ለብሔራዊ ጥቅማችን አንድ ሆነን የምንሰለፍበት ወቅት አሁን ነው

የአፍሪካ ቀንድ ክልላዊና ዓለም አቀፋዊ ኃይሎች ዓይናቸውን የጣሉበት ቀጠና ነው። ቀደም ሲል ይህ አካባቢ ዋና ትኩረታቸው አድርገው የነበሩት እንደ አሜሪካና ቻይና ያሉ ኃያላን ነበሩ። አሁን ግን የአፍሪካ ቀንድ ለአዳዲስ ተወዳዳሪዎች ወሳኝ የፉክክር ሜዳ ሆኗል። ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ቱርክ፣ ኳታር፣ ኢራንና ግብፅ በአፍሪካ ቀንድ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ዋና ቀጠናዊ ተዋንያኖች ናቸው።

በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ጃፓን፣ ቻይናን፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች፣ ቱርክን ጨምሮ ዘጠኝ ሀገራት በቀይ ባህር ዳርቻ ላይ የጦር ሰፈር አላቸው። የሀገራቱ በአካባቢው የመገኘታቸው ምክንያት እንደ የሀገራቱ ይለያይ ይሆናል እንጂ፣ በአንድም ይሁን በሌላ በግልጽ ይሁን በስውር በዋንኛነት የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ስለመሆኑ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።

ይህ ቀጠና የቀይ ባህር፣ ኤደን ሰርጥ መገኛ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ በቀደሙት ዘመናት በአካባቢው ብሔራዊ ጥቅሞቿን ማስጠበቅ የሚያስችሉ የባሕር በሮች ነበሯት። ይህ እውነታ ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በብዙ ፈተናዎች ውስጥ መቆየቱ ይታወሳል።

መላው ሕዝባችን ሀገራችንን ባሕር በር አልባ ስላደረጋት ታሪካዊ ክስተት ባሰበ ቁጥር በብዙ በቁጭት እውነታውን እንዲያሰላስለ፤ የሆነበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። ከሰሞኑ ይሄንን የሚቀይር የመግባቢያ ስምምነት በሶማሌ ላንድ እና በኢትዮጵያ መካከል መፈራረሙም ከቁጭት ወጥቶ አዲስ ተስፋን የሚያሰላስልበት መንገድ ላይ መሆን ችሏል።

ሁለቱ ሀገራት የተፈራረሙት የትብብርና የአጋርነት መግባቢያ ሰነድ በተለያዩ ዘርፎች በቀጣይ ለሚኖራችው ግንኙነት ማዕቀፍ እንዲሆንም ይታሰባል። ይህ የመግባቢያ ሰነድ ኢትዮጵያን አማራጭ ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ቀልጣፋ የባህር በር የማግኘት ፍላጎት እውን የሚያደርግ፣ የሁለቱን ወገኖች የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ፣ የፀጥታ እና የኢኮኖሚ ትብብርን የሚያጠናክር ነው።

በርግጥ በትውልድ የጊዜ ልዩነት በትላንትና በዛሬ መካከል ጥሩም መጥፎም ታሪክ ይፃፋል። ታዲያ ከትላንት ተምሮ ነገን የተሻለ ለማድረግ ዛሬ ትልቅ ድርሻ አላት። አሁን ላይ በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው። ትላንት በታሪክ ጉድፍ ወደ ባህር ትተነፍስበት የተነፈገች ሀገር ዛሬ ላይ ትውልድ የሚያወሳውን ታሪክ ከትባለች።

ኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚ የሚያደርጋት የመግባቢያ ሰነድ ከሱማሌ ላንድ ጋር በተፈራረመችበት ወቅት ስምምነቱን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ ስምምነቱ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል። የመግባቢያ ሰነዱ ለ50 ዓመታትና ከዚያ በላይ የማራዘሚያ አማራጭ ባለው የሊዝ ስምምነት ኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤት የሚያደርግ ነው።

የኢትዮጵያን የወደብ ተጠቃሚነት መብት ጥያቄ መልስ የሰጠው ስምምነቱ ታሪካዊና የመንግሥትን ቁርጠኝነት ያሳየ፤ የሀገራችን ዲፕሎማሲ አካሄድ ያስገኘው ውጤት ነው። ስምምነቱ ለሀገር ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንፃር በግዙፍነት የሚነሳ ታሪካዊ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል። ሰላማዊ በሆነው በዚህ መንገድ የባህር በር አማራጭ መገኘቱ የመሪዎቻችን ቁርጠኝነትና ቃላቸውን የሚጠብቁ፣ የሚያከብሩ መሆናቸውን ያመላክታል።

