የኢትዮጵያውያን መልክ የሚገለጥበት በአል ጥምቀት

 በኦርቶዶክስ እና በካቶሊክ ክርስቲያን አማኞች ዘንድ በየአመቱ ጥር 11 የሚከበረው በዐለ ጥምቀት፤ ምዕመኑ አምላኩን በአደባባይ በጋራ የሚያመሰግንበት ከዘጠኙ የጌታ በአላት መካከል አንዱ ነው። የበአሉ ታሪካዊ ዳራም ጌታ እየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጥምቁ ዮሃንስ እጅ መጠመቁን የሚያመላክት እና ሰው ከውሀ እና ከመንፈስ ካልተጠመቀ የእግዚአብሔርን መንግስት አይወርስም የሚለው መጽሀፍ ቅዱሳዊ መልዕክት ያለው ሆኖ እናገኘዋለን።

እየሱስ በዮሀንስ እጅ በዮርዳያኖስ ወንዝ ለምን ተጠመቀ? ብለን ስንጠይቅ ሶስት አንኳር መልሶችን እናገኛለን። የመጀመሪያው ምስጢረ ስላሴን (አንድነቱን ሶስትነቱን) ሊያስተምረን ነው። በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ደቀ መዝሙሬ አድርጓቸው ከሚለው መጽሀፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮት ጋር የሚዛመድ አንድምታ ያለው ነው። ሁለተኛው ከትህትና እና ከአርዐያነትን አንጻር የሚቃኝ ነው። የጌታን የትህትና አጽናፍ ከውልደቱ የምናውቀው ቢሆንም በሌሎች አስተምህሮቶች ላይም የምናገኘው ነው። በከብቶች በረት ተወልዶ ክብርና ጌትነት ምንም እንደሆኑ አሳይቶናል። በታናሹ በዮሀንስ እጅ መጠመቁም ለዚህ ነው።

በስተመጨረሻ የምናገኘው ጥምቀትን ይባርክልን ዘንድ መጠመቁን ነው። ይሄ የሚያሳየን ጥምቀት በፈጣሪና በተፈጣሪ መካከል ያለውን ውርስ እና ቁርኝት ነው። በእግዚአብሄር የሚያምኑትን ሁሉ የእግዚአብሄር ልጅነት ሰጣቸው ተብሎ እንደተጻፈ የእየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቅ ከላይ ባየናቸው ሶስት በኩር አላማዎች ምክንያት እንደሆነ ከማመን ባለፈ የጥምቀትን በአል ዓላማ አያይዘን መረዳት እንችላለን።

ጥምቀት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እና ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያናት ከሚያከብሯቸው የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ ነው። እንደ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ትርጓሜ ጥምቀት የሚለው ቃል “ማጥመቅ፣ መጠመቅ፣ አጠማመቅ፣ ጠመቃ፣ የማጥመቅና የመጠመቅ ስራ፣ ሕጽበት፣ በጥሩ ውሀ የሚፈጸም” ሆኖ ይፈታል። በቃሉ ስርወ መነሻ ተመርተን የጥምቀት በአልን ዓላማና ተልዕኮ መገንዘብ ይቻላል። ራሳችንን ለፈጣሪ የምናቀርብበትና ፈጣሪንም ወደራሳችን የምናቀርብበት የንጽህናና የጽድቅ በአል ብለን ልንወስደው እንችላለን።

ከዋናው በአል አንድ ቀን ቀደም ብሎ የሚከበረው የከተራ በዓልም ሌላው የጥምቀት በአል አካል ነው። ከተራ “ከተረ” ወይም ደግሞ “ገደበ” ከሚለው የግዕዝ ቃል የመጣ ሲሆን፤ የዋናው የጥምቀት በአል ዋዜማ ነው። በከተራ እለት በሕብረ ዝማሬ ያጌጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የእምነቱ ተከታዮች ክብረ እግዚአብሄር ታቦተ ሕጉን አጅበው ወደ ጥምቀተ ባህሩ የሚተሙበት እለት ነው። ይህ እለት ምዕምናን፣ ዘማሪያን፣ ካህናት በዝማሬና በሽብሻቦ ለአምላካቸው ምስጋና የሚያቀርቡበት እለት ነው።

ከገና በአል ቀጥሎ የሚከበረው ጥምቀት ከክርስቶስ መወለድ ቀጥሎ በአማኙ ዘንድ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ሀይማኖታዊ በአል ነው። መንፈሳዊ አንድምታውን ስንቃኘው በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች መካከል ያለውን የመፈጠር ዓላማ አጉልቶ የሚያሳይ የምስጋናና የአንድነት በአልም ሆኖ እናገኘዋለን።

