መንፈሳዊ በዓላት መንፈሳዊነታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ ?

መንፈሳዊነትና የፖለቲካ እሳቤ ትንታኔዎች የሁለት ዓለም ከርሰ ምድሮች ናቸው፡፡ በእንዴትም ያለ የላቀና የዘመነ ሀሳብ ቢዳሰሱ አንዱ በአንዱ ውስጥ ህልውና የለውም፡፡ የጨለማና የብርሀን ያክል ልዩነት ግዝፈት ያላቸው ወዲያና ወዲህ ርዕዮተ አለሞች ናቸው፡፡

መንፈሳዊነት የመጀመሪያ ተልዕኮው ፈጣሪን ማክበር ነው፡፡ የፖለቲካ አስተሳሰብ ከዓለማዊ መሻት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በእኚህ ሁለት የተራራቁ እሳቤዎች ውስጥ አንዱን በአንዱ ውስጥ አኑሮ አጀንዳ መፍጠር ለሰማዩም ለምድሩም የማይበጅ እኩይነትን መፍጠር ነው፡፡ በሕገ ዶግማና ቀኖና በሚተዳደር ሀይማኖት እና በተጻፈ ሕገመንግስት ስር በቆመ ፖለቲካ መሀል የሰላምና የኢትዮጵያዊነት ቁርኝት ካልሆነ ሌላ ነውጥ ፈጣሪ አስተሳሰቦች የማይስተናገዱባቸው ናቸው፡፡

በአጭር ቃል መንፈሳዊ በአል ማለት መንፈሳዊ ዓላማ ያነገቡ ሰውን ከፈጣሪና ፈጣሪን ከሰው ጋር የሚያገናኙ የጸሎት፣ የአምልኮ እንዲሁም የምስጋና እና የምጽዋት በዐላት ናቸው፡፡ ከዚህ አግንነን ካየነው ደግሞ ስለሀገርና ስለሕዝብ የሚጸለይባቸውና የሚጾምባቸው ምህላም የሚያዝባቸው ሁሉን አቃፊዎች ናቸው፡፡ እኚህ በአላት በእንዴትም ያለ መልኩ የአንድ ወገንና የአንድ ቡድንን ዓላማ ደግፈው ሌላውን ሊኮንኑ ዶግማና ቀኖና አይፈቅድላቸውም፡፡ ወይም ደግሞ ጊዜና አጋጣሚን እየጠበቁ የአንድን የሆነ አካል ዓላማ አያራግቡም፡፡ ይህ በፍጹም የሚጠበቅ አይደለም።

የፊታችን ዓርብና ቅዳሜ የሚከበረው የጥምቀት በዐል ሰላም ሰባኪ ከሆኑ የሕዝብ በአላት መካከል አንዱ ነው፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሀገርና ትውልድን በስነምግባርና በመቻቻል እሴት ሲቀርጽና ሲያስውብ የኖረ የአደባባይ በዐል ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንን በአንድ ተሰባስበው ከመንፈሳዊነት ባለፈ ፍቅርና አንድነትን የሚያወራረሱበትም ነው፡፡ ሀይማኖታዊ በዐላት ትውልዱ በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ ባሕልና ወጉን፣ አንድነትና ወንድማማችነቱን አስጠብቆ እንዲሄድ የጎላ ሚና ተጫውተዋል፡፡ መንፈሳዊ በረከታቸው እንዳለ ሆኖ ሀገራዊ የአብሮነት ውርርስና ቅብብሎሻቸውም እኩል ሊወሳ የሚችል በጎ ገጽታቸው ነው፡፡ የሀገርን ገጽታ ከመገንባትና ለውጪው ማሕበረሰብ ኢትዮጵያን ከማስተዋወቅ አኳያ ይሄ ነው የማይባል ሚና አላቸው፡፡ ይሄ ሀገራዊ ፋይዳቸው ታይቶም ነው በዩኒስኮ ላይ በቅርስነት የተመዘገቡት፡፡

የዓለም አቀፉ የባሕልና የቅርስ ተቋም አንድን መንፈሳዊም ሆነ ዓለማዊ በአል በዓለም አቀፍ ቅርስነት ሲመዘግብ የራሱን ሕግና መርህ ተከትሎ ነው፡፡ ከመርሆቹ አንዱ ሰላም ፈጣሪነት ነው፡፡ ጥምቀትም ሆነ ሌሎች ኢትዮጵያዊ በአላት በዩኒስኮ በቅርስነት ሲመዘገቡ ስለሀገርና ሕዝብ ያላቸው ሰላማና በጎ አሻራ ታይቶና ተጠንቶ ነው፡፡ የጥምቀት በዐል ለሀገርና ለሕዝብ በተለይ በሰላም ዙሪያ ያለው አንድምታ ደማቅ መሆኑ ታምኖ በቅርስነት ሰፍሯል፡፡ ጥምቀት የሰላም ምልክት..የኢትዮጵያዊነት ቀለም ነው፡፡ ትውልዱን በጨዋነት ያራመደ፣ ምዕመናኑን በእምነትና በእውነት ያቆመ፣ ሀገርን በበረከትና በጸጋ ያሻገረ በዐል ነው፡፡ አሁን ላይ ላሉብን ሀገራዊ ውጥንቅጦች ሰላም ከመስበክና እርቅና ተግባቦትን ከመመስከር አኳያ የበአሉ ሚና የማይናቅ ነው፡፡

