በብሄራዊ ምክክር -ከግጭት አዙሪት ለመውጣት

ሀገር ከምትጸናባቸው መንገዶች ውስጥ የተግባቦት ጽንሰ ሀሳብ ቀዳሚው ነው። ስልጣኔና የዘመናዊነት በትረ ጸዳሎች መነሻቸው ከሌላው ጋር እንዴት መኖር ይቻላል? የሚል ጽንሰ ሀሳብ ነው። በብዙ በርትተን ከሌሎች ጋር እንዴት መኖር እንዳለብን ካልገባን አላዋቂዎች ነን። በዓለም መንደር ከፖለቲካና ከኢኮኖሚ እንዲሁም ከመሰል የፉክክር አውድ እኩል የልዩነትን ጎራ ይከፈለው ይሄ አስተሳሰብ ነው። በብዙ የሀሳብና የፍላጎት መናር ውስጥ እርቅና ምክክርን ያቀፈው ሁለንተናዊው ዓለም ‹ተግባቦትን› የዘመናዊነት ሚዛን ሲል ይጠራዋል። እርግጥ ነው ዘመናዊነት ከማሰብና ሀሳብን ለበጎ ነገር ከመጠቀም የሚጀምር ነው።

በሰው ልጅ የማሰብ አቅም ውስጥ ከተደረሱ ሊዕቀ እሳቤዎች ውስጥ ቀዳሚው በተግባቦት አብሮነትን ማስቀጠል የሚለው ነው። በምክክር አብረን መኖር ካልቻልን አብሮ ሊያኖረን የሚችል ሌላ ምድራዊ ኃይል የለም። አንዳንድ በባህልና በማህበረሰብ ዙሪያ ጥናት የሚያደርጉ አጥኚዎች ሀገርና ሕዝብን፣ ባሕልና ታሪክን የሚያቆራኙት በብዙሀነት ውስጥ በተውጣጣ የጋራ ሀሳብና ተግባቦት ነው። ይሄ ማለት የአንድ ሀገር ትላንትናዊ፣ አሁናዊና ነጋዊ ታሪክ የተወሰነውና የሚወሰነው ማሕበረሰብ ተነጋግሮ ለመግባባት ባለው ልምምድ ልክ ነው ማለት ነው።

ደግሞም እውነት ነው። ያለፉ ታሪኮቻችንን መለስ ብለን ብንቃኝ በአንድ ሀሳብ፣ በአንድ ልብ፣ በአንድ ግብር ጀምረን የጨረስናቸው ናቸው። አሁን ላይ እንደጥንቱ ጸንቶ መቆም አቅቶን የምንገዳገደው ደግሞ ድሮነትን ሽረን እኔነትን በማራመዳችን ነው። ይሄን እውነታ ለመረዳት ጠቢብ መሆን አይጠይቅም። ትላልቅ ድሎቻችን የትላልቅ ሀሳቦቻችን ውጤቶች እንደነበሩ መካድ አይቻልም። ፍሬ አፍርተው ዛሬም ድረስ ባለሞገስ ያደረጉን የታሪክ ገድሎቻችን በሰፊ ሸራ ላይ በአብሮነት የጻፍናቸው እንደሆኑ የሚታወቅ ነው።

ዛሬ የብቻ ታሪክ ለመጻፍ እሽቅድምድም ላይ ነን። ከመቶ ሚሊዮን ቅይጥ ሕዝብ ውስጥ፣ ከሰማኒያ በላይ ጉራማይሌ መልክ ውስጥ በብዙ ባህል፣ በብዙ ታሪክ በተሰናሰለ ማሕበረሰብ ውስጥ እንደምን እኔነት ይቻላል? ስለምን ብቻነት ታሰበ? ሊገባንና እንዲገባን የምፈልገው እውነት እዚህ ጋር ነው ያለው። ኢትዮጵያን የብሄረሰብ እናት፣ የባሕልና የታሪክ አምድ ካልን መነሻችን አንድነት ነበር ማለት ነው። መጀመሪያችን ፍቅርና ወንድማማችነት ነበር ማለት ነው። ታዲያ ይሄ አይነቱ የራስ ወዳድነት አባዜ በዚህ ሕዝብ መሀል ምን ይሰራል? በእኛነት በቅለን በእኔነት መራመድ እንደምን ይቻላል? ተደባልቆና ተቀይጦ ለመኖርና እየኖረ ላለ ማሕበረሰብ የታሪክ ሽርፈት ምን ይበጀዋል? ።

