በውጭ የሚኖረው ሁለተኛው ትውልድ ወደ አባቶቹ ሀገር መምጣቱ ትሩፋቱ ብዙ ነው

ሀገር የምትገነባው በትውልዶች ቅብብሎሽ ነው። አንዱ ትውልድ ካለፈው ትውልድ የተረከበውን በማሳደግ የራሱን ዕሴቶች እየጨመረ አሻራውን እያሳረፈ ይሄዳል። ኢትዮጵያ በዚህ መልኩ ከአንዱ ትውልድ ወደ ሌላው ትውልድ እየተሸጋገረችና ሉዓላዊነቷንና አንድነቷን እያስጠበቀች ዛሬ ላይ ደርሳለች።

የዛሬዋ ኢትዮጵያ የትላንት ተከታታይ ትውልዶች ውጤት ነች። ኢትዮጵያ በአርሶ አደሩና ትምህርት ቀመስ በሆኑ ዜጎቿ እየተሠራችና እየተበጀች ዘመናትን የተሻገረች ሀገር ነች። በቀደሙት ዘመናትም የድንበር ተሻጋሪ ገናና ታሪክ ባለቤትም ነች።

እነዚህ ታሪኮች በፈጠሩት መነሳሳት በየዘመናቱ የነበሩ መንግሥታትም ይህንኑ እውን ለማድረግ የራሳቸውን መንገድ ሲከተሉ ቆይተዋል። ዘመናዊ ሥልጣኔ እንደሀገር ከተዋወቀበት ከአጼ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ከአደጉት ሀገራት ቀስመው ወደ ሀገር ለማምጣት በርካታ ዜጎች ለትምህርት ወደ አውሮፓና አሜሪካ አቅንተዋል።

አብዛኞቹ ከአውሮፓና አሜሪካ ያገኙትን ዕውቀት ወደ ሀገር ተመልሰው በተግባር ለመተርጎም ሲሞክሩ አንዳንዶቹ ደግሞ ኑሯቸውን በእነዚሁ ሀገራት አድርገዋል። ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ “pioneers of Ethiopia” በሚለው መጽሐፋቸው በአፄ ምኒሊክና በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት ወደ ውጭ ሀገራት ለትምህርት ከተላኩት ኢትዮጵያውያን ውስጥ አብዛኞቹ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በቀሰሙት ዕውቀት ሀገራቸውን ለማገልገል ሞከረዋል።

የደርግ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ጊዜ ጀምሮ ግን በሀገር ውስጥ በነበረው የፖለቲካ ሽኩቻና በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት በርካታ ኢትዮጵያውያን ኑሯቸውን በአውሮፓና አሜሪካ ለማድረግ ተሰደዋል። እነዚህ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው ሀገራት ትዳር መሥርተው ቤተሰብ አፍርተዋል። ልጆች ወልደዋል።

ከእነዚህ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን የተወለዱት ልጆች /ሁለተኛዎቹ ትውልዶች/ አብዛኞቹ ኢትዮጵያን በምናብ እንጂ በአካል አያውቋትም። የማንነታቸው መሠረት የሆነችውን የአባቶቻቸውን ሀገር ከወላጆቻቸው ከሚሰሙት ቁንጽል ታሪክ ውጪ በገቢር መጥተው አላዩዋትም። ይህ እውነትም ስለሀገራቸው በልበ ሙሉነት ለመናገር የሚያስደፍራቸው አይደለም።

ታደሰ ወልደ ጊዮርጊስ የተባሉ ምሑር ‹‹ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ትንተና›› በሚል ባዘጋጁት መጽሐፍና እና ሰለሁለተኛው ትውልድ ባወሱበት ምዕራፍ እንዳብራሩት “ የአዲሱ ትውልድ አባላት በትውልድ ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው በባሕላቸው፤ በአስተዳደጋቸው፤ በአመለካከታቸው፤ በኑሯቸው ኢትዮጵያዊ እንዲሆኑ እንጠብቃለን” ብለዋል።

