መንፈሳዊ በዓላትን ለመንፈሳዊ መልዕክት ብቻ

ሃይማኖትና ፖለቲካ የተደበላለቀ ይመስላል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሃይማኖት ቦታዎች ላይ ፖለቲካዊ መልዕክት፣ በፖለቲካ መድረኮች ላይ ሃይማኖታዊ መልዕክት መስማት እየተደጋገመ ነው። ይህ ድርጊት ሀገራችን የምትተዳደርበትን ሕገ- መንግሥት ጭምር የሚፃረር ነው።

ይህ መጥፎ ልማድ ነው። መጥፎ ልማድ ስለሆነም ነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፖለቲከኞች ጦርነት ቀስቃሽ ንግግር ከሃይማኖት አባቶች እየጠበቁ ያሉት። አሁን አሁን አንድ የሃይማኖት አባት ስለ ሰላም ካወሩ ጦርነትን ከሚደግፉ ኃይሎች ከፍተኛ ውግዘትና እርግማን ይወርድባቸዋል። የሚፈለገው ‹‹ ! ቁረጠው! ፍለጠው! ግደለው ..ወዘተ›› እንዲሉ ነበር ማለት ነው። እንዴት ከሃይማኖት አባት ይህን እንዲሉ ይጠበቃል? ፖለቲከኞች የሚሉት አይበቃም ወይ? የሃይማኖት አባት ይህን እንዲሉ ማድረግ የሃይማኖቱንስ ክብር መቀነስ አይሆንም?

የሃይማኖት ባህሪው ሰላምና መረጋጋትን ማበረታታት፣ ስለ ሰላም መጸለይ፣ ፀብን ማብረድ ነው። የትኛውም ሃይማኖት ጦርነትን እንደማይደግፍ ለየትኛውም ሰው ግልጽ ነው። ታዲያ በምን አግባብ ነው የሃይማኖት አባቶች ጦርነትን እንዲያበረታቱልን የምንጠብቀው?። በባህላችን እንኳን ሰዎች የከረረ ፀብ ውስጥ ሲገቡና ነገሩን በቅርብ ሽማግሌዎች ብቻ መፍታት የማይቻል ሲሆን የሃይማኖት አባቶች እንዲገቡበት ይደረጋል። ግጭቶች ከግለሰቦች አልፈው አካባቢያዊ ከሆኑ በሽማግሌ ብቻ በቂ ስለማይሆን የሃይማኖት አባቶች እንዲገቡበት ይደረጋል።

ይህ የሚሆነው የሃይማኖት አባቶችን ስለሰላም እምቢ ማለት ስለሚከብድ ነው። እነርሱን እምቢ ማለት ፈጣሪን እንደመቃወም ስለሚታይ ነው። ለእነርሱ መታዘዝ ለፈጣሪ መታዘዝ ስለሆነ ነው። ታዲያ እነዚህ የሃይማኖት አባቶች ጦርነት ቀስቃሽና ግጭትን የሚያበረታታ ንግግር እንዲያደርጉ መጠበቅ ይህን ክብራቸውን መቀነስ አይሆንም? እንዴት የባህልና የሃይማኖታችን ክብር በፀብ አጫሪነት እንዲቀየር እናደርጋለን?

ይህን ነገር ሊያስቀሩት የሚገባው ራሳቸው የሃይማኖት አባቶች ናቸው፤ መጀመሪያውኑም ያስጀመሩት አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች ናቸው። ጦርነት ቀስቃሽ ንግግር ሲያደርጉ ከአንዳንድ ወገኖች ድጋፍና አድናቆት ያገኛሉ። ከብዙ ወገኖች ግን ወቀሳ ነው የሚተርፋቸው። ደግሞስ ታማኝ መሆን ያለባቸው ለምድራዊ ደጋፊዎቻቸው ነው ወይስ ለፈጣሪያቸው ነው?

የሃይማኖት አባት በየትኛው ወገን ነው አድናቆት የማገኘው ብሎ ሊያስብ አይገባም። ይሄኛው ወገን ይወቅሰኛል ብሎም ሊፈራ አይገባም። የሚፈሩትም፣ የሚያከብሩትም ታማኝ ሊሆኑለት የሚገባም የሚያመልኩትን ፈጣሪ ብቻ መሆን ይገባል። አለበለዚያ ፖለቲከኛ ሆኑ ማለት ነው። ፖለቲከኛ ነው ደጋፊ እና ተቃዋሚን ታሳቢ አድርጎ የሚናገር፤ የሃይማኖት አባቶች መልዕክታቸው ስብከታቸው ሁሉ ሃይማኖታዊ መሆን አለበት። አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች ለአንድ የፖለቲካ ወገን ወግነው ሲናገሩ አማኙ ነው ሊገስጻቸው የሚገባው። ‹‹የሃይማኖት አባት ይገስጻል እንጂ እንዴት ይገሰጻል?›› ይባል ይሆናል፤ ፖለቲከኛ ሆነው ከተገኙስ? የሃይማኖቱን ክብር የማይመጥን ንግግር ከሆነስ?።

