24/7 የሚፋለሙበት የሳይበር ግንባር…! ?

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ እንደ ሀገር ከተሰነዘሩ 4 ሺህ 623 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች 4 ሺህ 493 ያህሉን ማክሸፍ መቻሉን፤ የኢንፎርሜሽን መረብ አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ ገልጸው፤ ከተቃጡ ጥቃቶች ውስጥም 4 ሺህ 493 የጥቃት ሙከራዎች ወይም 98 ነጥብ 56 በመቶውን ማክሸፍ ተችሏል።

ከሳይበር ጥቃት ሙከራ 130 ያህል መከላከል ሳይቻል መቅረቱን ጠቁመው፤ በመከላከል ሥራው ሀገሪቱ ላይ ሊደርስ የነበረ ከ10 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ማዳን መቻሉን፤ የከፍተኛ አደጋ ደረጃ ያላቸው የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸሩ በ115 በመቶ መጨመራቸውንም ጠቁመዋል።

የሳይበር ጥቃት ኢላማ የተደረጉ ተቋማት አብዛኛዎቹ የፋይናንስ ተቋማት፣ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ የክልል ቢሮዎች፣ የሕክምና እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሆናቸውን፤ የድረገጽ ጥቃት፣ ማልዌር፣ የመሠረተ ልማት ቅኝት፣ የመሠረተ ልማት ማቋረጥ፣ ሰርጎ የመግባት ሙከራ እንደየቅደም ተከተላቸው ከፍተኛ የጥቃት ሙከራ የተደረገባቸው መሆናቸውንም አስረድተዋል።

የሳይበር ጦርነት በአጭሩ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ እንደ ፋይናንስ ተቋማት፣ መከላከያ፣ ደህንነት፣ ቴሌኮም ያሉ ተቋማትን የበይነ መረብ የመረጃ ሥርዓቶችን ከጥቅም ውጪ ማድረግ ነው። ስለላ ማካሄድም የጦርነቱ አካል ነው። ራሽያ ዩክሬንን በመውረሯ አኖኒመስ የተባለ የሀክቲቪስቶች ስብስብ በራሽያ ላይ የሳይበር ጦርነት እንዳወጀው፤ በሀገራችን ላይም በህቡዕ የሳይበር ጦርነት የከፈቱብን ኃይሎች መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ሰነባበተ።

የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ቆየት ባለ አንድ መግለጫው፤ «…መሠረታቸውን ከግብጽ ያደረጉ የመረጃ መረብ ሰርሳሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ተቋማት የመረጃ መረብ መዋቅር ላይ ጥቃት ለማድረግ ሞክረው ነበር ። …» እንዳለው ተራ ሙከራ ሳይሆን የሳይበር ጦርነት ነው የተከፈተብን። በዋዛ ፈዛዛ ሙከራ በሚል ብቻ የሚታለፍ አይደለም።

በሉዓላዊነታችን፣ በደህንነታችንና በተቋሞቻችን የተቃጣ ጥቃት መሆኑ ሳይቃለል በልኩ ነው መታየት ያለበት። በ21ኛው መክዘ ጦርነት የሚካሄድበት ጦርነት በየብስ፣ በባሕርና በአየር ብቻ ሳይሆን በሳይበርና በስፔስ የታገዘ ስለሚሆን ሀገራት ከዚህ አንጻር ራሳቸውን እያዘጋጁ ነው።

በebs የ” Tech Talk With Solomon “ አዘጋጅ ሰለሞን ሙሉጌታ ካሳ” ግርምተ ሳይቴክ “ በሚል ርዕስ በ2010 ዓ.ም ለንባብ ባበቃው መፅሐፍ ፤ « የማይታየው ጦርነት» በሚል ምዕራፍ ስር ገፅ 157 ላይ ፤ «…በ21ኛው መክዘ አዲስ ዓይነት ጦርነት ብቅ ብሏል። ጦርነቱ የሚካሄደው በጥይትና በቦምብ ሳይሆን በሀከሮችና በኮምፒውተሮች ነው ። … ይህ በዓይን የማይታየው የሳይበር ጦርነት/ ዋርፌር / ነው።

