የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ናቸው። እድሜያቸው ከአስራ አምስት እስከ አስራ ሰባት የሚገመት አፍላ ወጣቶች ናቸው። በሚማሩበት ትምህርት ቤት ውስጥ ከአንደኛ ደረጃ ጀምረው አብረው ስለተማሩ መለያየት ይከብዳቸው ነበር። ከሰፈር ሲወጡ አንስተው ትምህርት ቤት ጊቢ ውስጥ እስኪደርሱ ድረስ አይለያዩም ነበር። ከልጅነታቸው ጀምሮ ተመሳሳይ ትምህርት ቤት በመማራቸው እንደ ወንድምና እህት ነበር የሚተያዩት። በልጆቹ ፍቅር የተነሳ ቤተሰቦቻቸው ተግባብተው ወዳጅ ሆነዋል።
ማጥናቱንም መማሩንም አብረው ሲያደርጉት የቆዩ ልጆች የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ሲሆኑ ሌሎች ጓደኞች ወደ ቡድኑ ቀላቀሉ። መጀመሪያ አካባቢ ጥሩ ቢሆንም ቀን ቀንን እየወለደ ሲሄድ ልጆቹ ከክፍል መቅረት ብሎም አጓጉል ባህሪዎችን ማሳየት ጀመሩ።
ወንዶቹና ሴቶቹ ልጆች አብረው በማደጋቸው መለያየት ባይፈልጉም በአዋዋላቸው መለያየት ምክንያት የጓደኝነት ቡድኑ ለሁለት ተከፈለ። ቀን ቀንን እየወለደ ለወራት የተለያዩት ጓደኛሞችን ይበልጥ የሚከፋፍል ነገር ተፈጠረ። እቤት ሆነው የሚሰሩትን አሳይመንት መምህር ካዘዛቸው በኋላ አንድ ለጥናት የሚመች ቦታ እንዳለ እና እዛ ሄደው የቤት ስራቸውን መስራት እንደሚችሉ አዲስ ወደ ቡድኑ ከተቀላቀሉት ልጆች ሀሳብ ይመጣል።
ሀሳቡ አሳማኝ ስለነበረ በእረፍት ቀናቸው ለየቤት ስራው የሚሆኑ መፅሀፍቶችና ደብተራቸውን ሸክፈው፤ በተቀጣጥሩበት ሰዓት ተገናኝው ወደ ቦታው ይሄዳሉ። ሴቶቹ ልጆች አብሮ አደግ ወንድ ጓደኞቻቸው ስላሉ ምንም ሳይሳቀቁ ነበር ወደ ቦታው ያቀኑት። በቦታው እንደደረሱ የአካባቢው ጭር ማለት ሴቶቹን ቢያሰጋቸውም ከወንድሞቻቸው እኩል የሚመለከቷቸው ወንድ ጓደኞቻቸው በመኖራቸው ቀለል ብሏቸዋል። እንደሄዱ ኮካ መሰል መጠጥ አይምሯችንን ነፃ እንዲያደረግን በማለት ጠጡ። ከዛም ወንዶቹ በወረቀት የተጠቀለለ ነገር ማጨስ ጀመሩ። ያን ጊዜ ሴቶቹ ራሳቸውን መቆጣጠርም መከላከለም በማይችሉበት ደረጃ ተዳከሙ። መዳከማቸውን የተመለከቱት ወንዶች ማድረግ የሚፈልጉትን ነገር ለማድረግ ምኙ ሁኔታ በመፈጠሩ ተጠቃቅሰው ተነሱ።
ከዛ በኋላ አብሮ አደግ ጓደኞቻቸውና አዲስ አብረዋቸው የተቀላቀሉት ጓደኞቻቸው ተራ በተራ ወሲባዊ ግንኙነት ፈፀሙባቸው። ከሀገራችን ባሕል የወጡ፤ የማሕበረሰቡን እሴት ያልተከተሉ ከተለመደው ውጪ የሆኑ ነገሮችን ሲያደርጉ በቪዲዮ እየቀረፁ ነበር። ከዛ በኋላ ያንን ቪዲዮ እያሳዩ ደግመን ካላደረግን ገመናችሁን ፌስ ቡክ ላይ እንለቀዋለን በማለት በማስፈራራት ልጆቹን የማይገባ ሕይወት ውስጥ ከተቷቸው። ደጋግመው ግንኙነት እንዲያደርጉ ከማስገደድም አልፈው ለተለያዩ ሱሶቻቸው ማስፈፀሚያ እንዲሆን ገንዘብ ከየትም አንዲያመጡ ያስገድዷቸው ጀመር።