አለማወቅ የእውቀት ክፍተት ወይም ደግሞ ካለመረዳት የሚጀምር እንደሆነ ይታመናል። አለማወቅ ግን መነሻው አለመረዳት ወይም ደግሞ የእውቀት ክፍተት ሳይሆን ሆን ብሎ መሳት ከሆነ ”አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም” እንደሚባለው ነው። ከዚህ የተነሳም አሁን ላይ ሁላችንም ወደራሳችን ልንመለከት ይገባል። ሀገርና ትውልድ፣ ሕዝብና ታሪክ ተሰናስለው በሚኖሩባት ኢትዮጵያ ላይ እየሄድንበት ያለነው መንገድ ምን ያህል እንደሀገር እንደሚጠቅመን ቆም ብለን እናስብ። ልዩነቶቻችንን አርቀን ወደተግባቦት የምናመራው በእውነትና ሁሉን ባማከለ አካሄድ ስንገኝ ነው።

እውነትን መሰረት አድርጎ መገናኘት ከፊታችን ላለው የተግባቦት መድረክ ጥሩ መነሻ የሚሆን ነው። ,ሀገራዊ ምክክር ሀገራዊ መፍትሄዎችን የምናመጣው ወደ ቀደመው የአብሮነት ከፍታ የምንሸጋገርበት የተሀድሶ ምዕራፍ ነው። ሀገራዊ ምክክሩ ልዩነቶቻችንን አድርቀንና አጥበን በእርቅና በይሁንታ አዲሷን ኢትዮጵያ የምንፈጥርበት የድህነት መድረክ ነው። መድረኩ የምንፈልገውን እንዲሰጠን መድረኩ የሚፈልገውን ልንሰጠው ይገባል። መድረኩ የሚፈልገው የሀሳብ ልውውጥ ነው። ነጻና ገለልተኛ፣ የማንም ጣልቃ ገብነት የሌለው የምክክር ቦታ ነው። ልባችንን ለፍቅርና ለይቅርታ፣ ለእርቅና ለአብሮነት አስገዝተን ከሆነ ለእርቅ የተቀመጥነው መድረኩ የሚሰጠን ብዙ ነገር አለው።

ጥንተ አብሮነታችንን ያወየቡ የብሔርና የዘረኝነት ካባዎች መውለቅ አለባቸው፡ ወንድማማችነታችንን ያደበዘዙ የቡዳኔና የጎጠኝነት መንፈሶች መሟሸሽ አለባቸው። ብዙሀነታችንን ያሳነሱ የእኔነትና የብቻነት ደዌዎች መሻር አለባቸው። ሀገር በእኔነት ውስጥ የክብር አክሊል የላትም። ትውልድ በመለያየት ውስጥ የብኩርና በትር የለውም። ሕዝብ በመናቅ ውስጥ የፊተኝነት ዳና የለውም። መነሻዎቻችን የበጎነት መንፈሶች ከሆኑ የመድረሻ ምኩራቦቻችን የእኔነትን ነውር አይጸንሱም።

ላሉብንና ለሚኖሩብን ፖለቲካዊም ሆኑ ሌሎች የልዩነት ተግዳሮቶች ትልቅ መፍትሄ ሆኖ ከፊት የሚመጣው የምክክር ባሕል ነው። የእኛ ባሕል ጦርነት ነው። በጦርነት ማንም እንደማይችለን እየተነገርን ያደግንና ዛሬም ድረስ በዛ አስተሳሰብ ስር የወደቅን ነን። ይሄ ያለንበት ዘመን የኃይል ፖለቲካን፣ የኃይል ርምጃን ሽሮ ተግባቦት ላይ ደርሷል። አሮጌውን ሽረን በአዲሱ ማዕቀፍ ውስጥ እስካልገባን ድረስ ህልሞቻችን ለመኖር ጊዜ ይፈጅብናል።

በብዙ ጥያቄና ልዩነት ውስጥ በምትዳክር ሀገር ላይ የኃይል አስተሳሰብ የፍቅርን በር አይከፍትም። እንዳይከፈቱ ሆነው የተከረቸሙ የአብሮነት በሮቻችን በኃይል የዘጋናቸው እንደሆኑ ብናውቅ ምን ያክል ለተግባቦት ወደ ኋላ የቀረን እንደሆንን እንደርስበት ነበር። ሆደሰፊነትን ከትዕግስትና ከመቻል፣ ከምክክርና ከተግባቦት ጋር ያዋሃዱ ከፓርላማ ወደ ሕዝቡ፣ ከመንግስት ወደትውልድ የሚንጸባረቁ አንዳንድ ፖለቲካዊ ልምምዶች ያስፈልጉናል። ልምምዳችን የኃይል ሆነና የፍቅር በሮቻችንን ጠርቅሞብናል። እውቀታችን ራስ ተኮር ሆነና እኛነትን ሽሮብናል።

