የሽልማቱ ፋይዳ የላቀ ነው

ከሰሞኑ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምግብ ዋስትናና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ቁርጠኝነትና የላቀ አመራርነት የተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ‹ፋኦ› የአግሪኮላ ሽልማትን አበርክቶላቸዋል፡፡ በአይነቱ ለየት ያለው ይሄ ሽልማት በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረግ ሂደት ውስጥ የመንግስትን ቁርጠኝነት ከሕዝባዊ ተሳትፎ ጋር መሳ ለመሳ አቁሞ አሁናዊና ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ጥያቄ ውስጥ በማስገባት እንደመስፈርት የሚያስቀምጥ ነው፡፡

ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ በኢኮኖሚ ራስን የመቻል ጥረት ውስጥ ናት፡፡ ጥረቱ ፍሬ እንዲያፈራ በመንግስት በኩል ሁሉንም አይነት እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ይሄን እውነታ ከሚመሰክሩ ሁነቶች ውስጥ የመጀመሪያው በግብርናው ዘርፍ በተለይም በበጋ ስንዴ ምርት ላይ እያሳየነው ያለው ለውጥ አንዱ ነው፡፡ ላለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ውስጥ በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ያሳየነውና ያመጣነው ሕዝባዊ ለውጥ ራስን በምግብ ለመቻል በምናደርገው እንቅስቃሴ ላይ አወንታዊ ጥላውን አጥልቶ አንድ ርምጃ አንፏቆናል፡፡

ያለማመንታት ያለፉት አምስት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ ምርጦቻችን ነበሩ ማለት ይቻላል። በተለይ በአንክሮ እንዲሰራባቸው ይፋ በተደረጉት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፣ አምራች ኢንዱሰትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎች ላይ ሰፋ ያለ ስራ በመሰራቱ የአሁኑን ሽልማት ጨምሮ ሌሎች በርካታ ለውጦችን እያስተናገድን እንገኛለን፡፡ ከዚህ የአምስት ዓመት ለውጥ ጋር ሊነሳ የሚችለው በግብርናው ዘርፍ የተሰሩ ተጨባጭ ስራዎች ናቸው፡፡

ቀደም ሲል ጾም ይውሉ የነበሩ፣ ካለጥቅም የተቀመጡ፣ በዳዋና በአረም የተዋጡ መሬቶች በማሻሻያ ትግበራው ምርት እንዲሰጡ የተደረገበት ሁኔታ የዚህ ተሀድሶ አንድ አካል ሆኖ የሚነሳ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ድርቅን የሚቋቋሙና የውሀ ፍጆታቸው ቁጥብ የሆኑ ሰብሎችን የማምረት ስራው አበረታች ከመሆኑም በላይ በቀጣይነት በተስፋ ሰጪነቱ የሚነሳ ነው፡፡

በልዩ አትኩሮት እየተሰራባቸው ያሉ የስንዴ፣ የጤፍ፣ የበቆሎና የገብስ ምርቶች ገበያውን ከማረጋጋትና የውጪ ተረጂነትን ከማስቀረት አኳያ ሚናቸው የላቀ ነው፡፡ እኚህ የምርት ውጤቶች እንደውሀና ለም መሬት ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶች በመጠቀም ያከናወናቸው ናቸው። በቀጣይም በተሻለ ቴክኖሎጂና በተማረ የሰው ኃይል ታግዘው የተሻለ ምርት እንዲሰጡ እየተደገ እንደሆነ በተለያዩ መግለጫዎች ላይ የሰማነው እውነታ ነው፡፡

ሌላው የዚህ ማሻሻያ አንድ አካል የሆኑት የወተት፣ የስጋ፣ የዶሮ፣ የአሳና የማር ምርቶች ናቸው፡፡ ከራስ ፍላጎት በላቀ ሁኔታ በኢኮኖሚ ግንባታ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ በማድረግ ጠጠር በማዋጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ መጪውን ጊዜ በበጎ እንድንማትር የሚያደርጉ እንደሌማት ትሩፋት አይነት ወጪ ቀናሽ ስትራቴጂዎች ከጀመርነው ራስን በምግብ የመቻል ንቅናቄ ጋር አብረው ትግላችንን ፍሬአማ አድርገውታል፡፡

