የሀገራችን ሰላም በእጃችን ነው!

አስራት ፈጠነ የተባለ ግለሰብ ’’ ከአንተ ሌላ ለአንተ ሰላም የሚሰጥህ የለም’’ በሚል ርዕስ በፃፈው መጣጥፍ፤ሰላም ምትክ የማይገኝለት በህይወት የመኖር፣ ሰርቶ የመለወጥ፣ ወጥቶ የመግባት፣ ተኝቶ የመነሳት ምስጢር መገለጫና በገንዘብ የማይተመን ስጦታን በውስጡ የያዘ ነው። ብሏል::

በእርግጥም ያለ አስተማማኝ ሰላም ህዝብም ሆነ ሀገር የመለወጥና የማደግ ተስፋው የሰማይ ያህል ሩቅና የማይደረስበት ይሆናል። በጫካ የሚኖሩ አእዋፋት እንኳ ሳይቀር የመኖሪያ ጎጇቸውን ጠብቀውና የእለት ምግባቸውን ጭረው ለመብላት፣ ተፈጥሮ የለገሳቸውን ዝማሬ ለማሰማት ሰላም ይሻሉ። የዱር አውሬም እንዲሁ።

በተለይማ ወደዚች ምድር ‹‹ለፍተህ፣ ጥረህ፣ ግረህና በላብህ ብላ›› ተብሎ ለተፈጠረው የሰው ልጅ ያለ ሰላም አንድ እርምጃ እንኳን መራመድ እንደማይችል ከተሞክሮ ማየት ይችላል። ሁከትና ብጥብጥ ለአእምሮም ይጨንቃል። ድምር ውጤቱም ጥፋትና ውድቀት ብቻ ነው።

የተራበ ምግብ እንዳያጣ፣ የተጠማም ጉሮሮው እንዳይደርቅ፣ ዳቦ በሌማት፣ ውሃ በእንስራ በበረንዳቸው የሚያኖሩ ዜጎች ዛሬ የሰላምን ንፋስ ይናፍቃሉ:: ከአንዱ ቀበሌ ወደ ሌላው ቀበሌ እንደቀደሙት ጊዜያት እንዳሻቸው መንቀሳቀስ እንዲችሉ ሰላም ያስፈልጋቸዋል::

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች የህዝቡን የዕለት ተእለት እንቅስቃሴ እያስተጓጎሉ ይገኛሉ::ይሑንና ከላይ ከጠቀስነው የሰላም ዋጋ አንፃር መሰል ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የምታገኘውን ሰላም ዘላቂ ማድረግ ያስፈልጋል::

የሀገራችን ዋነኛ የሰላምና ደህንነት ችግር ውስጣዊ ነው:: ዋልታ ረገጥ የሆኑ እና በእኔነት ላይ የተመሰረቱ የብሔርተኝነት ዕሳቤዎች ለኢትዮጵያ ፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ናቸው:: እነዚህ ውስጣዊ ችግሮች መፍትሄ እስካላገኙ ድረስ የቅርብ ሆነ የሩቅ ጠላቶቿ ሁኔታውን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ የተጨማሪ ችግሮች ምንጭ መሆናቸው የማይቀር ነው።

ባለፉት አመታት የተጋፈጥነው የግጭትና መፈናቀል አዙሪት ኢኮኖሚውን ጭምር ምን ያህል እንዳናጋው ታይቷል:: ሰላምን ለመጠበቅ ቅድሚያ ለመስጠት እንዲሁም የፖለቲካ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት ቀናኢ አለመሆን ደግሞ ላለፍናቸው የሰላም ናፍቆት ወቅቶች አጋልጠውናል::

አሁን የሚስተዋለው የኑሮ ውድነት ሀገራችን ካለችበት አሁናዊ ሰላም ጋር ይገናኛል:: አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት ገበያ ላይ አቅርቦ ለመሸጥ የሰላም እጦት ፈትኖታል:: የኢኮኖሚ አሻጥረኞችም ለግል ኪሳቸው ማደለቢያ እየተጠቀሙበት ነው::ሸጦ ለውጦ ህይወቱን መምራት የማይችልበት ሁኔታዎችም ተፈጥረዋል::

በእርግጥ ሰሞናዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ሀገሪቱ ቀደም ሲል አጋጥሟት ከነበረው የደህንነት ስጋት ስለመሻገሩዋ የሚናገረው ቢኖርም፤ከሰላም ጋር በተያያዘ ጎዶሎዋ ግን አሁንም ብዙ ነው:: አሁንም የሰላም ጉዳይ የህዝቡ ጥያቄ እንደ ሆነ ነው። ስለ ሰላም የሚጮሁም በርካቶች ናቸው:: ይሑንና እጅ ላይ ያለን አንፃራዊ ሰላም ጠብቆ ማፅናት የግድ ነው::