በሌላም በኩል አሜሪካ ውስጥ ተወልደው ስላደጉ አሜሪካዊ ባህል፤ አሜሪካዊ አኗኗር፤ አሜሪካዊ አስተሳሰብ፤ አሜሪካዊ አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል። እነዚህ ወጣቶች ግን ማን ናቸው? የሚል ጥያቄ አንስተዋል። በርግጥም ትልቁ ጥያቄ ይህ ነው። በእነዚህ ወጣቶችም ዘንድ ዘወትር የሚመላለሰው ጥያቄ ማንነታቸው የተሳሰረው የዘር ሐረጋቸው ከተቋጠረባት ከኢትዮጵያ ጋር ወይስ ተወልደው ካደጉባት ከአሜሪካ ጋር? ይህ በአግባቡ መልስ የሚያሻው ጥያቄ ነው።

ማንነትን መረዳት፤ በሕይወት ረጅም ጉዞ ውስጥ ለብዙ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ ጥልቅ ሰብዓዊ ጉዳይ ነው። ለጥቁር አሜሪካውያን እስካሁን ያልተመለሰ ጥያቄና ለሥነልቦናም ቀውስ እየዳረጋቸው ያለው ይኸው የማንንት ጥያቄ አለመመለስ እንደሆነም ብዙ ትናንቶች በስፋት የሚያስገነዝቡት ነው ።

በተለይም የእነዚህ ኅብረተሰብ ክፍሎች ዝርያዎች ወደ አሜሪካ ከመጡ ዘመናትን ያስቆጠሩ ከመሆናቸውም በሻገር በአግባቡም ሀገራቸውንና ማነንታቸውን እንዲያውቁ አለመደረጋቸው ሁልጊዜ ከራሳቸው ጋር እንዲሟገቱ አድርጓቸዋል። ኢትዮጵያውያንም ይህ ችግር እንዳይገጥማቸው ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

ታደሰ ወልደ ጊዮርጊስ ከላይ ባነሳነው መጽሐፋቸው እንዳወሱትም፤ ለአሜሪካ ሕዝብ ዋነኛው ጉዳይ ዜግነት ሳይሆን ባሕልና ማነንት ነው። አሜሪካ የተወለዱ እና ያደጉ ኢትዮጵያውያን ሕጋዊ ዜግነታቸው አሜሪካዊ ቢሆንም የሚታየው ባሕልና ማንነታቸው በመሆኑ ከኢትዮጵያዊ ውጭ በሌላ ሊታወቁ አይችሉም። በውጭ ዓለም መወለድና ማደግ ማንነትን እንደማይቀይርም አጠንክረው አመልክተዋል ።

ለነዚህ ኢትዮጵያውያን የማንነታቸው መሠረት የሆነው ኢትዮጵያዊነትን በሁለንተናዊ መገለጫው ማወቅ አለባቸው። እንግሊዝኛ አቀላጥፈው ቢናገሩም፤ ባሕሪና አኗኗራቸው አሜሪካዊ ቢሆንም ማንነታቸው ግን ኢትዮጵያዊነት ነው። ይህንን ማንም ሊቀይረው የማይችለው እውነት ነው።

ከዚህ የተነሳ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁለተኛ ትውልዶች ማንነታቸውን በአግባቡና በትክክል አውቀው እንዲያድጉ መደረግ ተገቢ ነው። ማንነታቸው ኢትዮጵያዊ፤ ሀገራቸው ደግሞ ኢትዮጵያ መሆኗን በተጨባጭ ማወቅ ይኖርባቸዋል። ይህንን ማወቁ ድንገትም ለነገ ሕይወታቸው ስኬት ተጨማሪ አቅም ሊሆን ይችላል ።

ይህ ትውልድ ሀገሩ የሰው ዘር መገኛ፤ የብዙ ሥልጣኔዎች ባለቤት መሆኑዋን ሊያውቅ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከአርባ ጊዜ በላይ ስሟ የተወሳ፤ በቁርዓን እና በሐዲስ ውስጥ ስሟ የተከበረ ድንቅ ሀገር መሆኑዋን ሊረዳ ይገባል። ከዚህም በላይ በማንነቱ እንዲኮራ የሚያስችሉት በርካታ ስጦታዎች ባለቤት እንደሆነች ሊያውቅ ያስፈልጋል።

