የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በተሻለ መልኩ እንዲያንሰራራ

ኢትዮጵያ የዓለም ቱሪስትን ቀልብ ከሚስቡ ሀገራት መካከል አንዷናት። ከዓለም የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) የቱሪስት ማዕከላት መካከል ስሟ ደጋግሞ የሰፈረው በሚዳሰሱና በማይዳሰሱ ቅርሶቿ ተጠቃሽ የሆነች ሀገር ነች። በዩኔስኮ የተመዘገቡ የቱሪዝም ሃብቶቿ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር የጎላ ድርሻ ይኖረዋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ የበርካታ ቱሪዝም ሃብቶች ባለቤት ብትሆንም ዘርፉን በሚገባ አልምቶ ተገቢውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲያመነጭ ከማድረግ አኳያ ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉባት ተደጋግሞ ይገለጻል። ሌሎች ሀገራት ያልታደሉትን ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ፀጋ ብትታደለም፣ የቱሪስት መዳረሻዎቿ በቅርብ ርቀት የሚገኙ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች የመጎብኘት እድላቸው እና ኢኮኖሚ የማመንጨት አቅማቸው በሚፈለገው ደረጃ አይደለም።

መረጃዎችን እና ካርታዎችን መሠረት አድርገው በራሳቸው መንገድ መንቀሳቀስ የሚችሉ፤ በሚፈልጉት ቦታ እየሄዱ እና እያረፉ ያለአስጎብኚ መጎብኘት እንዲችሉ የሚያደርግ አሠራርም አልተዘረጋም። ለሀገር ውስጥም ሆነ ለሀገር ውጪ ጎብኚ ቦታን የሚጠቁም ወይም መዳረሻው ምን ያህል እንደሚያስሄድ ወይም በጉዞ ሄደት ምን ያህል እንደቀረ በየቦታው የሚገልጹ የመንገድ ላይ ምልክቶች የሉንም። በየቱሪስት መዳረሻዎች በቂ የሚባሉ የእንግዳ ማረፊያዎች ባይኖሩም ያሉትንም የእንግዶችን መሻት በሚሞላ መስተንግዶና አገልግሎት ከማሟላት አንጻር ውስንነት ይታያል ።

ይህን ዘርፉን የሚፈታተነውን ችግር ለመቅረፍ፤ ከባለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በመንግሥት በኩል ይህን ታሪክ መቀየር የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች መታየት ጀምረዋል። በኢትዮጵያ የተደረገው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ (Homegrown Economic Reform) ውስጥ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው አምስቱ የኢኮኖሚ መሠረቶች ውስጥ ቱሪዝም አንዱ ነው።

በዚህ መልኩ ትኩረት በመስጠት ለዘርፉ ፈጣን እድገት ዋስትና የሚሆኑ ሞዴል የመዳረሻ ልማት ፕሮጀክቶች በ “ገበታ ፕሮጀክቶች” ከዚህ ቀደም ተገቢ ትኩረት ያልተሰጣቸው ቦታዎችን በመምረጥ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች የሚያበረታቱ ናቸው ። ከነዚህ ውስጥ ቀደም ባለው ጊዜ ተገቢ ትኩረት ሳይሰጠው የቆየው የጎርጎራ ፕሮጀክት አንዱ ነው ።

ከዚህ በተጨማሪ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች አካል የሆኑት የጨበራ ጩርጩራ ፓርክና የወንጪ-ደንዲ ኢኮቱሪዝም ፕሮጀክቶችም ሌሎች ተጠቃሽ ፕሮጀክቶች ናቸው። ከሰሞኑ የተመረቀው የወንጪ-ደንዲ ኢኮቱሪዝም ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ ሥራ መሥራት እንደሚቻል የተረጋገጠበት ነው። መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፉ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ስለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው። በሀገራችንም ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው የተሰጠው ልዩ ትኩረት ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ መጻዔ ጊዜዋ ብሩህ መሆኑን አመላካች ነው ።

ከላይ የተመለከትናቸው ሥራዎች ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው እድገት አዲስ አቅም የሚፈጥሩና ተስፋ የሚያሳድሩም ናቸው። ሀገሪቱ ካላት የተፈጥሮ ፀጋዎች አንጻር ዘርፉ ከዚህም በላይ ሀገራዊ አቅም እንደሚኖረው ይታመናል። ለዚህ ግን ከሁሉም በላይ የሠላም ጉዳይ ትኩረት የሚሻ ነው ።

የሠላምን ዋጋ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው የማይተካ ሚና እንዳለው ይታመናል ። ከዚህ አንጻር ሀገራችን እየገጠማት ያለው የሠላም እጦት በቱሪዝም ኢንደስትሪው ላይ አሉታዊ ጥላ እያጠላ ያለና ያልተደፈነ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ሽንቁር ሆኖ ይገኛል። እንደሚታወቀው በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተከስቶ በነበረው ግጭት ቀጥተኛ ተጎጂ ከነበሩት ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም ነው።