«ግብፅን በአየር፣ በየብስ ስንጠብቃት፤ ምን አልባት ባልጠበቅነውና ባልተዘጋጀንበት ስስ ብልታቸው ይሆናል ብላ በገመተችው በሳይበር ግንባር ጦርነት መክፈቷ ከፍ ብሎ ተመልክቷል። የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢንሳ/መሠረታቸውን ከግብፅ ያደረጉ የመረጃ መረብ ሰርሳሪዎች በሀገራችን ተቋማት የመረጃ መረብ መዋቅር ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ያደረጉትን ሙከራ ማክሸፉ አይዘነጋም። የዘንድሮዎቹ የሳይበር ጥቃቶች መሠረታቸው ከየት እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ባይገልጹም ለመገመት ግን አይከብድም።

በኤጀንሲው የወቅቱ መግለጫ መሠረት በሦስት የተለያዩ ቡድኖች አማካይነት የተሞከረው የመረጃ መረብ ጥቃት በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫናን ለመፍጠር ያነጣጠረ ነበር። የጥቃቱ ሙከራ ባደረጉት ቡድኖች ላይ አበክሮ ክትትል በማድረጉ በ13 የመንግሥት እና አራት መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ድረ-ገጾችን ኢላማ በማድረግ የተሰነዘሩ ከፍተኛ የመረጃ መረብ የጥቃት ሙከራዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ችሏል። የመረጃ መረብ ጥቃት ሙከራው የተደረገው ሳይበር ሆሩስ ግሩፕ፣ አኑቢስ ዶት ሃከር’ እና ሴኪዩሪቲ ባይ ፓስ በተባሉ መረጃ መረብ ሰርሳሪ ቡድኖች ነው።

የጥቃቱ ኢላማ የነበሩት ተቋማት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የመንግሥት ተቋማት፣ የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች እና የግል ድርጅቶች ድረ-ገጽ ላይ መሆኑን ኤጀንሲው በመግለጫው አብራርቷል። ሆኖም ባልተለመደ ሁኔታ በሀገሪቱ ባሉ ተቋማት የመረጃ መረብ ላይ ጥቃት ለማድረስ የሞከሩ ቡድኖች በግልፅ ኃላፊነቱን መውሰዳቸው ግብፅ ለሀገራችን ያላትን ንቀትና እብሪት የሚያስታውስ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ሌላው ኤጀንሲው የሳይበር ጥቃቱ አላማ፤ «በኢትዮጵያ ላይ በሁሉም አቅጣጫ ተጽእኖ ለማሳደር ነው። »

የሳይበር ጥቃቱ ተፅዕኖ ከመፍጠር በላይ ተጠናክሮ የሚቀጥል ጦርነት ነውና። አስቀድሞ ቅድመ ዝግጅት በማድረጉ የመረጃ መረብ ጥቃቱ ኢላማ በነበሩት ተቋማት ላይ ጉዳት አልደረሰም። ጥቃቱን ማክሸፍ ባይችል ኖሮ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችል እንደነበር ኤጀንሲው መግለጹ የሳይበር ጥቃቱን አደገኝነት አጉልቶ ያሳያል።

ቀጣዩ አውደ ውጊያ በሳይበር ግንባር ስለሆነ የጦር ዕቃውን ታጥቀን ፣ የራስ ቁሩን ደፍተን ፣ ጡሩሩን ለብሰን፣ ጦሩን እየሰበቅ፣ ዘገሩን እየነቀነቀን 24/7 ተጠንቅቀን ልንጠብቅ ይገባል። ከዚህ በኋላ የማይቀርልን ዕዳ/ ዘ ኒው ኖርማል / ነውና። ሰሞነኛው የአገልግሎቱ መግለጫ ይሄንኑ የሚያረጋገጥ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

