መንጋቱ ላይቀር …

በሚገርም፣ በሚያናድድና በሚያስቆጭ ሁኔታ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሆና ከሦስት አሥርተ ዓመታት በላይ ቆይታለች። ይሄ የኢትዮጵያ ወደብ ጉዳይ በሀገር ቤትም ሆነ በውጭው ዓለም ማኅበረሰብ እሳቤ ግብዓተ መሬቱ የተፈፀመና ያለቀለት ይመስል ነበር። በዚህ ጭጋግ በበዛበትና ደመናው በከበደበት ሰዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጉዳዩን የአደባባይ አጀንዳ አደረጉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብልጽግና አባላትንና የሚመለከታቸውን ክፍሎች ሰብስበው ስለ ጉዳዩ ሲገልፁ ብዙዎቹ ተገርመው ነበር። በተለይ ስለወደብ አስፈላጊነት የሰጡትን ትንታኔ ምንም ዓይኑን ሳያሽ ያመነው ዜጋ ቁጥር ቀላል አልነበረም። በርግጥም ጉዳዩ ዓይን የሚያሳሽ አልነበረም።

በጉዳዩ ላይ ያደረጉት ገለጣ ከወደብ አስፈላጊነት ባሻገር፣ አማራጭ አስተማማኝ የወደብ አገልግሎት ለማግኘት እንደ ሀገር የሚደረገው ጥረት ሰጥቶ በመቀበል፣ አብሮ በመለወጥ መርሕ የተገዛ መሆኑ፤ ዜጎች በጉዳዩ ላይ ወጥ የሆነ አቋም እንዲይዙ አድርጓል።

በተለይ ያለ ወደብ መኖራችን ልክ ጂኦግራፊያዊ እስር ቤት /geographical prison/ ውስጥ እንዳለን ከማስመሰሉ ጋር አያይዘው፤ ወደብ ለኢትዮጵያውያኖች ግድ ስለማለቱ ጉዳይ ያነሱት ለብዙዎቻችን አሳማኝ ነበር። አንድ ቀን መነሳቱ አይቀርም እያልን በየልቦናችን የምንጠብቀውና የምንፈልገውም በመሆኑ ሁላችንም ጆሯችንን የሰጠነው ስለመሆኑ መሸሸግ አይቻልም።

ይሄንን ሳይንሳዊ ትንታኔና ታሪካዊ ዳራ የተንተራሰ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ገለፃ በመገናኛ ብዙኃን የተከታተለ ሁሉ መገረሙ አልቀረም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ምን ሆነው ነው ግብዓተ መቃብሩ ከ30 ዓመት በፊት የተፈፀመውን ይሄን የወደብ ጉዳይ ዳግም በማንሳት የሕዝቡን ቁጭት መቀስቀስ የፈለጉት?” በሚል የታዘቡ መኖራቸውም አልቀረም።

ከዚሁ ትዝብት ጋር ተያይዞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ ከበስተጀርባው አንዳች ሸፍጥ ያለው ስለመኖሩ የጠረጠሩና በሽሙጥ ዓይናቸው አይተው የሸረደዱትም ወገኖች አልጠፉም። እነዚህ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለወደብ አስፈላጊነት የሰጡትን እውነታ አዘል ትንታኔ ሳይቀር ሽምጥጥ አድርገው ጠቀሜታውን ክደዋል።

እንዳውም “መንግሥት አሁን በተጨባጭ በኢትዮጵያ ውስጥ የገጠመውን አንዳንድ ተቃውሞና ወቅታዊ እውነታ ለመሸፈን የተጠቀመበት ዘዴ ነው” ሲሉም መላ ምታዊና ግላዊ ግምታቸውን ከየኪሳቸው እያወጡ የሰነዘሩ ነበሩ።

ያም ሆነ ይህ በማይታመን ፍጥነት ሀገራችን በወደብ ጉዳይ ከሶማሌ ላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟ ተሰማ። አስደማሚው ፊርማ በርበራ ወደብን ለመጠቀም የ50 ዓመት ውልን ማሰሩም ተበሰረ። በነገራችን ላይ ውሉ ከዚህም በላይ ሊራዘም መቻሉ ታሳቢ መሆኑ እንደተጠበቀ ነው።

ዞሮ ዞሮ ይህ ከአዲስ አበባዋ ፒያሳ ተነስቶ እስከ ዱከም እንደውም እስከ ደብረ ዘይት መዳረሻ የሚዘልቀው የ20 ኪሎ ሜትር የሊዝ ኮንትራት ውል መታሰሩ ተረጋገጠ። ይሄ ከ90 በመቶ ለሆኑ ኢትዮጵያውያኖች የምሥራች ነው። ብዙዎች ደስታቸውን ሲገልፁ ተደምጠዋል። ፌሽታም አድርገዋል።

