ትኩረት የሚሻው በምግብ ሸቀጦች ላይ የሚጨመሩ ባእድ ነገሮች ጉዳይ

በምግብና ምግብ ነክ በሆኑ ነገሮች ላይ የሚጨመሩ ባዕድ ነገሮች በጤና ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ነው። ከዚያ ባሻገር በኢኮኖሚ፣ በንግድ ልውውጥና በሌሎች ጉዳዮች ላይ በርካታ ጥፋቶችን ያደርሳሉ። ይህንን ወንጀል ለማስቀረት የሚደረግ ቁጥጥርና ክትትል ሥራ ጠንካራ ካልሆነ ሊያስከትል የሚችለው ሁለንተናዊ ጥፋት ለመገመት የሚከብድ ነው።

ኢትዮጵያውያን በባህል፣ በእምነት ጠንካራ ሥነ ምግባር ያለን ሕዝቦች ነን። እንግዳን ተቀብሎ አልጋውን ለቅቆ፣ እግሩን አጥቦ የሚያስተናግድ የሀገሬው ሕዝብ በንግዱም ዓለም ተመሳሳይ የሞራል ልእልና ይዞ ለዘመናት የቆየ ነው። አይደለም ባእድ ነገር ሊጨምር ከሀቁ ፈቀቅ ብሎ ትርፍን የማይሻ ነበር። አሁን አሁን ግን ይህንን ባህል ለመሸርሸር የሚጣጣሩ ጥቂት ሕገወጥ ነጋዴዎች እየተመለከትን ነው።

በመገናኛ ብዙሃንና በዲጂታል ሚዲያው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዚህ ሕገወጥ ተግባር የሚሳተፉ ግለሰቦች እየተበራከቱ ስለመምጣታቸው በስፋት ሲነገር እየሰማን ነው። ችግሩ በተለይ በአውድ ዓመት አካባቢ፤ የበዓላትን ገበያ ታሳቢ በማድረግ ሊበራከት እንደሚችል ለመገመት የሚከብድ አይደለም። ለዚህ ማሳያ የሚሆነኝ አንድ ጉዳይም ከሰሞኑ በአዲስ አበባ የካቲት 12 ሆስፒታል አካባቢ ገጥሞኝ ነበር።

በመገናኛ ብዙሃንና በልዩ ልዩ አማራጮች የምንሰማቸው ጆሮን ጭው የሚያደርጉ ሕገወጥ ድርጊቶች አንፃር እኔን የገጠመኝና ለትዝብት ያበቃኝ አጋጣሚ እንዲሁ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም። ለዚህ ነው በዛሬው ርእሰ ጉዳይ ላይ ለጥንቃቄ እንዲረዳ ርእሰ ጉዳይ አድርጌ ወደናንተ ይዤው የመጣሁት።

ባሳለፍነው ሳምንት በአንዱ ቀን በሆስፒታሉ አካባቢው እያለፍኩ በድንገት በጥቁር ፌስታል ምንነቱ ያልታወቀ ነገር ያንጠለጠለ ሰው ጎሸም አደረገኝ። ዞር ብዬ ተመለከትኩት። ካለባበሱና ከሁኔታው አንፃር ሲታይ ከክፍለ ሀገር በቅርብ የመጣ ከሚመስል ሰው ጋር ተፋጠጥኩ። የአነጋገር ለዛው ግን የከተማው ጬልሌዎችን ያስንቃል። ጊዜ ሳላባክን ምን እንደፈለገ ጠየቅኩት። የያዘው ቅቤ እንደሆነ ገልጾ ወደ እኔ እያስጠጋው እንድገዛው ጠየቀኝ።

በጠራራ ፀሐይ ቅቤን ያክል ነገር ይዞ በመዞር ግዙኝ እያለ ሲንከራተት አለመቅለጡ ገረመኝ። ስለ ሁኔታው ለማወቅ ጉጉት አደረብኝ። ሁኔታው እያጠራጠረኝም በአትኩሮት ቅቤውን ተመለከትኩት። መልኩ ቅቤ ይመስላል። ጎንበስ ብዬ አሸተትኩት። ምንም የቅቤ ሽታ የሚባል ነገር የለውም። የሻጩንና የእኔን ሁኔታ የተመለከቱ ሰዎች ተቀላቀሉን። በተመሳሳይ እነርሱም አሸተቱት። የቅቤ ሽታ እንደሌለው ምስክርነታቸውን ሰጡ።