በአሉ ፈጣሪ የሚከብርበት፣ ህዝበ ክርስቲያኑ ደግሞ ተባርኮና ተቀድሶ በአዲስ ማንነት ወደነገ የሚሄድበት እለት ነው። ለሌሎች ፍቅር የምንሰጥበት፣ በፍቅርና በይቅርታ ከሰው ልጆች ሁሉ ጋር የምናብርበት የመጠመቅ እለት ነው። በየትኛውም ሚዛን ላይ ቢቀመጥ ጥምቀት ከዚህ የተለየ አከባበር አይኖረውም።

ሰላምና መንፈሳዊነት የአንድ እጅ መዳፍና አይበሉባ ናቸው። በአንድ እጅ ላይ የበቀሉ መዳፍና አይበሉባ አንዱ ያላንዱ ታሪክ እንደሌላቸው ሁሉ እንዲህ ያሉ መንፈሳዊ በአላትም ከዓላማና ከመነሻቸው አንጻር ይሄን እውነታ የሚጋሩ ናቸው። ሰላም የማይሰበክበት በአል መንፈሳዊ ነው ሊባል አይችልም።

መንፈሳዊነት ስረ መሰረቱ ሰላምን መስበክ፣ አብሮነትን ማነጽ ነው። ጥልና ክርክርን በስመ እግዚአብሔር መኮነን፣ ጥላቻና መለያየትን መሻር ነው። ከዚህ ረገድ የሚነሳ መንፈሳዊነት በፈጣሪም ዘንድ ቅቡልነትን እንደሚያገኝ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።

ጥምቀት የሁሉም ኢትዮጵያውያን በአል ነው። የዓለም የቅርስና የባህል ተቋም በቅርስነት ሲመዘገብ ከአደባባይ በአልነቱ ጎን ለጎን የሕዝብ በአል መሆኑን በማመን ነው። ይህ እለት ኢትዮጵያውያን የሚጠያየቁበት፣ የሚመሰጋገኑበት፣ የሚመራረቁበትም ጭምር ነው። በተለይ ሙስሊሙ ለክርስቲያን ወገኑ በአል ድምቀት አብሮ መንገድ የሚያጸዳበት፤ የታቦታት ማደሪያዎችን የሚሰራበትና የሚጸዳበት፤ እንኳን አደረሰህ አደረሰሽ የሚልበት፣ የሚተቃቀፍበት እለት ስለሆነ በአሉ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ነው ያስብላል።

ይሄን እውነታ የሚያጠነክሩ በየዓመቱ በጥምቀት በአል ላይ የሚስተዋሉ አንድ ሁለት ምስክሮችን ላስታውሳችሁ። ጥምቀት የክርስቲያኖች ብቻ እንዳይደለ በተግባር ያሳዩ የሌላ ሀይማኖት ተከታዮች በጥምቀት በአል ላይ ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር በመደባለቅ ክብረ በአሉን ከማድመቅ ጎን ለጎን ታቦት ሲሸኙ እንደሚታዩ ማስታወስ ይቻላል። ሌላው በየዓመቱ የጥምቀት በአል በመጣ ቁጥር ታቦት በሚሄድበት መንገድ ላይ ምንጣፍ እያነጠፉ ከኦርቶዶክስ ወንድሞቻቸው ጎን የቆሙ ብዙ የሌላ እምነት ተከታዮች መኖራቸውም እሙን ነው።

በጣም የሚደነቀውና በኢትዮጵያ የሀይማኖት ቀለም ውስጥ ገኖ የወጣው ለዚህ ነጻ ሀሳብም እንደ ዋና የሰላም ምልክት ሊወሰድ የሚችለው ቀጥሎ የምነግራችሁ ፍሬ ነገረ ነው። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ከአንድ አጥቢያ ታቦት ይዘው ወደጥምቀተ ማደሪያ ሲሄዱ በዝማሬና በውዳሴ ታጅበው በእግር ጉዞ ነው። ጉዞው ረጅም ሊሆን ይችላል። በዚህ ጉዞ ውስጥ መራብ መጠማት፣ ድካምና የመሳሰሉ ስጋዊ ዝለቶች መኖራቸው ግድ ነው። ምዕመኑ ታቦት ሲሸኝ ረጅም መንገድ እንደሚሄድ የተረዱ ሙስሊም ወንድሞቻቸው ግን ይሄን የወገኖቻቸውን ድካም ዝም ብለው አያዩትም።

መንገድ ላይ የታሸጉ ውሀዎችን በማስቀመጥ፣ የተራቡ ካሉ እህል የሚቀምሱበትን ሁኔታ በማመቻቸት፣ እንዲያርፉና እንዲበረቱ መልካም መስተንግዶ በማድረግ አብሮነታቸውን የሚገልጹበትን እውነታ በደማቅ ማስታወስ ያስፈልጋል። ከዚህ ጋር አብሮ ሊነሳ የሚገባው በአንዱ መንፈሳዊ በአል ላይ የሌላው እምነት ተከታይ የሚያደርገው የኢትዮጵያዊነት መረዳዳት ባህል ነው።

