ትኩረት የዲጂታል ኢትዮጵያን ጉዞ ለሚያፋጥኑ ቴክኖሎጂዎች አቅርቦት

በዓለም ላይ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በሚያስገርም ፍጥነት እየተጓዘ ይገኛል፤ ቴክኖሎጂው ዓለምን ያንድ መንደር ያህል ማድረግ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ የመረጃ ለውውጡ፣ ክፍያው፣ ትምህርቱ፣ ሕክምናው፣ ወታደራዊው እንቅስቃሴ፣ ወዘተ በእዚህ ቴክኖሎጂ እየተሳለጠ መሆኑም ይህንኑ ያመለክታል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሰው ሰራሽ አስተውሎት/አርተፊሻል ኢንተለጀንስ/ የሰው ልጅን ስራዎች እየተካ ስራዎች ይበልጥ የሚፋጠኑበትን ሁኔታ እየፈጠረ ነው። ያደጉት ሀገሮች ይህን ቴክኖሎጂ ብዙ ርቀት በመጓዝ የልማታቸው፣ የደህንነታቸው፣ ወዘተ ተጨማሪ አቅም አርገውታል፡፡

የሀገራችን መንግስትም የዲጂታል ዘርፉን መሰረታዊነት ከግምት ውስጥ በማካተት ለእዚህ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቷል። ይህም ተከትሎም ቴክኖሎጂው እየተስፋፋ የልማት፣ የጸጥታው ዘርፍ ተጨማሪ አቅም እየሆነ መጥቷል፡፡ መንግስት የቴክኖሎጂው አገልግሎት ከዚህም በላይ እንዲሰፋ ይፈልጋል፡፡ ለእዚህም ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ለተግባራዊነቱ መሰራቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ዘርፉን በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የአስር ዓመት መሪ እቅድ ከአምስቱ የምጣኔ ሀብቱ ምሰሶዎች አንዱ አድርጎታል፡፡ ተቋሙ ፊትም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርነት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተዋቅሮ ራሱን ችሎ እየሰራ ነው። ቴክኖሎጂው ሊስፋፋባቸው የሚችሉ አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር ላይም ይገኛል፡፡

አንድ ለእናቱ ከነበረው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪው ኢትዮ ቴሌኮም በተጨማሪ ሳፋሪ ኮም የሀገሪቱን የቴሌኮም አገልግሎት ስራ መቋደስ መጀመሩ እንዲሁም ተመሳሳይ ኩባንያዎች ዘርፉን መቀላቀል እንዲችሉ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረው እየሰራባቸው መሆናቸውም ይህንኑ ያመለክታል፡፡

ቀደም ሲል ዓለም አቀፍ ተቋማትና ያደጉት ሀገሮች መንግስት እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉትን ተቋማት ወደ ግሉ ዘርፍ እንዲያዘዋውር፣ ወይም ሌሎች ተመሳሳይ ዘርፎች በሀገሪቱ የሚሰሩበትን ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥር ሲወተውቱ ኢትዮ ቴሌኮምን መሸጥ ማለት የምትታልብ ላምን እንደመሸጥ ይቆጠራል የሚል ምላሽ ይሰጥ ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን ዘርፉን ለሚያሻሻሉ ማናቸውም ኢንቨስትመንቶች መንግስት በሩን ወለል አርጎ ከፍቷል። የዚህን ተቋም የተወሰነ እጅ ለግሉ ዘርፍ ለማዞርም ቁርጠኛ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ሁሉ የሆነው የቴሌኮም ዘርፉን ለማዘመን፣ ዘርፉ በቀጣይ መስጠት ያለበትን አገልግሎት እንዲሰጥ በማሰብ ነው።

እንደሚታወቀው፤ ዲጂታል ኢትዮጵያን በ2025 እውን ለማድረግ ስትራቴጂ ተነድፎ ወደ ትግበራ ከተገባ ዓመታት ተቆጥረዋል። የቴሌኮም አገልግሎቶች ቀደም ሲል ከነበሩበት አቅም አኳያ በአይነትም በጥራትም በተደራሽነትም እየተስፋፉ የመጡበት እንዲሁም በቴክኖሎጂዎቹ አማካይነት ዲጂታል አገልግሎት እየተስፋፋ የመጣበትን ሁኔታም ከዚሁ አኳያ መመልከት ይቻላል፡፡

