ከቀጣናዊ እስከ ዓለምአቀፍ ትስስር

ወቅታዊና ሰሞነኛ ከሆኑ ኢትዮጵያዊ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የባሕር በር ነው፡፡ እንደ አንድ ሰፊና ነፃ ሀገር የባሕር በር ጥያቄን ስናነሳ በብዙ ሀገራዊና አፍሪካዊ ምክንያቶች ታጅበን ነው፡፡ ከምክንያቶቻችን ጥቂቶቹን ብንገልጽ እንኳን ከቀጣናዊ ጉርብትና ጀምሮ እስከ ዓለምአቀፉ የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ድረስ ያለውን ይይዛል፡፡ ለተረዱን ዓላማችን አንድና አንድ ኅብረ – ውህድ የበረታበት ቀጣናዊ አብሮ የመልማት ዓላማ ነው፡፡

እንደሀገር የመጀመሪያው ዓላማ ኢትዮጵያ እንድትጠቀም ማድረግ ነው። ኢትዮጵያ ትጠቀም ስንል ግን ሌላውን ሀገርና ሕዝብ ጎድተን አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን የምንጠቅምበት ሂደትም ያለንን በመስጠት፣ የሌለንን ደግሞ በመቀበል ነው፡፡ ይሄ ሂደት በቀጣናው ያሉ ሀገራትን ከማስተሳሰር ጀምሮ፣ አፍሪካን አንድ ወደማድረግና በዓለምአቀፍ ደረጃም የላቀ ሚናን ከመወጣት አንጻር የሚሰላ ነው፡፡

ሌላው የባሕር በር ጥያቄአችንንም ሆነ ሌሎች የሁለትዮሽ የጋራ ጉዳዮችን በተመለከተ ሁላችንንም የሚያግባባው እውነት የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲና የጉርብትና ትስስሮች በአንድ ሀገር የበላይነትና የብቻ ፍላጎት ነፀብራቅ የሚሆኑ አለመሆናቸው ነው፡፡ ይሄ ማለት ሁሉን አካታች የጋራ መር የሆነ ውይይትና ተግባቦትን ይሻል፡፡

እኚህ ሂደቶች በሰጥቶ መቀበል መርህ፣ በመነጋገርና በመግባባት ጽንሰ ሃሳብ፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ አብሮ በማደግ መርህ ሁሉን አቃፊ በሆነ ሥርዓት የሚመሩ ናቸው፡፡ እውነታው ይሄና ይሄ ከሆነ፤ ጥያቄአችን በየትኛውም መልኩ ቢታይ ፍትሐዊ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከታሪክ አኳያ ቢቃኝም ጥያቄአችን ነውር ያለው አይደለም፡፡

ከቀይ ባሕር ጋር የነበረንን የበላይነት ለማየት በዓለም ላይ አራት ከሚሆኑ የወቅቱ ገናና እና ሥልጡን ሀገራት አንዱ እንደሆንን የአክሱም ሥልጣኔን ማስታወሱ ብቻ በቂ ነው፡፡ ከተፈጥሮ አንጻር ደግሞ ቀይ ባሕርና ኢትዮጵያ በጥቂት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እየተያዩ ያሉ እንደሆኑ መረዳት ይቻላል፡፡

እንደሀገር የጥያቄአችን ትልቁ ዓላማ ‹ሁሉን አቃፊነት፣ የአብሮ ማደግ መርህ› ነው፡፡ በባሕር በር በኩል በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ በሌሎች የእርስ በርስ ግንኙነቶች በኩል ተጠቅመን ሌሎችን ለመጥቀም ያነሳነው የይገባኛል ጥያቄ እንጂ ማንንም ለመጉዳት አስበን ያደረግነው አይደለም፡፡