እንደ ሀገር አሁን ላይ የተፈጠረውን አንፃራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ የሰላምና ደህንነት ሥራን አጠናክሮ መስራት ያስፈልጋል:: ይህ የሰላምን አስፈላጊነት በማህበረሰቡ ውስጥ ከማፅናት ጀምሮ ሰላሙን በራሱ እንዲጠብቅ ማስቻልን የሚያካትት ነው::

ባለፉት ጊዜያት የሰላም አየር ለመተንፈስ የመቸገራችን ዋነኛ ምክንያት ተደርገው ከሚጠቀሱት መካከል የፖለቲካ ባህላችን አለመዘመኑ አንደኛው ነው::በተለይም አንድን ስርአት በድርድር፣ በሰላም አሊያም በዴሞክራሲዊ ምርጫ ሳይሆን በኃይልና በጉልበት ለመጣል ማሰባችን በንግግር እንፈልገዋለን የምንለውን ሰላም በተግባር አሳጥቶናል::ያለፍንበት የፖለቲካ ባህል እና ፖለቲካው ይሰራበት፣ይተገበርበት፣ ይደረግበት ከነበረው ዘዴ መውጣት አልቻለም:: በሰለጠነ ውይይት ሰጥቶ በመቀበል ሳይሆን በጠመንጃ አፈሙዝ አሸንፎ ሁሉንም አጥፍቶ እንደ አዲስ በመጀመር ነው:: ይሄ መንገድ በፖለቲካ ባህላችን የተለመደ ነው:: ይሄ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ስር ሰድዷል:: ትልቁ ነገር ከዚህ መላቀቅ አለመቻላችን ነው::

ሰላምን ያፀናሉ የምንላቸው የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪክ ማህበራት ተፅዕኖ የማሳደር ጉልበታቸው እየላላ መምጣትም ሌላኛው ነው::ይህም ሀገሪቱን ሰላም እንድታጣ፣ምጣኔ ሀብቷ እንዲዳከምና ከገባችበት ቅርቃር እንዳትወጣ አድርጓታል:: ይሑንና ካለፈው አዙሪት ልንፋታ የሚገባን ትክከለኛው ጊዜ አሁን መሆን አለበት:: ይህ ካልሆነ ሰላም እንደናፈቅን ይቀራል::ሰላምም ማጣጣም የምንሻ ከሆነ ደግሞ ስለሰላም መጨነቅ መስራት መተባበር ይኖርብናል::

በተለይ በሰላም እጦት ትርምስ ውስጥ እንዳንገባ መደረግ ካለባቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል የመጀመሪያው በልዩነቶቻችን ዙሪያ ሀገራዊ መግባባት ላይ መድረስ ነው:: ጠረጴዛ ስበን ቁጭ ብሎ በመነጋገር መግባባት ላይ ልንደርስ እንደምንችል ማመን ብሎም መስማማት አለብን:: የእኔ ብሄር፣ ጎሳ፣ ሰፈር…ወዘተ ከሚለው የተበላሸ እሳቤ መውጣትም ግድ ይለናል:: በተለይ የህዝብ ውክልና ያላቸው ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ልሂቃን ወይም ካድሬዎች ለሰላም በቁርጠኝነት አበክረው መስራት ይጠበቅባቸዋል ::

ለነገዎቻችን ብሩህነት ካለፈው ያለመግባባት ታሪካችን ብዙ ልንማር ይገባል:: ከሁሉ በላይ በኃይል የምንፈልገውን ማሳካት እንደማንችል ጠንቅቆ ሊገባን ግድ ይላል:: ኃይል አሁን ላይ ይህ ዘመኑን የሚዋጅ አስተሳሰብም ብሎም ድርጊት አይደለም።ከዚህ በፊት ተሞክሮ ያልተሳካ ነገር ነው:: ይህ እንደመሆኑም ካለፈው ታሪክና ነባራዊ ሁኔታ ተምረን በሰለጠነው መንገድ በምክክር ፣በምርጫ ስልጣን መያዝ እንዳለበት ማመን አለብን::ከዚህ ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለም በከፊል ሳይሆን በሙሉ ልብ መቀበል ያስፈልጋል::

ልዩነቶችን ሁሉ በጉልበት ለመፍታት የተደረጉት ሙከራዎች ሁሉ ያተረፉት ነገር ሰብአዊ እልቂትና ቁሳዊ ውድመት ብቻ ነው:: በዚህ መካከል ዋነኞቹ ተጎጂዎች የፖለቲካ ተዋንያኑ ሳይሆኑ ንፁሀን ናቸው:: በተለያዩ ምክንያቶች የሚነሱ ግጭቶችን በህገ አምላክ ብሎ ማስቆም ካልተቻለ መጪው ጊዜ ከበፊቱ የበለጠ መከራ ሊያስከትል እንደሚችል ለመገመት ነብይ መሆንን አይጠይቅም:: እዚህም እዚያም የሚታዩ የግጭት ምልክቶች ህብረተሰቡ ጭንቀትና ስጋት የወረረው ህይወት እንዲመራ ምክንያት እየሆነ ነው::