እኚህ ሁሉ እውነታዎች በአንድና ሁለት ቃል ቢገለጹ ‹የላቀ አመራርነት ከሕዝባዊ ተሳትፎ እና ቁርጠኝነት ጋር› የሚሉ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ለዓለም አቀፍ ሽልማትም አጭተውናል፡፡ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በዚህ ደረጃ ራስን መቀየር በእውቀትና በቁርጠኝነት የታገዘ አመራርነት ካልሆነ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡

ድሀ ነን ብለን ስናወራ ዘመናት ተቆጥረዋል። በተረጂነትና በልመና ብዙ ዓመታትን ተሻግረናል። ዋናውና ሀገርን ሊቀይር የሚችለው በቁርጠኝነት የታገዘ ሁሉን አቀፍ ልማታዊ እንቅስቃሴ ነው። ስራ ጠልነትን ውድቅ ያደረገ በራስ እውቀት፣ በራስ ልጆች፣ በራስ የተፈጥሮ ጸጋ ራስን ከድህነትና ከተረጂነት ነጻ ማውጣት ማለት ይሄ ነው፡፡

የሕዝብ ቁጥር እና ፍላጎት ያልተጣጣመባት ሀገር ከአርምሞ ለመውጣት ጥበብ የታከለበት የአመራርነት ብቃት የማስፈለጉን ያክል ምንም አያስፈልጋትም፡፡ ድሀ ነን ብሎ ከማውራት ይልቅ ከድህነት የሚወጡበትን መላ መፈለግ፣ አልችልምና አይሳካልኝም ብሎ እጅን አጣጥፎ ከመቀመጥ ሁሉንም ነገር መሞከር፣ በአንድነትና በሕብረት ለጋራ ክብር መረባረብ አንዱና ማንም እንዳይደርስበት የተደበቀ ሀገርን ከድህነት መታደጊያ መንገድ ነው፡፡ እኛም በመንግስታችን መሪነት በዚህ በኩል አልፈን ነው ራሳችንን ነጻ ከማውጣት እኩል ሽልማት እያገኘንባቸው ነው።

ያለፉት ጊዜ የሕዝብ ቁጥራችን ከፍላጎታችን ጋር ያልተጣጣመበት፣ የኤክስ ፖርት ምርታችን ወደሀገር ውስጥ ከምናስገባው ጋር አቻ የሌለው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከአፍሪካ የውሀ ገንቦነት በስተቀር የጣመ ስም ሳናተርፍ፣ ብዙ ለም መሬቶችን ከእልፍ የተፈጥሮ ጸጋዎች ጋር ይዘን፣ በሰው ኃይልና በወጣት ቁጥር ከፊት ቆመን ምንም አልሰራንም ነበር፡፡ እኚህ ሂደቶች ቀስ በቀስ ኢኮኖሚውን እንደሚያሳሱት የታመነ ነው።

ለእንደዚህ አይነቱ ችግር መፍትሄ ሆኖ ከፊት የሚመጣው ደግሞ የሀገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ እና ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን መቀነስ በዋናነት ደግሞ በግብርናው ዘርፍ ላይ የማሻሻያ ርምጃዎችን መውሰድ ነው፡፡ በዚህ በኩል የተሳካ ለውጥን አስመዝግበናል፡፡ በተሻሻለው የግብርና አቅጣጫ ስንዴን ከውጪ ማስገባጥ አቁመን፤ የውጪ ገበያን ለመቀላቀል እያሟሟቅን ነው፡፡

በበጋ መስኖና በመኸር የአዝመራ ወቅት ሰፊ መሬቶች በስንዴ ተሸፍነው ያየንበት ጊዜ ሁሉ ሞልቶን ባለመቻል እጃችንን አጣጥፈን ለተቀመጥነው ለእኛ እንደብርቅ የሚነሳ ነው። ይሄ የሆነው እንግዲህ አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ካለፈው ይልቅ የአሁኑ..ከአሁን ደግሞ መጪው ጊዜ የበረታ ተስፋን የሚሰጠን ነው፡፡

በእርዳታ ስንዴ የምትታወቅ ሀገር፣ የምታስገባው በዝቶ የኢኮኖሚ መዋዠቅ የተፈጠረባት ሀገር በአጭር ጊዜ ውስጥ በበረታ አመራርነት፣ ከመቀበል ወደመስጠት መሸጋገሯ እውን የማይመስል ግን ደግሞ እውን የሆነ ነገር ነው፡፡ እነዚህ ሂደቶች ናቸው በዓለም አቀፉ መድረክ ፊት በጠቅላይ ሚኒስትራችን በኩል ሀገራችን እንድትሸለም ያደረጓት፡፡