ንቅናቄአችን ለሁሉ የምትበቃ ሀገር መፍጠር ከሆነ ለሁሉ የሚበቃ አስተሳሰብና መረዳት ሊኖረን ይገባል። ከራስ ርቆ ሌሎችን መዋጀት በማይችል ስሜት ለበስ እውቀት ሀገር አትፈጠርም። በራስወዳድነት ያካበትናቸው ብዙ የጠበቡ ስርዐቶች አሉን። እነዚህ ስርዐቶች ሰፍተውና ገዝፈው ለሌላው እስኪበቁ ድረስ በሀሳብ፣ በልምድ፣ በእይታ፣ በምክክር፣ በእርቅ፣ በአቃፊነት፣ በአብሮነት መበርታት ለነገ የማንለው ጉዳይ ነው። ባንዳዎች እና ጽንፈኞች ያስተማሩን ዋጋ ከማስከፈል ባለፈ ያረቡን ግን ደግሞ የሙጥኝ ብለናቸው የምንቆስልባቸውና የምንደማባቸው አንዳንድ ሽሽቶች አሉ።

እንደ አለመታደል ሆኖ ማሕበራዊ ልምምድ በፖለቲካዊ ልምምድ የሚፈጠር ነው። ልክ የሚሆነውና ሀገርን በስርዐት የሚያቆማት ፖለቲካ በማሕበራዊ ልምምድ ቢፈጠር የሚለው ነው። ፖለቲካ በማሕበራዊ ልምምድ ቢፈጠር መነሻ የሚያደርገው የሕዝቡን ባሕልና ወግ፣ ስርዐትና አስተሳሰብ ነው። ማሕበራዊ ልምምድ በፖለቲካዊ ልምምድ ሲፈጠር ግን መነሻው እኔነትና ራስወዳድነት፣ ውሸትና ማስመሰል ነው። ለዚህም ነው በተመቸ ሀገር ላይ ባልተመቸ ፖለቲካ የምንሰቃየው።

ከሀገር ፖለቲካ ከገዘፈ፣ ከሕዝብ ፖለቲከኛ ከበረታ ትልቁ አደጋ ያለው እዛ ጋር ነው። እንደ ሀገር ዋጋ እየከፈልንም ያለው ለዛ ነው። በብሄራዊ ምክክሩም ሆነ ቀጣይ በሚኖሩ የአብሮነት መድረኮች ላይ የጋራ ስምምነቶች እንዲኖሩ በሕዝብ አስተሳሰብ የታነጸ ፖለቲካ ያስፈልገናል። በሕዝብ አስተሳሰብ የተቃኘ የፖለቲካ ምህዳር ሁሉን አቃፊ፣ ለማሕበረሰቡ ባሕልና እሴት የሚገዛ ነው። ዝም ብሎ ማሰብ ሳይሆን ሀሳባችን የቆመበትን፣ እግሮቻችን የረገጡበትን አውድ መቃኘት ያስፈልጋል። ምክንያታዊ ሳይሆኑ እና የእይታ አድማስን ሳያሰፉ ማሰብ ራስን ለተመሳሳይ ጥፋት ከመዳረግ ውጪ ወደፊት አያራምድም።

የተስፋዎቻችን ምስራቅ ብርሀን ሊረጩ እኛን እየጠበቁ ነው። ጥላቻ ያጨለማቸው የአብሮነት ቀንዲሎቻችን ንጋትን ሊያበስሩ የእኛን አብሮ መቆም የተጠባበቁ ነው። የመሸብን ስላልተያያዝን ነው። የረፈደብን ስለተራራቅን ነው። አንድ መሆን እስካልቻልን ድረስ ብዙ ማጥና ድጦች ይጠብቁናል። ብዙ ኖሮን ምንም እንደሌለው የሆነው የፍቅር ኩራዛችንን ስላጠፋን ነው። ዳግም እንድናብብ በኢትዮጵያዊነት ማዕድ ፊት ዳግም መፈጠር ይኖርብናል።

