የረመዳን ጾም ሊጠናቀቅ ከጫፍ ደርሷል። ህዝበ ሙስሊሙም የሚናፍቀው ወር ሊጠናቀቅ ሰዓታት ብቻ ቢቀሩትም የፀሎትና የበጎነት ተግባራትን አጠናክሮ ቀጥሏል። እኛም ወሩን አስመልክተን በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች ተዘዋውረን የእምነቱ ተከታዮችን አነጋግረናል። “ፆሙ እንዴት ይዟችኋል?” ስንልም ተወያይተናል። ካነጋገርናቸው የእምነቱ ተከታዮች መካከል አንዱ ወጣት ጥላሁን ውቤ ይባላል።
ትውልድና እድገቱ ደሴ፤ ስራው ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አፍሪካ ሬልዋይ ሴንተር የፕሮኪዩርመንት ስፔሺያሊስት የሆነው ወጣት ጥላሁን ለፆሙ ካለው ፍቅር፣ ክብር እና ፅኑ እምነት ባሻገር ለእስልምና እሴቶች ያለውን ጠንካራ አመለካከት ከሚሰጠው ገለፃ መረዳት አያዳግትም።
ፆሙ እንዴት ነው? ስንለው “ወላሂ ፆሙ በጣም አሪፍ ነው፤ ‘ረመዳን የራህመት ወር ነው’ አሁን የምንፆመውም 1440ኛውን የረመዳን ፆም ነው። እስካሁን በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው።” በማለት ነበር የመለሰልን። ረመዳንን አስመልክቶም “ረመዳን በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በመረዳዳት፣ በአንድነት፣ የተቸገሩትን በመርዳትና በሌሎች መልካም ስራዎች ነው የሚገለፀው።” የሚለው ወጣቱ እስልምና ከእነዚህም ሌላ በርካታ እሴቶች ያሉት መሆኑንም ይገልፃል። ወጣት ጥላሁን እንዳለው “አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ መባባል የእስልምና እሴት ነው፤ አገር መገንባት፣ መተጋገዝ፣ መረዳዳት እና ሌሎችም ሁሉ የእስልምና እሴቶች ናቸው።”
እኔ ባደኩበት ደሴ አካባቢ ልዩነት የሚባል ነገር የለም፤ ሁሉም ተግባብቶ፣ ተሳስቦ፣ ተቻችሎ ነው የሚኖረው። የሰውን የማይነካ፣ በአብሮነት የሚያምን፤ የራሱን በግሉ አገራዊ ጉዳዮችን ደግሞ በጋራ የሚያከብር ማህበረሰብ ያለበት ነው፤ ደሴ።
ይህን ደግሞ እኔ ከምገልፀው ይልቅ በተግባር ማየቱ ነገሩን የበለጠ ይገልፀዋል። በብሄር፣ በሀይማኖት ግጭት እኛጋ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። በማለት እስልምናን፣ ረመዳንን፣ የትውልድ አካባቢውንን እና ኢትዮጵያዊነትን አስማምቶ ይገልፃል።
“የዘንድሮውን ረመዳን ልዩ የሚያደርገው መሰረታዊ ጉዳይ አለ” የሚለው ወጣት ጥላሁን በተለይ “ሙእሚኑን (የእምነቱ ተከታይ ማህበረሰብ) በጣም አስጨንቆና አሳስቦ የነበረው የመከፋፈል ጉዳይ በሰላም መፈታቱ የዘንድሮውን ረመዳን በጣም ልዩ ያደርገዋል። ቀደም ባሉት ዓመታት ኢድን ስናከብር በጠመንጃ ነበር፤ ዛሬ ያ ቀርቶ ዘንድሮ በሚሌኒየም አዳራሽ የጋራ የማፍጠር ፕሮግራም መካሄዱ፣ የጋራ ምክር ቤት ምርጫ መከናወኑ፣ ከስድስት ወር በኋላ ደግሞ የጋራ መጅሊስ እንደሚቋቋም ተስፋ መደረጉም ልዩ ስለመሆኑ ማሳያዎች ናቸው።
“ከዚህ ቀደም ‘ዘምዘም ባንክ’ የሚባል የኢስላም ባንክ እንክፈት ብሎ የሙስሊሙ ህብረተሰብ ጠይቆ ተከልክሎ ነበር፤ ይህ አሁን መፈቀዱ ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው።” የሚለው ወጣቱ ምሁር “ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የሙስሊሙን ህብረተሰብ ወደ ልማት፣ አዲስ አበባን ወደማስዋብ፣ በጋራ ወደመስራትና የቱሪስት መስህብ የሆነች ከተማን ወደ መፍጠሩ ተግባር ለማምጣት ያደረጉት ጥሪ ግሩም ነው። በርካታ ቱሪስቶችም እንዲመጡ ያደርጋል። በመሆኑም አዲስ አበባን በማስዋቡ በኩል የሙስሊሙ ህብረተሰብም ሊሳተፍ ይገባዋል።” ሲልም የዶክተር አቢይ ጥሪ ያደንቃል።
