንደግለሰብ ለውጥ ማምጣት አንችልም፡፡ በዘመናዊው ዓለም አቅጣጫ የስኬትና የድል አድራጊነት አርማ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ራሳቸውንም ሆነ ሀገራቸውን ነጻ ያወጡ መንግስታትን የመጠየቅ እድሉ ቢገጥመን የምናገኘው ምላሽ ከአዲስ አስተሳሰብና እይታ ጋር የተዛመደ መልስ ነው፡፡

ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን የቻይና እና የሕንድ ስልጣኔ ነው፡፡ ቻይናና ሕንድ የቅርብ ጊዜ ስልጣኔና ኃያልነታቸውን ከማግኘታቸው በፊት ድሀ ከሚባሉ የዓለም ሀገራት ውስጥ ቀዳሚዎቹ ነበሩ፡፡ ድንገት በታሰበ ሀሳብና በተቀየረ አቅጣጫ ግን የአዲስ ታሪክ ባለቤቶች ሆነዋል፡፡ የቻይና የስልጣኔ መነሻ ወይም ደግሞ የአቅጣጫ ለውጥ ‹አይጥ የማትይዝ ድመት ምን ትሰራልናለች? የሚል ሕዝባዊ አንድምታ ያለው ንቃትና ብርታት ነው፡፡

በዚህ ንግግር ውስጥ በተለይ ምን ”ትሰራለች? ”በሚለው ውስጥ ብዙ ሀሳቦችንና አዲስ አቅጣጫዎችን መዞ ማውጣት ይቻላል፡፡ ቻይናውያን በመሪያቸው በኩል በተወሰደ የአዲስ አቅጣጫ ለውጥ የዓለምን ግዙፍ ኢኮኖሚና ፖለቲካ፣ ስልጣኔና ቴክኖሎጂ በቀዳሚነት መሪዎች ሆነዋል፡፡

የሕንድም የምጣኔ ሀብትና የኢኮኖሚ ግስጋሴም ከዚህ እውነታ ጋር መሳ ለመሳ የቆመ ነው፡፡ የአቅጣጫ ለውጥ በማድረግ በዚህ አውድ ስር የምትጠራው ሌላዋ ሀገር ደቡብ ኮርያ ናት፡፡ አብዛኞቹ የዓለም ሀገራት አሳፋሪ ከሚባል ድህነት የወጡት በአዲስ አስተሳሰብና በአዲስ የአቅጣጫ ለውጥ በኩል ነው። ሕይወት ምርጫ ናት፡፡ ልክ እንደዚህ ሀገርም በምርጫ የምትመራ ናት፡፡ ምርጫ ሁሉ ብልጫ አይደለም፡፡ ከሀሳባችን መካከል ምርጥ የሆነው ነው ወደ ብልጫ የሚወስደን፡፡

እኛም ይሄን እውነታ ወደተግባር በመቀየር ብልጫ ባለው ፖለቲካ፣ ብልጫ ባለው ምክክር፣ ብልጫ ባለው የሀሳብ የበላይነት እንዲሁም ብልጫ ባለው የአቅጣጫ ለውጥ አዲስ ለውጥን እንደምናመጣ እምነት አለኝ፡፡ ዋናውና ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ከነበርንበት፣ ለውጥ እና ሰላምን ካላመጣልን አቅጣጫ ፈቀቅ ማለት ነው፡፡

ችግሮቻችንን ነቅሰን ሰላም ለማምጣት ባዘጋጀነው ሕዝባዊ መድረክ ላይ እንደትልቅ ሊወሰድ የሚገባው የመድረኩ ዓላማ በብዙ ልዩነት ውስጥ እርቅን በሚያመጡ ሀሳቦች ወደተግባቦት መሄድ ነው፡፡ ይሄን መረዳት ወደ አንድነት የሚወስደን የአቅጣጫ ለውጥ ነው፡፡ እንዳለፈው ጊዜ ተነጋግረን ያለተግባቦት የምንለያይ ከሆነ በአዲስ የአቅጣጫ ለውጥ ላይ እንዳይደለን አመላካች ነው፡፡

ሀገራችን የሚያስፈልጋት ተግባቦት ነው፡፡ ለመግባባት መነጋገር ቀዳሚው ቢሆንም የአቅጣጫ ለውጥ ካልታከለበት ብቻውን አመርቂ ውጤት አያስገኝም፡፡ ለአዲስ ስርዐት ልምምድ የትኛውም የስልጣኔና የዘመናዊነት ተናጋሪ ጠቢብ እንደመነሻ የሚወስደው ተዐምርን ሳይሆን አዲስ እይታን ነው። በአዲስ እይታ ካልተግባባን አሁን ባለውና ጦርነት ፈጣሪ በሆነ አረዳድ ኢትዮጵያን ነጻ ማውጣት አንችልም፡፡ የሀገራችን ነጻ መውጣት፣ የትውልዱ የፍቅር አብራክ ያለው በፉክክር ውስጥ ሳይሆን በምክክር ውስጥ ነው፡፡

