ፕሮጀክቶቹ የሰላሙ ቀጣይነት መግለጫዎች ናቸው !

ሰላም የልማት ሁሉ መሰረት ነው:: ዘላቂ ልማት ያለ ዘላቂ ሰላም እውን ሊሆን አይችልም:: በሰላም ወቅት የሚካሄድ ልማት በጽኑ መሰረት ላይ እንደ ተገነባ መሰረተ ልማት ይቆጠራል፤ ይህ መሰረተ ልማት በየትኛውም ርደትም ሆነ ርጥበት አይናድም፤አይሰነጠቅ፣ አይዘምም:: ሰላሙ የጠበቀው ልማትም የትኛውም ኃይል ከጠበቀው ልማት ይልቅ ደህንነቱ አስተማማኝ ይሆናል::

የሰላምን ዋጋ ከዚህም ሻገር ብሎ መመልከት ይቻላል:: በግጭትና ጦርነት ሳቢያ ከፈረሰ እንዲሁም ሳይገነባ ከቀረ መሰረተ ልማት የሰላምን ዋጋ መረዳት ይቻላል:: እነዚህ መሰረተ ልማቶች ባለመኖራቸው ሳቢያ የሚጎዳውን ህዝብ ማሰብ ይቻላልና:: ከጠፋው የሰው ሕይወት፣ ከሞቀ ቤቱ ተፈናቅሎ በመጠለያ ከሚገኝ ህዝብ ስቃይ፣ ለስደት ከተዳረገ ወገን ፈተና፣ ከወደመው ጥሪትና ሀብት፣ ከተንሰራፋው አለመረጋጋት ሁሉ የሰላምን ዋጋ በሚገባ መረዳት ይቻላል::

በሰላም እጦት ሳቢያ በቀረ፣ በተጓተተ እንዲሁም በወደመ ፕሮጀክት ሳቢያ ህዝብና ሀገር ያጡት ተጠቃሚነትና ምን ያህል ወደኋላ እንደተመለሱ ሲታሰብም እንዲሁ ሰላም ለልማት ያለውን ፋይዳ ለመረዳት የሚቸግር አይሆንም ::

ኢትዮጵያውያን የሰላም ዋጋ ሲገልጹ ‹‹እየዬም ሲዳላ ነው›› ይላሉ:: አዎን፣ ሰላም በታጣ ወቅት ሰው ቢሞት በስርአቱ በቆየው ልማድ፣ ወግና ስርአት መቅበር አይቻልም፤ እንደ ፊቱ ተጎጂን ማስተዛዘንም አይቻልም:: ይህም ሌላው የሰላም ዋጋ ማሳያ ነው::

ሰላም ባለመኖሩ ሳቢያ ብዙ የሚጎል ሊኖር ቢችልም፣ ከመሆን የማይቀር እንዳለም መገንዘብም ይገባል:: ሰላም የለም ተብሎ ከመብላት ከመጠጣት መታቀብ አይቻልም፤ በስሱም ቢሆን ይበላል፤ ይጠጣል፤ እንኳን ሰው ጆንያም በእህል ነው የሚቆመው ይባል አይደል::

ለእዚህ ደግሞ ለክፉ ቀን ተብሎ ከተቀመጠው በተጨማሪ መስራትም የግድ ሊሆን ይችላል:: ከዚህም በሰላም አለመኖር ሳቢያ ከመሰራት የማይቀር እንዳለም እንረዳለን:: የሆነውን ያህል ከመስራት መታቀብ አይቻልም:: በአስቸጋሪ ወቅት፣ ሰላም በሌለበትም ወቅት ቢሆን እንደልብ ተንቀሳቅሶ መስራት ባይቻልም፣ መስራት ግን የግድ ይሆናል:: ካልተሰራ መኖር አይቻልምና::

ሰፋ ወዳለው የሥራ አይነት ወደ ልማቱም ሲገባ እንደዚሁ ነው፤ የልማቱ ልክ ይለያይ ይሆናል እንጂ በሰላም ጊዜ ያለውን ያህል ባይሆንም በልማቱ መንቀሳቀሱ አይቀርም:: ጦርነት ተግ ሲል ግጭት ጋብ ሲል በሬ መጠመዱ፣ ማሳ በዘር መሸፈኑ፣ ዶማ አካፋ መነሳቱ ያለ ነው:: ለሸቀጥ ፈላጊው ለሸማቹ የኢንዱሰትሪውንም የግብርናውም ምርት ማቅረቡም አለ::

