ያለ አግባብ እየባከነ ያለው ሀብታችን!

ድሮ በእርሻና በጂኦግራፊ ክፍለ ጊዜ አስተማሪዎቻችን ሲያስተምሩ ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብቷ ከአፍሪካ አንደኛ፣ ከዓለም አሥረኛ ናት ሲባል ከአስተማሪዎቻችን የሰማሁትን አሁንም ድረስ አስታውሳለሁ፡፡ እንደዛሬው የቆዳና የሌጦ ዋጋ ባልወደቀበት ዘመን እንኳን ሀገራችን በቁጥር ብዙ እንስሳት ቢኖራትም ከእንስሳት ሀብቷ የሚገባትን ያህል ጥቅም እያገኘች አይደለም ብለው ምሑራን ይተቹ ነበር፡፡

የምሑራኑ ትችት የሚያጠነጥነው ሀገሪቱ ከእንስሳት ሀብቷ በቂ ሥጋ፣ ወተትና የወተት ተዋፅዖ አምርታ ለውጭ ገበያ ባለማቅረቧ ነበር፡፡ አሁን ግን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ኢትዮጵያ የቆዳና ሌጦ ተጠቃሚነቷ አሽቆልቁሎ፤ ቆዳና ሌጦ በየቆሻሻ መጣያው ተጥሎ ውሻ ሲጎትትው ማየት የተለመደ ነው፤ ከውሻ የተረፈውም ለጤና ጠንቅ እየሆነ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ደግሞ ለአንድ ሀገሩን ለሚወድ ዜጋ ትልቅ የራስ ምታት ነው፡፡

በአለፉት ጊዜያት እንደ ሀገር ለቆዳና ሌጦ ልዩ ትኩረት ይሰጠው ስለነበር፤ ሀብቱ ከቡና ቀጥሎ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ ሸቀጦች አንዱ ነበር። ከዚህ የተነሳም የሚያመርቱትና የሚሰበስቡት አካላት ለሀብቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር። ሀብቱን በማልማት ሆነ ወደገበያ በማቅረብ ሂደት ውስጥም የሚመለከታቸው አካላት ተናበው ይሠሩ ነበር።

ዛሬ ዛሬ ቆሻሻ በአግባቡ ተሰብስቦ ጥቅም ላይ ከዋለ የሀብት ምንጭ ነው በሚባልበት ዘመን ለውጭ ምንዛሪ መሠረት የነበረው ቆዳና ሌጦ እንዳልባሌ ዕቃ በየቆሻሻ መጣያው ተጥሎ ማየት፤ ለምን በዚህ ልክ ወደቀ የሚለውን ጥያቄ መጫሩ አይቀርም፡፡ የሚመለከታቸው አካላት በጉዳዩ ዙሪያ ዝምታን መምረጣቸውም ተመሳሳይ ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም ፡፡

ቢያንስ ቢያንስ የየከተሞች ማዘጋጃ ቤቶች ይህንን ትልቅ የሀገር ሀብት አግባብ ባለው መንገድ በመሰብሰብ መሰብሰብ ባይችሉ እንኳን፤ ከቆዳና ሌጦው የሚፈጠረውን የአካባቢ ብክለት ለማስወገድ ኃላፊነት ወስደው አለመንቀሳቀሳቸው ለብዙ ትዝብት የሚዳርጋቸው ነው፡፡

እዛሬ ላይ ትዝታ ሆነ እንጂ፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት ለዓመት በዓላት የሚታረድ በሬ፣ ላም፣ በግና ፍየል ተገዝቶ በየግቢው ሲታሰር የቆዳና ሌጦ ነጋዴዎች በቂ ብር ካላቸው ሙሉውን ከፍለው፤ በቂ ብር ከሌላቸው ቀብድ ሰጥተው በዕለቱ በሚውለው ዋጋ ሊገዙ ተስማምተው ይሄዱ ነበር፡፡

ሌላው የበዓሉ ታዳሚዎች ከቤተሰቡና ከጎረቤቱ ጋር እየተጫወተና እየተዝናና ሲያከብር የቆዳና ሌጦ ነጋዴዎች ለራሳቸው ተገቢውን ትርፍ አግኝተው፤ በተዘዋዋሪም ለሀገራቸው የውጭ ምንዛሪ ምንጭ የሆነውን ቆዳና ሌጦ በመሰብሰብ ሀገራቸው የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ ቀላል አልነበረም፡፡