ቅቤ ከያዘው ሰው ጋር አብሮ ሌላም ሰው አለ። እርሱም ማር መያዙን እየነገረን እንድንገዛው ጠየቀን። ማሩ ቅልጥልጥ ያለ ነገር ነው። በዙሪያችን ብዙ ሰዎች አሉ። ከእነርሱ መካከል አንዷ ባለቅቤውን እውነተኛ ንፁህ ቅቤ ከሆነ በዚህ ጠራራ ፀሐይ ለምን እንደማይቀልጥ ጠየቀችው። ፌስታል ስለደራረበበትና ውሃ ስለነከረው መሆኑን ጠቅሶ ሊያብራራላት ሞከረ፤ በሃሳቡ መስማማት ግን አልቻሉም።

ይብሱኑ ‹‹ምን አገባሽና ነው ገበያዬን የምታበላሽው ፤ ከገዛሽ ግዢ ካልገዛሽ ተይው›› የሚል ሀይለቃል ተናገራት። ጉዳዩ ከግዢ ድርድር ወጥቶ ወደ ግብብብ ተለወጠ። ሊገዙት የከበቡትም ነገሩ ስላላማራቸው ጥለውት ሄዱ። በዚህ መካከል በርካታ ሰው ሲሰበሰብና ፖሊስ እጠራለሁ ስትል ማርና ቅቤ ግዙን ባዮቹ የከበብናቸውን እየገፈታተሩ ወደ ጃን ሜዳ እግሬ አውጪኝ አሉ።

የያዙት ቅቤና ማር ጤናማ ቢሆን ፤ አንዳች በአድ ነገር የተቀላቀለበት ባይሆን በሩጫ እንደማይሸሹ መገመት የሚከብድ አይደለም። በአድ ነገር የተቀላቀለበት ቅቤና ማር ገዝተው እንደከሰሩ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች ስለገጠሙኝ ግምቴ፤ ግምት ብቻ እንዳልነበር ለማረጋገጥ አልከበደኝም።

ለረጅም ቀናት ተቀምጦ የማይሻግትና የማይበላሽ በርበሬ እና ሽሮ፤ መታጠፍና መቆረጥ ቀርቶ ለመጉረስ በእጅ እንኳን ለመቁረስ ሲሞከር ባለበት ተፈረካክሶ የሚቀር እንጀራ መግዛታቸውን በግርምት ሲናገሩ ያደመጥኳቸው አሉ። በገበያ ላይ ምንም ያህል ወተት የሚፈለግበት ወቅት ቢሆን ሰርክ የማይጠፋባቸው ሱቆች መበራከታቸውንም ታዝቤያለሁ። ከነዚህ ሱቆች የሚገዛው ወተት ለፈለገ ቀናት ቢቀመጥ እንደማይረጋ የማየቱም ዕድል ገጥሞኛል።

ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ባዕድ ነገር የሚቀላቀልባቸው ምግቦች ሆኑ ምግብ ነክ ነገሮቹ ከቀላል እስከ ከባድ የጤንነት ችግር የሚዳርጉ ናቸው። ካንሰርን ጨምሮ ሌሎች ለረጅም ጊዜ ስር የሚሰዱ የጤና ችግሮችን ሊያስከትሉ ይችላሉ።

ባዕድ ነገሮቹ የመቀላቀሉ ተግባር ከተራ ማጭበርበር ውጪ ለሁለት ምክንያቶች ይከናወናሉ። አንደኛው ምግቡ ወይም ምርቱ ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ እንዲቆይ ለማስቻል ነው። ለምሳሌ ወተትን ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ ለማቆየት ሲባል ፎርማሊን፤ ሀይድሮጅን ፕሮክሳይድ እና ሌሎችም ከፍተኛ የጤና ችግር ሊያስከትሉ የሚችሉ ጎጂ ኬሚካሎችን የሚጨምሩ እንዳሉም የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጉዳዩ ዙሪያ ያጠናቸው በቤተ ሙከራ የተደገፉ ጥናቶች ያትታሉ።