ይህን ሁሉ ስል ሰላም ከሌለ የለማው ሊወድም፣ እቅዱ ሊሰረዝ አይችልም ማለቴ አይደለም፤ ይህ ብቻም አይደለም፤ ማሰብም ሊያዳግት አይችልም ማለቴም አይደለም:: ይህ ሁኔታ ጦርነትና ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች በሚገባ የታየ እውነታ ስለሆነ እሱን ወደማብራራት አልገባም፤ ጦርነትና ግጭት በሌለበት አካባቢ ያሉ ሰዎችም ጭምር ጦርነት እና ግጭት ሊያደርሱ የሚችሉትን ምስቅልቅል በሚገባ ያውቁታል:: ለዚያም ለእኛ ሀገር አንባቢ:: እናም የሰላም እጦት የብዙ ነገር ጸር ነው::

ሰላም ባለመኖሩ ሳቢያ የቆመ፣ ሰላም መመለስ ሲጀምር መንቀሳቀስ ይጀመራል፤ ደረጃው ሊለያይ ይችላል እንጂ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ለመኖር ሲባል ወደ መስራት ይገባል:: አንድ አንድ እየተባለም ወደ ልማት ይገባል:: የሰላም እጦትና የሰላም እጦት ጠበሳዎች ከልማት ጨርሶ አያቅቡም፤ የልማቱ ልክ ላይ ልዩነት ሊኖር ይችል ይሆናል እንጂ የልማት ጠረኑ ጨርሶ አይጠፋም::

እርግጥ ነው ብዙ ሚሊዮን እና ቢሊዮን በር የወጣባቸውና በርካቶችን እንጀራ እያበሉ የነበሩ የኢንቨስትመንት ተቋማት፣ እንደ ትምህርት ቤት የጤና ተቋማት ያሉ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ማእከላት በሰላም እጦት ሳቢያ ወድመው የተመለከተ፣ ስለጉዳዩ የሰማ፣ ሌላ ተመሳሳይ ተቋም በአካባቢው ለእዚያውም ሰላም በሌለበት ሁኔታ መገንባት ሊከብደው ብቻ ሳይሆን ላያስበውም ጭምር ይችላል:: እነዚህ የሰላም እጦቱ ያስከተላቸው ውድመቶች ፊት ለፊት በሚታዩበት ስፍራ አይደለም በብዙ ርቀት ላይ ሆኖም ተመሳሳይ ተቋማትን መገንባት አይደለም ማሰብ ሊከብድ ይችላል::

ይሁንና ተቋማቱን የሚፈልጋቸው ህዝብ አለና መገንባቱ የግድ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም:: የግብርና ፣ የንግድ ፣ የህክምና ሥራ ሊያስፈልጉ ይችላሉና ተቋማቱ ፈርሰውም ከሆነ መልሰው መገንባታቸው ወይም አዳዲስ መሰረታቸው ሊያስፈልግ እንደሚችል መጠራጠር የሚያስፈልግ አይመስለኝም:: ግንባታው በልማቱ አይነትና ለልማቱ በሚያስፈልገው ፋይናንስ አቅርቦት የሚወሰን ይሆናል፤ የጦርነትና ግጭት ስጋት እያለም በእነዚህ ላይ መሰራቱ አይቀሬ ነው::

በቅርቡ ከአንድ ግጭት ላይ ከቆየ የክልል ቢሮ ኃላፊ ጋር ባደረግነው ቃለ ምልልስ ኃላፊው በክልሉ እየተካሄደ ስለነበረው የመኸር አዝመራ ስብሰባ ሲያብራሩ የመኸር አዝመራ ስብሳበውን አስፈላጊነት ከቀይ መስቀል ስራ ጋር አመሳስለውታል፤ ክልሉ በግብርናው ላይ አልሰራም ማለት በክልሉ ያለውን ችግር ይበልጥ ያወሳስበዋል ሲሉ ኃላፊው ገልጸው፣ የአዝመራ ስብሰባ ሥራ ለክልሉ የቀይ መስቀል ሥራ ያህል ተደርጎ ተወስዶ እንደተሰራበት ገልጸውልኛል:: ይህም የሰላም እጦት እያለም ልማትን ማስቀጠል ወሳኝ ለመሆኑ አንድ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል::

የልማቱ አስፈላጊነት ከዚህም ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል:: ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት አመታት በሰሜኑ አካባቢ ጦርነትና በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ተወጥራ በነበረበት ወቅት ታላላቅ ፕሮጀክቶች ተገንብተውባታል፤ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ወደ ሥራ እንዲገቡም ተደርገውበታል:: ለፕሮጀክቶቹ አያሌ ሀብት ወጪ ተደርጓል::