ለመሆኑ የመረጃ መረብ ወይም የሳይበር ጥቃት ሲባል ምን ማለት ነው? በሰለሞን ሙሉጌታ ካሳ «ግርምተ ሳይቴክ» መፅሐፍ ፤ «የማይታየው ጦርነት» በሚል ምዕራፍ ስር ገፅ 157 ላይ ፤ «… ምስጢራዊ የሆነና ያልሆነን ዲጂታል መረጃን ከባለቤቱ ፈቃድ ውጭ መስረቅ ፣ ይዘቱን ማበላሸት ፣ ከእነ አካቴው ማጥፋት…» ሲል ይበይንና ታሪካዊ ዳራውን እንዲህ ያብራራል።

«ከሙከራ ላብራቶሪ በዘለለ መልኩ የመጀመሪያው ‘ ኤልክ ክሎነር ‘ የተባለ የግል ኮምፒውተርን የሚያጠቃ ቫይረስ በ1982 ዓ.ም የ15 አመት ወጣትና የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ በነበረው አሜሪካዊው ሪቻርድ ስክሬንታ ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ በኮምፒውተር መረጃዎች ያነጣጠረ ‘ ሳይበር ‘ ጥቃት በመንግሥታት መካከል ጭምር ሳይቀር የሚካሄድ የሳይበር ጦርነት / ሳይበር ዋር / አሀዱ ብሎ ጀመረ።

በወቅቱ ኢንተርኔት ገና ለሕዝብ ጥቅም ያልዋለበት ጊዜ ስለነበር ወንጀሉ በስፋት አልተስተዋለም። በ1980ዎቹና 90ዎቹ አጋማሽ ድረስ ጥቃቱ በብዛት ይሰነዘር የነበረው እንደ ‘ ፍሎፒ ዲስክ ‘ እና ‘ ሲዲ ‘ በመሳሰሉ ተንቀሳቃሽ የመረጃ ማስቀመጫ ቁሶች አማካኝነት ቫይረስ ከአንድ ኮምፒውተር ወደ ሌላ ኮምፒውተር በማስተላለፍ ነበር።

በ1990ዎቹ አጋማሽ በኋላ የኢንተርኔት አጠቃቀም እያደገ ሲመጣ ጥቃቱም መልኩን ቀይሮ ብቅ አለ። በ2003 ዓ.ም ገደማ የሳይበር ወንጀል ፍፁም አዲስ በሆነ መልኩ ድረ ገጾችን የማጥቃት አላማ ይዞ ተነሳ። ይህ የሆነበት ምክንያት በወቅቱ የኢንተርኔት ‘ ኢኮሜርስ ‘ ግብይት ሥርዓቱ እየተጧጧፈ በመምጣቱ ነው።

በተለይ የክሬዲት ካርድ ቁጥሮችን በመስረቅ ላይ ያነጣጠረ የሳይበር ወንጀል በ2000ዎቹ ተጧጡፎ ቀጠለ። ከ2005 እስከ 2007 ዓ.ም ባለው ጊዜ አልበርት ጎንዛሌዝ የተባለ አደገኛ አሜሪካዊ የኮምፒውተር ሀከርና የሳይበር ወንጀለኛ የተለያዩ ግዙፍ የንግድ ኩባንያዎችን የኮምፒውተር ሲስተሞችን በማጥቃት፤ የግለሰቦችን ክሬዲት ካርዶችን ቁጥር በመመንተፍ 45 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ዘርፏል ። …” ዛሬ የሳይበር ጥቃት ምርጫን ፣ ኢኮኖሚንና ማኅበራዊ ግልጋሎትን በማስተጓጎል ውድ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል።