ሁለት ሶስተኛ የሚሆነውን ክፍሏን በውሃ በሸፈነችው ምድራችን 90 በመቶ የሚሆነው የምድር እንቅስቃሴ የውሃ መስመሮች ላይ ጥገኛ እንደሆነ ይነገራል። ከዚህ የተነሳም በዘመናችን የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ውሃ ከውሃነቱ ገዝፎ የኢኮኖሚ ፣ የፖለቲካ ፣ የዲፕሎማሲ ከዛም ባለፈ የወታደራዊ ጉዳዮች አጀንዳ እየሆነ ነው።

ስምምነቱ ሀገራችን የበርካቶች ዓይን ካረፈበት ቀይ ባህር አንድ ርምጃ መጠጋቷ ከምጣኔ ሀብት እስከ ኢኮኖሚ፣ ከጂኦፖለቲካ እስከ ብሔራዊ ደህንነት ተጠቃሚ ያደርጋታል። የመልከዓ ምድር አቀማመጥ ተጋሪ የመሆን እድልን ያሰፋለታል። በቀጠናው ላይ የሚደረጉ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የፀጥታ ጉዳዮች ላይ እንድትሳተፍ ያስችላታል።

በተለይም በቀጠናው ያለውን የፖለቲካና የፀጥታ የአሰላለፍ ለውጦችን በቅርበት እንድትከታተል ያግዛታል። በኢትዮጵያ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ላይ የራሳቸው ጥቅምም ጉዳትም ያላቸውን አሰላለፎች ትለይበታለች። ይህንን የተከተለ ብሔራዊ ዝግጁነት ለመፍጠር እንደ አንድ ትልቅ እድል የሚታይ ነው።

በሀገራቱ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ፤ ኢትዮጵያ በኤደን ባህረ ሰላጤ ላይ መልህቋን እንድትጥል ብሎም የባህር ኃይሏን እንድታደራጅ ፍቃድ የሚቸር ነው። በበጎ ህሊና የማየት ፈቃደኝነት ካለ ክስተቱ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ሱማሌ ላንድንና የቀጠናው ሀገራት በብዙ መልኩ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ነው።

ኢትዮጵያ የባህር በር አላት ማለት የመርከብና የሎጀስቲክ ሂደቱ የሚሳለጥና የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ የመሆን እድሏን የሚያሰፋ፣ የንግድ ፍሰቱንም የሚያሳላጥ በሀገር ውስጥ ደግሞ የሥራ እድል ፈጠራን የሚያሰፋ ነው። የገቢ መዳረሻም እንድትሆን እድል ይፈጥራል። በስምምነቱ መሰረት ያገኘችውን ወደብ በስፋት በማልማት ከወደብ ክፍያ፣ መርከቦች ሲያርፉ በሚከፍሉት ቀረጥ እና በመርከብ ኢንዱስትሪው የራሷ አቅም እንድትገነባ ያስችላታል።

አሁን ላይ ለኢትዮጵያ ብቸኛ የባህር መተንፈሻ ሆኖ የቀረበው የኤደን ባህረ ሰላጤ በባብል መንድብ አድርጎ ወደ ቀይ ባህር የሚሻገር ነው። ይህም ኢትዮጵያ በቀጠናው ያላትን ጥቅም እንድታስጠብቅ ብሎም የወሳኝነት ሚናዋን እንድትወጣ እድል ይፈጥራል። ለዚህ እውን መሆን ታዲያ ሰሞኑን በወረቀት ላይ የሰፈረውን የመግባቢያ ሰነድ መሬት ላይ አውርዶ ለተግባራዊነቱ መሥራት የግድ ይላል።

የስምምነቱ አንድምታ ከፍ ያለ ከመሆኑ በዘለለ ለኢትዮጵያ ይዞ የመጣው አማራጭ ሰፋ ያለ ነው። ስምምነቱ ታሪክ ሆኖ የሚመዘገብ ነው። ሳንካ እንዳይገጥመው፣ ንፋስ እንዳይገባበት እና ውሃ እንዲቋጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ አሰራሮች ተዘርግተውለት ወደ ተግባር መቀየር አለበት። ስለ ባህር በር ማውራት ነውር የነበረበት፣ ኢትዮጵያም ለባህር የቅርብ ሩቅ ሆና የከረመችበት የጊዜ ግንብ ፈርሷል። ስኬቱን ወደ ውጤት ለመቀየር ግን አሁንም ብዙ ሊሰራ ይገባል።

ስምምነቱ አንድም ቀጠናዊ ትስስርን የሚያጠናክር፣ የሰጥቶ መቀበልን እሳቤ የሚያዳብር፣ በአፍሪካ ቀንድ ወንድማማችነት ከማጠናከር ባለፈ አብሮ መበልፀግን ያለመ ነው። ከኃይልና ጉልበት መንገድ ትብብርና ብልፅግናን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ አካታ የምትተገብረው ኢትዮጵያ ከሱማሌ ላንድ ጋር ያደረገችው ይህ ስምምነት በምጣኔ ሀብት፤ በወጪና ገቢ ንግድን በማሳለጥ ረገድ አሁን የምታወጣውን ቢሊዮን ዶላሮች የሚያስቀር ነው።

ለዚህ ነው ብሔራዊ ጥቅሙ የሚልቀው፤ ለዚህ ነው የባህር በር አስፈላጊም ግድ የሚሆነው። ይህ የኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ ጥቅም የሚወሰነው ከዛሬ ባሻገር ለነገ የሚጠቅመው ስምምነት የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ ይጠይቃል። ጥቅሙን አስበን ለነገ ብልፅግና እና ልማታችን ያለውን ፋይዳ አውቀን መሥራት የሚኖርብንም ምክንያቱ ይሄው ነው።

በረጅሙ ዘመን ታሪካችን ኢትዮጵያዊነትንና ብሔራዊ ስሜታችንን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች መከሰታቸው ተስተውሏል። ይህ አባዜ ዛሬም ድረስ አልተወንም። ኢትዮጵያዊ በመሆናችን በዚች ሀገር በመፈጠራችን ብቻ ብሔር፣ ዘር፣ ሃይማኖት ሳይለየን በጋራ መቆም ባሉብን ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ስንከፋፈል ይታያል።

ይህ ሀገርን የሚያስቀድም ብሔራዊ ስሜት ተሸርሽሮ ግለሰባዊ ጥቅም ፖለቲካዊ አቋም ወይም ጊዜያዊ ኩርፊያና ቁርሾ ከሀገር መፃኢ እድልና ከትውልድ ተስፋ በላይ ሆኖ ከሀገር በተቃራኒ የቆሙ ኢትዮጵያዊያን ይታያሉ። ይህ የረጅሙ ታሪካችን አካል ነው። ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ አንስቶ ሰሞኑን በተፈረመው የወደብ ስምምነት ድረስ ከሀገር በተቃራኒ የመቆም ዝንባሌዎች ተስተውለዋል።

ብሔራዊ ስሜት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሆነ ሁሉ ከክልል ክልል ሳይለይ፣ ከብሔር ብሔር ሳይነጣጠል፣ ሰሜን ከደቡብ፣ ምስራቅ ከምዕራብ ሳይል ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ብቻ በሀገሩ ጉዳይ አንድ የሚያደርገው ስሜትንና ህብረትን የሚያገኝበት ነው። ታዲያ በኛ ዘመን የተሸረሸረ ብሔራዊ ስሜት የሚወልደውን ሀገርን ያለማስቀደም አባዜ ከየት አመጣነው? ካልን እንደሚባለውና እንደሚታሰበው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በጥልቅ በሀገር ፍቅር ስሜት የተገነባ አለመሆኑን ያመላክታል።

መጠላለፍ የበዛበት፣ የስልጣን ሽኩቻ የተጧጧፈበት፣ በኃይል የሚመራ ፖለቲካ ሌላው ብሔራዊ ስሜትና መግባባት የሚፈልጉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንዳንቆም ሳንካ የሆነ ዋነኛ ችግራችን ነው። ሁላችንም፤ አሁን ያለነው ትውልዶች የነገ ትውልዶቻችንን መፃኢ እጣ ፈንታ በእጆቻችን መዳፍ የያዝን በትከሻችን የተሸከምን ነን።

ሀገር ነገዋ የተሻለ እንዲሆን ዛሬ ሀገርን ወደፊት በሚያደርጉ የጋራ ጉዳዮች መግባባት በጋራ መቆምና መታገል ይጠበቅብናል። ለዚህ ደግሞ ብሔራዊ ስሜትን መፍጠር ያስፈልጋል። የተዛቡና አሉታዊ ትርክቶች ከትልቁ ሀገራዊ የጋራ ጉዳይና ምስል ይልቅ በጥቃቅን እና በሚለያዩን ጉዳዮች እንድንጠመድ፣ ህብረታችንን እንድናጣ፣ በጋራ እንዳንቆምም ያደርጋሉ።

