አዲስ አበባ :- ሴቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላቸው ሚና እንዲጎለብት እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የሴቶች ህጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ወይዘሮ ኤል ሳቤት ገብረስላሴ ትናንት በሚኒስቴሩ የስ ብሰባ አዳራሽ በተካሄደው መድረክ ላይ እንደተናገሩት ሴቶች በቴክኖሎጂ ያላቸው ተሳትፎ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው።ይሄንን ውስንነት ለመፍታትም አዲስ ፕሮግራም ይፋ ተደርጓል።
በዕለቱ “የእንጦጦ ቴክኖሎጂ ፌሎሺፕ” የተሰኘ ፕሮግራም የማስተዋወቅ እና ወደ ተግባር መግቢያ ቀን መሆኑን ጠቅሰው ፕሮግራሙ የሴቶችን የቴክኖሎጂ ተሳትፎ የሚያሳድግና ተሳታፊ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል። ይህ ፕሮግራም በወጣት ወንጌል እና ጓደኞቿ ተቀርጾ ሲመጣ በደስታ ተቀብለን ወደ ተግባር ነው የገባነው ብለዋል፡፡
ወይዘሮ ኤልሳቤት እንዳሉት እስከዛሬ ቴክኖሎጂ እና ቴክኖሎጂ ነክ የሆኑ ነገሮችን ከውጭ ነው የምና ስመጣው፤ ታዲያ ይህንን ለመቅረፍ ብሎም ወጣቶችን ስራ ፈጣሪ ለማድረግ ያለመው ፕሮግራም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተመረጡ 25 ሴት የቴክኖሎጂ ምሩቃንና በመማር ላይ ያሉ ተማሪዎች ፈጠራ እና ክህሎትን በሚያዳብሩበት ፕሮግራም ገብተው ችግር ፈቺ ሆነው እንዲወጡ ይደረጋል ፡፡
አምባሳደር ገነት ዘውዴ በበኩላቸው ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ሴቶችን ለማብቃት እየሰራ ያለውን ተግባር አድንቀው በየትኛውም ደረጃ ቢሆን እንቅፋቶች እና ችግሮች እንደሚያጋጥማችሁ አስባችሁ ወደ ፊት መሄድ እና ተግታችሁ በመማር፣ በብልሃት እና ከስሜታዊነት በራቀ አስተሳሰብ አሽናፊ መሆን አለባችሁ ብለዋል፡፡
የእንጦጦ ቴክኖሎጂ ፌሎሺፕ መስራች እና ባለራዕይ የሆነችው ወጣት ወንጌላዊት ተካ እንዳለችው በስኮላርሺፕ ካናዳ ከገባች እና የትምህርት ዕድሉን ካገኘች በኋላ የአገሯን ልጆች ልትረዳበት የምትችልበትን መንገድ በመፈለግ ከሁለት ካናዳውያን የክፍል ጓደኞቿ ጋር ፕሮግራም በመቅረጽ እንዲሁም ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር አብሮ በመሆን እና በመመካከር ፕሮግራሙ እውን ሊሆን መቻሉን ተናግራለች፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2011
አብርሃም ተወልደ