ደመወዝ በዲጂታል የክፍያ አማራጮች አማካይነት በባንክ በኩል መፈጸም ከጀመረ ቆይቷል፤ እንደ ውሃ ኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮምና የመሳሰሉት የአገልግሎት ክፍያዎችን ለመፈጸም ተቋማቱ ዘንድ በግንባር መገኘት ቀርቷል፤ ለአገልግሎት የሚደረጉ ምዝገባዎችን፣ ግብርን፣ የነዳጅ ክፍያን ፣ ወዘተ. በእዚህ ቴክኖሎጂ መክፈል ውስጥ ተገብቷል ፡፡ የመንግስት ግዥዎች በእዚሁ አገልግሎት መፈጸም ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ ከባንክ ባንክ፣ በአንድ ባንክ ውስጥ ከአንድ አካውንት ወደሌላ አካውንት ገንዘብ ለማዘዋወር ባንክ ቤት መሄድ አያስፈልግም፡፡

ሀገሪቱ ይህን የአገልግሎት አሰጣጥ ከጀመረች ብዙ ዓመታትን ባታስቆጥርም፣ በቴክኖሎጂው በኩል በትሪሊዮን ብሮች መንቀሳቀስ ጀምረዋል። የፋይናንስ ተቋማትና የቴሌ ብር ሪፖርቶችን ዋቢ ያደረጉ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎችም ይህንኑ ያመለክታሉ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚነስቴርን ዋቢ ያደረገውና በታህሳስ ወር የመጀመሪያ ሳምንት/ታህሳስ 7/ የወጣ የአዲስ ዘመን እትም እንዳመለከተው፤ በስድስት ወራት በኤሌክትሮኒክ የገንዘብ ዝውውር ከአንድ ትሪሊየን ብር በላይ ተዘዋውሯል፡፡ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር እዮብ ተካልኝ የዲጂታል ከጥቂት ወራት በፊት እንደገለጹትም፤ የክፍያ አማራጮቹ የጥሬ ገንዘብ ዝውውሩን ቀንሰውታል፤ በዲጂታል አማራጮች በዓመት እስከ አራት ትሪሊዮን ብር ድረስ እየተዘዋወረ ነው፡፡

ይህ መሆኑ ሀገሪቱ ጥሬ ገንዘብ ለማተም የምታወጣውን ወጪ ያስቀራል፤ በጥሬ ገንዘብ ዝውውር ወቅት ሊደርስ የሚችል ጥቃትንም ያስቀራል፤ በጥሬ ገንዘብ እጥረት ሳቢያ ከባንኮች ገንዘብ ለማውጣት በሚፈለግበት ወቅት ሊያጋጥም የሚችለውን የጥሬ ገንዘብ እጥረትም ያስቀራል፡፡ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርንም ያስቀራል፡፡

በዘርፉ እየተመረቁ የሚወጡ ኢትዮጵያውያን ብዛት የትየለሌ ሆኗል፤ እነዚህ ዜጎች ሶፍትዌሮችን በማልማት፣ የቴክኖሎጂውን ቁሳቀስ በመገጣጠምና በመጠገን፣ የኔት ወርክ መሰረተ ልማት በመዘርጋት ወዘተ ዘርፎች ተሰማርተዋል። ከዚህም አለፍ ብለው በሀገር ቤት ሆነው ለውጭ ኩባንያዎች ሶፍትዌር የሚያለሙበት ሁኔታም እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉሉ፡

ስፋትና ጥልቀቱ ይለያይ እንጂ በአሁኑ ወቅት ዘርፉ የማያስፈልግበት የስራ ዘርፍና ተቋም የለም። እነዚህን አገልግሎቶች ለመስጠት በርካታ ሶፍትዌሮች እንዲለሙ እየተደረገ ነው። በርካታ ስራዎች ቢሮ መግባት ሳይስፈልግ ከመኖሪያ ቤት በመሆን የሚሰሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ በኮቪድ ወቅት የዚህ ቴክኖሎጂ ፋይዳ በሚገባ ተለይቷል። ስራን ከቤት ሆኖ መስራት አስችሏልና፡፡ በሽታው ብዙ ዘርፎችን ቢጎዳም፣ ይህ ዘርፍ ግን ትርፋማ የሆነበት ሁኔታ ነው የታየው፡፡