የቤት ስራ ለመስራት በሚል ሰበብ ከቤታቸው የወጡት ገና በአስራዎቹ እድሜ አጋማሽ ላይ የሚገኙት ሴት ልጆች በየዕለቱ ከማይፈልጉት ሰው ጋር ግንኙንት ከማድረግም አልፎ የአደንዛዥ ሱስ ተጠቂ ሆኑ። በትምህርት ሰዓት ከቤታቸው ቢወጡም ያገኙትን ገንዘብ ይዘው በሱስና በወንዶቹ ልጆች አስገዳጅነት ያልሆነ ቦታ መዋል ጀመሩ።
አሁን ላይ ልጆቹ በተፈጠረባቸው ሁኔታ የተነሳ ትምህርታቸውን መማር ያቃታቸውና በስነ ልቦና የተጎዱ መሆናቸውን የሰማነው ታህሳስ 4 ቀን 2016 ዓ/ም አዲስ አበባ የዘንድሮውን የ16ቱ ቀናት የጸረ ጾታ ጥቃት ንቅናቄ ማጠቃለያ አስመልክቶ በተካሄደ ውይይት ወቅት ነበር።
በመድረኩ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ጽንሰ ሀሳብ፣ የጥቃት አይነቶችና መንስኤዎች፣ ታዳጊና ወጣት ሴቶች የሚገጥሟቸው ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችና የሚያደርሱት ስነ ልቦናዊ እና አእምሯዊ ተጽዕኖ፣ ጥቃቶችን ማስቆም በሚቻልባቸው መንገዶች፣ በመሳሰሉት ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ ከተደረገ በኋላ የተለያዩ ሀሳቦች ከተሳታፊዎች ተንጸባርቀው ውይይት ተደርጓል። ተሳታፊዎችም በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው የሚገጥሟቸውን ልምዶች አካፍለዋል።
በውይይት መድረኩ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ታዳጊና ወጣት ሴቶች፣ ወጣት ወንዶች እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎችና ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን ከላይ ያነሳነውና ሌሎች ተመሳሳይ ታሪኮች ሲነሱ ውለዋል።
ከተነገሩት ታሪኮች መካከል በወንድና ሴት ጓደኝነት መካከል በሚደረግ የፍቅር ግንኙነት ወንዱ ልጅ ከጓደኛው ጋር መኝታ ክፍል ውስጥ በመምጣት ሴቷ ለፍቅር ብላ በነፃነት የሆነችውን በሙሉ ቀርፆ በዩትዩብ በመልቀቅ የልጅቷን ሕይወት ወዳልተፈለገ ሁኔታ ያስገባበትም አጋጣሚ መኖሩን የሕግ ባለሙያ የሆኑት የመድረኩ ተሳታፊ ተናግረዋል።
ዩትዩብ ላይ ለሚገኝ ክፍያ ሲባል ሴቶቹ በላወቁበት ሁኔታ የተቀረፁ ቪዲዮዎችን መልቀቅ፤ በተለያዩ ምስሎችን ከማሕበራዊ ሚዲያ ላይ በመውሰድ እነሱ በላደረጉት ሁኔታ የተቀነባበሩ ቪዲዮችን በማሰራጨት የበርካታ ሴት እህቶችን ሕይወት የሚረብሹ ተግባሮች እየተከናወኑ መሆኑን ሰዎቹም በሕግ አግባብ ሊጠየቁ የሚችሉበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን የሕግ ባለሞያዋ አብራርተዋል።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች ወጣት ማሕበራት የተውጣጡት ወጣቶች እንደተናገሩት በወጣትነት ጊዜ ላይ መልካቸውን እየቀያየሩ የመጡትን ጥቃቶች ለመከላል ሁሉም ሰው በጋራ መስራት ይገባዋል። ይህም ማለት ወጣቶችን የሚያነቃቁ መድረኮችን ማዘጋጀትና ራሳቸውን ከጥቃት እንዴት መከላከል እንደሚችሉ ማስተማር የግለሰቦችም በዘርፉ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎቸም ኃላፊነት መሆኑን በውይይቱ ላይ አንስተዋል።
