በባህር በር ጉዳይ ሁሉም ዜጋ በኃላፊነት መንፈስ ሊንቀሳቀስ ይገባል

የሰሞኑ ትልቁ ሀገራዊ አጀንዳችን የባህር በር ይኑረን አይኑረን የሚል መሆኑን ብናገር ለቀባሪው አረዱት ይሆንብኛል። ነገር ግን የባህር በር ጥያቄ ጦርነት ሊያስነሳ ይችል ይሆን የሚል ሰጋት በአብዛኞቻችን ዘንድ እንደነበር ይታወሳል። ስጋቱ እውነት መሰረት አለው? ወይስ መሰረተ ቢስ? የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በዓለምአቀፍ ህጎች እይታ እንዴት ይታያሉ? የሚለውን ለመመልከት ሞከርኩ።

የባሕር በርን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ሕጎች ፤ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በአቅራቢያቸው የሚገኝ የባህር ወደቦችን በተለያየ አመራጮች የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይደነግጋሉ። ለምሳሌ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባህር ሕግ አንቀጽ 69 ንዑስ አንቀጽ 1 እስከ 5 ያለው ላይ እንደሰፈረው፤ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ካለው ባህር የተፈጥሮ ሀብት እኩል የመጠቀም መብት አላቸው።ዓሳ ማጥመድን፣ በባህር ውስጥ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን ፍለጋ ጨምሮ ሌሎች ከባህር ተፈጥሮ ሀብት ጋር የተያያዙ ሀብቶች ተጠቃሚነት መብትን ያካትታል፡፡

በዚሁ ሕግ አንቀጽ 125 ንዑስ አንቀጽ 1 እንደተመለከተው ደግሞ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ያለውን ባህር የመጠቀም እና የመሸጋገር ዓለም አቀፍ መብት አላቸው። የባህር በር በሌለው ሀገር፣ የባህር በር ባለቤት በሆነው ሀገር እና በቀጣናው መካከል በሚደረግ ስምምነት ሊፈጸም እንደሚገባ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ተመላክቷል፡፡ አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ደግሞ እነዚህ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በስምምነት ከተደረገ የተለየ የአገልግሎት ክፍያ ከሌለ በስተቀር ለተገለገሉበት ባህር ምንም ዓይነት የትራፊክ ታክስ ወይንም ሌላ ክፍያ እንደማይጠየቁ ይደነግጋል፡፡

የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በምስረታ ቻርተሩ መግቢያ ላይ በባህር ሕግ ጉዳዮች ላይ ባሰፈረው ሀተታ የአፍሪካ ሀገራት የባህር በር ያላቸውን ጨምሮ ከባህር ሊያገኙት የሚገባቸውን ጥቅም እያገኙ እንዳልሆነ ጠቅሶ፣ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ከባህር የመጠቀም መብታቸው ሊጠበቅ እንደሚገባ እና ይህም ከዓለም አቀፍ መርህ አንጻር መታየት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ከላይ ባነሳናቸው ድንጋጌዎች መሰረት ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት መብት የላትም ትላላችሁ ? እንደኔ እንደኔ ከታሪክ፣ ከሞራል፣ ከዓለም አቀፍ ህግም አኳያ አካባቢዋ ባሉ ወደቦች የመጠቀም መብት አላት።

ኢትዮጵያ ከባህር በር ጋር ያላት ታሪካዊ ዳራ ሲታይ የጎን ስፋቱ ፤ከ50 እስከ 60 ኪሎ ሜትር የማይበልጠውን እና ከመርሳ ፋጡማ ተነስቶ የትግራይን እና አፋርን ምድር እየታከከ ቁልቁል እስከ ራስ ዱሜራስ የሚወርደውን ቀጭን መሬት ያየ ሁሉ፤ የኢጣሊያ ቅኝ ገዢዎች ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር የሚያስወጣ መሬት እንዳይኖራት ሆን ብለው ያጠሩት አጥር መሆኑን መረዳት ይሳነዋል ብዬ አላስብም። ኢትዮጵያ ይህንን አጥር አፍርሳ ኤርትራን ለመቀላቀል ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ጥያቄ ባቀረበችበትና ሙግት ባካሄደችው የዲፕሎማሲ ዘመቻ ወቅት የባህር በር እንድታገኝ የሚያስችል መሬት ተፈቅዶላት እንደነበረ ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማርያም “አሰብ የማን ናት? (የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ)” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ አስፍረዋል።