ብሔራዊ ስሜት እንዲኖር ቅድሚያ ብሔራዊ መግባባትና የጋራ ትርክት መፍጠር ያስፈልጋል። የጋራ ትርክት የአንድን ሀገር ሕዝብ አብሮነት በማጠናከር የጋራ ሀገራዊ አላማ ለመሰነቅ ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው እንደመሆኑ በዚያ ውስጥ በፈተና የሚፀና፣ የቅድሚያውን ሁሉ ቅድሚያ ለሀገር የሚሰጥ፣ ሀገር ወዳድ፣ ብሔራዊ ስሜትን የተላበሰ ትውልድና ማህበረሰብን መፍጠር ያስችላል።

በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አመለካከቶችን መፍጠር፣ በውይይት ልዩነቶችን ማጥበብና መግባባት ላይ እንዲደረስ መሥራት በዋናነት ከመንግሥት እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላትም የሚጠበቅ ተግባር ነው። እኛ የምንኖረው ሀገር ስትኖር ነው። የኛ ጥቅም የሚከበረው የሀገራችን ጥቅም ባስከበርን ቁጥር ነው የሚለውን አስተሳሰብ ማሳደግ ያስፈልጋል።

ሀገር የእውነት ሙዳይ ናት። ሀሰት በሆንን ቁጥር እያጎሳቆልናት እንሄዳለን። እውነት በሆንን ቁጥር ደግሞ እያፀናናት እንሄዳለን። ሀገራችንን በእውነት መፍጠር የሁላችንም ግዴታ ነው። በትላንትናና በነገ መካከል መናጣችንን ትተን ዛሬያችንን በጥሞናና በስክነት ብንሰራ ለራሳችንም ለሀገራችንም ውለታ እንሰራለን። ለልጆቻችን የምናወርሰው ሀገር ይኖረናል። መጠራጠርና መፋጠጥ፣ እርስ በእርስ መገዳደልን በመተው አንድነታችንን ስናስጠብቅ ሀገር አንድነት፣ አንድነት ሀገር መሆኑን እንገነዘባለን።

አሁን ባለንበት ወቅት ሀገራት የሀገራቸውን ምጣኔ ሀብት አቀጣጥለው ከሌሎች ጋር ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ጥምረትን እያዋለዱ ነው። ትላንት ሀሩርና አሸዋ ላይ ሀገር ያቆሙ የቀይ ባህር ማዶ ሀገራት የውጭ ዜጎችን በገፍ ተቀብለው ያሰራሉ። ዛሬ ሀገራት ለዜጎቻቸው የተቃና ኑሮ ወደፊት እየገሰገሱ ናቸው።

ቻይናዊያን ለዘመናት የፀናውን መጠን አልባ ችግር ንደው ዛሬ ሌሎችንም ከጨካኙ ጉስቁልና ለመታደግ በሩቁ አስበዋል። አቅም አንሷቸው እኛ ጭምር የዘመትንላቸው ደቡብ ኮሪያዊያን ዛሬ የበለፀገ ሀገር ፈጥረዋል። ከ50 ዓመታት በፊት ጎስቋላ መንደር የነበረችው የኢምሬቶቹ ግዛት ዱባይ ዛሬ ቢጠሯት አትሰማም። ትንሿ ሲንጋፖር የበለፀገችበት የእድገት ደረጃ ተአምር አስብሏታል። ማሌዢያ እና ቬትናም እየተመነደጉ ናቸው።

ሀገራቱ ግጭትና ፀብን በታሪክ ሙዚየም ውስጥ አስገብተውታል። ትላንት ዓለምን አጀኢብ ያሰኘውን የዘር ፍጅት ያስተናገደችው ርዋንዳ ቂሟን ሽራ ሕዝቧንም አፋቅራ ዛሬ በእድገት ግስጋሴ ላይ ናት።

ሀገራችን ኢትዮጵያ የተኛችው የአፍሪካ አናብስት ሲሉ የጠሯት ጭምር የንቃቷን ጊዜ ሲጠብቋት ኖረዋል። ልዩነታችንን ተነጋግረን እንፍታ። እንደ ንብ ተባብረን እንደ አንበሳ ተከባብረን የሁላችንንም ነገ በጋራ እንስራ። የዛሬ ልዩነታችን ሳያግደን ክፉአችንን የሚመኙ ወሬ ሳይገደን እኔም ለሀገሬ አለሁ ብለን የዜግነታችንን መወጣት ያለብንና አብረን አለን የምንልበት ጊዜው አሁን ነው። ሁላችንም ለሀገራችን ጠበቃ፣ የእውነታችን ዲፕሎማት ልንሆን የሚገባበት ትክክለኛ ወቅትም ዛሬ ነው ! ።

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ጥር 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You