ከጩኸቶች በስተጀርባ …

መስማማት፣ መነጋገር፣ መወያየት፣ መመካከርና መሰል ቃላት፤ አንዳንድ አካላትን የሚያስቆጣቸው ለምን እንደሆነ አይገባኝም፡፡ በመስማማት ውስጥ እኩልነት፤ በመነጋገር ውስጥ መደማመጥ፤ በመወያየት ውስጥ መግባባት፣ በመመካከር ውስጥም መተዛዘን አለ፡፡ የእነዚህ ቃላት ተግባራዊ መሆን ሰላምን የማጽናት ያህል ነው፡፡ በተቃራኒው ሲሆን ግን ተደላድሎ መኖር ቀርቶ በሕይወት መቆየት በራሱ ያሳስባል፡፡

ከሰሞኑን ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሠነድ ፈርማለች፡፡ ሰኞ ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ያከናወነችውን ስምምነት ተከትሎም በሚመለከታቸውም ሆነ በማይመለከታቸው አካላት በርካታ መግለጫዎች ወጥተዋል፡፡ እየወጡም ይገኛሉ፡፡ በተለይ ደግሞ በሱማሊያ በኩል ዛቻ አዘል መልዕክቶች ተደም ጠዋል፡፡

እርግጥ ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንዳሉት፤ እነዚህ መግለጫዎች ተጠባቂዎች ናቸው፡፡ እጅግ ጎልተው ሲደመጡ የቆዩት እና አሁንም ድረስ እየተነገሩ ያሉ “የሱማሊያ ሉዓላዊነት ያሳስበኛል፤ የሱማሊያ ሉዓላዊነት መከበር አለበት፤ የሶማሊያ የግዛት አንድነት ሊጠበቅ ይገባል፤ ውጥረት እንዲረግብ ጥሪ አቅርባለሁ” የሚሉና የመሳሰሉ ናቸው፤ ከዚህ በተጨማሪ በቀጣናው ሀገራት መካከል ጠላትነትን ሊፈጥር እንደሚችል ብዙ እየተባለ ነው፡፡

የታሪክ መዛግብት እንደሚያመለክቱት፤ ኢትዮጵያ በዘመኗ የማንንም ሉዓላዊነት ተጋፍታ ሆነ ተዳፍራ አታውቅም፡፡ በዚህ በሰለጠነ ዘመን ደግሞ በጭራሽ አትሞክርም፡፡ እርግጥ ነው ሉዓላዊነቷን ለመዳፈር የቃጡትን በዓለም አቀፍ አደባባይ አሳፍራ መልሳለች ይህ የሚካድ አይደለም፡፡ ከዚህም ስጋት የተነሳ ብዙዎች እድገቷ ያስበረግጋቸዋል፡፡ ትልልቅ ውሳኔዎቿ ያቃዣቸዋል፡፡ ይበልጡኑ ደግሞ ለአህጉራችን አፍሪካ መልካም የሆነ አርዓያነቷ ሰላም ይነሳቸዋልና በሰበብ አስባቡ መተነኳኮሱን ተያይዘውታል፡፡

ወራሪም ሆነ ተወራሪም በሌለበት በስምምነት ለተከናወነ ሰነድ የዚያን ያህል ጩኸት ለምን አስፈለገ፤ የሶማሌ ላንድ ህዝብና መንግሥት ከማንም በላይ የሚጠቅመውን ያውቃል፤ ለዚህ አማክሩኝ፤ችግር አጋጠመኝ ድረሱልኝ ፤ ጩሁልኝ አላሉም። ስምምነቱን ተከትሎ የሱማሊያ መንግሥት የተለያየ መግለጫዎችን አውጥቷል። መግባቢያ ሰነዱ ሕገ ወጥ ነው በሚልም ዓለም አቀፍ ድጋፍ ለማፈላለግ ሰፊ ጥረቶች እያደረገ ይገኛል፤ ይህ ቀጣናው ላይ ካለው የቆየ የፖለቲካ ባህል አንጻር ብዙ ሊያስብል የሚችል አይደለም፤ ተጠባቂ ነው።

ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው ግን፤ ከሀገራቸው ኢትዮጵያ በተቃራኒ የቆሙ አካላት መኖራቸው ነው፡፡ እነዚህ አካላት ስምምነቱን በአደባባይ ለመቃወም ሲወጡና ሲያብጠለጥሉ ከመስማት የበለጠ ምን አንገት የሚያስደፋ አሳፋሪ ነገር ሊኖር ይችላል? ይህ ክስተት በሀገሪቱ ታሪክ ፈጽሞ የሚታሰብ አይደም ።

የመግባቢያ ስምምነቱ መላውን ኢትዮጵያዊ ደስ ያሰኘ ለብዙ ጊዜ አንገት ካስደፋው እውነታ የሚወጣበት ነው። እንደ ሀገር አብዝቶ ሲመኙው የነበረው ነው፡፡ ከዚህ የተነሳም ነው ደስታውን መቆጣጠር አቅቷቸው አደባባይ ወጥተው ደስታውን ለመግለጽ የተገደዱት፡፡