“ኢትዮጵያን ወደ ፊት ለማራመድ ሁላችንም ለለውጥ፣ ከድህነት ለመውጣት፣ ለሰላም፣ ለፍትህ፣ በሰላም አብሮ ለመኖር መጣር አለብን። ኢትዮጵያ የምትታወቀው በሰላም አገርነቷ ነው፤ ለዚህም ነው ነቢዩ መሀመድ የመረጧት።” የሚለው ወጣት ጥላሁን የዶክተር አቢይ መንግስት ጥሩ እየሄደ መሆኑንም የገለፀ ሲሆን ባንድ ጊዜ በሁሉም መስክ ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልጉ ሰዎች ትንሽ ሊታገሱ እንደሚገባም አሳስቧል። በተለይ ይህን ዘመን አመጣሽ “አንተ እንዲ ነህ፤ አንቺ እንዲህ ነሽ፤ እከሌ ውጣ እከሌ ግባ የሚባለው ጉዳይ ኢትዮጵያዊ እሴት ካለመሆኑ አንፃር በፍፁም ተቀባይነት የለውም። በመሆኑም እስላሙም ሆነ ሌላው በአንድ ላይ ሆኖ በዱአም በተግባርም ለያወግዘው ይገባል” በማለት መልዕክቱን ያስተላልፋል።
ሌላው ያገኘናቸው ደግሞ የአዲስ አበባው ነዋሪና በግል ቢዝነሳቸው የሚተዳደሩት አቶ ቢላል ከማል ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት ረመዳን ደስ የሚል ወር ነው። ለየት የሚል ነገር አለው። በፊት የመከፋፈል፣ የመለያየት ነገር ነበር። አሁን አቢይ አንድ አድርጎናል። ተፈርቶ ነበር፤ አሁን በጣም ደስ ይላል፤ ሰላም ነው።
አቶ ቢላል ረሱል (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) “ረመዳንን አምኖ እና ምንዳውን ከአላህ ከጅሎ የፆመ ያለፈው ወንጀሉ ይማርለታል። ይህ ወር ለአንድ ሙስሊም ህይወት ዕድል ነው።” ማለታቸውን በተደጋጋሚ በማንሳት በዚህ በረመዳን ወር በሚገባ በአላህ ቃል ለተመራና ለሰራ ሁሉም ነገር እንደሚሳካለት ይናገራሉ።
ለ“አንድነት” ልዩ ክብርና ፍቅር ያላቸው አቶ ቢላል “አንድነት በጣም ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ነው። እስላም ክርስቲያኑ፤ ሁሉም አንድ ነው። እኛ አንድ ነን። ልብስ እንኳን ለልጆቻችን ስንገዛ ሌሎችንም እማንረሳ ህዝብ ነን። እስልምና እንደዚህ ነው። እስላም ክርስቲያኑ ተጠራርቶ ነው የሚበላው። ብሄር ምን ምን ልዩነት የሚባል ነገር ፈፅሞ የለም። ድሮ እኛ ውሀ ተበከለ እንጂ ሰው ተበከለ ሲባል ሰምተን አናውቅም። ይሄ አሁን ነው የመጣው። እስልምናም ሆነ ሌላው ይህን በጭራሽ አይፈልግም፤ ይሄ ፖለቲካው ያመጣው ጣጣ ነው። ህዝቡ ይህን አይፈልግም። የኢትዮጵያ ህዝብ ከድሮ፤ ከጥንት ከናት ካባቶቹ ጀምሮ አብሮ የመጣ፣ እርስ በእርሱ የተዋለደ፤ አንድ ሆኖ እስከ ዛሬ የኖረ ህዝብ ነው። እንለያይህ ቢሉት በፍፁም የማይሆን ነገር ነው። እንዴት አድርጎ መለያየት ይቻላል? በፍፁም አይቻልም።” በማለት ሲገልፁ ሀሳባቸው ካንጀታቸው መሆኑ ከፊታቸው በግልፅ ይነበባል።
“ሁሉም የሆነው ባንድነት ነው፤ ጣሊያን እኮ ባንድነት ስለተነሳንበት ነው የተባረረው። አንድነት ነው የሚያስፈልገን። የመለያየት አጀንዳው የማን እንደሆን እናውቃለን፤ የሌላ ፖለቲካ ነው። አይጠቅመንም፤ አይቻልምም።” የሚሉት አቶ ቢላል ከማል ፈገግ ሲሉም “ጉዳዩ የግል ጥቅም ነው፤ ከነዚህ ሰዎች ህዝቡ እራሱን በራሱ መጠበቅ አለበት። ለአንድነታችን ስንል ሁላችንም እራሳችንንና አገራችንን ከእንደዚህ አይነቶቹ መጠበቅ አለብን” አሳስበዋል።
“አንድነት ያስፈልገናል፤ አንድነት ከሌለ አንተም የለህም፣ እኔም የለሁም፣ ሁላችንም የለንም፣ አገርም የለችም። ከዛስ? በቃ የማንም መጫወቻ መሆን ነው። ይህ ሁሉ እንዳይሆን ማሰብ ያስፈልጋል። እኛ ከማንም በላይ አንድነት ያስፈልገናል። የኖርነው ባንድነት ነው። የሚያምርብን አንድነት ነው። ሁሉ ነገራችን በአንድነት ነው።” ሲሉ ስለአንድነት ያላቸውን ፅኑ አቋም ገልፀውልናል።
እንደ አቶ ቢላል አጋላለፅ አንዳንድ በአገራችን የሚታዩ ጉዳዮች ከእስልምናም ሆነ ከሌሎች ሀይማኖቶች አኳያ ሲታዩ ትክክል አይደሉም። ለምሳሌ “በእስልምና መስረቅ በጣም ክልክል ነው። አገር የሚፈርሰውም በዚህ ነው። በእስልምና ስራ አለመስራት ያስጠይቃል። ስንፍና አይደገፍም። በመሆኑም ሁሉም ከሙስና እርቆ፣ ስራን ሰርቶ” አገራችንን ማሳደግ ይገባዋል።”
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2011
ግርማ መንግሥቴ