ጥምቀት የእግዚአብሄር ክብር የሚገለጥበት፣ በታቦተ ሕጉ ፊት አማኙ ስለተደረገለትና ስለሚደረግለት እልል የሚልበት፣ ከተከተረ እና በቡራኬ ከበቃ ጸበል ሕይወቱን የሚያለመልምበት ነው፡፡ እኚህ ሁሉ ሂደቶች የበዐሉን ዓላማና ይዘት የሚገልጹ ለሀገርና ሕዝብ ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ የሚመሰክሩ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊነት አማኝነት እንደሆነ በፈጣሪና በኢትዮጵያውያን መሀል ያለውን የመተማመን ትስስር አጉልቶ የሚያሳይ በዐል ነው፡፡,ይሄ የሰላም ምልክት የሆነ በዐል በምንም አይነት መልኩ ተፈጥሮአዊም ሆነ ሀይማኖታዊ መልኩን ስቶ ለማይሆን እኩይ ዓላማ መጠቀሚያነት ሊውል አይገባም፡፡

አንዳንዶች እንዲህ ያለውን ሀይማኖታዊና ኢትዮጵያዊ ቀለም ያለው በዐል ለእኩይ ዓላማ ማስፈጻሚያነት ሊጠቀሙት ሲዳዳቸው ይስተዋላል። መንፈሳዊም ይሁን ዓለማዊ በዐላት ሀገርና ሕዝብን በተመለከተ ሚናቸው አንድ ነው፤ ፍቅርን መስበክ፣ አብሮነትን ማጽናት ነው፡፡ ትውልዱ ከለመደው መንፈሳዊነት እንዳይወጣ ማጽናት እንጂ ዘርና ብሔር ተኮር በሆነ የእኩያን ፍላጎትና ዓላማ ፈሩን እንዲስት ማድረግ አይገባም፡፡ ለዘመናት በዐላት ሲመጡ ጾምና ጸሎትን የመሳሰሉ የለመድናቸው የአምልኮ ስርዐቶች አሉ፡፡ ትውልዱ ሰውና ኢትዮጵያዊ የሆነው በዚህ ስርዐት ተገርቶ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት የአማኝ ሀገር የተባለው በዚህ እውነት በኩል ነው፡፡ በዐላት አላማቸውን ሲስቱ አንድ ወገንን ብቻ አይደለም የሚጎዱት እንዳለ ትውልዱን ነው የሚጎዱት፡፡ የትውልድ ጉዳት ደግሞ የሀገርና የመጪው ጊዜ ጉዳት ነው፡፡ በሕገ እግዚአብሄር ተገርቶ በጨዋነት ያደገ ትውልድ የሚያውቀውና ያደገበት በዐለ አምልኮ ለእኩይ ዓላማ ሲውል ሲያይ ውደ ስህተት ነው የሚገባው፡፡ ሀይማኖታዊ በዐላት አንድና አንድ ዓላማቸው እግዚአብሄርን መስበክ ነው፡፡ እግዚአብሄር ደግሞ በፍቅርና በእርስ በርስ መዋደድ ውስጥ የሚሰብክ ነው። በስርዐት የተገነባው የትውልዱ ቤት እንዳይፈርስ፣ በእምነትና በእውነት የጸናው የኢትዮጵያዊነት ስማችን እንዳይጎሽ ፈር ከሳተ እኩይ ዓላማ መቆም አለብን፡፡