ለብዙ አፍሪካውያን የነፃነት ትግል አቅም የነበረች ሀገር እና ሕዝብ፤ በምንም ዓይነት ሚዛን ሌሎችን የምትጎዳበት የሞራል ልዕልና የላትም፡፡ በባሕር በር ጥያቄአችንም ሆነ በሌሎች አፍሪካዊ ጉዳዮቻችን ላይ ትልቁ ዓላማ አብሮ ሠርቶ አብሮ ማደግ የሚል ነው፡፡ ከጥቂት ለሀገራችን በጎ የማይሹ ሀገራት በስተቀር ይሄንን ፍላጎታችንን ብዙዎች ይረዱታል፡፡

አንዳንድ ሀገራት በወቅታዊው ሁኔታ ምቹ አጋጣሚ ያገኙ መስሏቸው ተገቢ ጥያቄአችንን ተገቢ እንዳይደለ በማናፈስ ታሪካዊ ትስስራ ችንን ለማላላት ይሞክራሉ፡፡ በይገባኛል ስም ያነሳነውን የባሕር በር ጥያቄ ታሪክ ነጋሪና ተፈጥሮን ዘካሪ ከሆኑ ጥያቄዎች ሁሉ ምርጡ ጥያቄ ነው፡፡ ምርጥነቱን የሚያጎላው ደግሞ ከሕዝብ የዕለት ተዕለት የፍላጎት መናር ተነስተን የተፈጥሮ ሀብታችንን ለጋራ ዓላማ በጋራ እንጠቀም የሚል የእሳቤ መሠረት ላይ የታነጸ መሆኑ ነው። ከጎረቤቶቻችን ጋር የነበረንን ትስስር ከማሳደግና ከሌሎች ሀገራት ጋር አዲስ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉርብትናን ከመፍጠር አኳያ የላቀ ስለሆነ ነው፡፡

ዓለም ወደ አንድ መንደር እየመጣች ባለችበት በዚህ ጊዜ፣ ሀገራት አብሮ በፍቅር ተያይዞ ከማደግ ውጪ ምርጫ በሌላቸው በዚህ የትስስር ወቅት፤ አብረን እንልማ፤ አብረን እንደግ የሚለው የኢትዮጵያ ጥያቄ እንግዳ ጥያቄ ሊሆን አይገባም፤ ከሱማሌ ላንድ ጋር የተደረገውም የሁለትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት የዚሁ እውነታ አካል ነው፡፡

ቀጣዩ እንቅስቃሴ እንደ መነሻችን አብሮነትን ያቀፈ፣ ከአፍሪካ ቀንድ ጀምሮ ዓለም አቀፋዊነትን የዋጀ ነው፡፡ እንዲህ ላለው አብሮ ሠርቶ አብሮ ማደግን እንደመርህ ለያዘ አፍሪካዊ ዓላማ ሁሉን አግባቢ አቀራራቢና አስታራቂ ሃሳቦች እንጂ ጎራ ለይቶ የማይሆን ቃላትን መለዋወጥ ለማንም የማይጠቅም ድርጊት ነው።

ኢትዮጵያና ሶማሊያ ጎረቤት ሀገራት ብቻ ሳይሆኑ፤ ታሪክ አብሮ የገመዳቸው፣ ባህል፣ ልማድ፣ ታሪክ የተወራረሱ ሀገራት ናቸው፡፡ ይሄን በመሰለው ሁኔታ በባሕር በር ጥያቄአችን ታሪካችን ይጠነክራል እንጂ አይላላም። ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት የንግድ እና የአጋርነት መንገድ የሚያሳልጥ እንጂ በማንም ሉአላዊነትና የአንድነት ግዛት ላይ አደጋ የሚጥል አይደለም፡፡

ከማስታረቅና ከማግባባት ውጪ እኩይ ዓላማ ይዘው የቆሙ ሀገራት የቀጣናውን ሰላምና መረጋጋት፣ እድገትና ጉርብትና የማይፈልጉ ስለመሆናቸው ለማወቅ ጠቢብ መሆን አይጠይቅም፡፡ እነኚህ ሀገራት የባሕር በር ጥያቄአችንን ዓላማ በሚገባ የተረዱ ቢሆንም በተጻራሪው ለመቆም ተገደዋል፡፡