ሽልማቱ ሀገር የምትነሳበት፣ ሕዝብ የሚከበርበት ከሁሉ በላይ ደግሞ የድህነት ታሪካችን ቀለሙ የሚደበዝዝበት መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ አንድ ሀገር ወይም አንድ ድርጅት ሽልማት ሲሰጥ በብዙ ግምገማ ውስጥ አልፎ ነው፡፡ የአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትራችን ሽልማት የአምስት ዓመት የአመራርነት ጥበብ፣ የዓመታት የሕዝብ እንቅስቃሴ፣ የብዙ ጊዜ ቅንጅትና ውህደት ውጤት ነው፡፡ ከዚህ ጋር አብሮ የሚነሳው ድህነትን ለማሸነፍና ተረጂነትን ለማስቀረት ምን ያክል ጠንክረን እየሰራን እንደሆነ ነው፡፡

ሽልማት የጠንካራ አእምሮና ልብ ውጤት ነው፡፡ ሰርተን በማሳየታችንና ተጨባጭ ለውጦችን በማምጣታችን እንሆ በዓለም አደባባይ ውጤቱን ተመልክተናል፡፡ በሽልማቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ራስን በምግብ ለመቻል እንዲሁም ለተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነት ለሰራነው እና እየሰራነው ላለው ስራ እውቅና በመቸሩ ደስታ እንደተሰማቸው ከምስጋና ጋር ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ርሀብን ሙሉ በሙሉ ከማጥፋት ባለፈ የምግብ ተደራሽነትን በማረጋገጥ ሀገራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ጠንክሮ እየሰራ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የተሰሩትን ወደፊትም የሚሰሩትን ከቁርጠኛ አመራርነትና ሕዝባዊ ተሳትፎ ጋር አዋህደው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ለዚህ ለውጥ የበቃነው ያሉንን ተፈጥሮአዊ ጸጋዎች በአግባቡ በመጠቀም፣ ከጠንካራ አመራርነት ጋር ሙያዊ ማሻሻያዎችን በማድረግ ነው ብለዋል። በሽልማቱ ወቅት አጽንኦት ከተሰጠባቸው ንግግሮች መካከል በቀጣይ የላቀና የበረታ ስራ እንደሚሰራ ነው፡፡

ለዚህ ሽልማት መብቃት እንደሀገር ክብሩ ላቅ ያለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ነው የተሸለመችው፡፡ ሕዝቡ ነው አክሊል የደፋው፡፡ በአንድ መሪ በኩል ሀገርና ሕዝብ ነው የሚነሱት፡፡ በአንድ በጎ ስራ በኩል ታሪክና ትውልድ ናቸው የሚንጸባረቁት ስለሆነም ሽልማቱ ትላንትን በመዘከር ዛሬን በማውሳት ለነገ ኃይል የሚሆን መሆኑ እሙን ነው፡፡ በጀመርነው መንገድ ለመቀጠላችን ዋስትና ከመሆን እኩል አደራ የሚሆንም ነው፡፡

በቁርጠኛ አመራርነት እና በሕዝባዊ ተሳትፎ በዓለም አቀፍ መድረኮች ፊት ስማችን ሲነሳ ይሄ ለብዙኛ ጊዜ ነው፡፡ የሰሞኑ የፋኦ ሽልማት ለየት የሚያደርገው በብዙ ተግዳሮትና ውጣ ውረድ ውስጥ ሆነን አመርቂ ድል መቀዳጀታችን ነው። የትንሳኤዎቻችን ምልክቶች በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ሲፈነጥቁ ማየት ከጀመርን ሰነባብተናል። በኢኮኖሚው፣ በዲፕሎማሲው ከቀጠናው ትስስር እስከ ዓለም አቀፍ ውህደት ድረስ ስማችንን የበረታበት ጊዜ ላይ ነን፡፡