በብዛት ጥቃት አድራሾችም በተለያዩ የስነ ልቦና ችግሮች የተጠቁ የሚሆኑበት ጊዜ ከፍተኛ መሆኑን የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች አንስተው ጥቃት አድራሹም የደረሰበት የስነ ልቦና ጉዳት ታክሞ ጠቃሚ ዜጋ ይሆን ዘንድ የመንግስት የስነ ልቦና ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ኃላፊነት ይኖርበታል።
ለሁሉም ወጣት በቀላሉ በጓደኝነትና በስርአት ሊያደርገው የሚችለውን ነገር በኃይልና በፀያፍ ሁኔታ ለማድረግ መሞከሩ የስነ ልቦና ችግር መሆኑን ተወያዮቹ አስረድተዋል። ይህ ዘመን አመጣሽ ማሕበራዊ ሚዲያ ተፅእኖም ከወጣቶች መካከል እንዲወጣ አስተሳሰብ ላይ በተገቢው መልኩ መሰራት እንደሚገባው በመድረኩ ላይ ተነስቷል።
የስርአት ፆታ ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ መስከረም ተካ በበኩላቸው ፆታዊ ጥቃት የምንላቸው በርካታ ናቸው። ጥቃቶቾ ፆታዊ፤ ስነ ልቦናዊ፤ አካላዊና ኢኮኖሚያዊ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ጥቃቶች በተለያየ ሁኔታና በተለያዩ አይነት ሰዎች ሊደርሱ ይችላሉ። ይህም ማለት ባልታወቁ ሰዎች ወይም በቅርብ ሰዎች፤ በስራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት፤ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ጥቃት አድራሾቹ ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም ጥቃት ይፈፅማሉ።
̋ በአብዛኛው ጥቃቶች ቤት ውስጥ ሊፈጠር ይችላል። ይህ አይነት ጥቃት ደግሞ ከሚደርሰው ማሕበራዊ ጫና አንፃር እየታየ ኅብረተሰቡ ይታገሰዋል። በሃገራችን የሴቶች ጥቃት በየጊዜዉ ብናወራበትም፤ ቀላል ቢመስለንም፤ ሁሉ ሰው ኃላፊነቱን ቢወጣ ሊቀረፍ የሚችል ይመስላል እንጂ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለዉ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ አይነቱ እየጨመረ ነዉ የመጣዉ ̋ ይላሉ ባለሞያዋ።
ጾታዊ ጥቃት እየጨመረ የመጣዉ ማኅበረሰቡ ወንድን የሚያስቀድም በመሆኑ፤ ከባሕል አስታኮ የመጣ መሆኑ፤ በኢትዮጵያ የሚታየውን ብሎም ተባብሷል የተባለውን የፆታዊ ጥቃትን ለማስቀረት ግን በርካታ የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
«አሁን አሁን በሃገሪቱ ውስጥ በሴቶች ላይ የሚደርሰዉን ጥቃት አይቶ፤ ሕግ ይከበርላቸዉ፤ መንግሥት ተገቢውን ትኩረት ይስጣቸዉ፤ ፍትሃዊነት ይኑር ብዬ አንድ ሺ ጊዜ ስናገረዉ የነበሩትን ነገሮች መድገም አልፈልግም፤ አልችልምም። የሚያዋጣዉ ራስዋን ያበቃች ሴት የሚፈጥሩ፤ በሴቶች ጉዳይ ላይ አለን የሚሉ በሴቶች ጉዳይ ላይ እንሰራለን የሚሉ፤ ተምረናል የሚሉ፤ ሰብዓዊነት ግድ ይለናል የሚሉ፤ ፖለቲከኛ ነን የሚሉ በጋራ ሲንቀሳቀሱ ነው፡» ሲሉ አስረድተዋል።