አሁን ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋ ከቴክኖሎጂው ውጪ መሆን የማይችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በሶስተኛ ወገን በኩልም ቢሆን ቴክኖሎጂውን መጠቀሙ የግድ ሆኗል። ገንዘብ የግድ ሊባል በሚችል መልኩ እየተንቀሳቀሰ ያለው በዲጂታል ስርዓቱ በኩል መሆኑ ይህን ሁኔታ የግድ ያደርገዋል፡፡ ጉዳይ ለመፈጸም የትኛውም መስሪያ ቤት የሄደ አገልግሎቱን የሚያገኘው በዲጂታል መንገድ መሆኑም እንደዚያው ነው፡፡

ተማሪዎች በቴሌግራምና በመሳሰሉት መጻህፍት፣ የቤት ስራ፣ ወዘተ እንዲደርሳቸው እየተደረገ ነው። እነዚህ የዘርፉ አገልግሎቶች ከብዙ በጥቂቱ ናቸው፡፡

ቴክኖሎጂው በዚህ ልክ ማገልገል የቻለው ብዙ ኢንቨስት ተደርጎበት ነው፡ ቴክኖሎጂው ከዚህም በላይ እንዲያገለግል ይፈለጋል፤ ለእዚህም ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል፡፡ ይህን አገልግሎት መሰጠቱን በአግባቡ እንዲወጣ የሚያስችል መሰረተ ልማትና በርካታ ከቴክኖሎጂው ጋር የሚሄዱ አቅርቦቶችን ዝግጁ ማድረግ ላይም በትኩረት መሰራት ይኖርበታል፡፡

በቴክኖሎጂው ብዙ ለመስራት የታሰበ ቢሆንም፣ ይህን የሚያሰራ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በኩል ተከታታይነት ያለው ስራ እየተሰራ ነው ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ የኔት ወርክ መጨናነቅ የሀገሪቱ መሰረታዊ ችግር ሆኖ መቀጠሉም ይህንኑ ይጠቁማል። በየተሄደበት ተቋም በኔትወርክ መጨናነቅ ሳቢያ ጉዳይ የሚዘገይበት፣ የሚያድርበት ሁኔታ በስፋት እየታየ ነው፡፡

በኔትወርክ መጨናነቅ ሳቢያ አጭር የጽሁፍ መልዕክት ማግኘት የማይችልበት ሁኔታም ጥቂት ተብሎ የሚታይ አይደለም፡፡ በዚሁ የክፍያ ስርዓት በኔትወርክ ችግር ሳቢያ ሰዎች ገንዘባቸውን ማንቀሳቀስ እየተቸገሩ ያለበት ሁኔታም ሌላው የዘርፉ ደንቃራ ሲሆን ይስተዋላል፡፡

ገንዘብ ሲወጣና ሲገባ ለደንበኞች መተላለፍ ያለባቸው አጭር መልዕክቶች በወቅቱ ለደንበኞች አይለቀቁም፡፡ በእዚህ በኩል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስም በጥሩ አይነሳም፡፡ አጭር የጽሁፍ መልዕክት ማለት ደረሰኝ ነው፡፡ ገንዘብ በወጣ በገባ ቁጥር ወዲያውኑ የጽሁፍ መልዕክት የማይደርስ ከሆነ ችግሩ በእርግጥም አሳሳቢ ነው፡፡

ይህ በዋና ዋና ከተሞች በስፋት የሚታይ ችግር ወደ ገጠሪቱ የሀገሪቱ ከተሞች ሲደርስ ምን ያህል የከፋ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ ይህ ደግሞ ዲጂታል ኢትዮጵያን እአአ በ2025 እውን ለማድረግ ደንቃራ ይሆናል፡፡