ወደትላንት መለስ ስንል ደግሞ ስለሰላም ያገኘነውን ታላቅ ክብር እናገኛለን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዓመታት በፊት ስለሰላም በሰሩት ታላቅ ስራ ዓለም አቀፉን የሰላም የኖቬል ሽልማት በመውሰድ ለሰላም ያለንን ቁርጠኝነት ያሳየንበትን አጋጣሚ አንዱ ነው። ከትላንት እስከዛሬ ባለን የተግባቦትና የውይይት መርህ በእርቅና በይቅርታ እንዴት አብሮ መኖር እንደሚቻል ለዓለም ያሳየንበት ከክብራችን ትልቁን ነው፡፡

ስለሰላም በከፈልነው ዋጋ የሰላም ሀገር እና የሰላም ሕዝቦች ተብለን ኒሻን አጥልቀናል፡፡ ያ አጋጣሚ ከየትኛውም ሁነት በላይ የሀገርን ገጽታ በበጎ የሚያነሳ ነው፡፡ ስለኢትዮጵያ የተዘመረበት፣ የተዘፈነበት፣ የተነገረበት፣ የተወራበት ጊዜ ነው፡፡ ታሪክ ራሱን ተክቶ አሁን ደግሞ በሌላ ዓለም አቀፍ ሽልማት መጥተናል፡፡ ይሄኛውም እንደዛኛው ሁሉ በበጎ የምንነሳበት፣ እጆቻችን ለስራ፣ ሀሳቦቻችን ለተግባቦት የተዋሃዱበት በሀገር ገጽ ግንባታ ላይ ሰፊ ድርሻ ያለው ነው፡፡

ስለሰላም በእርቅና በተግባቦት ከወንድሞቻችን ጋር ታርቀን፣ ከጎረቤቶቻችን ጋር ተቃቅፈን አንድነትን የፈጠርንበት ያ ጊዜ የታሪካችን ደማቁ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በልማቱም ሆነ በሰላሙ ጉዳይ አሁንም የሚቀሩን የቤት ስራዎች አሉ፡፡ እርቅና ተግባቦትን ከፊት አስቀድመን ልዩነቶቻችንን አጥበን የጀመርነውን ልማት ማስቀጠል ቀዳማይ ጉዳያችን ነው፡፡

ሰላምና ልማት ከየትኛውም ምድራዊ ኃይሎች በላይ እንዳይለያዩ ሆነው የተጣበቁ ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት አሁን ላይ ርእሱን ባላስታወስኩት መጣፍ ውስጥ .‹ዓለም ከሰላም ውጪ ሁሉን አጥታ መኖር ትችላለች› የሚል አንብቤያለሁ። ይሄ ማለት ሰላም በምድር ላይ በምንም የማንደራደርበት ጉዳያችን እንደሆነ ነው፡፡

እንደ እድል ሆኖ በዓለም አደባባይ ፊት የተሸለምነው በሰላም እና በልማት ነው፡፡ በትንሽ ሰላም ውስጥ ለሽልማት የታጨንበትን ይሄን ያክል ብርቱ ስራ ከሰራን በእርቅና በይቅርታ፣ በውይይትና በተግባቦት ብንጸና ደግሞ ከዚህም በላይ መስራት እንደምንችል የሚያመላክት ነው፡፡

በዓለም አቀፉ መድረክ ፊት ስለሰላምም ሆነ ስለልማት ሽልማት ለመቀበል ራሱን የቻለ አስፈላጊ መስፈርት ያለው ነው፡፡ ከነዚህ ዘርፈ ብዙ መነሻዎች ውስጥ ቀጠናዊና አፍሪካዊ ፈቀቅ ሲልም ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው አስተዋጽኦ መኖር አለበት። የሰላም ኖቬል ሽልማት ስናገኝ እኚህ መስፈርቶች ታይተው ነው፡፡

በምግብ አቅርቦትና በተመጣጠነ ምግብ ዋስትና ተጨባጭ ለውጥ ማምጣታችንን ስናስመሰክር በእኚህ መስፈርቶች ተፈትሸን ነው፡፡ በቁርጠኝነት አሸንፈናል ወደፊትም ልናሸንፋቸው የሚገቡ በርካታ ተግዳሮቶች አሉብን፡፡ ሰላምን ለልማት..ልማትን ለሰላም በሚል መሪ ሀሳብ ተነቃንቀን አዲስ ታሪክ እንደምንጽፍ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡ ላንቆም ላንዝል ከሽልማትና ከለውጦቻችን ጋር ወደፊት እንላለን ! ፡፡

 ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ጥር 24/2016

Recommended For You