ሁለተኛው ዓላማ ለዓይን እይታ ማራኪና ሳቢ እንዲሆኑ ለማስቻል የሚጨመሩ ናቸው። ከዚህ ጋር ተያይዞም የኢንስቲትዩቱ ጥናት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለምግብ ቀለምነት እንዳይውል የተከለከለና ‹‹ዳይ›› የተሰኘ ኬሚካል የሚቀየጥበት ሁኔታ እንዳለም ያመለክታል።

ኢንስቲትዩቱ በቅርቡ በሀገር ደረጃ ከ300 በላይ በሽታዎች ላይ ጥናት ማድረጉን ይፋ አድርጓል። በጥናቱ ይፋ ካደረጋቸው በሽታዎች መካከል የደምን ጨምሮ ካንሰር፤ የኩላሊት ኢንፌክሽን የልብ ህመምና ሌሎች የረጅም ጊዜና ስር የሰደደ የጤና ችግርን የሚያስከትሉ ተጠቃሽ ናቸው። ለበሽታዎቹ በማህበረሰቡ ውስጥ ዋነኝው ምክንያት በምግቦች ላይ የሚጨመሩ ባዕድ ነገሮች ስለመሆናቸው አመልክቷል።

በነገራችን ላይ በሀገራችን ብዙ ቦታዎች እንደየአካባቢው ባህልና አኗኗር ዘይቤ ምግብና ምግብ ነክ ነገሮች ውስጥ ሊቀራረቡ የሚችሉ የእህል ዘሮችን መቀላቀል የተለመደ ነው። ለአብነት ብንጠቅስ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እንጀራ ከጤፍ፣ ከማሽላ፣ ከበቆሎ ጋር ተቀላቅለው ለምግብነት ይውላሉ። ከስንዴ ዱቄት ጋር ሊቀራረቡ የሚችሉ የእህል ዓይነቶች ሊቀላቀሉ ይችላሉ።

ወደ ደቡቡ የሀገራችን ክፍል ለምሳሌም አርባ ምንጭና ወላይታ ስንሄድ ደግሞ ሥራ ስሮች ተቀላቅለው ለምግብነት ይቀርባሉ። ቦዬ እና ጉደሬ ከሚቀላቀሉት ውስጥ ይጠቀሳሉ። በተለይ ቦዬ የሚባለው ስራስር ሲፈጭ ንጣቱ ልክ እንደ ጀሶ በመምሰሉ እንጀራውን ባዕድ ነገር የተቀላቀለበት ነው ብለን ብንጠረጥር አይፈረድብንም። እንጀራው አቅም እንዳይኖረውና ሳይቆርሱት እንዲፈረካከስ ሊያደርግም ይችላል።

ከእነዚህ ጋር ተያይዞ ከሕብረተሰቡ ወደ ፖሊስ የሚመጡም ብዙ ጥቆማዎች መኖራቸውንም መረጃዎች ያሳያሉ። መረጃዎቹ ቦዬን እንጀራ ውስጥ መጨመር ከጥራት ጋር ተያይዞ ቅሬታዎች የሚነሱበት እንዳለም ይጠቁማሉ። ለፖሊስ ሪፖርት ተደርገውም ቦዬ የተቀላቀለበት ሊጥ ከነቦሃቃው እጅ ከፍንጅ የተያዘበትም አለ። ሆኖም በተደጋጋሚ በነዚህ ላይ የቤተ ሙከራ ፍተሻ ተደርጎ ከተለመደው የእንጀራ ባህርይ ውጭ አልታየባቸውም። ግን የተለየ ባህርይ አልታየባቸውም ተብለው የሚታለፉ አይደሉም።