እነዚህ ፕሮጀክቶች ከጦርነትና ግጭት ቀጣና ብዙ ርቀት ላይ ያሉ ናቸው፤ ይህን ሥራ በጦርነት ቀጣና ውስጥ የተሰራ አርጎ መቁጠር አይቻልም ብሎ የሚሞግት ሊገጥም ይችላል:: ለእዚህም በቂ መልስ መስጠት ይቻላል:: ከእነዚህ ፕሮጀክቶች አንዳንዶቹ ግጭት ይታይባቸው በነበሩ አካባቢዎች የተካሄዱ ናቸው ፤ በውጭው ዓለም ለሀገሪቱ የተሰጣት ገጽታ የጦርነትና ግጭት ሆኖ እያለም ነው እነዚህ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ያሉት::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ በአንድ የልማት ተቋም ምረቃ ይሁን ጉብኝት ላይ ሰላም የለም ተብሎ ልማት እንደማይቆም ያስገነዘቡበት ሁኔታም ለእዚህ አንድ ማጠናከሪያ ይሆናል:: በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት ሀገሪቱ በጦርነትና በግጭት ውስጥ በቆየችባቸው ባለፉት አመታት በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡት የቱሪዝምና የመሳሰሉት መሰረተ ልማቶች መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው::

ባለፉት አመታት የተገነቡት እነዚህ በርካታ ፕሮጀክቶች በሰላም እጦት ወቅትም እጅን አጣጥፎ መቀመጥ እንደማይገባ አስገንዝበዋል:: የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የወንጪ ደንዲ የኤኮ ቱሪዝም መሰረተ ልማት ሲገነባ ነገሮች አልጋ ባልጋ እንዳልነበሩ ይታወቃል፤ ሸኔ ጉዳት ያደረሰበት ሁኔታም ነበር፤ እንዲያም ሆኖ መንግሥት ግንባታውን ከማካሄድ አልተቆጠበም:: ፕሮጀክቱም ተገንብቶ በቅርቡ ተመርቋል:: በሌሎች በክልል መንግሥታትም ሆነ በከተማ አስተዳደሮች እና ዜጎች በርካታ ፕሮጀክቶች የተገነቡት ከኮሽታም በላይ የሆኑ የጸጥታ ችግሮችና ያንን ተከትሎ የተከሰቱ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ባሉበት ነው::

አስቸጋሪነቱ ደግሞ የልማት ፋይናንስ ማግኘት በመቸገር የተወሳሰበ ነው፤ ሰላም በታጣበት፣ ኮሽታ በኮሽታ በተሆነበት ሁኔታ የሚያበድር የፋይናንስ ተቋም አይኖርም:: የፋይናንስ ተቋማት ማበደር አይደለም ሰዎች ካስቀመጡት ገንዘብ ለልማቱ የሚያስፈልጋቸውን ያህል ገንዘብ ለመስጠት የማይችሉበት ሁኔታም ጭምር የሚያጋጥምበት ሆኔታ ይኖራል::

ተቋራጮች ፣ ሰራተኞች በሰላም እጦቱ ሳቢያ በአካባቢው መቆየት የማይችሉበት፣ የግንባታ ግብአት አቅራቢዎችም እንዲሁ ግብአት ለማግኘት፣ ለማጓጓዝ የሚቸገሩበት ሁኔታ ሊያጋጥማቸው ይችላል::

ከዚህ ሁሉ አልፎም ሀገር በጦርነት ቀጣና ውስጥ ሆናም ልማቷን እየሰራች መሆኗ እየታወቀ ጠላቶቿ በሚያነፍሱት አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ አልሚዎች አይደሉም እርዳታ ሰጪዎች ወደ ሀገሪቱ እንዳይመጡ እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ልማቱ እየተካሄደ ያለው::

መንግሥትን ጨምሮ ሌሎች የልማቱ ተዋንያን የሰላም እጦት ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ሳይረዱ ቀርተውም አይደለም ግንባታዎችን የሚያካሂዱት:: አሳምረው ያውቃሉ፤ ሕይወት ይቀጥላል፤ ነገም ሌላ ቀን ብለው በማሰባቸው፣ ባለራእይ በመሆናቸው ነው::

ባለፉት አመታት በክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን ተነጥቀዋል፤ ሌሎች በርካታ ዜጎች አካላቸውን ተስፋቸውን ተነጥቀዋል:: ሀብትና ንብረታቸውን ያጡትንም ቤት ይቁጠራቸው::