ሌላም የኢትየጵያውያንን ጌጥ እንጥቀስ ካልን ተጠቃሽ እውነት አናጣም። ከሕዝበ ክርስቲያኑ ለምነው መስኪድ ያሰሩ መነኩሴ እንዳሉ ሁሉ፤ ለቤተክርስቲያን ማሰሪያ ገንዘብ የሚለግሱ ሙስሊም አማኞችም ያሉት በኢትዮጵያ ነው።

ይሄ እኔ ብቻ ያየሁት ወይም ደግሞ አንድ ቦታ በተወሰኑ ሰዎች የሆነ አይደለም። በሁሉም ቦታ በሁሉም ዘማኞች ዘንድ የሆነ ኢትዮጵያዊነትን ዛሬም ከነወዙ እንዳለ የሚያሳይ እንደ አንድ የመቻቻል ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው እውነታ ነው። ይሄን በመሰለው እውነታ የጥምቀትን ዓላማ መረዳት እንችላለን። እንደ ጥምቀት ያሉ የአደባባይ በአሎችን ሰላም ሰባኪ እና አስታራቂ ይዘት ባላቸው በጎ መልዕክቶች ሀገራችን ላለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ለእርቅና ለሽምግልና፣ ለአንድነትና ለአብሮነት ልንጠቀምባቸው እንችላለን።

በጥምቀት በአል ላይ ምዕመኑ ከአምልኮ እኩል ፍቅርና አንድነትን ሊሰብኩ ይገባል። ፍቅር በሌለው ልብ ውስጥ ፈጣሪ አይገኝም። ለየትኛውም መንፈሳዊ በአል ፍቅር ከፈጣሪ ጋር መገናኛ ከፍጡር ጋር ደግሞ አብሮ የመኖሪያ ጥበብ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በብዙሀነት ውስጥ ለበዙና ለሰፉ አገርና ሕዝብ ሰላም ሰባኪ፣ ፍቅርን የሚያጸና አእምሮና ልብ ያስፈልጋል። ያለንበት ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነትና ፍቅራችንን አጽንተን ወደፊት የምንቀጥልበት እንጂ አጋጣሚ እየጠበቅን ጥላቻ የምንነዛበት ሊሆን አይገባም።

ኢትዮጵያን ከማጽናት አኳያ መንፈሳዊ በአላት ሚናቸው ላቅ ያለ ነው። ከአምልኮው ጎን ለጎን አብዛኛው ሕዝብ የሚሰባሰብበት፣ አብሮ የሚበላበት፣ የሚጠያየቅበት በአል ነው። አብረን በሆንን ቁጥር ኢትዮጵያዊነት እያበበ፣ ባህል ስርዐት እየጠነከረ ይመጣል። በመንፈሳዊ አስተምህሮትም ይሄን አይነቱ መሰባሰብና መጠያየቅ በፈጣሪ ዘንድ ዋጋ ያለው እንደሆነ የተመሰከረለት ነው። በበአንድ ልብ ወደፈጣሪ እንደመቅረብ ያለ የበረከት ምንጭ የለም። ከትላንት እስከዛሬ ጸንተንና ተዋደን በኢትዮጵያዊነት ስም የተጠራነው አንድነትን በሚሰብኩ፣ አብሮነትን በሚያገኑ በጎ አንደበቶችና ተግባራት ነው።

መንፈሳዊ በአላት ፈጣሪ በፍጡር የሚመሰገንበት፤ ፍጡር ከፈጣሪው በረከት የሚገኝበት እንጂ ማንም የግል ፍላጎቱን የሚያራምድበት አይደለም። ለየቱም አይነት ግለሰባዊም ሆነ ቡድናዊ ዓላማ ማስተናገጃነት የሚውል መንፈሳዊ በአል አላማውን የሳተ ነው። መንፈሳዊነት ለፍቅር የሚወግን መለያየት ቢኖር እንኳን በጣመ ስብከት መዳን እና መሻር የሚያመጣ የሰላም አርማ ነው። እንዲህ ያሉ ሕዝባዊ በአላት እኩይ አላማን ለማስተናገድ ለአንዳንዶች ምቹ ሲሆኑ አይተናል። መለያየትና ጥላቻን የሚሰብኩ የእኩይ ዓላማ ባለቤቶች ከድርጊታቸው ተቆጥበው ፈጣሪያቸውን ቢያገለግሉበት ትርፉ የላቀ ነው።

