ኢትዮጵያ ድርቅ በተደጋጋሚ ከሚያጠቃቸው የአፍሪካ ሃገራት አንዷ ናት፡፡ በተለይም ቆላማና አርብቶ አደር የሃገሪቱ አካባቢዎች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በሚከሰቱ ድርቅ፣ ጎርፍና የአንበጣ ወረርሽኝ የመሳሰሉ ችግሮች ተጋላጭ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተውም፤ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ስፋት 62 በመቶ የሚሆነው ቆላማ አካባቢ ሲሆን፣ በዚህ አካባቢ ደግሞ ከሀገሪቱ ህዝብ 12 በመቶ የሚሆነው ኑሮውን የመሰረተውም በዚሁ አካባቢ ነው፡፡
ይህ ቆላማና በርሃማ የሃገሪቱ አካባቢ በተደጋጋሚ በአየር ንብረት ለውጥ በከፍተኛ ደረጃ ተጎጂ ሲሆን፣ በዋናነትም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብን ተከትሎ በሚከሰት ጎርፍና ዝናብ እጥረት አርብቶ አደሩም ሆነ የህልውናው መሰረት የሆኑት እንስሳት ለከፋ ችግር የሚጋለጡበት ሁኔታ ሰፊ ነው፡፡
እምቅ የተፈጥሮ ሃብትና አቅም ያለበት አካባቢ እንደሆነ የሚጠቀሰው ይህ አካባቢ በአንፃሩ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ለአደጋ ስጋት ተጋላጭ መሆኑም ይገለጻል፡፡ ይህም ሁኔታ ባለው ሃብት ተጠቃሚ እንዳይሆን እያደረገው መሆኑን ነው መረጃው የሚያመለክተው፡፡
የኢትዮጵያ ስታስቲክስ ኤጀንሲ በእ.ኤ.አ 2020 ያወጣው መረጃ እንደሚጠቆመው፤ ኢትዮጵያን በቀንድ ሃብቷ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም መሆን የቻለችው ከዚሁ አርብቶአደር አካባቢ ከሚገኝ የእንስሳት ልማት ሃብት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት 65 ሚሊዮን የቀንድ ከብት ፣ 40 ሚሊዮን በግ ፣ 51 ሚሊዮን ፍየል፣ ስምንት ሚሊዮን ግመል፣ 49 ሚሊዮን ዶሮ እንዳላት ይገመታል፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 90 በመቶ የሚሆነው የእንስሳት ሃብት የሚገኘው ከዚሁ አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ ነው፡፡
ኢጋድ በእ.ኤ.አ ባወጣው መረጃ ደግሞ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ወደ ውጭ ከምትልከው የቀንድ ከብት ከ200 እስከ 300 ሚሊዮን የሚገመት ዶላር የምታገኘው ከዚሁ አካባቢ ነው፡፡
ከባህል ጠለል አንድ ሺ 500 ሜትር በታች ላይ የሚገኘው ይህ ቆላማ አካባቢ በዋናነት አዋሽ ፣ዋቢ ሸበሌ፣ ገናሌ ፣ ባሮ፣ ዳዋ እና ኦሞ ወንዞች ይገኙበታል። ይሁንና በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖረው አርብቶ አደር በየዓመቱ በሚከሰተውና ተከታታይነት ባለው ድርቅ የአደጋ ስጋት ተጋላጭ ሆኗል፡፡ ይህንንም አደጋ ሽሽት ቀዬውን ለቆ ለመሰደድ የተገደደው ይኸው ማህበረሰብ፣ በምግብ እህል ራሱን መቻል ተስኖት የበጎአድራጊዎች እጅ የሚጠብቅ ሲሆን ይስተዋላል፡፡
ይህንን ማህበረሰብ ከተጋረጠበት የድርቅ አደጋ ለመታደግና ሃገሪቷንም በእንስሳት ሃብቷ ተጠቃሚ ለማድረግ መንግስትም ሆነ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ፕሮጀክት ቀርፀውና በጀት መድበው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየውም፤ በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖረውን ማህበረሰብ ህይወት ለመታደግና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ፕሮጀክቶች በዓለም ባንክ ፣ አሜሪካ ልማት ድርጅት፣ አውሮፓ ህብረት፣ ጀርመን ተራድኦ ድርጅት፣ አፍሪካ ልማት ባንክ የመሳሳሉት ድርጅቶች ድጋፍ እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡
ይህም ድጋፍ የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለመለወጥ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። ይሁንና የእነዚህ የልማት አጋሮች በተናጠል የየራሳቸውን በጀት፣ የሰው ሃይልና አቅም አሰባስበው የሚሰሩት ሥራ የሚፈለገውን ውጤት በፍጥነት ማምጣት አለማስቻሉ ይገለጻል፡፡ በተለይም ባለመናበብ በተመሳሳይ ቦታ፤ ተመሳሳይ የልማት ሥራ ለመስራት የሚያደርጉት ጥረት ችግሩን ስር ነቀል በሆነ መልኩ ለመፍታት አለማስቻሉን ነው የዘርፉ ተዋናዮች የሚያስረዱት፡፡
ማህበረሰቡን በዘላቂነት ከድርቅ ተጋላጭነት ማላቀቅ ያስችል ዘንድ እነዚህ በተናጠል የሚማስኑትን የልማት አጋር ድርጅቶች ሥራ ወደ አንድ ማምጣትና የመፈፀም አቅምን ማጠናከር ዓላማው ያደረገ ፕሮጀክት ከሰሞኑ በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ይፋ ተደርጓል፡፡ በአሜሪካ የበጎ አድራጎት ድርጅት (ዩ.ኤስ ኤይድ) ድጋፍ የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት በዋናነት የልማት ስራዎችን የማስተባበር፤ የማቀናጀትና የግንኙነት አግባብን ለማጠናከር ያስችላል ተብሎ እምነት ተጥሎበታል፡፡
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እንድሪያስ ጌታ እንደተናገሩት፤ ከዩ.ኤስ. ኤይድ ጋር በጋራ በመሆን የሚተገበረው ይኸው ፕሮጀክት በዋናነት በአራት ክልሎች የሚገኙ ቆላማ አካባቢዎች ላይ የሚሰሩ አጠቃላይ ሥራዎችን ለማቀናጀትና ለማስፈፀም የሚያስችል ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በአሜሪካ መንግስት እርዳታ በተገኘ ሶስት ሚሊዮን ዶላር የሚከናወን ሲሆን፣ የማስፈፀም አቅም ለመገንባትና የትብብር ስራን ለማያስኬድ ያግዛል፤ ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታትም በተመረጡ አካባቢዎች ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፣ በተለይም በኦሮሚያ ክልል አርብቶአደር ዞኖች፤ ሱማሌ፤ አፋር እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኦሞ ዞን ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ዝርዝር ሥራዎች ተለይተው ውጤታማነትን ሊያረጋግጥ በሚችል አግባብ ተመርጦ ይተገበራል፡፡
እስካሁን ድረስ ቆላማ አካባቢዎች በተለይም በአርብቶ አደር አካባቢዎች በርካታ ፕሮክቶች መንግስታዊ፣ ሀገር-በቀልና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተለያዩ የልማት አጋሮች የሚገኘውን ሃብት ተጠቅመው የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን ዶክተር እንድሪያስ ያስታውሳሉ። ‹‹እነዚህ በተለያዩ አካላት የሚከናወኑ ስራዎች በውጤታማነት ደረጃ ሲለካ ያን ያህል የህብረተሰቡን ኑሮ ሲቀይሩ አይታዩም›› ይላሉ፡፡ እንደ ድርቅ የመሳሰሉ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሲደርሱ የእለት ደራሽ እርዳታ ከመለገስ ባለፈ ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም መፍጠር አለመቻላቸውን ያስረዳሉ፡፡
‹‹በፌደራል ደረጃ በእኛም ሆነ በግብርና ሚኒስቴር፤ በክልል መንግስታት እንዲሁም በበርካታ የልማት አጋሮች የቆላማ አካባቢዎችንና አርብቶ አደሮችን ኑሮ ለማሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎች ይሰራሉ፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ሁሉም በተናጠል የሚንቀሳቀስበት፤ ትብብር፤ ቅንጅት የማይታይበት፤ ተጠያቂነት የሌለበት፤ ውጤታማነት በአግባቡ የማይፈተሽበት ሁኔታ ነው ያለው›› ሲሉ ያብራራሉ። በዚህም ምክንያት በተለይም ድርቅን ለመከላከል እና ቀጣይነት ያለው ልማት ለማምጣት የተሰሩ የመስኖ እና መሰል ሥራዎች አመርቂ ውጤት አለማምጣታቸውን ያመለክታሉ፡፡
