ድምቀት የጎደለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሚያዘጋጃቸው ውድድሮች መካከል ትልቁ የሆነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በ1963 ዓ∙ም ነበር የተጀመረው። ውድድሩ ሀገርን በዓለም አቀፍ ደረጃ መወከል የቻሉ አትሌቶችን ማፍራት ዋነኛ ዓላማው ሲሆን፤ አንጋፋዎቹን አትሌቶች እነ ሻምበል ምሩጽ ይፍጠርን ጨምሮ አሁን በውድድር ላይ እስካሉት ወጣት አትሌቶች ድረስ በርካቶችን አፍርቷል። ዘንድሮ ለ53ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በመካሄድ ላይ ያለው ይህ ዓመታዊ ቻምፒዮና አዋቂ እና ተተኪ አትሌቶችን እያፎካከረም ይገኛል።

ከአጭር እስከ ረጅም ርቀት የመም ሩጫ፣ የውርወራ እና ዝላይ ስፖርቶች በሚያካትተው ውድድሩ 5 ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፤ እንዲሁም 27 ክለቦች 1ሺህ 102 የሚሆኑ አትሌቶቻቸውን እያሳተፉ ነው። በተለያዩ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከላት እና አካዳሚ የሚሠለጥኑ ተተኪና ወጣት አትሌቶችም አቅማቸውን የሚለኩበትን እና ሀገራቸውን የሚወክሉበትን ዕድል የሚያስገኝላቸው ውድድርም ነው። በመሆኑም ክለቦችና የማሠልጠኛ ተቋማቱ ትኩረት ሰጥተው በዓመታዊ የውድድር መርሃ ግብራቸው የሚያስቀድሙት ነው።

ከትናንት በስቲያ የተጀመረው ቻምፒዮናው በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ክቡር አቶ ቀጀላ መርዳሳ፣ የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ አቶ ዳዊት አስፋው፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ አትሌቶች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል። ውድድሩ በዓለም አቀፍ ቻምፒዮና ደረጃ መሠረት የመክፈቻና መዝጊያ መርሐ ግብሩ ከሰዓት በኋላ የሚደረግ ሲሆን፤ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ለአትሌቲክስ ቤተሰቡ ሊደርስ ችሏል። ሆኖም ከዚህ ቀደም ይህ ቻምፒዮና ከዚህ ቀደም ይካሄድበት ከነበረው ድምቀት በእጥፍ ባነሰ ሁኔታ መቀጠሉን ለመታዘብ ይቻላል። የኢትዮጵያ ቻምፒዮና በርካታ ደጋፊዎች በተገኙበት ይካሄድ የነበረው በአትሌቶች መካከል በነበረው እልህ አስጨራሽና እጅግ ጠንካራ የፉክክር ስሜት ነበር። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ውድድሩ የተለመደው ድምቀቱ እምብዛም እየታየበት አለመሆኑ የስፖርት ቤተሰቡ የሚስማማበት ነው።

በእርግጥ ቻምፒዮናው ለዓመታት ይካሄድ የነበረው በአንጋፋው የአዲስ አበባ ስታዲየም በመሆኑ ለደጋፊዎችና የአትሌቲክስ ወዳጆች ለመታደም ምቹ ነበር። ስታዲየሙ ከእድሳት ጋር በተያያዘ ውድድሮችን የማያስተናግድ መሆኑ ቻምፒዮናው በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ መም ላይ ለማካሄድ አስገዳጅ በመሆኑ የተመልካቹም ቁጥር ሊቀንስ መቻሉ እሙን ነው። እንደ ሀገር ስፖርቱ እያለፈባቸው ከሚገኙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች መካከል የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አለመኖር ቀዳሚው ነው። ይህንን ሁኔታ በተለይ እየተጋፈጡ ከሚገኙ ስፖርቶች መካከል አንዱ አትሌቲክስ ሲሆን፤ በዚህ የተነሳም ቻምፒዮናውን በአካዳሚው የመለማመጃ መም የውርወራ ስፖርቶችን ደግሞ ሱሉልታ በሚገኘው የቀነኒሳ በቀለ የአትሌቲክስ ማዘውተሪያ እየተካሄደ ይገኛል።

ነገር ግን የውድድሩ ድምቀት ለመደብዘዙ ይህ ብቻውን ምክንያት ሊሆን አይችልም። ይልቁኑ በተወዳዳሪዎች መካከል ያለው የፉክክር መንፈስ እና አቅምንም የሚያካትት ነው። ክለቦችና ማሠልጠኛ ተቋማቱ ከዓመት ዓመት ‹‹ባለህበት እርገጥ›› የሆነ አካሄድ መከተላቸው በአትሌቶች አቅም ላይ አሁንም መልስ ሊገኝለት ያልቻለው ጉድለት እንዲቀጥል ምክንያት በመሆኑ ውድድሩን ሳቢ ሊያደርገው አልቻለም። ከዘመኑ ጋር ሊዘምኑ ያልቻሉ ክለቦችና ማሰልጠኛ ተቋማቱ በሥልጠና እና የስፖርት ቁሳቁስ ማነስ ለውድድር ብቁ ያልሆኑ አትሌቶችን እያፈሩ መቀጠላቸውን ከውድድሩ መታዘብ ይቻላል። ለአብነት ያህል የውድድር ማስጀመሪያ ሕግን ባለማወቅ ከውድድር ውጪ የሚሆኑ፣ በሜዳ ተግባራት ደግሞ መሣሪያዎቹን በትክክል ለመጠቀም ባለባቸው የልምድ ማነስ ዕድላቸውን የሚያበላሹ አትሌቶችን ማንሳትም ይቻላል።

በቀጣዩ ወር በጋና/አክራ በሚካሄደው 13ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ኢትዮጵያ ከአጭር ርቀት እስከ ሜዳ ተግባራት ለመሳተፍ ዕቅድ አላት። በመሆኑም መሰል አትሌቶችን ማሰለፍ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል አስቀድሞ መመልከት ያሻል። ክለቦች ከጊዜው ጋር ለመራመድ ያላቸው እንቅስቃሴ ከማነሱ ባለፈ ፌዴሬሽኑም ውድድሩ ላይ ከወትሮ ያልተለየ አካሄድ መከተሉም ሊነሳ የሚችል ጉድለት ነው። ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ተመሳሳይ ውድድር በተመሳሳይ ሁኔታ ማካሄድ ተሳታፊዎች እንዳይነቃቁ ማድረጉ አልቀረም። በመሆኑም ፌዴሬሽኑ አስገዳጅ መመሪያዎችን በማውጣት፤ እንዲሁም ግንዛቤ በማስጨበጥ ውድድሩ የወትሮ ድምቀቱን እንዲያገኝ ሊተጋ ይገባል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ጥር 23/2016

Recommended For You