ይህንኑ ተጨባጭ እውነታ ታሳቢ በማድረግ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መጥተው ታሪካቸውን፤ ወግና ባሕላቸውን እንዲያውቁ መንግሥት ያቀረበው ጥሪ በሁሉም መልኩ የሚደገፍና የሚበረታታ ነው። ይህንኑ ጥሪ ተቀብለው እየመጡት ላሉትም የአየር ትኬትና የሆቴል መስተንግዶ ቅናሽ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ ማበረታቻዎች መደረጉም እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው።

በመንግሥት የተደረገውን ጥሪ ተከትሎም ከታኅሣሥ 20 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ መስከረም ወር 2017 ዓ.ም መጨረሻ ቀናት በሦስት ዙሮች በርካታ ቁጥር ያላቸው የትውልዱ አባላት ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ ተብሎ ይታሰባል። ወደ ሀገር ውስጥ መምጣታቸው በርካታ ትሩፋቶችን ይዞም እንደሚመጣ ይጠበቃል ።

ጥሪው በዋነኝነት ትውልዱ ሀገሩን እንዲያውቅ ዕድል ይሰጠዋል። ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ፤ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ብቸኛዋ ሀገር እና የጥቁር ሕዝቦች ኩራት፤ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች፤ በዩኔስኮ 16 ቅርሶችን ያስመዘገበች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር፤ የአፍሪካ ዋንጫ መሥራች፤ በኮርያ፤ በኮንጎ እና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሰላም በማስከበር አንቱታን ያተረፈች ሀገር የመሆኑን እውነታ ያውቃል።

የአባቶቹ ሀገር /ሀገሩ/ በዓለም ውስጥ የራሳቸው ፊደል ካላቸው ጥቂት ሀገሮች አንዷ፤ በአፍሪካ ደግሞ ብቸኛዋ ሀገር እንደሆነች በዚህም ከራሷ አልፋ ለአፍሪካውያን ኩራት ጭምር የሆነች ሀገር እንደሆነች ለማወቅ የተመቻቸ ዕድል ይፈጠርለታል።

ኢትዮጵያ ጥንታዊ የሰው ልጅ መገኛ ከመሆኗም ባሻገር የራሷን ማነንትና ታሪክ አስጠብቃ የቆየች የጥቁር ሕዝቦች መመኪያ መሆኗን፣ ይህ ታሪክ ደግሞ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን /የሁለተኛውን ትውልድ/ መኩሪያ ታሪክ ጭምር ነው። ይህን ማወቅ በራሱ/በማንነቱ ያለውን ኩራት ከፍ የሚያደርግ ነው።

ትውልድ በማኅበራዊም ሆነ በሥነ ልቦና ረገድ ጠንካራ ማንነት ሊገነባ የሚችለው ታሪኩን፤ ባሕልና ወጉን መረዳት ሲችል ነው። ከኢትዮጵያ ይዞት የሄደው ባሕልና ማኅበራዊ ሕይወት ስለሌለው እና ሙሉ ለሙሉ በውጭ ባሕል ያደገ በመሆኑ እንደ ቀደመው ትውልድ ጠንካራ ስብዕና አይኖረውም። ጥሪውን ተከትሎ ሲመጣ የሀገሩን ታሪክ፤ ወግና ባሕል እንዲሁም ማኅበራዊ ሕይወት በቀላሉ በመረዳት በራሱና በሀገሩ ይኮራል።

ከወላጆቻቸው ሀገር ጋር ቁርኝት እንዲፈጥሩ፣ መነሻ ሀገራቸውን በአግባቡ እንዲረዱና በማንነታቸው እንዲኮሩ ያስችላል። ከዚህም ባለፈ ከሀገራቸው ጋር ቋሚ ግንኙነት እንዲፈጥሩ እና መነሻቸውንም እንዲያውቁ ይረዳቸዋል። በአባት አያቶቻቸው ታሪክ እንዲኮሩ ዕድል ይፈጥርላቸዋል።