በርካታ ሰዎች ከሞቀ ቤታቸው ከእነቤተሰባቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ካምፕ ውስጥ ኖረዋል:: የደረሱት መፈናቀሎች በአንድ ወቅት ሀገሪቱን በተፈናቃይ ብዛት ከፊት ለፊት ከነበሩት የዓለም ሀገሮች ተርታ እንድትሰለፍ ያደረጉበት ሁኔታም ነበር::

ይህ ምስቅልቅል ደርሶባቸው አካባቢውን ለአንዴም ለመጨረሻ ጊዜም የለቀቁም ጥቂት አይደሉም፤ ይህ ብቻም አይደለም፤ ፊታቸውን ወደለቀቁት አካባቢ መመለስ የማይፈልጉ በርካታ ናቸው:: እነሱ ብቻም አይደሉም ዜናውን የሰሙትን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ ሰዎችም ይህ ችግር ባለባት ሀገር አልኖርም ብለው ሀገር ጥለው የወጡም አሉ::

በአንጻሩ በጦርነቱ ወይም በግጭቱ የወደመባቸውን ሀብት በፍጥነት በመተካት ወደ ስራቸው የተመለሱም ጥቂት የማይባሉ ናቸው:: በቀድሞው ደቡብ ክልል አንድ ከተማ በግጭት የተነሳ የሆቴላቸው ዋና ዋና ቁሳቁስ የወደመባቸው አንድ አባት/እሳቸው ድርጊቱ ሲፈጸም በጤና ይሁን በሌላ ምክንያት በአካባቢው አልነበሩም/ ፤ ግጭቱ ከቆመ በኋላ ወደ አካባቢው ደውለው ያሉት ቀልቤን ስለገዛው ነው እሳቸውን ማንሳቴ:: እኚህ ባለሆቴል ወደ አካባቢው ይደውሉና ምን ጠፋ፣ ወደመ ሲሉ ይጠይቃሉ:: በግጭቱ የተዘረፉት፣ የወደሙት ቁሳቁስ ዝርዝር ተነገራቸው::

እሳቸውም ሰሞኑን እልክላችኋለሁ ፤ ስራውን ለመጀመር ተዘጋጁ ሲሉ ይመልሳሉ:: ይህን የሰሙት በስፍራው ያሉ ቤተሰቦች እንዴ ጋሼ … ሲሉ እርምጃቸው ትክክል እንዳልሆነ አርገው ሲመልሱላቸው እሳቸው የሰጡት ምላሽ የሚገርም ነበር:: ‹‹ እሱን ተውት ፤ የሆነው ነገር ጎርፍ ነው፣ አሁን ስለወደፊቱ አስቡ :: ነበር ያሉት::

አዎን የግጭትና የጦርነት ዳፋ ከበድ ነው፤ ግን ችግሩን እንደ ድንገተኛ አደጋ እንደ ጎርፍ ተመልክቶ ወደ ልማቱ መመለስ ትክክለኛ እርምጃ ነው፤ የሆነውን ክፉ ነገር እየመላለሱ ማዳመጥና መተረክ የሚፈይደው የለም:: የህይወትን፣ የሀገርን ቀጣይነት ለማረጋገጥ መስራት እንጂ ሌላ አማራጭ የለም::

በጦርነት ፣ በግጭት ውስጥ የኖሩ ሀገሮች ታሪክም የሚያስገነዝበው ይህንኑ ይመስለኛል:: ጦርነት ያኖረው ጠበሳ ከልማት የሚያቅብ ቢሆን ጦርነት ክፉኛ በልቷቸው የነበሩና ዛሬ እድገትን አሳምረው እያጣጣሙ ያሉት ሀገሮች ለእዚህ እድገት ባልበቁ ነበር:: ከዚያ ትቢያ ወጥተው ነው እዚህ የደረሱት:: ከጦርነት የተረፋቸውን ሀብትና ህዝብ ይዘው እንደ እባብ አፈር ልሰው ተነስተው ነው ለታላቅ ቁም ነገር የበቁት::

ጦርነትና ግጭት ጉዳት አደርሷል፤ ያደርሳል ተብሎ ከመልማት መታቀብ የሚባል ነገር መኖር የለበትም:: እርግጥ ነው፤ የደረሰው ጉዳት መጀመሪያ ላይ ብዙ ሊያስብል ይችላል፤ የመጨረሻው ውሳኔ ግን ፊትን ወደ ልማት መመለስ ነው፤ ህይወት ይቀጥላል፤ ሀገር ትቀጥላለች:: ስለዚህ ይህን የሚመጥን ሥራ መስራት ያስፈልጋል::