ያለፉትን በርካታ ዓመታት በተግባቦት ይልቅ በመናናቅ፣ ከምክክር ይልቅ በፉክክር የመጣን ነን። ውጤቱም ዛሬም ያልዳነች..ዛሬም ያልሻረ ሕዝብን ሰጥቶናል፡፡ ጠቢብ ማለት ካለፈው ተምሮ ዛሬን በማስተዋል የሚኖር ነው፡፡ እኛ ደግሞ ብዙ አስተማሪ ታሪኮች ያሉን ሕዝቦች ነን፡፡ በነዚህ ታሪኮቻችን ተገርተን ሰላም ፈጣሪዎች ካልሆንን በምንም የሚበረታ አቅም አይኖረንም፡፡ ፉክክር የስልጣኔ በኩር ቢሆን ከማንም ቀድመን አንደኛ የምንሆነው እኛ ነበርን፡፡ አንደኛ ልንሆን ቀርቶ መጨረሻ ቆመንም ኋላ ባቆመን የጥላቻ መንፈስ ውስጥ ነን፡፡ አንደኛ ልንሆን ቀርቶ ኋላነት የማይቆጨን ሆነናል፡፡

ሰላም በሌላት ሀገር ውስጥ ምንም ነገር ልክ ሊሆን አይመጣም፡፡ መኪና ያለሞተር፣ ሰው ያለ ነፍስ ምንም እንደሆነ ሁሉ ሀገርም ያለሰላም ምንም ናት፡፡ ሰላም የሀገር ሕልውና ነው፡፡ በእኔ እበልጥ እኔ በህልውናችን ላይ አሲዘን ብዙ ጸጋዎችን ተበልተናል። አሁን ጊዜው በፍቅር እነዛን የተበላናቸውን ጸጋዎቻችንን የምናስመልስበት ነው። በአዲስ አቅጣጫ አብሮነትን ፊተኛ ያደረገች አዲስ ሀገርን የምንሰራበት ነው፡፡

አቅጣጫችን ካልቀየርን ሕይወታችንን አንቀይርም፡፡ እንደነበርን ኖረን እንደነበርን እናልፋለን፡፡ ብዙዎቻችን ፈጣኖች ነን፡፡ በፍጥነት ለመብለጥ ያለ የሌለ ኃይላችንን ተጠቅመን የምንሮጥ ነን፡፡ እንደሀሳባችን ከፊት ቆመን ግን ስንታይም ሆነ ሲጨበጨብልን አይታይም ምክንያቱም ስንሮጥበት የነበረው አቅጣጫ ልክ ያልሆነ ስለነበር ነው፡፡ ይሄን እውነታ ወደሀገር ስንቀይረው የማደግና የመለወጥ፣ የሰላምና የአብሮነት መንፈሳችን እንዲመለስ የአቅጣጫ ለውጥ እናድርግ፡፡

ለሰላም የሚከፈሉ ዋጋዎች ማንንም ባለእዳ አድርገው አያውቁም፡፡ ባለእዳ ያደረጉን ስለጦርነት በእልህ የተወራወርናቸው ቃላቶች፣ ስለጥላቻ ማይክ ጨብጠን የተናገርናቸው አንደበቶቻችን ናቸው፡፡ ባለእዳ ያደረጉን ስለእኔነት የሰበክናቸው የጥላቻና የዘረኝነት ስብከቶች ናቸው፡፡ እዳዎቻችንን ወደሚያቀልልን የፍቅር አፍ እንመለስ፡፡ የተግባቦት አቅጣጫ እንይ፡፡ ብሄራዊ ምክክር የልዩነታችን ማብቂያ፤ የአንድነታችን ማበቢያ እንዲሆን ሁላችንም ስለኢትዮጵያ አደራ አለብን፡፡

በሰላም ውስጥ እንጂ በጥላቻ ውስጥ የሚሰምር ትልም የለም፡፡ የዓለም ስርዐት የሚያሳየው ይሄንን ነው፡፡ ለሰላም የምንከፍለው የትኛውም ዋጋ ጦርነት ካስከፈለን ዋጋ ቢያንስ እንጂ አይበልጥም፡፡ በመሸነፍ ውስጥ ማሸነፍ እንዳለ የገባው በቃ የሚል ድምጽ አጥተን ብዙ ዋጋዎችን ከፍለናል፡፡ እንደሀገር አሁን ላይ ከምንተነፍሰው አየር እኩል የሰላም ናፋቂዎች ነን፡፡ ሰላም ናፍቆን እንዳይቀር በአዲስ አቅጣጫ የተዘጉ የሰላም ደጆቻችንን እንክፈት፡፡

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ጥር 27/2016  ዓ.ም

Recommended For You