እንዳጠቃላይ ይህንን ብናነሳም በጣም እየተባበሰና ባልተለመደ ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ የመጣው የማሕበራዊ ሚዲያ ጥቃት የሚመለከተው አካል ቁጥጥር ካላደረገበት የሚያስከትለው ማሕበራዊ ጫና ቀላል አንደማይሆን የስርአተ ፆታ ባለሞያዋ ይናገራሉ።
በተቀነባበሩ ቪድዮችና ምስሎች የተነሳ የፈረሱ ትዳሮች፤ በፍቅር ጓደኞቻቸው ከህደት ተፈፅሞባቸው በተለቀቁ ቪዲዮች የተነሳ ራሳቸወን ያጠፉ ወጣት ሴቶች፤ ከመዋረድ መሰደድ ይሻላል ብለው ብን ብለው የጠፉ ወጣት ሴቶች መኖራቸውን የስርአተ ፆታ ባለሙያዋ ይናገራሉ።
ለሁሉም ጥቃቶች መነሻ ከማሕበረሰበ ስለሚቀዳ ማሕበረሰቡ ቀድሞ የነበረውን ባሕልን አክብሮ የመኖር፤ ግብረ ገብን ለልጆቹ የማስተማር ነገርን ቅድሚያ ቢሰጥ መልካም ይሆናል። የወንዶች የበላይነት የሚታይበት ሁኔታንም ማስተካከል፤ ቤት ውስጥ የሚደርሱ ጥቃቶችንም ለመከላከል የጋራ ጥረት ማድረግ ተገቢ እንደሆነ የስርአተ ፆታ ባለሙያዋ ይናገራሉ።
ከዓለም ጤና ድርጅት በተገኘ መረጃ መሠረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሦስት ሴቶች መካከል አንዷ በሕይወቷ ውስጥ አካላዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት ይደርስባታል ይላል። በዚህ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ መሰረት እድሜያቸው 15 እና ከዚያ በላይ የሆነ 736 ሚሊዮን ያህል ሴቶች ጥቃት ደርሶባቸዋል ማለት ነው።
ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው በጎርጎሮሳውያኑ 2020 የዓለም የጤና ድርጅት ከሠራው ጥናት ወዲህ የተጎዱ ሴቶች ቁጥር በአብዛኛው ባይለወጥም ይሄኛው ግን ጥቃት የሚጀምረው ገና በልጅነት መሆኑን አመልክቷል። እድሜያቸው ከ 15 እስከ 24 ዓመት ከሆኑት አራት ሴቶች መካከል አንዷ ዕድሜዋ እስከ ሃያዎቹ አጋማሽ እስኪደርስ በቅርብ አጋሯ ጥቃት ይደርስባታል።
ሰው ከእንስሳ የሚለይበት ሰብኣዊ ክቡሩን ጠብቆ ሊያደርግ የሚገባው የፍቅር ግንኙንት በኃይል ማድረግ ከአንድ ሰው ነኝ ከሚል ግለሰብ የማይጠበቅ መሆኑን የሚያስረዱት የመድረኩ ተሳታፊዎች እነዚህን ጉዳዮች ቸል ማለት የማይገባ መሆኑን አስረድተዋል።
መልኩን እየቀያየረ የሚደረገው የሴት ልጅ ጥቃት ሀይ ባይ ያስፈልገዋል። ይህ ጉዳይ የሚመለከታቸው የሕግ አከላት ፤ ሁሉም የማሕበረስብ አባላት፤ የሀይማኖት አባቶችም ሆኑ ሌሎች ይሄንን ችግር ለመቅረፍ በጋራ ርብርብ መስራት ይገባዋል በማለት የዛሬውን አበቃን። ከጥቃት የፀዳች ሀገር ትኖረን ዘንድ ምኞታችን ነው።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 21 ቀን 2016 ዓ.ም