ይህ አጋጣሚ አባቶቻቸውና አያቶቻቸው ያቀኗትን ሀገር እንዲያውቁና የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲኖር ያደርጋል። የወላጆቻቸው ሀገር ክብርና ዝና በአካል ተገኝተው እንዲረዱ ያስችላል። ኢትዮጵያ በትውልድ ቅብብሎሽ የጸናች ሀገር ነች። የትላንቱ ትውልድ በከፈለው መስዋዕትነት የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት አክሊል ሆና ዘለቀች ሀገር ነች። ይህችን ድንቅ ሀገር በአካል ተገኝቶ ማየትና መረዳት ከዕድልም በላይ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ሀገራቸው ላይ ዕውቀታቸውንና ገንዘባቸውን እንዲያፈሱ ዕድል ይሰጣል። አዲሱ ትውልድ በሠለጠኑት ዓለማት ያገኘውን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕውቀት ወደ ሀገሩ በማምጣት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩትን ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ዕድል ይሰጠዋል።

የኢትዮጵያም ሆነ የሦስተኛው ዓለም አጠቃላይ የኑሮ ደረጃ ከአሜሪካና ከምዕራባውያን የኑሮ ደረጃ ጋር ሲነጻጸር ሰፊ ልዩነት ያለው በመሆኑ ልዩነቱ እስኪጠብ ድረስ አሁንም ፍልሰት ሊቆም አይችልም። ኢትዮጵያውያንም ሀገራቸውን በልባቸው ውስጥ አድርገው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ምዕራቡ ዓለም በስፋት ሲሰደዱ ቆይተዋል። ከአፄ ኃይለሥላሴ አስተዳደር መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ እስዛሬ ድረስ ፍልሰቱ አልቆመም።

ሆኖም ዋናው ጉዳይ ወደ ውጭው ዓለማት የፈለሱት ዜጎችም ሆኑ እዛው የተወለዱት የሁለተኛው ትውልድ አባላት ለሀገራቸው ምን አበረከቱ? የሚለው ነው። የሚሰደደው ዜጋም ሆነ እዛው የተወለደው ሁለተኛ ትውልድ ዋነኛ ትኩረቱ የምዕራባውያን የአኗኗር ስልት እየተከተሉ በዛው ሰምጦ መቅረት ሳይሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ ዘላቂ ችግሮች ለማሻሻል መሞከር ሊሆን ይገባል።

በተለይም በውጭ የሚኖረው ሁለተኛ ትውልድ የተሻለ ትምህርት የቀሰመ፤ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕውቀት የተራመደ፤ በመጠኑም ቢሆን ጥሪት የቋጠረ በመሆኑ ያሉትን የዕውቀትና የመዋዕለ ንዋይ ሃብቶች ይዞ ወደ ሀገሩ በመምጣት የበኩሉን አሻራ ማሳረፍ ይችላል።

ሁለተኛው ትውልድ ሀገሩን የማወቅ ዕድል ማግኘቱ ትልቅ እድል ከመሆኑም ባሻገር ለኢትዮጵያም ትልቅ ትልቅ ተስፋ ነው። አዲሱ ትውልድ ትምህርት ለማስፋፋት፤ መንገዶችን ለመሥራት፤ መንገዶችን ተደራሽ ለማድረግ፤ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ በአጠቃላይ የተጀመረውን ልማት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የማይተካ ሚና ይጫወታል።

ዛሬ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቁ የሆነውን የዓባይ ግድብ ገንብታ በማጠናቀቅ ላይ ትገኛለች። ለ33 ዓመታት ተዘግቶባት የነበረውን የባሕር በር ለማስከፈት ከሶማሌ ላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርማለች። የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡ በርካታ ተፈጥሮ ሃብቶችን በማልማት ላይ ትገኛለች።

እነዚህና መሰል ተግባራት ደግሞ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገሩና የኢትዮጵያን ሕዝብ ሕይወት እንዲለውጡ በሀገር ውስጥ ካለው አቅም በተጨማሪ በውጭ የሚኖረውን ዲያስፖራ በተለይም ደግሞ የሁለተኛውን ትውልድ እውቀትና መዋዕለ ንዋይ ትፈልጋለች።

ይህ ዕድል ደግሞ የኢትዮጵያን ብልጽግና ከማፋጠኑም ባሻገር ሁለተኛውን ትውልድ ከሀገሩ ጋር ቋሚ የሆነ የሥነ ልቦናና የማኅበራዊ ትስስር እንዲኖረው ያደርገዋል።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You