ኢትዮጵያ ለአፍሪካ እግር ኳስና ነፃነት

እአአ 1976 ካናዳ የኦሊምፒክ አዘጋጅነት ተራ በማግኘት ሞንትሪያል ላይ የታላቁን ስፖርት ድግስ አሰናዳች። ከዚያ ቀደም በተካሄዱ ኦሎምፒኮች ላይ በተደጋጋሚ ተሳትፋ ልምዷን ያካበተችው ኢትዮጵያም ከምንጊዜውም የተሻለ ተዘጋጅታ ነበር። የአትሌቶችን ሞራል በመጠበቅ እንዲሁም በሌሎች ድጋፎች ባልተለመደ ሁኔታ ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቆ በርካታ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ለመሰብሰብ በማቀድም ቡድኑ ወደዚያው ተጓዘ። ነገር ግን በወቅቱ በደቡብ አፍሪካውያን ጥቁሮች ላይ ይፈጸም የነበረውን የዘር መድልዎ የሚቃወም ፖለቲካዊ ውሳኔ ላይ በመድረሱ ቡድኑ ራሱን ከውድድሩ አገለለ።

በእርግጥ የስፖርትም ሆነ ኦሊምፒክ መርሕ መደጋገፍና ወንድማማችነት በመሆኑ የውሳኔው ተገቢነት አያጠያይቅም። ከዚያ ባለፈ ግን የኢትዮጵያውያኑን የአፍሪካዊነት ስሜት ሃገር ልታገኝ ከምትችለው ሜዳሊያ፣ ክብርና ዝና በላይ ለሰው ልጆች መብት በመቆርቆር ማንጸባረቅ ችለዋል።

በወቅቱ ከኢትዮጵያ ባለፈ ከ20 በላይ የሚሆኑ አፍሪካውያን ሃገራት ከውድድሩ ራሳቸውን በማግለል አጋርነታቸውን ማስመስከራቸውም የሚዘነጋ አይደለም። ይህ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ካደረገችው ዓባይን በጭልፋ እንደማለት ሲሆን፤ ስፖርትን ጨምሮ በየትኛውም ዘርፍ ያላትን ሚናም ሊፋቅ በማይችል አሻራዋ አኑራለች።

ከኦሊምፒክ ባለፈ እግር ኳስ እጅግ በሚወደድባት አህጉረ አፍሪካ የኢትዮጵያ ሚና ከጽንሰት እስከ ጉልምስና የሚጓዝ ነው። በሞንትሪያሉ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን እየመሩ አፍሪካዊ ተቃውሟቸውን በጨዋነት ካሳዩ የቡድኑ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ደግሞ ለዚህ ቋሚ ምስክር ናቸው።

በዘመናዊ ስፖርት ከኢትዮጵያ ባለፈ በአፍሪካም እንዲስፋፋ የነበራቸው ከፍተኛ ሚናም ‹‹የአፍሪካ ስፖርት አባት›› ተብለው እንዲጠሩ አድርጓቸዋል። እኚህ ሰው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ተመስርቶ አሁን ካለበት እንዲደርስ፣ አፍሪካውያን ኅብረትና ጥንካሬ እንዲኖራቸው እንዲሁም በዓለም ዋንጫ አፍሪካ ድርሻዋ እንዲጨምር ብዙ ሠርተዋል።

ስፖርተኛና የስፖርት አስተዳደር አዋቂው አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን (ካፍ) ከመመሥረት ባለፈ እአአ ከ1964 እስከ 87 ድረስ በምክትልና በፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል። በዚህም የአፍሪካ ስፖርት ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባልና የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት በመሆን የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ አገዛዝ እና ጭቆናን በጽኑ ከመቃወም ባለፈ ከየትኛውም ዓለም አቀፍ ውድድሮች እንድትታገድ ከፍተኛ ጥረት በማድረግም ይታወቃሉ።

ይህም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካውያን እንዲሁም ለስፖርት ዋስ ጠበቃ መሆናቸውን ያረጋግጣል። ከሰሞኑ የተጀመረውን የአፍሪካ ዋንጫም (እአአ በ1957) ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ሱዳን እና ደቡብ አፍሪካን አስተባብራ ነበር የመሠረተችው።

በአፍሪካውያን አንድነትና ተባብሮ መቆም ላይ ጠንካራ አቋም ያላት ኢትዮጵያ አህጉሪቱን በሚመለከት ከስፖርቱ ባለፈ እአአ በ1963 የአፍሪካ ኅብረትን (በቀድሞ አጠራሩ የአፍሪካ አንድነት) በመመሥረትም የቀደማት አልነበረም። ከቅኝ ግዛት በተላቀቁበት ማግስት በአህጉሪቱ ያሉ ጭቁንና በነጮች ከፍተኛ ግፍ ሲደርስባቸው የኖሩ ሃገራትን በማስተባበር የነፃነት ተምሳሌት በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ላይ መቀመጫውን በማድረግ እስካሁን ዘልቋል።