ከፍ ብዬ የጠቀስሁት ደራሲና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ በመጽሐፉ ይበልጥ እንዲህ ያብራራዋል። «… የመረጃ ፍሰቱ ዓለምን ማጥለቅለቁ ፤ መንግሥታትም አሠራራቸውን በኢንተርኔትና በኮምፒውተር ማድረጋቸው ፤ መሠረተ ልማታቸውን የሚያስተዳድሩት፤ መረጃዎቻቸውን የሚያስቀምጡት፤ አገልግሎት የሚሰጡት እንዲሁም ታላላቅ ወታደራዊና የደህንነት መረጃዎችን በዲጂታል መልክ መያዛቸው ለጥቃት አጋልጧቸዋል። የእንግሊዝ የደህንነት ተቋማት እነ ኤም አይ ፋይፍና ኤም አይ ሲክስ እንዲሁም የአሜሪካው ኤፍ ቢ አይ የሳይበር ጥቃትን ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት አድርገው ወስደው መሥራት ከጀመሩ ውሎ አድሯል ። … »

እንደ መውጫ

የሳይበር ጥቃት በሚቀጥሉት ጥቂት አመታት እስከ ስድስት ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንደሚያስከትል ጥናቶች አበክረው ይተነብያሉ። ከዓለምአቀፍ ሽብርተኝነት ባልተናነሰ የደህንነት ስጋት እስከ መደቀንም ደርሷል። ዓለም በሉላዊነት / ግሎባላይዜሽን / እና በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ወደ ትንሽ መንደርነት በተቀየረችበት የሳይበር ጥቃትና ጦርነት ለሀገራችንም ስጋት መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል። በንግድ ባንክ በተደጋጋሚ የተቃጡ ጥቃቶቸ ፤ የፈተና ስርቆት በተማሪዎች ሥነ ልቦና እንዲሁም በጊዜያቸው ላይ ያስከተለው ጉዳት እንዳለ ሆኖ በሀገር ኢኮኖሚ እና በተቋማት አመኔታ ላይ ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም።

የሳይበር ጥቃት በተደጋጋሚ የሚሰነዘር ቢሆንም መከላከል እንደሚቻል የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ሆኖም 99 በመቶ የሚሆኑ ድርጅቶች ለሳይበር ጥቃት የተጋለጡ ናቸው። የሀገራችን ተቋማት ይህን ተጋላጭነታቸው መቀነስ ላይ አበክሮ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በተለይ የደህንነት ፣ የፋይናንስ ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የሚዲያ ተቋማት ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

የሳይበር ጥቃት ዋና መከላከያ ዘዴ ከጫፍ ጫፍ ሁሉንም ኔት ወርኮች፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮችንና የመረጃ መነሻና መዳረሻዎችንና ክላውዶችን ታሳቢ ያደረገ ተጋላጭነት የመቀነስ ሥራ መከወን ነው። ጠንካራ የሳይበር መከላከያ፣ ጥቃቱን መለየት ላይ ከማተኮር ይልቅ መከላከል ላይ በማተኮር፣ ጥቃት ሊቃጣባቸው የሚችሉ አሠራሮችን በመከላከል ፣ የመጨረሻውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም እና ስለ ስጋት ምንጮች ወቅታዊ ግንዛቤ መጨበጥ ከዋና ዋናዎቹ የመከላከያ ዘዴዎች የሚጠቀሱ ናቸው። አበው እመው ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ስለ ሳይበር ጥቃት ከተነሳ አይቀር አኖኒመሶችን በስሱ ላስተዋውቃችሁ።

«ማንነታችን የማይታወቅ ወይም ስም አልባ አልያም አኖኒመስ ነን። ጭፍራ ነን። ይቅር አንልም ። አንረሳም ። ጠብቁን ።» መለያቸው ወይም ሞቷቸው ነው። ለማንም አይመለስም። የአሜሪካውን ግዙፍ የስለላ ተቋም ሲአይኤ ላይ ሳይቀር የሳይበር ጦርነት መክፈት የቻለ ኃይል ነው።