እንደ ጥምቀት ያሉ በሰላም ሚዛን ስለሰላም ባዋጡት አስተዋጽኦ እውቅና የተቸራቸው በዐላት ከዚህ ተልኳቸው እንዳይጎሉ ዓለም አቀፉ የቅርስ ጥበቃ ያሳስባል፡፡ አንድ ጊዜ ተመዝግበው የሚያበቁ አይደሉም፡፡ በየዓመቱ ሲከበሩ ዓላማና እያደረጉ ያሉት አስተዋጽኦም ይገመገማል፡፡ እንደዛ ካልሆነ የቅርስነት እውቅናቸው ሊሰረዝ ሁሉ ይችላል፡፡ የሰላም ዋጋ በተመን የሚሰላ አይደለም። አሁን ያለችው ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላም ያስፈልጋታል፡፡ ሰላም ብቻ አይደለም ሰላምን አጽንቶ የሚያቆይ ማህበራዊ ስርዐት ግድ ይላታል። ከስርዐቶቻችን መካከል ደግሞ ጥምቀትና መሰል የአደባባይ በዓላት ሰፊውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ በጥምቀት የሚመጣው የአማኝ ቁጥር እጅግ የበዛ ነው፡፡ በዛ ቀንና በዛ አማኝ መሀል የምትነገር የፍቅር ቃልም ሆነች የጥላቻ ንግግር ብዙዎች ዘንድ የመድረስ እድሉ ሰፊ ነው፡፡

ጥምቀትን ፍቅርን እንስበክበት፡፡ አንድነትና አብሮነትን እንናገርበት፡፡ እርቅና ይቅርታን ከትዕግስትና ከስክነት ጋር እናውራበት፡፡ ውይይትና ምክክርን ከወንድማማችነት ጋር እናጽናበት፡፡ ይሄ ሲሆን ነው በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ግዳይ ጥለን በፈጣሪና በፍጡራን መሀል ባለማዕረግ የምንሆነው፡፡ በጾምና ጸሎት በምስጋናም በፈጣሪ ፊት መቆማችን ትርጉም የሚያገኘው እንዲህ ባለው በጎ ስራ ስንበረታ ነው፡፡ የጥምቀት በዐል ከሰላም እና አንድነትን ከመስበክ አኳያ የላቀ መድረክ እንደሆነ መናገር ይቻላል፡፡ በታቦቱ ፊት ለአምልኮ ስንቆም፣ በባሕሩ ዳር ጸበል ሲነካን ዓመት ዓመት አድርሰን ብለን ስንመራረቅ ደስታ የዋጀው ውስጣችን የሚሰርግ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል አለ፡፡

እዚህ ጋ ማስታወስ የምፈልገው አንድ ጉዳይ ቢኖር ታቦቱም ሆነ ጸበሉ ከስጋችን አልፎ ነፍሳችን ላይ የሚያርፈው ልባችን ውስጥ ባስቀመጥነው እምነትና እውነት በኩል ነው፡፡ ካለፍቅር፣ ካለይቅርታ፣ ካለወንድማማችነት በፈጣሪ ፊት የምናገኘው ሞገስ የለም፡፡ ዓመት ዓመት አድርሰን ብሎ መጸለይ እጅግ መልካም ነገር ነው፡፡ ግን ዓመት ዓመት ለመድረስ ኢትዮጵያ ደህና መሆን አለባት፡፡ የሀገርና የወገን ሰላም መጠበቅ አለበት። ፍቅርን ሰብከን፣ አንድነትን አጽንተን የበኩላችንን ስናዋጣ ነው የምንደርሰው፡፡ ደግሞም ዓመት ዓመት የምንደርሰው በአፋችን ፍሬ በኩል ነው፡፡ ስለሰላም የምናወራ ከሆነ የአፋችን ፍሬ ወደነገ እንድንሸጋገር መንገድ ይሰጠናል። የምንራገምና ስለጥላቻ የምናወራ ከሆነ የአፋችን እኩይ ቃል የነገ መንገዳችንን ይዘጋብናል፡፡

ይሄን አስመልክቶ ታላቁ መጽሀፍ ቅዱስ በምሳሌ መልዕክቱ ላይ ‹ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ውስጥ ናቸው› ይለናል፡፡ በዛም በምሳሌ መልዕክት ላይ ‹ሰው ከአፉ ቃል በጎውን ይበላል› የሚል ጥቅስ ሰፍሮ እናገኛለን፡፡ ስለሀገራችን የምናስበው፣ የምንናገረው ነው ነገ ላይ ዓመት ዓመት የሚያደርሰን፡፡ በአሁኑ የጥምቀት በዐል ላይ ጥልና ክርክርን፣ ጥላቻና መለያየትን የሚሽሩ ስብከቶች፣ መልዕክቶች ናቸው ከጦርነት ታድገው ለነገ ብርሀን የሚያጩን፡፡ ዓመት ዓመት አድርሰን ብለን ስንጸልይ በአፋችን ምን እየተናገርን፣ በስብከቶቻችን፣ በመልዕክቶቻችን ምን እያስተላለፍን እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል፡፡