ቴክኖሎጂውን እንዲሁም በቴክኖሎጂው የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚጠየቀው ገንዘብ ከፍተኛ እየሆነ መምጣትም ሌላው የዲጂታል ዘርፍ ፈተና ነው። አሁን ለሚሰጠው አገልግሎት የሚጠየቀው ክፍያ በእያንዳንዱ ግለሰብ ደረጃ ከፍተኛ መጠን ያለው በጀት መያዝን የሚጠይቅ ሆኗል፡፡

ለዳታ የሚደረግ ክፍያ ከፍተኛነት ሌላው ደንቃራ ነው፡፡ በጠራራ ጸሀይ በዳታ እንደ ልብ መገናኘት አይቻልም፤ በእዚህ ሳቢያ ገባ ወጣ ማለት የአብዛኛዎቹ የቴክኖሎጂው ተጠቃሚዎች ኢትዮጵያውያን ፈተና እየሆነ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ መረጃዎችን በወቅቱ እንዳያገኙ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡

በተለይ ለሞባይል ስልክ አገልግሎት የሚወጣው ወጪም እየበዛ መጥቷል፤ አሁን ካርድ ተሞልቶ አሁን ያልቃል፡፡ እነዚህ ወጪዎች እንግዲህ ተራ አገልግሎት ለማግኘት ሲባል የሚወጡ ናቸው፡፡ የሚፈለገው አገልግሎት እየጨመረ ሲሄድ ክፍያውም በዚያው ልክ እየጨመረ ይሄዳል፡፡

ገንዘብ ሲንቀሳቀስ የሚከፈለው ክፍያ በዚህች ሀገር አዲስ ነው፤ በእርግጥ ገንዘቡን ባንክ ሄዶ ለማውጣት በሚደረግ እንቅስቃሴ ሊወጣ የሚችለው የትራንስፖርት ወጪ እና ገንዘቡን ለማውጣት የሚደርስ እንግልትን በማስቀረት ወዘተ. ሊካካስ ይችል ይሆናል፤ ይህ ተጠቃሚነት አለ ተብሎ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መጠየቅ ተገቢ አይደለም፡፡

የሚፈጸመው ክፍያ ብዙ አይነት ነው፤ ሁሉም ገንዘብ ይፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ የአብዛኛው ማህበረሰብ ገቢ ዝቅተኛ ለሆነባት ኢትዮጵያ ሕዝብ ፈታኝ አይሆንም ተብሎ አይታሰብም፡፡

በሀገሪቱ እየተጠየቀ ያለውን ክፍያ በሌሎች ሀገሮች ከሚጠየቅ ክፍያ ጋር እያነጻጸሩ የሚተቹ እንደነበሩም አውቃለሁ፡፡ የክፍያው እየበዛ መምጣት አስመልክቶ ለሚመለከተው አካል ቅሬታ ሲቀርብ ቀደም ሲል ይሰጥ የነበረው ምላሽ ክፍያው እየበዛ የመጣው ለመሰረተ ልማቱ ማስፋፊያ ሲባል ነው ይባል ነበር፡፡ መሰረተ ልማት የማስፋፋቱ ስራ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮቴሌኮም ትከሻ ላይ የወደቀ ነበር፤ አሁን ተገዳዳሪ ኩባንያ ወደ ሀገሪቱ ገብቶ እየሰራ ነው፡፡ ሌሎችም ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ያኔ የተረጋጋ ክፍያ ሊኖር ይችላል ብለን እናስብ፤ እዚያው ድረስ ግን ክፍያው እየናረ እንዳይሄድ ማድረግ ላይ ቢሰራ መልካም ነው እላለሁ፡፡

በዲጂታል ቴክኖሎጂ ብዙ እንደሚሰራ ይጠበቃል፡፡ ለእዚህ ደግሞ መሰረተ ልማት ማስፋፋት ላይ በስፋት መስራቱ አንድ ነገር ሆኖ ዜጎች በሚገባ እንዲጠቀሙበት ማድረግ ላይም መስራት የግድ ይሆናል፡፡ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ተግባር በሚፈለገው መልኩ ስኬታማ እንዲሆን አሁንም፣ በቀጣይም ለአቅም ግንባታ ስራዎች ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡

የቴክኖሎጂው ቁሳቁስ ዋጋ ውድነትና እንደ ልብ አለመገኘት ሌላው ትልቁ ተግዳሮት ነው፡፡ በዚህች ሀገር በቴክኖሎጂው ብዙ መሰራት እየተፈለገ፣ ለእዚህ ደግሞ እንደ ስማርት ስልክ ያሉት ወሳኝ መሆናቸው እየታወቀ እነዚህ ቁሶች በመንግስት በኩል አሁንም የቅንጦት እቃዎች ተደርገው እየታዩ ናቸው፡፡

የእነዚህ ቁሶች የቅንጦት እቃነት ጊዜው አልፎበታል፡፡ ይህን ችግር የዘርፉ ባለሙያዎች በእጅጉ እየተቹት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ቁሶች ከፍተኛ ገንዘብ እየተጠየቀባቸው እየተቀረጡ እንዲገቡ ማድረግ ዜጎች በዲጂታል ቴክኖሎጂው ብዙ ርቀት እንዳይጓዙ እንደሚያደርግ ጥርጥር የለውም፤ ዜጎች ብቻ አይደለም የሚጎዱት፤ ስራዎች ሁሉ በቴክኖሎጂው እንዲከናወኑ እየሰራ ባለው መንግስት እቅድ ላይም አሉታዊ ተጽእኖ ያሳርፋል፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮ ቴሌኮምና ሳፋሪ ኮም አንዳንዴ እነዚህን ቁሶች በዝቅተኛ ዋጋ እያቀረቡ ያለበት ሁኔታ ሊበረታታ ይገባዋል፡፡ አቅርቦቱ ግን ከዚህም በላይ መሆን ይኖርበታል፡፡

ታብሌቶች፣ ላብቶፖችና ዴስክ ቶፕ ኮምፒውተሮችም እንዲሁ የማግኘት ችግር አለ። እነዚህ ተቋማት ለተማሪዎች፣ ለመምህራን፣ ለተቋማት ሰራተኞች፣ ወዘተ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፤ ቁሳቁሱ ከእነዚሀ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተጨማሪ ለእያንዳንዱ ዜጋም በሚያስፈልጉበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡

እነዚህን ቁሳቁስ ምንም አይነት ይሁኑ ምንም አይነት፣ ለዜጎች የሚዳረሱበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል፡፡ እነዚህን አለማስፋፋት ሰራዎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ በሚከናወኑበት ፍጥነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳርፋል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ወይም የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሀይምናን የሚያበራክትም ነው የሚሆነው፡፡

እነዚህን ቁሳቁስ በእርዳታም፣ በአነስተኛ ዋጋ ግዥም ሆነ በሌላም በሌላም መንገድ ዜጎች የሚያገኙበትን ሁኔታ መፍጠር ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር አይደለም፡፡ ቢያንስ ዴስክ ቶፕ ኮምፒውተሮች እንደልብ ሊገኙ የሚችሉባቸውን እንደ ላይብራሪ ያሉ ተቋማትን በቅርብ ርቀት ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡

ይህ ሲሆን ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ውጪ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች ማግኘት ይችላሉ፤ በዚህም ትምህርት ቤት ያገኙትን እውቀት በአካባቢያቸው በሚያገኟቸው በእነዚህ ቁሳቁስ ማዳበር ይችላሉ፡፡ ከቴክኖሎጂው ጋር የበለጠ ቤተሰብ እየሆኑ መጥተው የዲጂታል ኢትዮጵያ ማህበረሰብ መሆን ይችላሉ፡፡

የዘርፉ ቴክኖሎጂዎች እንደልብ አለመገኘት የዘርፉ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ከተመረቁ በኋላ ከቴክኖሎጂው እንዲርቁ እያደረጋቸው ነው። ተመራቂዎቹ ሶፍትዌሮችን ያለሟሉ ሲባሉ፣ ለዘርፉ ብዙ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ተብለው ሲታሰቡ በቁሳቁሱ እጥረት ሳቢያ ከተመረቁበት ሙያ ውጭ ሌላ መስክ ላይ እየተሰማሩ ናቸው፡፡ ይህ ትልቅ እጦት ነው።