ከዚህም ባለፈ ምናልባት አድራሻውን ያላገኙት የበሬ ቆዳ፣ የፍየልና የበግ ሌጦ እንዳያመልጣቸው ከላይ ታች ሲባዝኑ መዋላቸው የተለመደ ተግባራቸው ነበር፡፡ እነዚህ ነጋዴዎች ለአካባቢው ወጣቶችም ኮሚሽን በመክፈል ገንዘብ ሰጥተው ሀብቱን በመሰብሰብ ለሥራ ዕድል ፈጠራም አስተዋፅዖ ነበራቸው፡፡

ዜጎችም ከገዟቸው እንስሳት ቆዳና ሌጦ ጠቀም ያለ ዋጋ ያገኙ ስለነበር ቆዳና ሌጦ እንዳይቀደድ ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር። ለዚህም ለአራጁ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ መስጠት የተለመደ ነበር፡፡ አራጁም ቆዳውን ወይም ሌጦውን ካበላሸ ሊከፈለው የነበረው ገንዘብ ስለሚቀንስበት እጅግ በጣም ጥንቃቄ ያደርግ ነበር፡፡

የሚገርመው ይህ ሁሉ ትዝታ በሆነበት ሁኔታ፤ በበዓላት ሰሞን እንስሳቱን ስታርዱ ለቆዳና ሌጦው ጥንቃቄ አድርጉ የሚለው የይስሙላ መልዕክት አለመቅረቱ ነው። ከቆዳና ሌጦ ጥቅም ካልተገኘ /ጥቅም ላይ ካልዋለ/ በምን መስፈርት እና ለምንድን ነው ጥንቃቄ የሚያደርገው ?፡፡

 ቆዳና ሌጦው ጠቀም ያለ ዋጋ ሊያገኝ ቀርቶ፤ የበዓል ሰሞን ቆሻሻ እየሆነ ባለበት ሁኔታ የመልእክቱ አስፈላጊነት እስከምን ድረስ ነው። ይህ ችግር ሁላችንንም ሊያሳስበን የሚገባ ነው፡፡ እያንዳንዳችንን የመፍትሔው አካል እንድንሆን በኃላፊነት መንፈስ እንድንቀሳቀስ ሊገፋፋን የሚገባ ነው ፡፡

አሁን ላይ ሀገራችን እያስመዘገበችው ባለው የኢኮኖሚ ዕድገት ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ ከውጭ ለምታስገባው ሸቀጦች ከፍያለ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስፈልጋት ግልፅ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር ተዳምሮ በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተፈጥሯል። በዚህም ግንባታዎች ሲጓተቱ፣ በአንዳንድ ምርቶች ላይ እጥረት ሲፈጠር ይስተዋላል፡፡

አሁን ላይ እንደ ሀገር በውጪ ምንዛሪ ዙሪያ ያጋጠመንን ችግር በመፍታት ሂደት ውስጥ ለቆዳና ሌጦ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ የውጭ ምንዛሪው ገቢያችንን ማሳደግ የሚያስችል የተጠናከረ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። በየሰፈሩ የሚመነጨው ቆዳና ሌጦ የውሻ መጫወቻ እንዳይሆን የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከተቻለም ቆዳና ሌጦን በጥሬው ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ቢቻል ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ በአንድ ደረጃ ከፍ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህ እንኳን ባይቻል ለውጭ ገበያ በጥሬው የሚላከውን ቆዳና ሌጦ በአግባቡ ሰብስቦ ለገበያ ማቅረብ እንዲቻል የሚመለከታቸው አካላት ፈጥነው ሊንቀሳቀሱ ይገባል፡፡

ይህንን ያለ አግባብ እየባከነ ያለ ሀብት ከብክነት ለመታደግ፤ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች፣ ቆዳ ነጋዴዎች፣ ባለሀብቶችና የሚመለከታችሁ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሐሳባችሁን በማዋጣት የራሳችሁን ጠጠር መጣል ይጠበቅባችኋል። “ልብ ያለው ልብ ይበል” ። አበቃሁ፤ ቸር እንሰንብት፡፡

ጋሹ ይግዛው (ከወሎ ሰፈር)

አዲስ ዘመን ጥር 22/2016

Recommended For You