የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ተቀባይነትን በስፋት ለማሳደግ

የጥሬ ገንዘብ ዝውውር እየወረደ የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ማደጉ የተለያዩ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ እየተገለፀ ነው። የመጀመሪያው ጠቀሜታ በጥሬ ገንዘብ ለመላክ ሰፋ ያለ ጊዜ የሚጠይቅ ሲሆን፤ ገንዘብ አንቀሳቃሹ ባንክ ከመሔድ ጀምሮ የባንክ አገልግሎት ሰጪው ገንዘቡን ሲስተም ላይ እስከሚመዘግብ ድረስ የሚፈጀውን ጊዜ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት በእጅጉ አሳጥሮታል። በዲጂታል ባንኪንግ የባንክ ሠራተኛው ምንም ሳይሳተፍ ተገልጋዩ ባለበት ቦታ በላከበት ቅፅበት ተቀባዩ ጋር ይደርሳል።

የባንክ ተጠቃሚው በእጅ ስልኩ የወጣውን እና ያለውን የገንዘብ መጠን ማወቅ የሚችል በመሆኑም፤ የተለያዩ ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ ብዙ አይቸገርም። ይህ ሌላኛው ጠቀሜታው ነው ፤ የባንክ ደንበኛው በእጁ ጥሬ ገንዘብ ባይኖርም የፈለገውን አገልግሎትም ሆነ ቁስ በዲጂታል የባንክ አገልግሎት ተጠቅሞ መግዛት መቻሉም ቴክኖሎጂውን የበለጠ ተመራጭ አድርጎታል።

ከዚህም በላይ በፈለገው ፍጥነት ገንዘብ መላኩ፤ አገልግሎትም ሆነ ዕቃ መግዛቱ ሕይወቱን ቀላል እና ውጤታማ በማድረግ ነፃነቱን በማጎናፀፍ በኩል የሚኖረው አስተዋፅዖም የሚናቅ አይደለም።

የዲጂታል የባንክ አገልግሎት ከቀን ወደ ቀን ቴክኖሎጂውን ተከትሎ ተለዋዋጭነት እየታየበትም ነው። ቀደም ሲል በመልዕክት መረጃ በመላክ ይካሔድ የነበረው ልውውጥ አሁን በሶፍት ዌር በተሻለ ፍጥነት እና ቅልጥፍና እየተከናወነ ይገኛል። ግልጽነትን በመፍጠር በኩልም የዲጂታል የባንክ አገልግሎት እጅግ ተወዳጅነትን አትርፏል።

ገንዘብ ሲንቀሳቀስ ለምን ዓላማ ለማን ገንዘቡ እንደተላከ ቴክኖሎጂው መዝግቦ የሚይዝ በመሆኑ፤ በቀላሉ ያለምንም ክርክር ልውውጡን ማረጋገጥ ይቻላል። ከግለሰብ ባሻገር መንግሥት ለወረቀት ገንዘብ ማሳተሚያ የሚያወጣውን ወጪ ከመቀነስ በተጨማሪ ሌሎች ብዙ ጥቅሞች አሉት ።

ይህ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት የፋይናንስ አስተዳደርን ከሌሎች የንግድ ሥራዎች ጋር በማቀናጀት በዓለም ላይ ከፍተኛ ውጤት እያስገኘ ነው። በኢትዮ ጵያም በ2015 የበጀት ዓመት በዲጂታል የክፍያ አማራጮች የተንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን ከ4 ነጥብ 7 ትሪሊዮን ብር በላይ ደርሷል። ይህ የገንዘብ መጠን ከቀዳሚው ዓመት ከ2014 ዓመተ ምሕረት ጋር ሲነፃፀር በ3 ነጥብ 1 ትሪሊዮን ብር ብልጫ አለው ሲል ሪፖርተር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ጠቅሶ አብራርቷል። ይህ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት እና የዲጂታል የግብይት ሥርዓት መጨመሩን የሚያሳይ ነው።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የጥሬ ገንዘብ ፍሰት ለመቀነስ የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ መሆኑም እየተነገረ ነው። ይህ በራሱ የዲጂታል የግብይት ሥርዓት እንዲስፋፋ የሚያስገድድ ሲሆን፤ ኅብረተሰቡ ለዲጂታል አገልግሎት ያለው የመቀበል ሁኔታም ጨምሯል። ነጋዴዎች በዲጂታል አማራጭ ገንዘብ ለመቀበል ፈቃደኛ እየሆኑ ይገኛሉ። የግለሰብ ተገልጋዮችም በዲጂታል ክፍያ ለመፈፀም ዝግጁ ሆነው ታይተዋል። በፊት አንድ አገልግሎትን ወይም ዕቃን ለመሸመት ኪሴን ልፈትሽ ይል የነበረ ዜጋ፤ አሁን በተንቀሳቃሽ ስልኬ ላይ ገንዘብ እንዳለኝ ላረጋግጥ እያለ ነው።