የኢትዮጵያ ጠላቶች ሀገሪቱን የጦርነት ቀጣና የግጭት ቀጣና አርገው በሳሉበት ሁኔታ፣ ሀገሪቱ ከእዚህ ማጥ መውጣት አትችልም ባለቡት ሁኔታ በሀገሪቱ በተለይ በመንግሥት እየተካሄዱ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች፣ ጦርነትና ግጭቶች ያደረሱትን ጉዳት አስመልክተው የጠቀስኳቸው አባት እንዳሉት እንደ ጎርፍ በመቁጠር እየተካሄዱ ያሉ ፕሮጀክቶች ናቸው::

የፌዴራል መንግሥት በገበታዎቹ ያከናወናቸው ፕሮጀክቶች ሀገር በጦርነትና ግጭት ቀጣና በተፈረጀችበት ወቅት የተካሄዱና እየተካሄዱ የሚገኙ ናቸው:: ፕሮጀክቶቹ ደግሞ በአዲስ አበባ ብቻ የተወሰኑ አይደሉም፤ በክልሎች ለእዚያውም የመንገድና የመሳሰሉት መሰረተ ልማቶች ፍጹም በሌሉባቸው የሀገሪቱ ገጠር አካባቢዎች ጭምር የሚከናወኑ ናቸው::

እነዚህ ፐሮጀክቶች ጦርነትና ግጭት እዚህም እዚያም አለ ተብሎ እጅ አጣጥፎ መቀመጥ እንደማያስፈልግ፣ ልማቱ መቀጠል እንዳለበት የሚያስገነዝቡ፣ የሀገርና የህይወት ቀጣይነት ማሳያዎች ናቸው::

መንግሥት ገና ብዙ ይሰራል:: በገበታ ለሸገር የአዲስ አበባ ፈርጥ መሆን የቻሉ የህዝብ መዝናኛ፣ የሀገር ገጽታ መገንቢያ ፓርኮችን ገንብቶ ወደ ሥራ አስገብቷል፤ በተደጋጋሚ እንዳስታወቀውም ፓርኮቹ የህዝብ መዝናኛ ስፍራ፣ የቱሪስቶች ቆይታ ማርዘሚያ፣ የከተማ ውበት መሆን ችለዋል:: ይህም በህዝብ ጭምር ተመስክሮለታል::

መንግሥት ይህን ውብ ስራውን በአዲስ አበባ ላይ ብቻ አካሂዶ አላበቃም፤ በገበታ ለሀገር ወደ ክልሎች ይዞ ወጥቷል:: በእዚህም የገበታ ለሀገር የኮይሻ ፕሮጀክት ሁለት አካላት ግንባታቸው ተጠናቋል፤ አንዱ ወደ ሥራ ገብቷል፤ ሌላውም ይቀጥላል:: የወንጪ ፕሮጀክት አካል የሆነው የኤኮ ቱሪዝም መንደርም በቅርቡ ተመርቋል:: የጎርጎራ ፕሮጀክትም እየተጠናቀቀ ይገኛል::

የመንግሥት የልማት ቁርጠኝነት በእነዚህ ሁለት ፕሮጀክቶች ብቻ አላበቃም:: በገበታ ለትውልድም ይቀጥላል:: ለእዚህም በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ፕሮጀክቶች እየተጀመሩ ናቸው::

መንግሥት በተደጋጋሚ እንደገለጸው በተለይ እነዚህን የቱሪዝም መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች እየገነባ ያለው ሁሉንም ሥራ እሰራለሁ ብሎ አይደለም፤ የግሉን ዘርፍ ወደ ልማቱ ለመሳብ ነው:: የግሉ ዘርፍ ይህን ተነሳሽነት በመመልከት ልማቱን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል:: ልማት ሰላም እስኪ ሰፍን ድረስ የማይጠበቅ ስለመሆኑ የልማት ፕሮጀክቶቹ አመላክተዋልና የግሉ ዘርፍም ይህን ተነሳሽነት በመጠቀም ልማቱን ማካሄድ ይኖርበታል::

እነዚህ ፕሮጀክቶች በአስቸጋሪ ወቅትም ልማትን ማካሄድ እንደሚቻል ያመላከቱ ናቸው:: መሰል ፕሮጀክቶችን ሰላም ሲሰፍን ብቻ ሳይሆን መገንባት ያለብን ሰላም ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እያለችም መሆን እንደሚኖርበት አስገንዝበውናል:: ባለፉት አመታት የተገነቡ ፕሮጀክቶችም በእዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው የተካሄዱት:: እንዲህ ሲሆን ፕሮጀክቶቹ የሰላሙ ቀጣይነት መገለጫዎች መሆንም ይችላሉ::

አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You