የኢትዮጵያ የወቅቱ ጥያቄ መላዋን ኤርትራ ከኢትዮጵያ ማዋሃድ ስለነበር የተፈቀደላትን የባህር በር የማግኘት አማራጭ አልተቀበለችውም ነበር። ክርክሩ እና የዲፕሎማሲው ዘመቻ ፍሬ አፍርቶ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትቀላቀል ተወስኖ ኢትዮጵያም ዳግም የባህር በር መሆኗ ይታወቃል። እንደ ዶክተር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም ፤በወቅቱ የነበሩት መንግሥታት በፌዴሬሽኑ አያያዝ ላይ በተከታታይ በፈፀሟቸው ስህተቶች ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ጦርነት ተካሄደ።በጦርነቱም ብዙ ደም መፋሰስ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል።ኤርትራ ነጻ ሀገር እንድትሆን በተፈቀደበት ወቅትም ኢትዮጵያ ሕጋዊ የባህር በር ባለቤትነቷን እንዳታቀርብ በወቅቱ የነበሩት መሪዎቿ ተቃውመው ባዶ እጇን እንድትቀር አደረጓት፡፡

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ ከተደረገ ጀምሮ በትኩረት እየተሰራባቸውና ለውጥ እየመጣባቸው ካሉ ጉዳዮች አንዱ የባህር በር ጥያቄ ነው።መንግሥት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለዘመናት ቁጭት ፈጥሮ የነበረውን የባህር በር ጥያቄ በመመለስና ስብራትን በመጠገን ታሪካዊ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል። አሁን ላይ ከብዙ ጥረት በኋላ ኢትዮጵያ ከሶስት አስርት አመታት በኋላ የባህር በር የምታገኝበት አማራጭ ተገኝቷል።ሰላማዊ አማራጭን ሲከተል የቆየው የኢትዮጵያ መንግሥት ሰሞኑን ከሶማሌ ላንድ ጋር የባህር በር የሚገኝበትን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል።ይህ ሲሆን፤ ታዲያ በርካታ ዜጎች በደስታ ጮቤ ረግጠዋል።የኢትጵያን ከፍታ የሚናፍቁ ወገኖችም ደስታቸውን ገልጸዋል።

በተቃራኒውም ለኢትዮጵያ በጎ የማይመኙ አንዳንድ ሀገራት እና ታሪካዊ ጠላቶቻችን ልክ የባህር ባር ልታገኝ ቀርባለች ሲባል የተቃውሞ ድምፃቸውን ማሰማት ጀመሩ። የሚያሳፍረው፤ አንዳንድ ዜጎቻችን ስምምነቱን ከሌሎቹ እኩል ሲቃወሙ መስማታቸው ነው።ይህ አሳዛኝ ታሪካዊ ክስተት በዓለም አቀፍ ደረጃም ግርምት ፈጥሯል። የቀደሙ ታሪኮቻችን እንደሚያመለክቱት፤እንደ ሀገር ለባህር በር (ለወደብ) ብዙ መስዋአትነት ከፍለናል። የባህር በር ጉዳይ ለየትኛውም ኢትዮጵያዊ ከፖለቲካ እምነትና አስተሳሰብ በላይ ነው። ይህንን ሀገራዊ ጉዳይ አቅልሎ ማየት በየትኛውም መመዘኛ ተገቢ ያልሆነ የታሪክ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ነው።

አሁን ላይ እስከ ዛሬ በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ከእጃችን የወጣውን ይህንን መብት ለመመለሰ በምን መልኩ እንሂድ የሚለው ጉዳይ፤እንደ ዜጋ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳችን ሊሆን ይገባል፤ ለዚህ ጥንቃቄ የታከለበት በሳል አካሄድ ልንከተል ይገባል።ለዚህ ደግሞ ሁሉም ዜጋ በኃላፊነት መንፈስ ሊንቀሳቀስ ይገባል።

 አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ጥር 15/2016

Recommended For You