«ቢበርም ነብር ነው!»

ግብጽ ከሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በተለያዩ ጊዜያት ለድርድርና ለውይይት የማያመች የተምታታ ባህርይ እያሳየች ያለችውን ሁኔታ ስመለከት፤ በተደጋጋሚ የተደረጉ የሦስትዮሽ ድርድሮች ያለስምምነት መበተናቸውን ሳስታውስ፤ በአንድ ወቅት አንድ ወዳጄ የነገረኝ ታሪክ ትውስ ይለኛል። ታሪኩ የሚጀምረውም ሆነ የሚጠናቀቀው በአንድ የእንስሶች ፓርክ ውስጥ ሁለት ሰዎች ቆመው በሚያደርጉት ክርክር ነው።

ታሪኩ እነሆ! ከዕለታት በአንዱ ቀን፣ ሁለት ሰዎች ፓርክ እየጎበኙ ሳለ የአንድ ዛፍ አስተዳደግ ማርኳቸው ያደንቃሉ። አድናቆታቸውን እየገለጹ ባሉበት ጊዜ፣ አንደኛው የዛፉ ዝርያ ምን እንደሚባልና በሚያዩት መልኩ ቁመቱ ለማደግ የሚወስድበት ዓመት ስንት እንደሚሆን በመተንተን ያስረዳል። በመቀጠልም በዛፉ ላይ ቆሞ የሚታየው የአዕዋፍ ዝርያ እንደሆነ ይናገራል።

ሁለተኛው ተመልካች ስለዛፉ ዝርያ የዕጽዋት ዕውቀት ስለሌለኝ አላውቅም፤ ከፊት ለፊታችን ትንሽ ራቅ ብሎ የሚገኘው ዛፍ ላይ ተኝቶ ያለው ግን የአዕዋፍ ዝርያ ሳይሆን የዱር እንስሳ የሆነው ነብር ነው ይለዋል። የመጀመሪያውም ተናጋሪ የእሱ ትክክል መሆኑን ለማሳመን የመከራከሪያ ሃሳቡን ያጠናክርልኛል ያለውን ከነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ለማስረዳት፣ ራቅ ስላለ አልታይህ ብሎ ይሆናል እንጂ ከታች መቁጠር ስንጀምር ሦስተኛው ቅርንጫፍ ላይ ያለው መንቁሩ ነው እየውልህ ሲያንቀሳቅሰው አለው።

ሁለተኛውም፣ እንዲያውም ሦስተኛው ቅርንጫፍ ላይ ያለው አሁን እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የነብሩ ጥፍር ነው፤ ከጥፍሩ አጠገብ ያለው ጭራው አይታይህም ወይ? በማለት ይጠይቀዋል። ጥያቄውን ሲመልስለት ጭራ ያልከው የአዕዋፉ ክንፍ ነው፤ እንዲያውም ሊበር ነው በማለት በአሸናፊነት መንፈስ መለሰለት። ይህ ይሁን እንጂ የሚከራከሩበት አካል ሳይንቀሳቀስ ብዙ ጊዜ ዛፉ ላይ ስላሳለፈ ክርክራቸው መቋጫ አላገኘም።

እንዲህ እንዲህ እያሉ የራሳቸውን የመከራከሪያና የማሳመኛ ሃሳብ እያነሱ ሲነጋገሩ ከቆዩ በኋላ፣ በመጨረሻ ዛፉ ላይ ያለው አዕዋፍ ነው በሚል ሲከራከር የቆየው ሰው ክርክራቸው መቋጫ እንዲያገኝ በሚል የሚያስማማ ያለውን የተለየ ሃሳብ ያነሳል። ይኸውም፣ ዛፉን ድንጋይ ልወርውርና ልምታው። አዕዋፍ ከሆነ ደንግጦ ይበራል፤ ነብር ከሆነ ይዘላል። በዚህ ትስማማለህ ወይ? በማለት ያመጣውን ሃሳብ በማድነቅ ይጠይቀዋል።

