የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ የሚፈጥረውን መልካም አጋጣሚ ለምጣኔ ሀብት እድገት ለማዋል

ኢትዮጵያ በኃይል በቅኝ ለማስተዳደር የመጣን የፋሽስት ጣሊያን ወራሪ ኃይል በጀግንነት አሳፍራ በመመለስ፣ ከራስዋ አልፋ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት እንደሆነች ዓለም መስክሮላታል፡፡ በጀግኖች ልጆችዋ ታፍራና ተከብራ የኖረችው ሀገራችን ለአፍሪካ ሕብረት መቋቋም ያደረገችው አስተዋጽኦም እንዲሁ ግንባር ቀደም ያደርጋታል፡፡ እንዲህ ስሟ ከፍ ብሎ እንዲጠራ ያደረጓትን እነዚህን ሁለት የታሪክ ኩነቶች አስጠብቆ ለትውልድ እንዲሸጋገር በማድረግ ረገድም በተለያየ ጊዜ ሀገሪቱን ያስተዳደሯት መሪዎችም የየራሳቸውን ሚና ተወጥተዋል፡፡

37ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በቅርቡ ይካሄዳል፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ የሚካፈሉ የሀገር መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ከሌሎች ሀገሮች የተጋበዙ እንግዶች ከጉባኤ በኋላ የቆይታ ጊዜያቸው አስደሳችና ያማረ እንዲሆን፤ ኢትዮጵያ ቀድማ አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት አድርጋለች፡፡ እንግዶች ከጉባኤው በኋላ በሚኖራቸው ቆይታ በሚያርፉበት ሆቴል፣ በሚዝናኑበት ቦታ ሁሉ ጥሩ መስተንግዶ እንዲኖራቸው የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

የከተማዋ ዋና ዋና አደባባዮች ለእይታ ያማረና ማራኪ ሆነው እንግዶችን እንዲስብ፣ የመንገድ ላይ መብራቶችንም በመጠገን፣ በጽዳትና ውበት ሥራ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡ በተለይም ዋና ዋና የሚባሉት የመዲናዋ መንገዶችና መዳረሻዎችን የማልማቱ ሥራ ቀድሞ ነው የተጀመረው፡፡

ከመኝታ፣ ከምግብና ተያያዥ የሆኑ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በጥራት መጓደል፣ የተጋነነ ዋጋ በመጠየቅ በአጠቃላይ የእንግዳ አያያዝ (ሆስፒታሊቲ) ተላብሰው ሙያው የሚፈቅደውን ሥነምግባር ካለ መወጣት ጋር ከዚህ ቀደም የሚቀርቡትን ቅሬታዎች ለማስቀረትም እንዲሁ ቅድመ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ጉባኤውን ታሳቢ በማድረግ የተቋቋመ ኮሚቴ፤ ሰሞኑን ከሆቴል ቤት ባለቤቶች ጋር ባካሄደው የጋራ መድረክ ላይም የጋራ መግባባት ላይ ደርሷል፡፡

ሆቴሎች ከኢትዮጵያ አየርመንገድ ቀጥሎ የሀገር ገጽታ በመገንባት ካላቸው ከፍተኛ አበርክቶ አንጻር፣ ከዚህ ቀደም የሚነሱባቸውን ክፍተቶች በተለይም አሁን በሚካሄደው 37ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ላይ እንዳይደገሙ ጥንቃቄ ማድረግና ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለሀገር ገጽታ ግንባታ በኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በውስጥ በገጠማት አለመረጋጋት፣ በተለይም በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል በተካሄደው ጦርነት እንዲሁም የዓለም ስጋት በነበረው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ተፈጥሮ የነበረውን አሉታዊ ገጽታ በመልካም ለመቀየር መረባረብ ከመንግሥት ብቻ የሚጠበቅ ኃላፊነት አይደለም፡፡

እንግዶች ከጉባኤው በኋላ ቆይታ የሚኖራቸው በማረፊያቸው ውስጥ ነው፡፡ ማረፊያቸው ውስጥ የሚያገኙት መስተንግዶና ሰላም እንዲሰማቸው የሚደረገው ጥረት ቦታ ሊሰጠው ይገባል። የሆቴል ቤት ባለቤቶች አካባቢያቸው ላይ የሚያውክ ነገር እንዳይኖር ቀድመው በመዘጋጀት የፀጥታ ኃይሉ ለጉባኤው ስኬት የሚያደርገውን ጥረት ማገዝም ይኖርባቸዋል፡፡

በመሠረተ ልማት በኩልም መብራት ኃይል አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር፣ ኢትዮ ቴሌኮምም እንዲሁ ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የገጽታ ግንባታ አካል መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ በአንዱ አገልግሎት ሰጪ የሚፈጠረው ክፍተት በሀገራዊ ገጽታ ግንባታ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል፡፡ ክፍተቶች እንዳይኖሩ በጋራ መንቀሳቀሱ ደግሞ የበለጠ ይጠቅማል፡፡

በዚህ የአፍሪካ ሕብረት ዓመታዊ ጉባኤ ምክንያት የሚገኘውን እድል ወደ ምጣኔ ሀብታዊ በመለወጥ ረገድም እንደሀገር ሊታሰብ ይገባል። በጉባኤው ላይ የአፍሪካ የሀገር መሪዎችና ሚኒስትሮችና ብቻ ሳይሆኑ፣ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚጋበዙ እንግዶችም እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ በመሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተሳታፊ እንደሚኖር ይታሰባል፡፡

ጉባኤውም የተለያዩ አጀንዳዎች ያሉት በመሆኑ ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ ያላቸው የቆይታ ጊዜ ከሳምንት በላይ ሊሆን ይችላል። ከጉባኤው በፊት ቀድሞ የመግባትና ጉባኤው ከተጠናቀቀ በኋላም ዘግይቶ የመውጣት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም ማሰብም ተገቢ ነው፡፡

አጋጣሚውን ወደ ኢኮኖሚ ጥቅም ለመለ ወጥ የንግዱ ማኅበረተሰብ እራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ከጉባኤው ቀድሞ አስፈላጊ ዝግጅቶችን ማድረግ በመቻል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ የእንግዳ አቀባበልና ተያያዥነት ባለቸው ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል፡፡ መስተንግዶው እንግዳው ወደ መጣበት ሲመለስ ሌሎች እንዲመጡ የሚያነሳሳና የሚያነቃቃ መሆን ይኖርበታል፡፡

በመንግስት በኩል ተበታትኖ የነበረውን የቱሪዝም አደረጃጀት መቀየሩ በራሱ ኢንደስትሪውን የበለጠ ማነቃቃት የሚቻልበት እድል ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል። ተቀዛቅዞ የነበረው ቱሪዝም እንዲነቃቃና ከዘርፉ የሚገኘውን ምጣኔ ሀብት ለማሳደግ የዘርፉ ተዋንያን ብቻ ሳይሆኑ፣ ማኅበረሰቡም ለእንግዶች ተገቢውን ክብርና እንክብካቤ በማድረግ የራሱን ሚና መወጣት ይኖርበታል፡፡

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ጥር 27/2016  ዓ.ም

Recommended For You