ስለ ሠላም ሲባል …

ሠላም የማይነካው ጉዳይ የለም፡፡ የሠላም በር እየተዘጋ፤ የግጭት፣ የጦርነት፣ ተስፋ የማጣት እና የመሳሰሉት ችግሮች እየገዘፉ መምጣት እንደ ተራ የምናያቸው ነገሮች ቅንጦት እንዲሆኑብን ያደርጋል። ቢያንስ በአንድ ቀን ሁለት ጊዜ መመገብ ቀርቶ የዕለት ጉርስን ያስናፍቃል፡፡ ጥጋብ ቀርቶ መቅመስን ብቻ ያስመኛል፡፡ ውሃ ጠጥቶ ከመርካት ይልቅ ጠብታው አፍን መንካት እጅጉን ያስናፍቃል፡፡ አገርን ለቆ ወደ ማያውቁት አገር ያስናፍቃል፣ ያስኮበልላል፤ ያሰድዳል፡፡

በጦርነት፣ በጸጥታ መደፍረስ፣ በተፈጥሮ እና በሠው ሠራሽ ችግሮች ጉዳት ከሚደርስባቸው መካከል እናቶች ሴቶች ሕፃናት አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለእነርሱም ሆነ ለመላው ሕዝብ ሠላም ልክ እንደ ‹‹አየር›› ነው። ያለ ሠላም መኖር አይቻልም፡፡ መኖር እንኳን ቢቻል ኑሮ አይባልም፡፡

ያለ ሠላም ምንም ማድረግ አይቻልምና ሁሉም ነገር ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ ይሆናል፡፡ የተራቡትን፣ የታረዙትን፣ የተቸገሩትን ለመርዳት እንኳን የአገር ሠላም መሆን ግድ እና ግድ ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር አይደለም የሌላውን ጉድለት ለመሞላት ይቅር እና ለራስ መሆንም ብርቅ ይሆናል፡፡

ሠላም ሲደፈርሱ ሁሉም ነገር እንዳልሆነ ይሆናል፡፡ የትምህርቱ ዘርፍ ላይ የሚጥለው አሻራ ቀላል አይደለም። ከታችኛው የቅድመ አንደኛ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በራቸው እንዲዘጋ ያስገድዳል። በዚህም መጪው ትውልድ ከትምህርት፣ ከስልጣኔ፣ ከቴክኖሎጂ፣ ከእውቀት፣ ከአምራችነት፣ ከሥራ ፈጣሪነት እና ከመሳሰሉት ነገሮች ተጠቃሚ እንዳይሆን ያግዱታል፡፡

የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች መማር ሲኖርባቸው ከትምህርታቸው ሳይወድ እና ሳይፈልጉ ገሸሽ እንዲሉ ያደርጋቸዋል፡፡ እንደ እኩያዎቻቸው እውቀት ለመገብየትም ሆነ እገረ መንገዳቸውን ተጫውተው ለመግባትም የሠላም አስፈላጊነትን ማስረዳት ለቀባሪው እንደማስረዳት ያለ ነው ፡፡

ንግዱም፣ ግብይቱም፣ ቁጭ ብሎ ማውጋቱ፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለብዙ ዓላማ መዘዋወር የሚቻለው ሠላም ሲኖር እና ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ለደስታም ይሁን ሀዘንን ለመጋራት የሚደረጉ ጎዞዎች መጨረሻቸው የሰመረ እንዲሆን የሰላም ዋጋው እጅግ እልፍ ነው ፡፡

ይሁንና ዛሬም ቢሆን ተስፋ የሚሰጡ ነገሮች አልጠፉንም፡፡ በመንግስት እና በትግራይ ክልል በተደረሰው የሰላም ስምምነት ውጤቱን እያየነው እንገኛለን፡፡ በዚህም ምክንያት ዛሬ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች የእለት ጉርሱን የማግኘት እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ይሻሻሉልን እንጂ ሠላም አስፍኑልን ከሚለው አጀንዳ ከፍ ብሎ ታይቷል፡፡

ዛሬ ላይ መንግስታዊም ይሁኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ወደ ክልሉ በማቅናት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠሩ ከመሆን ባሻገር ብዙ ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት የመጣው የሠላም ተስፋ ቦግ ብሎ በመታየቱ ነው፡፡

