ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቁ ሦስት ሺህ 452 ቤቶች ለጨረታ ሊቀርቡ ነው

አዲስ አበባ፡- ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቁ ሦስት ሺ 452 የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን ለጨረታ ሊያቀርብ መሆኑን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ ኮርፖሬሽኑ ግንባታቸው ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቁ ሦስት ሺ 146 የመኖሪያ ቤቶችና 306 የንግድ ሱቆች በድምሩ ሦስት ሺህ 452 ቤቶች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በከተማዋ እየጨመረ የመጣውን የነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ አማራጮች ይዞ እየሰራ ይገኛል ብለዋል። መንግሥት በባንክ በተገኘ የቦንድ ብድር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እየገነባ ለነዋሪው ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውሰው፤ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግሩ በመንግሥት ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ የግል ባለሀብቱን በማስተባበር ጭምር ነዋሪው ቤት የሚያገኝበት አሰራር መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

 ኮርፖሬሽኑ ከዚህ ቀደም በመንግሥት አስተባባሪነት በቦንድ ብድር ያስገነባቸው ቤቶች ላይ ብድር ስላለበት 36 ቢሊዮን ብር ከዕዳው መቀነስ ቢችልም አሁንም 37 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ያልተከፈለ ዕዳ እንዳለበት አመላክተዋል፡፡ ዕዳው ተቋሙ በመንግሥት አስተባባሪነት የሚገነባቸው ቤቶች በሚፈልገው ፍጥነት ለማስኬድና ቆጥበው ቤት ላልደረሳቸውም ሆነ አዳዲስ የቤት ፍላጎቶችን ለማስተናገድ የሚያስችል የባንክ ብድር አቅርቦት እንዳያገኝ ማገዱን አስረድተዋል።

የፋይናንስ እጥረቱን ለመፍታትና የመንግሥትን ተሳትፎ ለማሳደግ ኮርፖሬሽኑ ባለፉት አራት ወራት የተገነቡ የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን ለጨረታ ለማቅረብ መወሰኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡ ቤቶቹ በኮርፖሬሽኑና በዲዛይን ግንባታ ቢሮ በኩል በመንግሥት በተመደበ ካፒታል የተገነቡ ሲሆን፤ በሽያጩ በሚገኘው ገንዘብ በአጠረ ጊዜ የሚጠናቀቁ የኪራይ ቤቶችን ገንብቶ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች ለማስተላለፍ እንደሚውል ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ሁሉንም የቤት አቅርቦት አማራጮችን በማቀናጀት የነዋሪዎችን ቤት ችግር ለመፍታት መስራቱን ይቀጥላል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የኪራይ ቤቶችን ለመገንባት የሚደረገው ጥረትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ቤቶችን ከመገንባት ጎን ለጎን በርካታ የከተማዋ ነዋሪ የሥራ ዕድል በመፍጠር ፣የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ዕውቀት ሽግግር በማድረግና በከተማ አስተዳደሩ በባለቤትነት የተያዙ የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን የማስተላለፍና የማስተዳደር ሥራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል። የሦስት ሺ 452ቱን ቤቶች የጨረታ ሰነድ ከጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ መግዛትና መወዳደር እንደሚቻል ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል።

 መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ጥር 26/2016

Recommended For You