ተጨባጭና አርብቶ አደሩን ማዕከል ያደረገ ለውጥ ለማምጣትም እነዚህን በተለያዩ አካላት የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግም ያስረዳሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ አቅም ሊኖር እንደሚገባ ተናግረው፤ ‹‹እስከ አሁን ድረስ በፌዴራልም፤ በክልል ደረጃም የማስተባበርና ወደ አንድ ማምጣት የሚያስችል አቅም በሚፈለገው ደረጃ አልተገነባም፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ደንብም መመሪያም አልነበረም›› ሲሉም ያብራራሉ፡፡
ችግሩ የፋይናንስ ድጋፍ እጥረት ብቻ እንዳልሆነ የሚያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በዋናነት የተገኘውን ድጋፍ አጣምሮ ለወሳኝና ተፈላጊው ልማት ማዋል አለመቻሉ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹በአሜሪካ መንግስት ድጋፍ የሚሰራው ይህ ፕሮጀክት በአጠቃላይ በቅንጅት ለመስራትም ሆነ ይህንን ለማስፈፀም የሚያስችሉ ስልጠናዎችን፤ የቴክኒክ ድጋፎችን ለመስጠት የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት ያግዛል››ይላሉ፡፡ በርካታ ዜጎች ችግር ላይ የሚወድቁበትና ለእለት ደራሽ እርዳታ ፍለጋ ከቀያቸው የሚፈናቀሉበትን ሁኔታ ለማስቀረት እንደሚረዳም ያመለክታሉ፡፡
‹‹የፕሮጀክቱ ዓላማ በዋናነት ችግሮችን የሚቋቋም /ሪዚሊየንት/ ማህበረሰብ መፍጠር ነው›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህ ሲባልም የማስተባበር፤ የመፈፀምና ማስፈፀም አቅም በማጠናከር ረገድ ያለውን ክፍተት ሸፍኖ ጎን ለጎን የሚሄዱ ቅንጅታዊነት የጎደላቸው በርካታ ፕሮጀክቶችን ወደአንድ ሊያመጣ የሚችል እንደሆነ ያነሳሉ፡፡ በተጨማሪም ግልፅነትና ተጠያቂነት በሚላበስበት ሁኔታ ሥራዎችን ለመስራት እንደሚረዳ ይናገራሉ፡፡
ዶክተር እንድሪያስ እንደሚሉት፤ ይህ ፕሮጀክት የቆላማ አካባቢ ዜጎችን ህይወት ማሻሻል የሚያስችል ማስተባበሪያ ተደርጎ ይታያል፡፡ ትግበራው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በይፋ የተጀመረ ሲሆን፣ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ዝርዝር እቅዶች ፤ የምክክር መድረኮች በየክልሉ ወረዳዎች ይካሄዳሉ፡፡ ይሁንና ለዚህ ሥራ በአሜሪካ መንግስት የተመደበው በጀት ውስን በመሆኑ ሁሉንም አካባቢዎች ተጠቃሚ ለማድረግ እንደየሃብቱ ግኝት ወደፊት ተጨማሪ ሥራዎች ይሰራሉ፡፡
‹‹የዚህ ፕሮጀክት ተግባራዊ መደረግ የሃብት ብክነትና ድግግሞሽ እንዳይኖር፤ ችግሮች በሚከሰቱበት ጊዜ ደግሞ በተቀናጀ አኳኋን ምላሽ መስጠት በሚያስችል ሁኔታ የተናበበ ስራ እንዲሰራ ያደርጋል›› ሲሉ ያስረዳሉ። ተጨማሪ ሃብቶች የሚገኙ ከሆነ የበለጠ በማስፋት ከአራቱ ክልሎች ውጪ ያሉ አርብቶአደር አካባቢዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መስኖና አርብቶ አደር ልማት ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ሮባ ቱርጬ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ዝናብ በተጠበቀው ጊዜ አይጥልም፤ ቢጥልም በቂ ስለማይሆን አብዛኛዎቹ አርብቶአደሮች ለድርቅ ይጋለጣሉ፡፡ ይህንን ችግር ለመከላከል የዝናብ ውሃን በማጠራቀም መካከለኛ መስኖዎች እንዲሰሩ ተደርገዋል። ለአብነት ኦሮሚያ በተደጋጋሚ ድርቅ በሚያጠቃው ቦረና አካባቢ የተሰሩ ሰፋፊ የመስኖ መሰረተ ልማቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ኩሬዎችም ውሃ እንዲይዙ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡
‹‹ሰው ሰርቶ ራሱን እንዲችል ለማድረግም በግብርና በኩል ውሃ የማቅረብ ሥራ እየሰራ ነው›› ያሉት የቢሮ ኃላፊው፤ በተመሳሳይ ሌሎች ማገዝ የሚፈልጉ አካላትን በማቀናጀት በመንግስት የተጀመረው ጥረት ክፍተት እንደሚሞላም ያስረዳሉ፡፡ በፌደራልምና ክልል መንግስት የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን ሕይወት ለማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡ በተለይም በክልሉ 40 በመቶ የሚሆነው ማህበረሰብ አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር መሆኑን ጠቅሰው፣ እነዚህን አካባቢዎች ማዕከል ያደረጉ የልማት ስራዎች ከፍተኛ በጀት ተመድቦላቸው እየተሰሩ እንደሆነም ነው ያስገነዘቡት፡፡