ቁሳቁሱን ማግኘት አንድ ነገር ሆኖ በቁሳቁሱ ለመገልገል የሚያስችሉ የዋይፋይና የመሳሰሉት አቅርቦቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኙበት ሁኔታም መፈጠር ይኖርበታል፡፡ ይህ ደግሞ ለይስሙላ መሆን የለበትም፡፡ በሚገባ መገልገል የሚያስችል የኔትወርቅ አቅምም አብሮ ሊኖር ይገባል፡፡

የዘርፉን ቴክኖሎጂዎች ማግኘት እንደ መሰረታዊ መብት መቆጠር ይኖርበታል፡፡ ሁሉንም አገልግሎት በዲጂታል ስርዓት ለመፈጸም የወሰነና ወደ ስራ የገባ መንግስት በአነዚህ ቴክኖሎጂዎች አቅርቦት እጥረት ስሙ መነሳት የለበትም፡፡ ከፍ ብዩ እንደጠቀስኩት በእርዳታም፣ ልዩ በጀት በመመደብም ቢሆን ዜጎች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንዲሆኑ መስራት፣ ቴክኖሎጂዎቹ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ የቅንጦት እቃ በሚል የሚጠይቅባቸውን ታክስም መልሶ ቢመለከተው ጥሩ ይሆናል፡፡

አሁን በስራ ላይ ያሉት በየተቋማቱ የሚገኙ የቴክኖሎጂው ውጤቶች ዘመኑን የዋጁ አይደሉም። በአንዳንድ ተቋማት አሉ የሚባሉት ኮምፒውተሮች ዘመን ያለፈባቸው ናቸው፤ ዳታ ለማውጣት፣ ፕሮሰስ ለማድረግ ሴቭ ለማድረግ ለመክፈትም ሆነ ለመዝጋት በእጅጉ የደከሙ ልብ አድክሞች ናቸው፡፡ እነዚህንም ዘመኑን በዋጁ ኮምፒውተሮች መተካት ድረስ የዘለቀ ተግባር ማከናወን ይገባል፡፡

ቴክኖሎጂዎቹን ከውጭ እየገዙ ማሟላት ሊያስቸግር ይችላል፡፡ ቴክኖሎጂዎቹን በሀገር ውስጥ መገጣጠምና ማልማት ላይም መስራት ያስፈልጋል። በቅርቡ አንድ መንግስታዊ የልማት ተቋም ሀገሪቱ የሚያስፈልጋትን የትራክተር እና ኮምባይነር ብዛት በግዥ ማሟላት እንደማይቻል በማመን በእነዚህ የሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች መገጣጠምና ማምረት ላይ በስፋት እንደሚሰራ ማስታወቁን አስታውሳለሁ፡፡

በዲጂታል ዘርፉ ላይ የሚሰሩት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የመሳሰሉት መንግስታዊ ተቋማትና የግሉም ዘርፍ የዚህን ተቋም እርምጃ በአርአያነት በመውሰድ መተግበር ይኖርባቸዋል። የዚህች ሀገር የዲጂታል ቴክኖሎጂ ልማት ግብ ሰፊ መሆን ይህንን ማድረግም ይጠይቃል፡፡

ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት ከአፍሪካ ሀገሮች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፤ በፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት በኩል ግን በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው፡፡ የዚህ አንዱ ምክንያት በዲጂታል ቴክኖሎጂ በኩል ብዙ ርቀት አለመጓዟ ነው፡፡ መንግስት ይህን ለመቀየር እየሰራ ነው፡፡ መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ ብሄራዊ ባንክ እአአ በ2025 የሀገሪቱን ዜጎች የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት 70 በመቶ ለማድረስ ግብ ጥሎ እየሰራ ነው፡፡

በእዚህ ልክ የሚሰራ መንግስት፣ ለእዚህ እውን መሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በሚያደርጉ እንደ ስማርት ስልክ፣ ታብሌት፣ ላፕቶፕና ዴስክ ቶፕ ኮምፒውተሮች ያሉትን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግም በትኩረት መስራት ይኖርበታል፡፡ በእነዚህ ቁሳቁስ ላይ መስራት በሀገሪቱ በሰው ሰራሽ አስተውሎት/አርተፊሻል ኢንተለጀንስ /ላይ በስፋት ለመስራት ለተያዘውም እቅድ ስኬት ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል፡፡

ዘካርያስ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You