ኅብረቱን በመመሥረት እንዲሁም ጠንካራ ሥራዎችን በመምራት ረገድም የወቅቱ የሀገሪቱ መሪ ንጉሥ ኃይለሥላሴን ጨምሮ እስካሁንም ድረስ ኢትዮጵያን የተረከቡ መሪዎች አስተዋፅዖና ተፅዕኖ ፈጣሪነት አልተለየውም። ኅብረቱ ከመሠረቱ አንስቶ የራሱን ቅርጽ ይዞ እንዲቆም፣ ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምስራቅ አፍሪካ የቀጣናውን ሰላም በማስጠበቅ እንዲሁም በአህጉሪቱ ትልልቅ ሊባሉ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ባላት ተሳትፎ የተነሳም የአፍሪካ ኅብረት ብቻም ሳይሆን፣ የፓን አፍሪካ ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ፣ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል እንዲሁም የሌሎች ዓለምና አህጉር አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ለመሆን ችላለች።

ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ላይ ያላት ሚና እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪነት መንግሥታትና የፖለቲካ ቅርጻቸው በተለዋወጠ ቁጥር ሳይናወጥ ስድስት አስርተ ዓመታትን ሊያስቆጥር ችሏል። ይህም የሀገሪቷን አቋም በግልጽ የሚያንጸባርቅ ነው። በአንጻሩ የአፍሪካ ኅብረትን ቀድሞ በብርቱ ልጇ የተቋቋሙት አህጉር አቀፍ የስፖርት ተቋማት ግን ኢትዮጵያውያንን የበይ ተመልካች ካደረጓት ዘመናትን አስቆጥረዋል። በስፖርት አመራርነትም ሆነ በውድድሮች ላይ ባላት አቅም ተፎካካሪ መሆን ባለመቻሏም የመሥራችነት ታሪኳን ታቅፋ የአፍሪካ ዋንጫን በቴሌቪዥን መስኮት መመልከት ግድ ሆኖባታል።

የአፍሪካ ስፖርት አባት ይድነቃቸው ተሰማ እና ፍቅሩ ኪዳኔን የመሳሰሉ ዕንቁዎች ከኢትዮጵያ ወጥተው፣ ከአፍሪካም አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትና ከበሬታን ባገኙበት ዘመን፤ ዛሬ የአውሮፓን እግር ኳስ ያደመቁትና መላው ዓለም በአድናቆት የሚያጨበጭብላቸው ቡድኖች አልተፈጠሩም ነበር።

ለአብነት ያህል 34ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በማስተናገድ ላይ የምትገኘው ኮትዲቯር የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን እና የአፍሪካ ዋንጫ ምሥረታ ላይ በነበሩባቸው ዓመታት ከቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ ጋር ከነበረባት ፖለቲካዊ አዙሪት መላቀቅ አልቻለችም ነበር። ከ1960 ወዲህ ያቋቋመችው ብሔራዊ ቡድኗም አሁን ላይ በአፍሪካ 7ኛ በዓለም ደግሞ 49ኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ነው። በዚህ ወቅት በርካታ ተጫዋቾችን በአውሮፓ ሊጎች በማጫወት፣ ዘመናዊ የስፖርት መሠረተ ልማትን በመገንባት፣ የአፍሪካ ዋንጫን ለሁለተኛ ጊዜ በማስተናገድ እንዲሁም ሀገሪቷን እስከ ዓለም ዋንጫ ከመወከል ባለፈ ለዓመታት የዘለቀ የእርስ በእርስ ግጭትን እስከማስቆም የደረሰ አቅም ያለውን ቡድንም መመሥረት የቻለች ሀገር ናት።

የአፍሪካ እግር ኳስ መሥራች ሆና ተመልካች ለመሆን የተገደደችው ኢትዮጵያ በበኩሏ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ከዓመታት አንዴ የሚሳካላት፣ ተሰጥዖ ያላቸውን ታዳጊዎች አሳድጋ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መመሥረት ያልቻለች፣ ዘመናዊ ስታዲየም ገንብታ ውድድር ማዘጋጀት አይደለም ቡድኗን እንኳን በራሷ ሜዳ ማጫወት ያልቻለች፣ እንደቀድሞ በአህጉር አቀፉ የስፖርት ማኅበራት ያላት አስተዋፅዖ የተቀዛቀዘባት ሆናለች።

በእርግጥም ይህ ሁኔታ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ሊያስቆጭ የሚገባ ነው። ነገር ግን አፍሪካ ዋንጫ ሲዳረስ ብቻ ቁጭትን ከማንጸባረቅ ይልቅ እንደቀደመው ጊዜ በተፅዕኖ ፈጣሪነት ልትነሳ የምትችልበትን ሥራ ማከናወን የግድ ይላል።

በመጪው ወር አዲስ አበባ ላይ የሚሰባሰቡት መላው አፍሪካውያን፤ ኢትዮጵያን ተጠሪያቸው፣ ከተማይቱን መዲናቸው፣ ሕዝቦቿን ወገናቸው፣ ብለው እንዲጠሩ ካደረገው የአፍሪካ ኅብረት ብዙ መማርም ይገባል። የጊዜ መለዋወጥ፣ የመሪዎችም መተካካት የማይቀይረውን አፍሪካዊ አቋምና ሚና በስፖርቱ ዘርፍ መድገም ተገቢ ነው።

ብርሃን ፈይሳ

 አዲስ ዘመን ጥር 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You