በዚህ ሁሉ መሀል ግን በላቀ የተግባቦት መንፈስ፣ በበረታ የውይይት መድረክ ሀገራችን ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትስስርን በመፍጠር ከሁሉም ጋር በሰላም ከመኖር ጋር በትብብር ለመሥራት እየጣረች ትገኛለች፡፡ ውጥረትን ከሚፈጥሩና ከሚያባብሱ መግለጫዎች ታቅባ ሁኔታዎችን እንደየ ባህሪያቸው እያስተናገደች ትገኛለች፡፡

በርግጥ ችግሮችን መፍታት የሚቻለው እዚያና እዚህ ሆኖ ቃላት መለዋወጥ ሳይሆን፣ ቀረብ ብሎ መነጋገር ነው፡፡ አሁን ባለው ሂደት የባሕር በር ጥያቄአችን ምላሽ እንዲያገኝ በሁሉም ረገድ የዓላማውን አስፈላጊነትና የአብሮ ማደግ መርሁን ሁሉም እንዲረዱት የዲፕሎማሲ ሥራ ያስፈልጋል፡፡

ይሄን አቅጣጫ በተመለከተ በርካታ ባለሙያዎች የጋራ መግባባት አላቸው፡፡ ለአብነት ያክል ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ቆይታ ያደረጉት በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ‹ኢትዮጵያ በተገቢው ዲፕሎማሲና የሰጥቶ መቀበል መርህ የባሕር በር የማግኘት ሙሉ መብት አላት› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

‹እንደ ኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ከሰፊ ፍላጎት ጋር ይዛ የባሕር በር የሌላት ሀገር በዓለም እንደሌለ አስታውሰው፤ በቀጣዮቹ አምስትና ስድስት አመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ 150 ሚሊዮን እንደሚደርስና ይሄም በዓለም ላይ ብዙ ሕዝብ ካላቸው ሀገራት ውስጥ ከፊት እንደሚያስቀምጣት በመጠቆም የባሕር በር ጉዳይን ከህልውና ጥያቄ ጋር መሳ ለመሳ አቁመውታል፡፡ ይሄን መሰል የሕዝብ ቁጥርና ፍላጎት የሚስተናገደው ደግሞ እንደባሕር በር ባሉ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው ላቅ ባሉ ጉዳዮች በኩል እንደሆነ መስክረዋል፡፡

ከአምባሳደሩ ንግግር ብንነሳ የባሕር በር ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ትርጉሙ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባለፈ ገመናችንን የምንጠብቅበት፣ የደህንነት ዋስትናችንን የምናረጋግጥበት፣ እንደሀገር እየጨመረ ለመጣው ለሕዝብ ቁጥራችን ደግሞ ተመጣጣኝ የፍላጎት ምላሽ የሚሰጥ እፎይ ማያ ነው፡፡ ይሄን ዘርፈ ብዙ ዋጋ ያለው ጥያቄ ሰላም ተኮር በሆነ ውይይትና የዲፕሎማሲ እርምጃ ካልሆነ በእኛም ሆነ በሌላው ወገን በኃይል ትንቅንቅ የማይሞከር ነው፡፡

ወቅታዊውን የኢትዮጵያና የሱማሌላንድ ስምምነት ተከትሎ የመጣውን እሰጣ አገባ በተመለከተም ‹‹ካነሳነው ጥያቄ ጋር በተቃራኒ የቆሙም ሆኑ የሚቆሙ ሀገራት ኢትዮጵያ ወደብ በማግኘቷ ተጎድተው አሊያም የሚጎዳ አካል ኖሮ ሳይሆን እድገትና መጻኢ ንቃታችንን በበጎ ካለመመልከት የመጣ ነው›› ብለዋል። ይሄ የአምባሳደሩ መልዕክት ከይገባኛል ጥያቄአችንም ሆነ ከሌሎች ቀጣናዊ መሻቶች ጋር አሁን ያለንበትን ሁኔታ በግልጽ የሚያስረዳ እውነታ ሆኖ የሚቃኝ ነው፡፡