ከሰሞኑ የብልጽግና ፓርቲ ባደረገው ስብሰባ ላይ እንዳስታወቀው፤ የተሟላ ሀገራዊ ሰላም ለማስፈን እንዲቻል ከታጣቂ ቡድኖች ጋር የተጀመሩ ሰላማዊ አማራጮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ይህም የሚበረታታ እና ብዙ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

በሰላማዊ የፖለቲካ መንገድ ጥያቄዎቻቸውን ለሚያቀርቡ አካላት ሰላማዊ መንገዶች እስከሚቻለው ድረስ እንዲመቻቹ፤ በፕሪቶርያው ስምምነት የተገኙ የሰላም ፍሬዎችን በመንከባከብ፣ የጎደሉ ክፍተቶችን በመሙላት፣ ወደ ዘላቂ ሰላም እንዲሸጋገር ፓርቲው የተጀመሩ ጥረቶችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማሳወቁም የሚደነቅ ነው።

አሁን እየታየ ባለው የጸጥታ ችግር ሠላምን ሙሉ በሙሉ ለማስፈን ሂደቱ እና ጉዞው ቀላል እንደማያደርገው ይጠበቃል፡፡ ስለ ሰላማችን ከእኛ በላይ ማን ጠንቅቆ እና አብልጦ ሊያውቅልን አይችልም፡፡ የውጭ አገራት ሸምጋዮቻችንም ሠላም እንዲሰፍን ከራሳቸውን ጥቅም እንዲሁም የሕልውና ስጋት በመነሳት ነውና እነርሱን ለጥረታቸው በማመስገን የራሳችንን ችግር በራሳችን አቅም ፈተን ማሳየት፤ አንድም ብልሃት አንድ በራስ መተማመንን ማሳየት ነው፡፡

 ጉልበትም ሆነ አቅም መፈታተሹ ትርፉ ኪሳራ፤ መጨረሻውም ያላማረ እና ሀገሪቱን የቁልቁለት ጉዞ እንድትሄድ የሚያደርግ መሆኑን የሁለት ዓመት የጦርነት ጉዞ በሚገባ የሚያስተምረን ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩን የጸጥታ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ልንፈታ ይገባል።

ቁጭ ብለን ችግሮቻችንን ለዘለቄታው እንዴት እንፍታው? ብሎ ሰከን ብሎ ማሰብ፣ መወያየት መነጋገር እና መተማመንን ይተበቅብናል፡፡ ይህ እንዲሳካ ደግሞ የአገር ሽማግሌዎች ተሰሚነታቸውን እና ቱባ ባህላችንን እንድንጠቀም ድልድይ በመሆን ለተፈፃሚነቱ የድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡

የሀይማት አባቶችም እውነተኛ የሆነውን ፍቅርን፣ መዋደድን፣ ሠላምን እና መተማመንን በመስበከ አርአያነታቸውን በሚገባ ማሳየት ይኖርባቸዋል፡፡ ተከታዮቻቸውን በቃላት ከማስተማር ይልቅ በተግባር የተረጋገጠ አርአያነታቸውን ማሳየትም ይጠበቅባቸዋል፡፡

መንግስትም እንደ መንግስት ስለ ሰላም ሲል ሆደ ሰፊነቱን ማሳየት፤ ለውይይት ፍላጎት ከማሳየት ባሻገር በሰላም ግንባታ ዙሪያ ምሁራን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን እና መላውን ሕዝብ አቀናጅቶ መንቀሳቀስ ይኖርበታል። የሲቪክ እና ሌሎች ድርጅቶች እንዲሁም ሁሉም ዜጋ የአቅሙን እና የድርሻውን ሚና በመወጣት ስለ አገር ሰላም የበኩለን አስተዋጽኦ መወጣት ይኖርበታል፡፡

ሀገር ከጥቅም ውጭ ሆና ዳግም ለማቅናት ተጠራርቶ ለመነጋገር እና ለመወያየት ከመሞከር ይልቅ ዘመኑ እና ወቅቱ እንደሚፈልገው አስቀድሞ ችግሮችም ከመለየት ባሻገር ችግሮቹን ተወያይቶ እና ተነጋግሮ መፍትሄ ማበጀት ቅድሚያ ብሎም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው መሆን ያለበት፡፡

በምስጋና

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You