ስለሰላም የሚያወሩ የሃይማኖት አባቶች በተቃዋሚዎች በኩል ‹‹የመንግሥት ካድሬ›› የሚል ወቀሳ ይሰነዘርባቸዋል። አንዳንድ አባቶች ጦርነትን የሚያበረታታ ንግግር የሚያደርጉት ከዚያ ወቀሳ ለመዳን፤ ወይም ጦርነቱን በሚደግፉ ወገኖች ለመመስገን ይመስላል። ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም ነው፤ ከዚህ የተነሳም በሁለንተናዊ መልኩ ሰላም እንዲሰበክለት ይፈልጋል? ለራሱም ሆነ ለትውልዱ ለሰላም አጥንቶ ይቆማል ፤ ታዲያ ስለ ሰላም መስበኩ ከሕዝብም ከፈጣሪም ጎን መቆም የሚያስችል እድል አይደለም።

በየትኛውም አግባብ ይሁን፣ ከየትኛውም ወገን ይሁን የሃይማኖት አባት የእርስ በርስ ጦርነትን የሚያበረታታ ንግግር ካደረጉ ተወቃሽ ይሆናሉ። ከሁለት ዓመት በፊት በነበረው ጦርነት ‹‹ጦርነትን ደግፈዋል›› የተባሉ አባቶች ብዙ ወቀሳ ደርሶባቸዋል። ያ የሆነበት ምክንያት እንደ ሃይማኖት አባት ‹‹ተው›› ማለት ሲገባቸው አበረታተዋል በሚል ነው። እንዴት ከዚያ ስህተት መማር አልተቻለም ? ለምን ችግሩን ቤተ ክርስቲያን በአደባባይ ማውገዝ ፤ወይም ምእመኑን ይቅርታ መጠየቅ ተሳናት?።

ከዚህ የሚከፋው በሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት ላይ ከሃይማኖት አባቶች የሚደረግ ፖለቲካዊ መልዕክት ያለው ንግግር ነው። ንግግሮቹ ለምሳሌ፤ እንደ ጥምቀት ያሉ ብዙ ሕዝብ የሚገኝባቸው ደማቅ በዓላት ስጋት የተጫናቸው እንዲሆኑ ያደርጋል። መንግሥት በዓሉ በሰላም እንዲከበር ካለው ኃላፊነት የተነሳ በበዓላቱ ላይ ብዙ ገደብ ሊያደርግ ይችላል፤ ብዙ ቁጥር ያለው የፀጥታ ኃይል ይሰማራል። እነዚህ ነገሮች ሕዝባዊ የነበረውን በዓል ሌላ መልክ ይሰጡታል።

ሌላው ችግር የሃይማኖት አባት የፖለቲካ ንግግር ሲያደርግ ደጋፊና ተቃዋሚ ይኖራል። በሚቃወሙት ወገን ብዙ እርግማን እና ከጨዋነት ያፈነገጠ ስድብ ሁሉ ይኖራል። ይህ ሆነ ማለት ለሃይማኖት አባት ይሰጥ የነበረው ትልቅ ክብር እና የነበረው አስፈሪ ግርማ ሞገስ ይሸረሸራል። ለዚህ ደግሞ የሃይማኖት አባትን በድፍረት መሳደብ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ያየነው መጥፎ ልማድ ነው። ልክ እንደ ፖለቲከኛ ሁሉ የሚሰደቡ እና የሚረገሙ እየሆኑ ነው።

ፖለቲካዊ ትግል ራሱን የቻሉ ሰዎች አሉት። የእነዚህ ሰዎች ትግል ሊሳካ የሚችለው በራሳቸው ጥረት እንጂ በሃይማኖት አባቶች ተደግፎ ሊሆን አይችልም። በራሳቸው ማሳካት ያልቻሉትን የሃይማኖት አባቶች እንዲቀሰቅሱላቸው ማድረግ የራስን ሃይማኖት ማቅለል ነው። ሰው ናቸውና የሃይማኖት አባቶችም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በፍፁም መሳተፍ የለባቸውም ሊባል አይችልም። ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ መናገራቸው አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ ሌላ ዓለማዊ መድረክ መፈለግ ይጠበቅባቸዋል።

መንፈሳዊ በዓላት ላይ ፖለቲካዊ መልዕክት ማድረግ እንደ አንድ አባት ብቻ ሳይሆን እንደ ጠቅላላው የእምነቱ ተከታይ ሊታይ ይገባዋል። እዚያ መንፈሳዊ ቦታ ላይ የሄዱ ሰዎች ለንስሐና ለጸሎት እንጂ ብሽሽቅ እና እልህ ለሚበዛበት ፖለቲካዊ ጉዳይ አይደለም። ፖለቲካ በባህሪው እልህ፣ ቁጣ እና ብሽሽቅ ያለበት ነው። ስለዚህ መንፈሳዊ ቦታ ላይ ሰዎችን ለእልህ፣ ቁጣ እና በቀል እንዲነሳሱ ማድረግ ሃይማኖታዊ ባህሪ አይደለም ?።

የሃይማኖት አባት፣ ጥፋተኛ የሚሉትን ወገን እንደ አባት መገሰጽና መቆጣት ሃይማኖታዊም ባህላዊም መሰረት ያለው ነው። ዳሩ ግን ጦርነት ቀስቃሽና እልህ የሚያስገቡ ንግግሮች ማድረግ ሃይማኖታዊም ሆነ ባህላዊ መሠረት የለውም። በመንፈሳዊ በዓላትና በመንፈሳዊ ቦታ ሲሆን ደግሞ የበዓሉንም ክብር የማይመጥን ነውና አባቶችም የእምነቱ ተከታዮችም እንዲህ ዓይነት ድርጊቶችን ሊያወግዙ ይገባል!።

ሚሊዮን ሺበሺ

አዲስ ዘመን ጥር 9/2016

Recommended For You