ማንንም የሚጎዳ አእምሮና ልብ የለንም። ብዙዎችን አስጠልለን ቀን ያወጣን የታሪክ ፊተኞች፣ ከእኔነት የበቀለ ራስወዳድነት ያልጎበኘን የፍትህ ሚዛኖች ነን፡፡ ማንም በሚዛናችን ፊት አንሶና ተጨቁኖ ማየትን አንወድም፡፡ በዚህ ሁሉ ብርቱነታችን ውስጥ ደግሞ ለማንም ጥቅሙን አሳልፎ የማይሰጥ፣ ማንንም የማይፈራና ስለሀገርና ሕዝብ ወደ ኋላ የማያፈገፍግ ወኔ የታደልንም ነን፡፡ ሁላችንንም የሚያግባባ፣አግባብቶም ወደአብሮ መሥራት የሚወስደን መርህ ሰጥቶ መቀበል የሚለው መርህ ነው፡፡

ከጥንት እስከዛሬ ፍላጎቶቻችን ማንንም ጎድተው አያውቁም፡፡ የመጪው ጊዜ እድገትና ተጽእኖ ፈጣሪነታችን አስግቷቸው እንጂ በየትኛውም ዘመን ላይ ያነሳነው ጥያቄ የቀጣናውን ሀገራት ጎድቶ አያውቅም። በውይይት እና በተግባቦት በአጭር ማለቅ የሚችለውን ጥያቄ ነው እሰጣ አገባ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ቀጥተኛውን መንገድ የሚያጠማዝዙት፡፡

ለየትኛውም አብሮ የማደግ ጥያቄም ሆነ የሁለትዮሽ ጉዳይ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ የላቀ ዋጋ አለው፡፡ እዛም እዚህም የሚሰሙ፣ ለማንም ክብር የማይጨምሩ ቃላቶች ቀጣናውን የጦር አውድማ ከማድረግ ባለፈ ትርፍ የለሽ ስለሆኑ፤ ጉዳዮቻችን ወደጠረጴዛ እንዲወርዱና እንድንጨባበጥባቸው ማድረግ ቀሪ የቤት ሥራችን ይሆናል፡፡

ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በላቀ የዲፕሎማሲ ጥረት ከትንሳኤው እንዳደረስነው ቀጣይ ሂደቶቻችንም በዚያ መልኩ መቃኘት አለባቸው። ዓላማው ሰጥቶ መቀበልና ተቀብሎ መስጠት የሆነ ሀገር፤ በማንም ላይ ጫና ለማድረስ ሞራሉ አይፈቅድለትም። የዚህ ሞራል ባለቤት ከሆኑት ውስጥ ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን ቀዳሚዎቹ ነን፡፡ ማንንም ሳንጎዳና ማንም እንዲጎዳን ሳንፈቅድ እንደመጣንበት የአብሮ ማደግ ትናንትና ወደ ነገ ለመሄድ መቁረጥ ጥያቄአችንን እውን ከሚያደርጉ ሂደቶች አንዱ ነው፡፡

እንደ አንድ ትልቅና ሰፊ ሀገር የሕዝባችንን ህልውና ለማስቀጠልም ሆነ መጻኢ ገናናነታችንን ለመቀበል የባሕር በር ያስፈልገናል፡፡ በሕዝብ ቁጥሯም ሆነ በፍላጎት መናር፣ በኢኮኖሚ ግስጋሴም ሆነ በቀጣናዊ ሰላም ማስጠበቅ ሀገራችን ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስፈልጋታል፡፡ አሁን ያለችውም ሆነች ወደፊት የምትፈጠረው ሀገራችን በዚህ የሕዝብ ጥያቄ ውስጥ ስታልፍ ነው ትንሳኤዎቿ እውን የሚሆኑት፡፡

በተያይዞ ማደግ ዓላማችን የገባቸው በባሕር በር ጥያቄአችን ላይ ጠጠር በማዋጣት አብረውን ይቆማሉ፡፡ ይሄ አሁን ላለው መንግሥትና ለትውልዱ ኢትዮጵያን የመታደጊያና የማዋለጃ መርህ ነው፡፡

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You