“የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘናው ያለማቋረጥ እየተሰጠ ነው” – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጫ ማዕከል
ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ለስራ ስምሪት ለመሄድ በመንግስት የወጣውን መመሪያ ተከትለን የተሰጠንን ስልጠና በአግባቡ ብናጠ ናቅቅም የብቃት ማረጋገጫ ፈተናውን መውሰድ አልቻልንም ሲሉ ቅሬታቸውን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያቀረቡ ሰልጣኞች ተናገሩ፡፡
ስማቸውና ማንነታቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት እነዚሁ ቅሬታ አቅራቢዎች እንደሚሉት፤ መንግስት ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት ስልጠናውን ቢያጠናቅቁም እስከአሁን ግን የብቃት ምዘናውን መውሰድ አልቻሉም፡፡
ምዘናው በተለያዩ ዙሮች ሲሰጥ እንደነበርና አሁን ግን በማያውቁት ምክንያት እንደተቋረጠ የገለጹት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ለበርካታ ጊዜያት የወጣላቸው የፈተና ፕሮግራም እንደተሰረዘባቸው በዚህም አዲስ አበባ ከመጡ ሶስት ወራት ማለፉን ተናግረዋል፡፡
የችግሩን ምክንያት ለማወቅ የሰለጠኑበትን ተቋም በተደጋጋሚ ቢጠይቁም “ችግሩ እኛ ጋር አይደለም፤ ዝርዝራችሁን ልከናል፤ ጠብቁ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸውም ነው ቅሬታ አቅራቢዎቹ የገለጹት፡፡
አብረዋቸው ስልጠና የወሰዱ ጓደኞቻቸው ምዘናውን እንደወሰዱ የሚናገሩት እነዚሁ ቅሬታ አቅራቢዎች፤ “የምግብ አሰራር ስልጠና አልወሰ ዳችሁም ተብለን ወደማሰልጠኛ ተቋም እንደገና ገብተን ስልጠናውን ብናጠናቅቅም ምዘናውን መውሰድ ባለመቻላችን ለከፋ ኢኮኖሚያዊ ችግር ተጋልጠናል” ብለዋል፡፡
የሰልጣኞችን ቅሬታ ይዘን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጫ ማዕከልን አነጋግረናል፡፡
የማዕከሉ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ ቅሬታ አቅራቢዎቹ የቀረበውን አቤቱታ እንደማያውቁት አስታውቀዋል። ምዘናው ያለማቋረጥ እየተሰጠ መሆኑንና የዘገየበት ምክንያትም አለመኖሩን የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ ለዚህም ጥብቅ የክትትልና ቁጥጥር ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጫ ማዕከል ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራት ለስራ ለመሄድ ስልጠና ለወሰዱ ሰልጣኞች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘና በመስጠት በኩል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ ሸዊት፤ ስልጠናቸውን በአግባቡ ሲያጠናቅቁ ከማሰልጠኛ ተቋማትና ፈቃድ ሰጪ አካላት ጋር በመቀናጀት በተቻለው ፍጥነት ምዘናውን እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ቢሮው ከሌሎች ክልሎች የተሻለ አፈጻጸም አለው። የቀረበውን ቅሬታ መነሻ በማድረግም የማጣራት ስራ ይሰራል፤ ችግሩ ካለም በፍጥነት ይስተካከላል።
ማዕከሉ በአምስት ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች አገልግሎቱን እየሰጠ ሲሆን፤ ባለፉት ስድስት ወራት በ32 የምዘና ጣቢያዎች ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራት ለስራ ስምሪት ለሚሄዱ 16 ሺህ 19 ሰልጣኞች የብቃት ማረጋገጫ ምዘና መስጠቱንና ከእነዚህም ውስጥ 13 ሺህ 315 የሚሆኑት ምዘናውን ሲያልፉ 2 ሺህ 704 የሚሆኑት ግን አለማለፋቸውን ወ/ሮ ሸዊት ገልፀዋል፡፡
ማዕከሉ በ32ቱም የምዘና ጣቢዎች ባደረገው ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥርም ዘጠኝ ጣቢያዎች ችግር ስለተገኘባቸው ከምዘና ስራ የታገዱ ሲሆን ለ13 ደግሞ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል ተብሏል፡፡
ከተለያዩ ክልሎች በደላሎች ተታለው ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ሰልጣኞች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱን የተናገሩት ዳይሬክተሯ፤ ስልጠናውም ይሁን ምዘናው የሚሰጠው መንግስት ባወጣው መመሪያ ብቻ በመሆኑ ለአላስፈላጊ ወጪና እንግልት ላለመዳረግ በሚኖሩበት ክልል አገልግሎቱን እንዲያገኙ እና ከምንም በፊት ብቃታቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2011
ድልነሳ ምንውየለት