ነቅተንና በቅተን፣ አውቀንና ገብቶን ሀገር ለማቆም ካልተነሳን የሚያንገዳግደን ብዙ ነው። ስለሆነም ስለሰላምና ፍቅር እያሰማናቸው ያሉ የእርቅ ድምጾች ጎልተው መሰማታቸው አለባቸው። አንድነትን ለመውለድ እያደረግን ያለነው ትግል ያለዝለት ከፍጻሜ መድረስም አለበት።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀሳብ ልውውጥ በኩል የዳመነ ማንነታችንን ለማጥራት ብዙ ተጉዞ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱ ይታወቃል። የምክክር መድረኮችን ከማዘጋጀት ጀምሮ የልየታ ስራዎችን በማጠናቀቅ ለተግባቦት በሩን ከፍቶ እየጠበቀን ነው። ኮሚሽኑ ስራ ሲጀምር አብረውት ሊሰሩ ፍቃደኝነታቸውን ያሳዩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር አነስተኛ እንደነበር የሚታወስ ነው። አሁን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የሁሉም ይሁንታን አግኝቷል።

በዚህ መልክ በጋራ ምክር የጋራ መፍትሄ ሊያመጣ ዝግጅቱን ጨርሷል። ይሄ የሚያሳየው እንደኮሚሽን የሄደበትን ረጅም ርቀት ነው። እኛም የራሳችንን ግዴታ በመወጣት ለሰላም በተከፈተው በር ውስጥ አልፈን አሻራችንን ማሳረፍ ይጠበቅብናል። ብርቱዎች ሁልጊዜም በፍቅርና በምክክር የልቦናቸውን በር የሚከፍቱ ናቸው። በይቅርታና በአብሮነት ለዘወትር ተኝተው የሚነቁ ናቸው።

እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን የሚል አንድ ወገን የረገጠ ጽንፈኝነት በታሪካቸው ውስጥ የለም። ስለሆነም ከሌሎች ጋር አብሮ ለመኖር አይቸገሩም። በተቃራኒው ብርታታቸውን በእልህና በቁጣ የተቀዳጁ እነሱ ከሌላው ጋር እንዴት መኖር እንዳለባቸው ያልተረዱ፣ ከሌላው ጋር ሳይዛመዱ የራሳቸውን ሀሳብ ብቻ የሚያራምዱ እኔዎች ናቸው። ስለሆነም በታሪካቸው ውስጥ ፍቅርና አብሮነት፣ አንድነትና ሕብረት የለም። ስለዚህም ራሳቸውን ከሌላው ጋር አስማምተው ለመጓዝ ይቸግራቸዋል።

ይሄን ግለሰባዊ እውነታ ወደሀገር ስናመጣው አሁን ላሉብን ብሄራዊ ውጥንቅጦች እንደመስተዋት መሆን የሚችል ነው። በእኛም ሀገር መሰል ነገር መስተዋል ከጀመረ ሰነባብቷል። በጋራ ቤት ውስጥ የብቻ ታሪክና መሰል ሀሳብ የለም። እንዳመጣጣችን አካሄዳችንም ተያይዘንና ተደጋግፈን መሆኑ ለሰላማችን አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ጸንተንና በርትተን እልፍ ሽምድምድ ሀገራትን ያበረታነው ሀገርን አስቀድሞ ሰውነትን ባስከተለ የአብሮነት መንፈስ ነው። እንደሰንደቅ ከፍ ብለን በሌላው ልብ ውስጥ በነጻነት ፋናወጊነት ስንውለበለብ ዓለም ያውቀናል። እንደዋርካ ገዝፈን ለሌሎች ጥላ መሆን የጋራ ታሪካችን ነው።

ስልጣኔውን ሰላም ተኮር ያላደረገ የፖለቲካ ስርዐት እንዴትም ቢበረታ መዛሉ አይቀርም። የሰላም እጦት ባለመግባባት የሚመጣ እንደሆነ ሁሉ አብሮነትም በመግባባት የሚመጣ ነው። በመነጋገርና በመመካከር ልዩነቶችን መፍታት ያልተለማመደ ሀገርና ሕዝብ በልዩነቱ ከመጠቃት ባለፈ እርባና አይኖረውም። እንደ ቱባ ክር የመከራዎቻችንን ጫፍ ይዘን የተለተልናቸው የታሪክና የልዩነት ጽንፎች ብዙ ናቸው። እንዲነጋልን ለአንድነት በተከፈቱ የእርቅ በሮች ስር እንለፍ። ከሁሉ በላይ ከግጭት አዙሪት ለዘለቄታው ልንወጣ የምንችለው ቁጭ ብለን ስንመካከር ብቻ መሆኑን ልንረዳው ይገባል።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ጥር 21/2016

Recommended For You