ጥምቀት ዘር፣ ቋንቋ፣ ጎጥና መንደር የሌለበት የሁሉም ኢትዮጵያውያን የምስጋና በአል ስለመሆኑ መናገር ለቀባሪ ማርዳት ነው የሚሆነው። ኢትዮጵያዊ ውበታችን በአንድ ቦታ ስለአንዱ ፈጣሪ የሚታይበት የአምልኮ ስፍራ ነው። በፍቅር ካልሆነ መንፈሳዊ ዓላማችን ግቡን እንደማይመታ የገባን ብዙዎች ነን። በፍቅር እና በወንድማማችነት መንፈስ ካልሆነ ፈጣሪን ፈልገን እንደማናገኘው የገባንም ጥቂቶች አይደለንም። እንዲህ ያሉ ሀይማኖታዊ በአላት አንድነታችንን የምናጠነክርባቸው እንጂ የምናላላባቸው አይደሉም።

ፈጣሪ ራሱን ከገለጠበትና ሰዎችን ለማዳን ከመረጠበት ሁነኛ መንገድ መሀል ቀዳሚው የፍቅር ሕግ ነው። ስለሰው ልጅ ሲወለድም ሆነ መከራን ሲቀበል፣ ሲሰቀልም ሆነ ትንሳኤውን ሲያሳየን ፍቅር በሚሉት የሕግ ስርዐት በኩል ነው። ጥምቀት ደግሞ ፍቅር ጀምሮ አንድነት የተከተለበት የፈጣሪ የሕግ መጀመሪያ ነው። ሁሉም ሀይማኖታዊ በአላት ከፈጣሪ መወለድ በኋላ እውቅና ያገኙ ናቸው። ፈጣሪ ፍቅር አስገድዶት ስለሰው ልጅ ተወለደ ካልን ስለእሱና እሱን አስበን የምናከብራቸው መንፈሳዊ በአላት ሁሉ የፍቅርና የአንድነት በአላት ናቸው ማለት ነው።

የጥምቀትን በአል በአንድ ሁነኛ ቃል ስናስረው ‹ጥምቀት የኢትዮጵያውያን መልክ› የሚል ይሆናል። አንዳንድ በአላት ኢትዮጵያን የሚገልጡ፣ ታሪክን የሚናገሩ የአብሮነትና የመቻቻል ምልክቶች ናቸው። ጥምቀትም በተለያዩ አለባበሶች፣ ዘር ቀለም ሳንል በአንድነት የምንታደምበት፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ፍቅርና መቻቻልን የምንሰብክበት በአላችን ነው። ተከባብረን እና ተዋደን ስናከብረው እንጂ ተጠላልተንና ተናንቀን ስናከብረው አያምርም።

በአሎቻችን መድመቂያዎቻችን ናቸው። ሁሉም በአላት ኢትዮጵያ የምትደምቅበት፣ ሕዝቦቿ የሚጠያየቁበት በአል ነው። የእኔ የአንተ የሌለባቸው ስለአንዱ ፈጣሪ በአንድነት የምንቆምባቸው ናቸው። ባልተገባና ስርዐቱንም ሆነ ዓላማውን በሳተ አካሄድ በጥላቻና በአጉል ፍላጎት ልናደበዝዛቸው አይገባም። አሁን ላይ በበአል ስም ሁከት ፈጣሪ አንዳንድ አላስፈላጊ ድርጊቶች እየተስተዋሉ ነው። እኚህ ድርጊቶች በአሉን ፈር ከማሳት ብሎም በአማኙ መካከል መተማመን እንዳይኖር ከማድረግ ባለፈ ዋጋ የሌላቸው ናቸው።

እውነተኛ አምልኮ በማስታረቅና በማግባባት፣ በማስተቃቀፍና ይቅር በማባባል ውስጥ የሚገለጥ ነው። ሌሎችን ከማቀፍ፣ ስለሌሎች በማሰብ ውስጥ የሚያብብ ነው። ተቃቅፈንና ተደጋግፈን ፈጣሪ በሚወደው እምነት ውስጥ ወደነገ ስንሄድ ብቻ ነው አምልኮታችን ፈጣሪን ፈጣሪም እኛን የሚያግዘን። ለጠብ ጫሪነት የሚውሉ በአላት በፈጣሪም ዘንድ ተገቢዎች አይደሉም።

ተረቱስ ቢሆን “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” አይደል የሚለው። ጥምቀት አዲስ የመልበስ ብቻ ሳይሆን የአዲስ ልብ እና የአዲስ አእምሮ መነሻ ነው። በጥምቀቱ ፊት ስንቆም ጠላቶቻችንን ይቅር ልንል፣ ለበደሉን ምህረት ልናደርግ ነው። በማደሪያው ፊት ስንቆም በፍቅርና ስለፍቅር ሰላም ወዳዶች ሆነን ነው። አዲስ መልበስ ሳይሆን አዲስ አስተሳሰብ ነው እንደሀገርም ሆነ እንደመንፈሳዊነት ዋጋ የሚያስገኘው።

 ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You