ሰዎች ለመጠባበቂያ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ ገንዘብ ይዘው መንቀሳቀስ ከመጀመራቸው ባሻገር፤ የተሻሻሉ እና ለአጠቃቀም ምቹ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች እየቀረቡ ናቸው። በዚህ ሂደት ውስጥ የበለጠ ስኬታማ ለመሆን ባንኮች ወይም ሌሎች የሚመለከታቸው የፋይናንስ ተቋማት ነጋዴዎችን መልምለው በቀለጠፈ መልኩ በዲጂታል ግብይት እንዲጠቀሙ የማሠልጠን ሥራ መከናወን እንዳለበት የዘርፉ ምሑራን በመናገር ላይ ናቸው ።

የዲጂታል የባንክ አገልግሎት፣ የተንቀሳቃሽ ስልክ የገንዘብ ዝውውር ወይም የዲጂታል ግብይት ሥርዓት ዕድገት አስደሳች ቢሆንም፤ አልፎ አልፎ በኔትወርክ መቆራረጥ ምክንያት እያጋጠመ ያለው ክፍተት መሻሻል እንዳለበት ። ከዚህም ባለፈ ዘርፉ ለተለያዩ ማጭበርበሮች ሊጋለጥ የሚችልበትም አጋጣሚ ብዙ ነው። ችግሮቹን ለመከላከል የይለፍ መለያዎችን/ኮዶችን መቀያየር እና የመግቢያ መረጃዎችን መጠበቅ እንደሚገባ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።

በሌላ በኩል አገልግሎት ሰጪው አውቆም ሆነ ባለማወቅ ግብይቱን በዲጂታል መንገድ ለመፈፀም ፈቃደኛ ካልሆነ፤ ጥሬ ገንዘብ ሳይዝ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት ተማምኖ የተንቀሳቀሰ ሰው የፈለገውን አገልግሎትም ሆነ ዕቃ ለመግዛት ይቸገራል። ከዚህም ባለፈ የተወሰነው የማኅበረሰብ ክፍል በተለያዩ ምክንያቶች በሞባይል ቴክኖሎጂ ገንዘባቸውን ሲያንቀሳቅስ ሌላው ደግሞ በተቃራኒው በቴክኖሎጂው ባለመተማመን ወይም በተለየ ወቅታዊ ችግር ወደ ኋላ ሊመለስ ይችላል፤ በዚህ ወቅት ባንኮች ሊፈጠር የሚችለውን ክፍተት ግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል ።

ይህንን እውነታ በአግባቡ ባለመረዳት ሰሞኑን በባንኮች በኩል የተፈጠረውን ችግር ማንሳት ይቻላል። በዓሉን አስመልክቶ በባንኮች አካባቢ የታየው ጥሬ ገንዘብ ላለመስጠት የነበረው ማንገራገር ደንበኞችን ቅር አሰኝቷል። አንዳንድ የግል ባንኮች ‹‹ለበዓል የዶሮ እና የበግ መግዣ የሚሆን ጥሬ ብር የለንም ግብይታችሁን በዲጂታል ፈፅሙ።›› ብለው፤ ማስገደዳቸው ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ ለማለት አስገድዷል።

ገበያው ላይ በበቂ መጠን ቴክኖሎጂው ተስፋፍቶ ከወረቀት የፀዳ ዝውውር ከመስፋፋቱ በፊት ደንበኛው ያስቀመጠውን ገንዘብ ‹‹በጥሬው አንሰጥም›› ብሎ መከልከሉ፤ የገበያ ሥርዓቱን ችግር ውስጥ ከመክተት ባለፈ፤ ደንበኞች ገንዘባቸውን ባስቀመጡባቸው ባንኮች ላይ ያላቸውን አመኔታ ችግር ውስጥ የሚከተው ይሆናል፤ የባንክ ዘርፉንም ስጋት ውስ ጥ ሊጨምረው ይችላል ።

አንዳንድ ጊዜ በአጋጣሚ ከተፈጠሩ ችግሮች በመነሳት የባንክ ደንበኞች የዲጂታል የባንክ አገልግሎት ደህንነቱ ያልተጠበቀ ነው ብለው ሊወስዱ፤ በዚህም ስጋት ሊያድርባቸው ይቻላል። ከዚህ የተነሳም ግብይቱን በጥሬ ገንዘብ ማከናወን ምርጫቸው ሊሆን ይችላል ።

ባንኮች አጋጣሚዎች ሊፈጥሯቸው የሚችሏቸውን ችግሮች በአግባቡ በማጤን በአሠራራቸው ላይ ተገቢውንም ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። ከሁሉም በላይ ደንበኞቻቸው የዲጂታል የባንክ አገልግሎትን ተጠቃሚ እንዲሆን ማበረታታት ፤ በአገልግሎቱ መተማመን እንዲፈጥሩ ሰፊ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ጥር 21/2016

Recommended For You