የባሕር በር ለተሳለጠ የወጪና ገቢ ንግድ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባሕር ሕግ አንቀጽ 69 ንዑስ አንቀጽ 1 እስከ 5 የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ካለው ባሕር የተፈጥሮ ሀብት እኩል የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። ይህም፣ ዓሣ ማጥመድን እና በባሕር ውስጥ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን ፍለጋን ጨምሮ ሌሎች ከባሕር ተፈጥሮ ሀብት ጋር የተያያዙ ሀብቶች ተጠቃሚነት መብትን ያካትታል።

የዚሁ ሕግ አንቀጽ 125 ንዑስ አንቀጽ አንድ፤ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ያለውን ባሕር የመጠቀም እና የመሸጋገር ዓለም አቀፍ መብት አላቸው። ይህ መብት የባሕር በር በሌለው ሀገር፣ የባሕር በር ባለቤት በሆነው ሀገር እና በቀጣናው መካከል በሚደረግ ስምምነት ሊፈጸም እንደሚገባ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ሁለት ላይ ተመላክቷል።

አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ ደግሞ፤ እነዚህ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በስምምነት ከተደረገ የተለየ የአገልግሎት ክፍያ ከሌለ በስተቀር ለተገለገሉበት ባሕር ምንም ዓይነት የትራፊክ ታክስ ወይንም ሌላ ክፍያ እንደማይጠየቁ ይደነግጋል።

የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በምስረታ ቻርተሩ መግቢያ ላይ ፤ በባሕር ሕግ ጉዳዮች ላይ ባሰፈረው ሀተታ የአፍሪከ ሀገራት የባሕር በር ያላቸውን ጨምሮ ከባሕር ሊያገኙት የሚገባቸውን ጥቅም እያገኙ እንዳልሆነ ያመለክታል፣ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ከባሕር የመጠቀም መብታቸው ሊጠበቅ እንደሚገባ እና ይህም ከዓለም አቀፍ መርህ አንጻር ሊታይ እንደሚገባ ይደነግጋል።

ከእነዚህ ዓለም አቀፋዊ የሕግ ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ከውሃ አካላት ካላት ቅርበት አንጻር፤ የባሕር በር የማግኘት መብት እንዳላጣች አመላካች ነው። ይህም ከሁሉም በላይ ሀገሪቱ የወጪ ገቢ ንግዷን በማሳለጥ፣ የጀመረችው ልማት የበለጠ ስኬታማ እንዲሆን ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው። ድንገትም እያደገ ካለው የሀገሪቱ የሕዝብ ብዛት አንጻር የወደብ ጉዳይ የህልውና ጉዳይ መሆኑ የማይቀር ይሆናል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በአምራች ዘርፉ ላይ ከተጋረጡ መሰናክሎች መካከል አንዱ የሎጂስቲክስ ሥርዓቱ በፍጥነት የተሳለጠ አለመሆኑና በዚህም ምክንያት የሚፈጠረው የዋጋ ውድነት ነው። የሎጂስቲክስ ሥርዓት ከአምራች ዘርፍ ውጤታማነት ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው። ፈጣንና ቀልጣፋ የምርት ግብዓቶችና የምርቶች ዝውውር በአምራች ዘርፉ ውጤታማነት ላይ ያለው ተጽዕኖም ቀጥተኛ ተፅዕኖ ነው።

ቀልጣፋ የሎጂስቲክስ ሥርዓት ምርት እንዲጨምር እንዲሁም የምርት ስርጭት ፈጣንና የተሳለጠ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። ግብዓቶችንና ምርቶችን በፍጥነት የማያገኙ አምራቾችና ምርት አከፋፋዮች፣ በምርት ሰንሰለት ውስጥ ውጤታማ ሆነው ሊቀጥሉ አይችሉም።

ከሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ 40 በመቶ ድርሻ ያለው የሎጂስቲክስ ዘርፍ፣ በርካታ ውስብስብ ችግሮች አሉበት። ከእነዚህ ሰንኮፎች መካከል የጭነት ዓይነቶችንና ብዛትን የሚያስተናግድ አቅም አለመኖር፤ መርከቦች በወደቦች አካባቢ ጭነት ለማራገፍ የሚያጠፉት ጊዜና በዚያም ሳቢያ የሚፈጠረው የወደብ መጨናነቅ፤ የተጓተተ የመርከቦች ኦፕሬሽን፤ የማከማቻና የጎተራዎች እጥረት፤ የጭነት መኪኖች በወደብ፣ በኬላዎች፣ በድንበርና በጭነት ክብደት መመዘኛ ጣቢያዎች የሚያጠፉት ጊዜ መብዛት ጥቂቶቹ ናቸው።

ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂ እንደሚያመለክተው፣ የኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ሥርዓት የሎጂስቲክስ ሥርዓት ውጤታማነት መለኪያ በሆኑት የሎጂስቲክስ ጊዜና ወጪ መመዘኛዎች ሲመዘን በእጅጉ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በትራንዚት ጊዜ፣ በዕቃዎች እና በመርከቦች የወደብ ላይ ቆይታ፣ ጭነት ከወደብ በማንሳት አቅምና በመሰል የሎጂስቲክስ የአፈጻጸም መለኪያዎች በተመሳሳይ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ነው።

ይህም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና እየፈጠረ ነው። በችግሩ ውስጥ ዘርፉ የሚመራበት ሕግና ፖሊሲ፣ የተዘረጋው መሠረተ ልማት፣ ዘርፉን የሚመሩና የሚቆጣጠሩ ተቋማት አሠራር፣ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ሰጪዎችና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ብቃት እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች የየራሳቸው ድርሻዎች አሏቸው።

የዓለም ባንክ የሎጂስቲክስ አፈፃፀም ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ ኢትዮጵያ በዋና ዋና የሎጂስቲክስ ክዋኔ መለኪያዎች የጉምሩክ አገልግሎት፣ መሠረተ ልማት፣ ዓለም አቀፍ ጭነት፣ የሎጂስቲክስ ብቃት፣ ክትትል እና ጭነትን በወቅቱ ማድረስ፣ ዝቅተኛ አፈፃፀም ያላት ሀገር ናት። ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ የሚያደርገው ብዙ ሀገራት የሎጂስቲክስ አፈፃፀማቸው እየተሻሻለ ሲሄድ የኢትዮጵያ ግን የበለጠ ማሽቆልቆሉ ነው።

ሀገሪቱ ላለፉት ተከታታይ ዓመታት ያስመዘገበችውን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ተከትሎ የገቢና የወጪ ዕቃዎችና የሀገር ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ በመጠንና በዓይነት በከፍተኛ ፍጥነት አድጓል። በመሆኑም የሀገሪቱን የወጪ ንግድ ልማት ለመደገፍ መከናወን ካለባቸው ቁልፍ ተግባራት መካከል አንዱ ቀልጣፋና ውጤታማ የሎጂስቲክስ ሥርዓት መዘርጋት ነው።

ቀልጣፋ የሎጂስቲክስ ሥርዓትን እውን ለማድረግ በብዛትና በጥራት ያደገ ውጤታማ የወደብ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን እጅግ አስፈላጊ ተግባር ነው። ይህ ዓይነቱ የወደብ አጠቃቀም ከላይ ለተጠቀሱት የሎጂቲክስ ሥርዓቱ ችግሮች ሁነኛ መፍትሔ ይሰጣል። በቀደመው ታሪኳ የብዙ ወደቦች ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ባለፉት 30 ዓመታት በወደብ እጦት ምክንያት ለከፍተኛ ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ተዳርጋለች።

ለወደብ ኪራይ ከፍተኛ ገንዘብ እያወጣች ነው፤ የጭነት አገልግሎት ሥርዓቱ ፈጣንና ቀልጣፋ ባለመሆኑ የሀገሪቱ የአምራች ዘርፍ የምርት ግብዓቶችን በሚፈለገው ፍጥነት እንዳያገኝና በሀገር ውስጥ ተመርተው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በአጭር ጊዜ ለዓለም ገበያ እንዳይደርሱ ትልቅ መሰናክል ሆኗል።

ከባሕር በር በቅርብ ርቀት ላይ እያለች የወደብ ተጠቃሚነትን የተነፈገችው ኢትዮጵያ ብዙ ዋጋ እየከፈለች እስካሁን ቆይታለች። የምጣኔ ሀብቷ እያደገና የሕዝብ ቁጥሯም እየጨመረ የመጣ በመሆኑ የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ከሆነ ሰነባብቷል። በዚሁ ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ ከ30 ዓመታት በፊት የሁለት ወደብ ባለቤት የነበረች ቢሆንም አሁን ላይ የሕዝብ ቁጥሯና ኢኮኖሚዋ በብዙ እጥፍ አድጎ አማራጭ ወደብ የሌላት በመሆኑ መቸገሯን አንስተው ነበር።

ኢትዮጵያ ይህንን ትልቅ ችግሯን የሚያቃልልና ብሔራዊ ጥቅሟን በእጅጉ ሊያስጠብቅ የሚችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሌ ላንድ ጋር በቅርቡ ተፈራርማለች። ይህ ስምምነት የኢትዮጵያ የአመታት ስብራት የሚጠግን ከመሆኑ ባሻገር በቀጣናው ሊኖራት የሚገባውን የኃይል ሚዛን በማስጠበቅ የሚጫወተው ሚና የጎላ ነው። ከዚህ አንፃር ሁሉም ዜጋ ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ሊንቀሳቀስ ይገባል።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ጥር 23/2016

Recommended For You