ዛፉ ላይ ያለው ነብር ነው በሚል የሚከራከረው ደግሞ ድንጋይ እስከመወርወር የሚያደርስ አይደለም፤ በግልጽ በሚታይ ሁኔታ ዛፉ ላይ ያለው ነብር ነው በማለት የመጀመሪያውን ሃሳብ ያጠናክራል። በመጨረሻ በስንት ክርክር ድንጋይ ተወርውሮ ፍተሻ ማድረጉ ላይ ስምምነት ይደርሳሉ። ከዚያም ድንጋይ ይወርወር ብሎ ሃሳብ ያቀረበው በተከታታይ ድንጋይ ወደ ዛፉ ይወረውራል። ሲከራከሩበት የነበረውም አካል ተነስቶ ይበራል።

በዚህ ጊዜ አዕዋፍ ነው ያለው ክርክሩን አሸንፌአለሁ በሚል፣ በኩራት ይኸው በረረ፤ ነበር አይደለም ሲለው፤ ያኛው ደግሞ ቢበርም ነብር ነው፤ እዘላለሁ ብሎ ነው የበረረው! በማለት ቀደም ሲል የያዘውን አቋም እንደማይለቅ አሳወቀው። የሁለቱ ሰዎች ክርክር በየትኛውም መመዘኛ መቋጫ እንደማያገኝ ‹‹ቢበርም ነብር ነው፤ እዘላለሁ ብሎ ነው የበረረው! ›› የሚለው አባባል ያመላክታል። ምናልባት መቋጫ የሚያገኘው አዕዋፍ ነው ያለው ልክነው ቢበርም ነብር ነው የሚለውን ሃሳብ ከተቀበለ ነው።

ሱዳን በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚደረግ ድርድር የራሷን ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር ይህ ነው የሚባል ጉልህ እንቅስቃሴ እያደረገች እንዳልሆነ ጉዳዩን በጥልቀት የሚከታተሉ ምሁራንና ተንታኞች ሲናገሩ ይደመጣል። ስለሆነም ከላይ የቀረበው ታሪክ ሱዳንን አይመለከትም። ግብጾች ግን በፖለቲካዊ ምክንያት በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ስምምነት ተደርጎ እንዲቋጭ የሚፈልጉ አይመስሉም፤ የዓባይ ጉዳይ ዘላለማዊ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ።

ዓባይ ለግብጽ ሕዝብ ሁሉ ነገራቸው ነው። ይህን የሚያውቁት የግብጽ ፖለቲከኞች ጠንከር ያሉበት ወቅት ሲመስላቸው እንዲሁም የሀገራቸውን ሕዝብ ድጋፍና የሕዝቡን የልብ ትርታ ያነሳሱ ሲመስላቸው ድርድሩን የሚያደናቅፍ ተግባር ያከናውናሉ። ከድርድሩ ወጥተናል፣ አልተስማማንም፣ ወዘተ. በማለት ይናገራሉ። ኢትዮጵያ አየል ብላ መታየት ጀምራለች ባሉበት ጊዜ ደግሞ በዓባይ ጉዳይ ለመደራደር ፍላጎት ያሳያሉ።

ግብጾች እንዲህ ያለ ወጣ ገባ ሃሳብ ይዘው ሲንቀሳቀሱ ግድቡ ተገንብቶ አጠቃላይ አፈጻጸሙ ከ94 በመቶ በላይ ደርሷል። አፈጻጸሙ እዚህ ደረጃ እንዳይደርስ ግብጽ ያልቆፈረችው መሬት፣ ያልቧጠጠችው ዳገት የለም። ነገር ግን በኢትዮጵያውያን የተባበረ ጥረት ግድቡ አሁን ላለበት ደረጃ ደርሷል። በአራት ዙር የውሃ ሙሌት 44 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ለመያዝ ተችሏል።

ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን 4ኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን ካሳወቀች በኋላ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ መግለጫ አውጥቷል። በመግለጫው፣ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ስምምነት ላይ ሳይደረስ የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት መቀጥል በ2015 የተፈረመውን የመርህ ስምምነት እና ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ ነው ብላለች። ኢትዮጵያም በሕዳሴው ግድብ ውሃ ለመያዝ ማንንም ፈቃድ የመጠየቅ ግዴታ እንደሌለባት አሳውቃለች።

ግብጽ በጎርጎሮሳውያኑ 1959 የተፈረመውና፣ የአብዛኛውን የውሃውን ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት ሙጥኝ ብላ «ታሪካዊ» ተጠቃሚነት በሚል መርህ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት አላት። ስምምነቱ ኢትዮጵያን ያላካተተ ከመሆኑ በተጨማሪ ግብጽ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃን እንዲሁም ሱዳን 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃን እንድታገኝና 86 በመቶ የናይልን ውሃ የምትገብረውን ኢትዮጵያ ያለ ውሃ የሚያስቀር አግላይና ኢፍትሃዊ ነው። ግብጽ ድርድሩን ምክንያት በማድረግ ይህንን ስምምነት ኢትዮጵያ እንድትቀበል ጫና እያደረገች ነው። ይህ ደግሞ በማንኛውም ሁኔታ ተቀባይነት የሚያገኝ ሃሳብ አይደለም።

ኢትዮጵያ የተለያዩ ጫናዎችን በመቋቋም እንዲሁም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በማለፍ ግድቡ ካለበት ደረጃ እንዲደርስ አድርጋለች። አሁን ግድቡ ተገንብቷል፤ ውሃ ይዟል። ስለሆነም ራሱን ይጠብቃል። ግድቡ መገንባት የለበትም፤ እናፈርሰዋለን የሚሉ ዛቻዎች አሁን ዋጋ የላቸውም። ግብጽ በተቻላት መጠን ሁሉ ለራሷ ደህንነት ስትል ግድቡን ለመጠበቅ የራሷን አስተዋጽኦ ከማድረግ ታፈገፍጋለች ብሎ ማሰብ ይከብዳል። አሁን ኢትዮጵያ ማድረግ ያለባት የተለያዩ ጫጫታዎች ቢኖሩም የራሷን የቤት ሥራ መሥራት ነው።

ሰሞኑን ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በአዲስ አበባ ሲያደርጉት የነበረው የሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ያለ ስምምነት ተጠናቋል። ድርድሩ ያተኮረው በሕዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል እንዲሁም ዓመታዊ የሥራ ሂደትን የተመለከተ መመሪያ ላይ ነበር። ግብጽ በምትከተለው እና ሙጥኝ ብላ በያዘችው የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብ ምክንያት ጉዳዩ ፈር ሳይዝ ቀርቷል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ የዓባይን ውሃ በፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መርህ ላይ በመመስረት የዜጎችን ፍላጎት ለማሟላት የምታደርገውን ጥረት እንደምትቀጥል አሳውቋል። በግብጽ በኩል ግን የቅኝ ግዛት አስተሳሰቧን በማጠናከር ‹‹ ቢበርም ነብር ነው፤ እዘላለሁ ብሎ ነው የበረረው! ›› የሚለውን አቋሟን እንደያዘች ነው ።

የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከዚህ በፊት እንዳደረግነው በመተባበር ፍጻሜውን እንዲያገኝ እስካደረግን ድረስ ግብጽ በድርድሩ ለመቀጠል ፍላጎት አለማሳየቷ ሊያሳስበን አይገባም። የእኛ መተባበርና መጠንከር ወደ ድርድሩ እንድትመጣ የሚያደርጋት አንዱ ገፊ ምክንያት ይሆናል። ወደፊት ደግሞ የእኛን አንድነት በማየት ‹‹ ቢበርም ነብር ነው፤ እዘላለሁ ብሎ ነው የበረረው! ›› የሚለውን አቋሟን በመቀየር ለእውነተኛ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለመተባበር መትጋቷ አይቀርም።

ስሜነህ ደስታ

አዲስ ዘመን ጥር 16/2016

Recommended For You