ጦርነቱ በውጪ እና በሀገር ውስጥ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ ጉልህ ተፅዕኖዎችን ፈጥሯል። የውጭ ጎብኝዎች ወደሚጎበኙት አካባቢ ከመሄዳቸው በፊት መጀመሪያ የሚያጣሩት የሠላምና የፀጥታን ጉዳይ ነው። የሠላም ስጋት እንዳለ ከተረዱ መንቀሳቀስ አይፈልጉም። ይህ የአብዛኛዎቹ ቱሪስቶች ዋና መገለጫ ነው። “ሠላም ከሌለ ቱሪዝም የለም” የሚባለውም ለዚህ ነው።

በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የቱሪዝም እንቅስቃሴ ሲቋረጥ በተለይም ሕልውናቸው ሙሉ በሙሉ በቱሪዝም ገቢ ላይ ለተመሰረተ ግለሰቦች እና ከተሞች ከፍተኛ አደጋ ሆኖ ቆይቷል። በከፍተኛ ሁኔታ ቱሪስቶችን በማስተናገድ የሚታወቁት የአክሱም ሐውልት፣ ከወጥ አለት የተፈለፈሉት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ሰሜን ተራሮች የችግሩ ሰለባ ሆነዋል ።

ከግሸን ደብረ ከርቤ እስከ ጎንደር አብያተ መንግሥታት፣ ከአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ እስከ ጣና ሐይቅ ገዳማት፣ ከጭስ ዓባይ ፏፏቴ እስከ ሐይቅ እስጢፋኖስ፣ ከጎርጎራ እስከ ጉና፣ ከዓባይ ሰከላ እስከ ሰቆጣ ሰሃላ በርካታ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ መዳረሻዎች በሠላም እጦት ምክንያት ሳይጎበኙ በመቅረታቸው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን አጥተናል።

ለሀገሪቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መሰናክል የነበረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተቋጨ በኋላ በተለይም በትግራይ አካባቢ የነበረው የቱሪዝም እንቅስቃሴ በተወሰነ መልኩ መነቃቃት ተፈጥሮበታል። ይህም ሆኖ ግን በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች በቱሪዝሙ ኢንዱስትሪው ላይ ሌላ ሥጋት መፍጠራቸው አልቀረም።

በርግጥ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ወደ ነበረበት እንዲመለስ በሀገር አቀፍ ደረጃ መንግሥት፣ ቱሪዝም ሚኒስቴር እና የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ከአጋር አካላት ጋር እየሠሩ ይገኛሉ። በዚህም አንጻራዊ የሆኑ መሻሻሎች ታይተዋል ። ለዚህም በቅርቡ በላሊበላ የተከበረውን የገና በዓልን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።

በቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልና የቤዛ ኩሉ ሥርዓት በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል። በዚህ ሥነሥርዓት ላይ ከ500 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥና የውጪ ቱሪስቶች ታድመውበታል። ይህም አንጻራዊ ሠላም በመኖሩና የማስተዋወቅ ሥራ በመሠራቱ የተገኘ ውጤት ነው።

የቱሪዝም እንቅስቃሴው መሻሻል ከገቢ በላይ ለቅርሶች እና ለቱሪዝም መዳረሻ አካባቢዎች ዋስትና ነው። በገና የታየው መነቃቃት በጥምቀት በዓል ላይ በተሻለ መልኩ የውጭ ጎብኝዎች ወደ ሀገሪቱ እንዲመጡ አድርጓል የሚል እምነት አለኝ ።

የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እንዲያንሰራራ ለማድረግ በሀገሪቱ ዘላቂ እና አስተማማኝ ሠላም ሊኖራት ያስፈልጋል። የሀገር ዘላቂ ሰላም ለቱሪዝም እንቅስቃሴና ያንን ተከትሎ ለሚፈጠረው ኢኮኖሚዊ ተጠቃሚነት ዋስትና የሚሰጥ በመሆኑ ለሠላማችን መትጋት ለነገ የምንለው ጉዳይ ሊሆን አይገባም።

” ጥበብ ይናፍቀኛል ፣

ተቻችሎ የሚኖር ሕዝብ ያስቀናኛል ፣

ድንቁርና ያስፈራኛል ፣

ጦርነት ያስጠላኛል” እንዳለው ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድሕን፤ ዓለም እንደቀደመው ዘመን በእንግዳ ተቀባይነት ያውቀን ዘንድ ሁላችንም ለሠላማችን ዘብ መቆም አለብን። በውጭ የሚኖሩ እና በሀገር ውስጥ ያሉ ዜጎች ሁሉ የሀገርን ገጽታ መገንባት እና ዘላቂ ሠላምን ማረጋገጥ ላይ መሥራት ይኖርባቸዋል። በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ነፍጥ ያነገቡ ኃይሎችም ለሠላም የቀረቡ አማራጮችን በኃላፊነት መንፈስ ሊጠቀሙበት ይገባል ።

ዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You