ለነዚህ አካላት ከሀገር እና ከህዝብ ጥቅም ይልቅ የራሳቸው ጥቅም የሚቀድምባቸው ፤ከዚህ የተነሳም ከጠላቶቻችን ጋር አብሮ ለመስራት ሁለቴ ለማሰብ ያልታደሉ፤ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሀገርን አደጋ ውስጥ ለመክተት የማይመለሱ ናቸው። ይህ ባህሪያቸው ደግሞ በተጨባጭ ባለፉት ሶስት ዓመታት በአደባባይ ታይቷል።

ለጥቅማቸው ሲሉ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር ጭምር ተቧድነው በሀገር ጥቅም ላይ ሰልፍ የሚወጡ፤“ወደፊት!” ሲባሉ፤ “ወደኋላ!” ‹‹እንደግ›› ሲባሉ፤ እንፍረስ የሚሉ ናቸው፡፡ ከራስ ጥቅም ይልቅ የሀገርን ጥቅም ማስቀደም ፤ ሀገር ከሚኖራት ትሩፋት ከመቋደስ ባለፈ ለትውልድም መትረፍ መሆኑን ለመረዳት ፈቃደኛ ያልሆኑ ናቸው፡፡

ግራም ነፈሰ ቀኝ እድሜ ለሱማሊላንድ፤ አሁን መተንፈስ የሚያስችለን ባቡር ላይ ልንሳፈር ነው፡፡ ጉዳዩ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተከተለ እንደመሆኑ መጠን ኢትዮጵያም በምትኩ ‹‹እንካችሁ!›› የምትላቸው የገዘፉ ስጦታዎች አሏት፡፡

ታድያ ፈጣሪ የሰው ልጆች እንዲጠቀሙበት የተፈጥሮ ሀብት ዓለም አቀፉን ሕግን ተከትለን ለማደግ ስንደረደር ብዙዎቹን የሚዘገንናቸው ስለምንድን ነው? መቼስ በልተን ከማደር በዘለለ ጡንቻ ለማፈርጠም መንደርደራችን ከወዲሁ ገብቷቸው ስለሆነ በብርቱ እያሳሰባቸው መሆኑን መረዳት አያዳግትም፡፡ እንዲያ ካልሆነማ ‹‹ ከሱማሊላንድ ጋር ተስማማን›› ባልን ዕለት ልክ ‹‹ጦር ልንማዘዝ ነው›› ያልን ያህል ከወዲህ ወዲያ ጫጫታ የበዛ አይሆንም ነበር፡፡

ብዙዎች በዙሪያችን ያለውን የጋራ ሀብት ከምንጠቀምበት ይልቅ አይን አይኑን እያየን እንደ ቅርስ እንድናስተውለው ይፈልጋሉ፡፡ ቅርስ እንኳን ተጎብኝቶ ገንዘብ ያመጣል፤ የእኛ የባህር በር ማግኘት ማንንም የማይጎዳ ሆኖ ሳለ ስለምን እንደ ወራሪ ተመለከቱን ያስብላል፡፡ ኢትዮጵያ በእጅ አዙር እንጂ በራሷ መተንፈስ ካቆመች ሶስት አስርት ዓመት ተቆጥሯል፤ ይህን ልብ ልንል ይገባል፡፡

ቀደም ባሉ ጊዜያት በርካታ ስምምነቶችን ማድረጋችን ይታወሳል፡፡ እንዲያውም ከዚህቺው ሱማሊላንድ ጋር ከወደብ ጋር ተያይዞ ስምምነት ፈጽመናል፡፡ ምነዋ ያኔ ይህ ሁሉ መወናጨፍ አልተፈጠረ?! የአሁኑ የተለየው ለምን ይሆን? ስምምነቱን በአንክሮ፣ በጎሪጥ በጥብቅ፣ በጥንቃቄ በምናምን እየተከታተልነው ነው ማለታቸውስ የበዛው ስለምንድን ነው? ይህንን ለእናንተው ለአንባቢያን ትቼዋለሁ፡፡

ኢትዮጵያ ግን ስውር ፍላጎት ያላቸው አካላት አይናቸው እያየ በሁለት እግሯ የምትቆምበት ጊዜ ቅርብ ነው፤ ይህም አይቀሬ ነው፡፡ ከየአቅጣጫው እየወጡ ያሉ መግለጫዎችም የአንድ ሰሞን ስለሆኑ መምከናቸው የግድ ነው፡፡ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን በቂ ነው።

በስምምነቱ ላይ ያልተገቡ ድምጾችን የሚያሰሙ ኢትዮጵያውያንም የሀገራቸው እድገት የማይቀር መሆኑን በአይናቸው ማየታቸው ስለማይቀር የሚያፍሩበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ፡፡ ከዚህ በኋላ ሀገራችን የማደግ አማራጮቿ ብዙ ናቸው፤ ከእድገትና ልማቷ የሚገታት አይኖርም፡፡ ብትችሉ ኢትዮጵያ ከተያያዘችው የልማት ባቡር ላይ ተሳፈሩ፤ ‹‹ልማት ፣እድገት፣ ብልጽግና…ወዘተ አይመቸኝም›› የምትሉ ከሆነ ደግሞ ከመንገዷ ላይ ዘወር በሉ፡፡

ወጋሶ

አዲስ ዘመን ጥር 18/2016

Recommended For You