በራሽያው የደህንነትና የስለላ ተቋም ኤፍኤስቢ ላይም ተመሳሳይ ጥቃት ሰንዝሯል። የአሜሪካውን ኤፍቢአይና የእንግሊዙን ስኮትላንድ ያርድን ግንኙነት በተደጋጋሚ አስተጓጉሏል። ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን/ኔቶ/መረጃዎችን ሰርስሮ የዘረፈ ሲሆን ዓለምአቀፉ የፖሊስ ተቋም ኢንተርፖል ላይም ተመሳሳይ የሳይበር ጥቃት ፈጽሟል።

ለማንኛውም ርዕዮተ ዓለም የገባ ወይም ያደረ አይደለም። ግራ ዘመም ሆነ ቀኝ አክራሪ ወይም መሐል ሰፋሪ አልያም ሊበራል ወይም ኮንሰርቫቲቭ አልያም ሶሻሊስት፣ ኮምኒስት ፣ ካፒታሊስት አይደለም ። ውግንና አለው ከተባለ ለእውነትና ለፍትሕ ነው ሲሉ ይመሰክሩለታል። የግፉአን እንባ አባሽ ነው የሚሉትም አሉ። መርሁ ጸረ ጭቆና ነው ሲሉ ሀክትቪስት ብለው የሚጠሩትም አሉ።

በትሩን የቀመሱ አገዛዞች፣ ተቋማትና ድርጅቶች ደግሞ የሳይበር አሸባሪ ነው ሲሉ ይከሱታል። የሰራዊቱ አባላት ከመላው ዓለም በበጎ ፈቃደኝነት የከተቱ ናቸው። ደመወዝ አይቆረጥላቸውም። ቀለብ አይሰፈርላቸውም። ትጥቃቸው የኮምፒውተር ቁልፍ ሰሌዳ /ኪይቦርድ/ እና የተካኑበት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን እውቀት ነው። በሰው ልጆች ላይ በደል ፈጽሟል ያሉትን አገዛዝና ተቋም ወይም ድርጅት ላይ በኪይቦርዳቸው ያደባዩታል።

ባንኩን፣ የፋይናንስ ተቋሙን ፣ የኃይል ማመንጫውን ፣ መከላከያውን ፣ ደህንነቱንና ሌሎች ተቋማቱን ሽባ ያደርጉታል ። ሀገሩን ቀጥ ያደርጉታል። ያግቱታል። የመረጃ ቋቱን ሰርስረው ይገቡና/ሀክ ያደርጉና/መረጃ ይዘርፋሉ፣ ከጥቅም ውጪ ያደርጋሉ ፣ ያፋልሳሉ ፣ ያጠፋሉ ፣ በራሳቸው መረጃ ይተካሉ። ባልተለመደ ሁኔታ የሳይበር ጦርነትን በኦፊሴል በግልጽና በአደባባይ የሚያውጅ ብቸኛ የሳይበር ሰራዊት ነው።

ቀደም ባሉት ጊዜያት በአልቃይዳ፣ በአይኤስአይኤስ፣ በታሊባን ፣ በአልሻባብና በሌሎች ላይ የሳይበር ጦርነት ያወጀ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ በራሽያ ላይ ጦርነት አውጇል። የራሽያ ፌዴሬሽንን የመከላከያ ሚኒስቴር የመረጃ ቋትን ሀክ አድርጎ ጥብቅ ወታደራዊ መረጃዎችን ዘርፏል። አጥፍቷል። አፋልሷል። ከጥቅም ውጪ አድርጓል። የራሽያን የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎችን ሀክ አድርጎ ስለዩክሬን የሚያቀነቅኑ መረጃዎችን እስከማስተላለፍና የዩክሬንን ብሔራዊ መዝሙር እስከማዘመር ደርሶ እንደነበር የእንግሊዙ «ዘ ኢንዲፔንዳንት» ጋዜጣ የቴክኖሎጂ አዘጋጅ ዳን ሚልሞ በዚያ ሰሞን ዘግቧል።

ሻሎም ! አሜን ።

በቁምላቸው አበበ ይማም ( ሞሼ ዳያን )

አዲስ ዘመን ጥር 26/2016

አዲስ ዘመን ጥር 26/2016

Recommended For You