ኢንስቲትዩቱን በቀጥታ የሚመለከተው ለጤና ጠንቅ የሆነውን መለየት ከሚያስችል ጥናትና ምርምር ጋር የተያያዘው ብቻ ነው። ቢሆንም ይህም የጤፍ አስመስሎ የቦዬ እንጀራን ለገበያ የማቅረብ ጉዳይ ማህበረሰቡን ከማጭበርበር ጋር ተያዞ መፍትሄ ሊፈለግለት የሚገባ ነው። መሰል ሕገወጥ የወንጀል ተግባርን ፖሊስና እና የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን በትኩረት ሊሠሩበት ይገባል።

በአዲስ አበባ የተደረገው ፍተሻ በከተማዋ እንጀራ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ጀሶ፤ ሰጋቱራ እና ሌሎች በአድ ነገሮች የሚቀይጡ የሉም የሚለውን አያሳይም። በሆኑም በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪና ሰፋ ያለ ጥናት የሚጠይቅ ሆኖ ተገኝቷል። ኢንስቲትዩቱ ዘንድሮ በዚህ መልኩ አዲስ አበባ ላይ ያካሄደውን በቤተ ሙከራ የተደገፈ ፍተሻ ሰፋ አድርጎ በ11 ክልሎችና በተመረጡ 24 ከተሞችም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲያካሂድም መሰንበቱን ነግሮናል።

ፍተሻው የተካሄደው ባዕድ ነገሮች ሊቀላቀሉባቸው ይችላሉ ባላቸውና ማህበረሰቡ ተደጋጋሚ ቅሬታ እያቀረበባቸው ባሉ ዘጠኝ ምግቦች እና ምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ ነው። 4000 የእነዚህን ምግቦች ናሙናም ተጠቃሚ በመምሰል በተመራማሪዎቹ ተሰብስቧል።

እንደ መረጃው ከሆነ ከተሰበሰቡት ናሙናዎች መካከልም ሕብረተሰቡ አዘወትሮ የሚጠቀምባቸው እንጀራ፣ ዳቦ፣ ስንዴ ዱቄት፣ ወተት፣ ማር፣ ቅቤ ይገኛሉ። በቤተ ሙከራ ተደግፎ በመጀመር 2025 የሚዘልቅ ጥናትና ምርምር በስጋ አቅርቦት ላይ የሚሰሙ ሀሜቶችንም የሚያካትት ስለመሆኑ ግምት አለ።

ከላይ ካነሳሁት መረጃ መገንዘብ እንደሚቻለው በአድ ነገር በምግብ ምርቶች ላይ የሚቀላቅሉ ሕገ ወጦች መኖራቸውን ነው። ይህ ከሞራል ያፈነገጠ ተግባር ማህበረሰቡን ለጤና ቀውስ ከመዳረጉም ባለፈ ለህክምና ከፍተኛ ያጋልጣል። ከዚህ ባሻገር የማህበረሰቡን የሥነምግባር፣ ባህልና የሞራል ልእልና የሚሸረሽር ጠንቅ ነው።

በበዓላት ወቅት ኢትዮጵያውያን በብዛት ለምግብ የሚውሉ ምርቶችን ወደ ገበያ ወጥተው ይሸምታሉ። በብዛት ግዢና ሽያጭ በመከናወኑ ምክንያት ማጭበርበሮችም አይጠፉም። በዚህ ምክንያት ለከፋ የጤናና የኢኮኖሚ ችግር የሚያጋልጡ በአድ ምርቶች ያጋጥሙናል። ለዚህ ችግር ላለመጋለጥ ሸማቹም ሆነ ተቆጣጣሪ የመንግሥት አካላት ትኩረት በመስጠት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። ከፍተኛ ጥንቃቄንም መውሰድም ያስፈልጋል።

በሕገወጥ ተግባሩ የሚሠማሩ ግለሰቦችን ፍትህ ፊት ማቅረብም አንዱ መንገድ ነው። አጠራጣሪ ነገር ሲታይ ለሕግ አስከባሪ መጠቆም እራስን ከመጭበርበር ከማዳኑም በቀጣይ እንዳይደገም ማስተማሪያ ስለሚሆን ሁላችንም ዘብ መሆን ይገባና እላለሁ። ሰላም!!

አዲስ ዘመን ጥር 8/2016

Recommended For You