መንፈሳዊ በዐላት ከፖለቲካ አስተሳሰብ የጸዱ የአምልኮ በአላት ናቸው የሚለው ከሁሉ የበረታ እውነታ ነው፡፡ አንዳንዶች በእግዜር የክብር ቀን ቄሳርን ሆነው የግል ፍላጎትና ዓላማቸውን ያስፈጽማሉ፡፡ አንዳንዶች እድል አገኘን ብለው በሰላም መድረክ ፊት ጥላቻን ይነዛሉ፡፡ ይሄ ሀገርንም ሕዝብንም ወደ ነገ የማያራምድ ድርጊት ነው፡፡ ከቻልን ፍቅርን እንስበክና ከጥላቻ እንውጣ፡፡ ካልቻልን ዝም በማለት አስተዋጽኦ እናድርግ።

ምንም ማድረግ በማንችልበት ሰሞን ላይ ዝም በማለት ምንም ማድረግ እንችላለን፡፡ ባለማወቅ አስተዋጽኦ መስሎን የምናወራው፣ የምንናገረው አንዳንድ ነገር በምንም የማይጠፋ እሳት ሲያስነሳ እናያለን፡፡ ሀገራችንን ለኩሰው አልጠፋ ያለን እሳት የቆሰቆሱ እነሱ ዝም ማለት አቅቷቸው የዘባረቁ አፎች የወለዱት ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ትንሽ ነገር እንዲያስኮርፋቸው ሆነው በቆሙ ሕዝቦች መካከል ዝም ማለት ከመልካም አፍ በላይ ራሱን የቻለ በጎ አስተዋጽኦ ነው፡፡ ዝም ማለት አቅቶን በስሜት የምንተፋቸው ቃላቶች ናቸው በምንም የማይላላ ጥብቅ ቋጠሯችንን አላልተው ያራራቁን፡፡ መደማመጥና መነጋገር አቅቶን እዛና እዚህ ሆነን የተለዋወጥናቸው የይዋጣልን ቃላቶች ናቸው ከእርቅና ከተግባቦት አርቀው የዛሬዋን ኢትዮጵያና የዛሬውን እኛን የጸነሱት፡፡

አጋጣሚ እየፈለግን ጥላቻን ከመንዛት አጋጣሚን እየፈለጉ አንድነትን መስበክ ነው ኢትዮጵያን ቀና የሚያደርጋት፡፡ እድል ስናገኝ የማይሆን ከማውራት እድል ስናገኝ እርቅን ማስተጋባት ነው ታሪክ የሚያድሰው። እንደጥምቀት ባሉ የሰላም በዐላት ላይ የሚስተጋቡ በጎ መልዕክቶች ሀገር ከማጽናት አኳያ ፋይዳቸው የት የሌለ ነውና እንጠቀምባቸው፡፡ ከቻልን ክፉ ባለመናገርና በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ባለመሆን ለሀገራችን ውለታ እንዋል፡፡ ከቻልን አስታራቂና አዋዳጅ ቃላትን እንናገር፡፡ ከቻልን ስለፍቅር አፋችንን እንክፈት፡፡ ስለኢትዮጵያዊነት ድምጻችንን እናጉላ፡፡ ተከባብሮና ተቻችሎ ከሶስት ሺ ዘመን ለራቀ ዘመታት ስለኖረ ኢትዮጵያዊነት እንመስክር፡፡

ተዋልዶና ተጋምዶ በደምና በስጋ ስለተዋረሰ፣ ልዩነት ስለሌለው ጉራማይሌ መልካችን እንናገር። ተያይዞና ተደጋግፎ ከዛ ወደዚህ ስለመጣ ጥቁርነት እናውሳ። ስለለያዩን ጥቂት ነገሮች ሳይሆን ስላፋቀሩን ብዙ ነገሮቻችን ምስክርነት እንስጥ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታዩ ያሉ የአምልኮ ስርዐቶች መንፈሳዊ ዓላማቸውን እየሳቱ የተቃዋሚና የደጋፊነት አዝማሚያ እየተስተዋለባቸው ይገኛል። ይሄ አይነቱ አካሄድ ለማንም የማይጠቅም የደመቁ የአብሮነት መልኮቻችንን ከማደብዘዝ ባለፈ ክብር አይጨምሩልንም፡፡ ‹ጥምቀት ሰላም ነው..ሰላምም ለጥምቀት ነው› የሚል እና ንጹህና ዓለማዊ መልክ የሌለው አምልኮ ነው ፈጣሪን በማክበር ተቀናቃኝ የሌለው የሚል ይሆናል። ለጥምቀት በክት ልብሳችን፣ የክት ሀሳባችንን ትተን በፍቅርና በአንድነት ፈጣሪን የምናመልክበት እንዲሆን ከወዲሁ መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ፡፡

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ጥር 10/2016

Recommended For You