በዋናነትም ድርቅ በሚያጠቃቸው የክልሉ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ የውሃና የመኖ እጥረት መኖሩን ያመለከቱት ምክትል የቢሮ ሃላፊው፤ የልማት አጋሮችን በማስተባበር ለማህበረሰቡ ዘላቂ ውሃና አቅርቦት ማግኘት የሚያስችሉት ፕሮጀክቶች ተነድፈው ተግባራዊ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ ይሁንና ከችግሩ ስፋትና ለድርቅ ተጋላጭ ከሆነው ህዝብ ቁጥር አንፃር የሚሰሩት ሥራዎች አስተማማኝ በሆነ መንገድ ችግሩን መፍታት አለማስቻላቸውን ይጠቁማሉ፡፡ በሌላ በኩል ሁሉም ሥራዎች የሚሰሩት እንደየልማት አጋሩ ፍላጎትና አቅም መሆኑንም ተናግረዋል፤ በዚህ የተነሳም አመርቂ የሚባል ውጤት አለመምጣቱን እሳቸውም የሚስማሙበት ጉዳይ እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡
‹‹በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖረው በተለይ አርብቶ አደር እንደመሆኑ ከፍተኛ የውሃና የመኖ እጥረት አለ፡፡ ይህንንም ችግር ለመፍታት በመንግስትም ሆነ በተለያዩ አካላት ድጋፍ የሚሰሩ ሥራዎች አሉ፡፡ ይሁንና ስራዎቹ ባልተቀናጀ መልኩ የሚሰሩ በመሆናቸው የአርብቶ አደሩ ህይወት በዘላቂነት ሲለወጥ አይታይም›› ይላሉ። የዚህ ፕሮጀክት ተግባራዊ መሆን የአርብቶአደርን አቅም በተሻለ ደረጃ ማጠናከር ያስችላል ብለው እንደሚያምኑም ጠቅሰው፣ እዚህም እዚያም ያለው ሃብት በተጨባጭ አርብቶአደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ያግዛል ባይ ናቸው፡፡
ከዚህም ባሻገር የሚነደፉ መመሪያዎች፤ የሚዘረጉ የአሰራር ስርዓቶች አርብቶ አደሩን ማዕከል ባደረገ መልኩ እንዲዘጋጁ አቅም እንደሚፈጥር ያስረዳሉ። በተለያዩ አካላት የሚሰሩ ሥራዎች ወደአንድ ማዕቀፍ ሲመጡ የሰው ሃይሉን በአንድ ጉዳይ ላይ ለማብቃት እንደሚያግዝ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ድርቅ ፈፅሞ እንዳይመጣ ማድረግ አይቻልም፡፡ ድርቅ ሲመጣ መቋቋም መቻል ግን ትልቅ አቅም ነው›› የሚሉት አቶ ሮባ፤ የፕሮጀክቱም ዋና አላማ ይህ እንደሆነ ነው ያስገነዘቡት፡፡
የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አማካሪ አቶ አህመድ ኢስማኤልም የፕሮጀከቱ ተግባዊ መሆን ፋይዳው ብዙ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ እንደእሳቸው ገለፃ፤ በክልሉ በርካታ ወንዞችና ተፋሰሶች ቢኖሩም አካባቢው ቆላማ እንደመሆኑ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ አቀናጅቶ መሄድ ላይ ውስንነት በመኖሩ አርብቶአደሩን በሚገባ ተጠቃሚ ማድረግ አልተቻለም፡፡ የተለያዩ የልማት ድርጅቶች ከክልሉና ከፌደራል መንግስት ጋር በመተባበርና በተናጠል ፕሮጀክት ነድፈው የሚንቀሳቀሱ ቢሆንም ሥራዎቹ በመናበብ የማይሰሩ በመሆኑ ብክነት ይስተዋላል፡፡ ያለውን ውስን ሃብት በአግባቡ መርቶ ሥራ ላይ ማዋል ባለመቻሉ አርብቶአደሩ አደጋ በመጣ ቁጥር የሌሎች እጅ ጠባቂ ይሆናል፡፡
የዚህ ፕሮጀክት ተግባራዊ መሆን ይህንን ውስን ሃብት በማቀናጀትና ወጥነት ያለው የልማት ሥራ ለማከናወን ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ የሚያነሱት አቶ ኢስማኤል፣ በተለይም በክልሉ ያሉ የተፋስስ ልማት ሥራዎችን እንዲሁም የመስኖ ልማቶች በተጨባጭ የአርብቶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ማዕከል አድርገው እንዲከናወኑ ለማድረግ ያግዛል የሚል እምነት እንዳላቸውም አስታውቀዋል፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም