የምርት ብክነት- የወቅቱ አንገብጋቢ አጀንዳ

ወቅቱ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ወሳኝ የምርት መከዘኛ እና መሰብሰቢያ ወቅት ነው፡፡ በተለይም የሰብዕል እህሎች የሚታጨዱበትና ወደ አውድማ የሚወሰዱበት እና የሚወቃበት ነው። ይሁንና በአብዛኛው አሠራሩ ባህላዊ ከመሆኑ የተነሳም ምርት ለከፍተኛ ብክነት የሚዳረግበት ነው፡፡

በእርግጥ የምርት ብክነቱ በዚህ ወቅት ብቻ ሳይሆን የተመረተው ወደ ቤት ከገባ በኋላም ምርት በሚከዘንበት ወቅት አሠራሩ በተለመደው መንገድ ባህላዊ ከመሆኑ የተነሳ ተጨማሪ የምርት ብክነት ያጋጥማል። ይህም አርሶ አደሩን በየወቅቱ የሚፈትን መሠረታዊ ችግር ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን አርሶ አደሩ የልፋት ዋጋውን በበቂ ደረጃ እንዳያገኝ እያደረገው ነው፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ኢትዮጵያ 110 ሚሊዮን ሄክታር መሬት አላት፡፡ ከዚህ ሀብት ውስጥ ግማሽ የሚሆነው ለእርሻ መዋል የሚችልና ምርታማነትን በአግባቡ የሚሰጥ ነው፡፡ ይህም ሆኖ በአግባቡ ጥቅም ላይ የዋለው እጅግ በጣም አነስተኛ ነው፤ ቢበዛ ከ25 እስከ 30 ከመቶ የሚሆነው ነው፡፡

ሀገሪቱ ካሉት አጠቃላይ የእርሻ መሬት ውስጥ ደግሞ በመስኖ መልማት የሚችለው 10 ሚሊዮን ሄክታር ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ እየለማ ያለው ገና አንድ ሚሊዮን ነው፤ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው መሬት በመስኖ ማልማት እየተቻለ አልለማም። በሀገሪቱ ከሚመረተው ዓመታዊ የሰብል ምርት ውስጥም በአማካይ ከ25 በመቶ በተለያየ ምክንያቶች ይባክናል።

መረጃዎቹ እንደሚያመለክቱት፤ ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ማምረት ከምትችለው በታች እያመረተች ነው፤ ይህ ደግሞ ገበያን በማረጋጋት፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ ድህነትን እስከ ወዲያኛው ድረስ ተረት ለማድረግ በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ከፍተኛ ፈተና እንደሚሆን ለመገመት የሚከብድ አይሆንም፡፡ በሀገሪቱ አሁን የሚስተዋለው የግብርና ሥራ በአብዛኛው በሚገባው መጠን በቴክኖሎጂ የታገዘ አይደለም፡፡ በተለምዶ አስተራረስ እና የምርት አሰባሰብ ላይ የተደገፈ ነው፡፡ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የነበረው የበሬ እና ገበሬ ቁርኝት አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡

ዘርፉን በቴክኖሎጂ ማዘመን የሚያስችል ሥራ በትኩረት ስላልተሠራ ዛሬም ድረስ የሀገሪቱ ግብርና ከእጅ ወደ አፍ ከመሆን የዘለለ ፋብሪካዎችን በሚፈለገው ደረጃ መመገብ አልቻለም፡፡ ሰፊ እና ለእርሻ ምቹ የሆነ መሬት ቢኖርም በታሰበው ልክ የተትረፈረፈ ምርት ማግኘት ሳይቻል ቀርቷል፤ ከዚህ የተነሳም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በምግብ እህል እጥረት ውስጥ ይገኛሉ።

ሀገሪቱን ክፉኛ እየተፈታተነ ያለውን የምርት ብክነት ማስቀረት መቻል በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የዋጋ ግሽበት ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ውጤታማነት ትልቅ አቅም እንደሚሆን ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡ ጉዳዩ በመንግሥት ፖሊሲ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶለት በሚገባ ሊሠራበት እንደሚገባም ምክረ ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡

የምርት ብክነት በሀገሪቱ ካለው የማክሮ ኢኮኖሚው ጋርም በቀጥታ የሚያያዝ እንደሆነ፤ በዚህ ደረጃ ከፍተኛ የሆነ ምርት እየባከነ ማክሮ ኢኮኖሚውን አያዛባውም ማለት እንደማይቻል ይናገራሉ፡፡ አስቸኳይ በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ሊፈለግለት እንደሚገባ ይመክራሉ። በየጊዜው እየጨመረ ካለው የሕዝብ ቁጥር እና የዜጎች መሠረታዊ ፍጆታ በፍጥነት እየናረ ባለበት ሁኔታ የምርት ብክነት ፈጥኖ መከላከል ካልተቻለ፤ ሊያስከትከል የሚችለው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ከፍያለ ይሆናል፡፡

ምርት ከተሰበሰበና ጎተራ ከገባ በኋላም በአይጥና ነብሳት እንዳይበላ የጥንቃቄ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ከአርሶ አደሮች ጋር የቀረበ ግንኙነት መፍጠርና ግንዛቤዎችን ማሳደግ ተገቢ ነው። የልፋቱ የተሻለ ተጠቃሚ የማድረግ ትክክለኛ መንገድም ነው። አርሶ አደሩ ከቴክኖሎጂ ጋር ያለውን ቁርኝትና ልምምድ በማሳደግ የምርት ብክነት የሚቀንስበትን መሠረታዊ ግንዛቤ መፍጠር፤ በማንኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች እንደ አስፈላጊነቱ እና እንደየምርቶቹ ሁኔታ የምርት ብክነትን ለመቀነስ ዘመናዊ የሰብል መሰብሰቢያ ማሽን በብዛት ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን ያለው የሚበረታታ ሆኖ መንግሥትም ለጉዳዩ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ ሊንቀሳቀስ ይገባል፡፡

በዚህ ደግሞ በውጤታማነቱ በአፍሪካ ደረጃ እንደተምሳሌት የሚነገርለት የሀገሪቱ ግብርና ኤክስቴንሽንን እንደ አንድ ስትራቴጂክ ማስፈጸሚያ አቅም አድርጎ መውሰድ፤ የምርት ብክነት መከላከልን ተጨማሪ የትኩረት አቅጣጫው አድርጎ እንዲወስደው ማድረግም ይቻላል። ከችግሩ አሳሳቢነት አንጻር የፖሊሲ ማዕቀፍ የሚያስፈልገው፤ ከዚያም ባለፈ የምሁራንን ወይንም በዘርፉ የሠለጠኑ ባለሙያዎች ንቁ ተሳትፎ በስፋት የሚጠይቅ ስለመሆኑም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

እንደ ሀገር በቅድመ ምርትና ድህረ ምርት ላይ የሚስተዋሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ማስተካከል ላይ ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር ሊከተሉ ይገባል፡፡ በተለይም ምርትን ከብክነት ለመታደግ ቴክኖሎጂ እና የቴክኖሎጂ ሥርፀት ላይ በአንክሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የምርት ብክነትን በማስቀረት ውጤታማ የሆኑ ሀገራትን ምርጥ ተሞክሮ እና ልምድ መቅሰምም እጅግ አስፈላጊው ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ኢትዮጵያ ምርትን ከብክነት ለመከላከል ያላትን አቅሞች፣ በተለይ ጽንሰ ሃሳብ እና ተግባርን በማዛመድ ይህ ነው የሚባል ሀገራዊ ውጤት ማስመዝገብ አልቻለችም፡፡ ምርት ከተመረተ በኋላ የሚስተዋለው ከፍተኛ ብክነት በበቂ ደረጃ አልተገታም፡፡ በመሆኑም ችግሩን እንደ አንገብጋቢ ችግር ወስዶ ለመፍትሔ መትጋት ለይደር የማይተው የቤት ሥራ ነው። በዚህ ላይ ሁሉንም አማራጮች መጠቀም ይገባል፡፡

 ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን ጥር 24/2016

Recommended For You