እንዲህ አይነት ተስፋ የሚያሳጡ ችግሮች ሲደጋገሙ የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር ህዝብን የሚያረጋጉና በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የባለቤትነት ስሜት በሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ነው:: እርግጥ ነው ሀገር ችግር ውስጥ በምትገባበት ጊዜ እያንዳንዱ ዜጋ የችግሩ ተጋሪ ብቻ ሳይሆን ከችግሩ የሚያወጡ መፍትሄዎችን እንዲያመነጭና አስተዋፅኦ እንዲኖረው ማበረታታት ነው::

የኢትዮጵያ ህዝብ እርስ በእርሱ ምንም ችግር የለበትም:: ኦሮሞ ከትግሬ፣ትግሬ ከአማራ፤አማራ ከኦሮሞ፣ ወላይታ ከከምባታ፣ ስልጤ ከጋምቤላ፣ ጉራጌ ከከፋው ጋር ምንም ችግር የለበትም::

በዚህ መልክ ከተሳሰረና ከሚዋወድ ህዝብ ዘንድ ዘልቆ ገብቶ የጠብ ዳቦ የሚጋጋረው የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ብሎም በህዝቦች ግጭት ለማትረፍ የሚታትረው ሴረኛው ነጋዴ ነው::

ይህን ሃቅ አሁን ላይ በርካቶች ጠንቅቀው ያውቁታል:: ይህ ማለት ግን ሁሉም ያውቀዋል ማለት አይደለም::አንዳንዶች አሁንም የሴረኞች ሰለባ ሲሆኑ ይስተዋላል:: ይህ መታረም ያለበት ድክመት ነው::ይህን ድክመት ማስተካከልም በኢትዮጵያ ምድር ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ከሚያግዙ ግንባር ቀደም መፍትሄዎች አንዱ ነው::

የሀገር ባለቤት የሆነው ህዝብ ምክረ ሀሳብ ቢጠየቅ መፍትሄዎችን እንደሚያመነጭ መጠራጠር የለብንም::አሁን የኢትዮጵያ ችግሮች የበዙ ቢመስልም በትብብርና በመነጋገር ግን መስመር እንዲይዙ ማድረግ አይከብድም። በሀገረ መንግስቱ ውስጥ ያሉትን ልዩነቶች ቢያንስ እንኳ አጥበን፣ ከሁሉም በፊት ሀገር ትቀድማለች የሚል የተረጋጋ የሰከነ መንግሥትም ከመፍጠርም አንፃር ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል::

የትናንት አብሮነታችን የጋራ ስኬቶቻችን ምስጢር ናቸው:: ለዚህም ነው በችግሮቻችን ላይ ተወያይተን ነገን ያለህፀፅ ለትውልድ ለማስተላለፍ የምናገኘውን አንፃራዊ ሰላምን ማፅናት የግድ ይለናል የሚባለው:: መፍትሄው በሁላችንም እጅ ነው::መንግሥት ሀገረ መንግሥትን የሚያጸኑ ተቋማትን የመገንባት ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት:: ይህን ታሪካዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የዛሬን ሳይሆን የነገዋን ኢትዮጵያ ታሳቢ ያደረገ የተቋማት ግንባታ ላይ ሊያተኩር ይገባል:: ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑም ለዚህ ትልቅ አቅም እንደሚሆን አይጠያይቅም::

መንግሥታዊ ያልሆኑ የሲቪክ ማህበራት፣ የሀገር ሽማግሌዎች በሀገሪቱ በሰላም በማጥናት ሂደት ውስጥ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው::ትክክል ያልሆነውን ትክክል አይደለም ማለት ፤መገሰፅ ያለባቸውን አካል ፊት ለፊት መገሰፅ መቻል አለባቸው:: ሁሉንም በትክክለኛው መንገድ በማስተካከል የኢትዮጵያ ሰላም እንዲፀና ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ::

የብርቱ አርሶ አደር ጎተራዎች በእህል እንዲሞሉ፣ ኢትዮጵያም ምጣኔ ሀብታዊ እድገቷን እንድታስቀጥል፤ የተጀመረው ሀገራዊ ልማት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሻገር ሁለንተናዊ እድገትን እውን ለማድረግ ከሁሉም በላይ ዘላቂነት ያለው ሰላም ማስፈን የግድ ነው:: ለዚህ ደግሞ ሁሉም ዜጋ ስለሰላም በኃላፊነት መንፈስ ሊነሳ ይገባል::

 ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ጥር 18/2016

Recommended For You