ሐርጌሳን መዲናዋ ያደረገችውን ሶማሌ ላንድ ጨምሮ ምሥራቁን የሀገሪቱን ክፍሎች ማልማቱ በተለይ ድሬዳዋን የምሥራቅ አፍሪካ የኢንዱስትሪ ከተማ ማድረጉን ምሑራን ተነተኑ። እስከ በርበራ የሚዘልቀው የፈጣን የባቡር መስመር ዕውን ሊሆን እንደሚችልም ተነበዩ። ትንቢቱ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ በተግባር ተፈፅሞ የመታየቱን አይቀሬነትም እየተነገረ ነው።

ስምምነቱ ተጎራባች ሀገራቱን ከጉርብትና ባሻገር በልማትም እርስ በእርስ የሚያስተሳስርና ሕዝቦቻቸውን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም አነሱ። ኢትዮጵያ ላለፉት 30 ዓመታት በተሳሳተ ፖሊሲና ስትከተል በቆየችው ከዚሁ ጋር የተወዛገበ የፖለቲካ አቅጣጫ ያጣችውን ወደብ በመጠቀም ልማቷን ማፋጠን እንደምትችል ሲገልፁ ሰነበቱ።

ሀገሪቱ ወደፊት ኢኮኖሚዋ እያደገ ሲሄድ በአካባቢው የሚገኙ ወደቦችን የመጠቀም አቅሟ እየጨመረ መሄዱ አይቀርም። እንደ ሶማሌ ላንዱ ወደብ ሁሉ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው በጋራ መልማት የሚችሉባቸው ሰፊ ዕድሎች አሉ። የነዚህ ሁሉ ይፋ መሆን ከወደቡ ተጠቃሚነት ፊርማ ጋር ተያይዞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ መባነን የጀመረው አቧራ ይበልጥ ተነሳ።

እዛም እዚህም በተፈጠሩ ግላዊ መላምቶችና ግምቶች ታጅቦ የባሰውኑ መቡነኑን ተያያዘው። በዜግነት “ኢትዮጵያዊ ነን” ብለው ወገባቸውን ይዘው የሚሞግቱ ግን በተግባር ኢትዮጵያዊነታቸው ጠብ ሲል የማይታይ ኢትዮጵያዊ ተብዬዎች ሁሉ አቧራ በማስነሳቱ ጎራ ታደሙ።

የሞቃዲሾዋ ሶማሌ “ለጊዜው ከሶማሌ ላንድ ጋር ብንለያይም አንድ ሀገርና አንድ ሕዝብ ነን” የሚል የያገባኛል ቅሬታ አነሳች። ይሄንኑ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ግብፅ ሳትቀር ከነዚሁ አቧራ አስነሽዎች ጎራ ተሰልፋና ከስድስት በላይ ቦታ እንደተከፋፈለች ለሚነገርላት የሞቃዲሾዋ ሶማሌ ተቆርቋሪ መስላም የቅሬታ ድምጿን አሰማች። እንዳውም ተቃውሞውን በግንባር ቀደምትነት በመምራት የጎላ ተሳትፎ በማድረግ የተነሳውን አቧራ የበለጠ አጨሰችው።

ግብፅንም ሆነ የሞቃዲሾን ሶማሌ እንደዚሁም በግብር ኢትዮጵያዊነት የማይንጸባረቅባቸውን ኢትዮጵያዊ ነን ባይ የዚህ የተቀደሰ የወደብ ተጠቃሚነት ጉዳይ ከዓላማው በራቀ መንገድ ከአቅሙ በላይ አጯጯሁት። ከጎረቤቷ ኢትዮጵያ ጋር በጋራ መልማት ላይ ልቧ የተንጠለጠለው ሶማሌ ላንድም በፍጹም ጆሮዋን አልሰጠቻቸውም።

በእርግጥም የሁሉም አቧራ አስነሽዎች ሁኔታ እዚህ ግባ የሚባል ዓይነት አይደለም። በርግጠኛውና በተጨባጩ ዓለም ወደቡ መልማቱ ላይቀር የነሱ እንዲህ መሆን ምን ይሉታል?። አቧራ ያነሱት ሰዎች ሀሳብ የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን ነገን ማየት ያልቻለ ፤በንጋት መንገድ ላይ መቆሟን ያላስተዋሉ ናቸው። ኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿ ይህንን ቀን መሻገራቸው፤ወደቡም መልማቱ የማይቀር ነው። መንጋቱ ላይቀር ይሉኋል ይኸው ነው !።

በሰላም

አዲስ ዘመን ጥር 17/2016

Recommended For You