የኢትዮጵያ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ርምጃዎች

ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚና የብልጽግና ብሎም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ሂደቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው መልካም የዲፕሎማሲ ግንኙነት ነው፡፡ በዚህም ረገድ ሀገራችን ኢትዮጵያ በበጎ የሚነሳ ስም አላት፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት በዚህ የዲፕሎማሲ ሂደት ውስጥ ተጉዛ ከራሷ አልፋ ለሌሎች የተረፈችባቸውን የሰላምና የአስታራቂነት ሚና እንዲሁም የነጻነትና የእኩልነት ፋና ወጊነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

የታሪክ ሰነዶቻችን ከጀግንነታችንና ከሉአላዊነት ክብራችን እኩል የሚያነሱት የተግባቦትና የሰላም ወዳድ ጽናታችንን ነው፡፡ እንደሀገር ተሳካልን ብለን አፋችንን ሞልተን በኩራት የምንናገረው ይሄን መቶ ዓመታት የተሻገረ የሰጥቶ መቀበል መርሀችንን ነው። አፍሪካንም ሆነ መላውን ጥቁር ሕዝብ ከተጫነበት የቅኝ ግዛጥ ቀንበር ነጻ እንዲወጣ በዚህ የዲፕሎማሲ ሂደት ውስጥ አልፈን ስለመሆኑ ነጋሪ የሚያሻው ጉዳይ አይደለም፡፡

ሰሞነኛው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንትም የዚህ ሂደት አንድ አካል ነው፡፡ ‹ከአፍሪካ መዲናነት እስከ ዓለም መድረክ› ” በሚል መሪ ሀሳብ ከጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ ጥር 24 ድረስ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አዘጋጅነት በሳይንስ ሙዚየም መከፈቱ ይታወቃል፡፡ የተለያዩ ዓላማዎችን ያነገበው አውደ ርዕዩ ሀገራችን የነበራትን ያላትንና የሚኖራትን የዲፕሎማሲ ሂደት በስፋትና በንቃት የቃኘ ነው። እንደ ሀገር የበለጸግንባቸውና ከራሳችን አልፈን ለሌሎች የተረፍንበትን መልካም ግንኙነት በማስታወስ ያንን ዘመን ከዚህኛው ትውልድ ጋር በማስተሳሰር ላበረቱን ክንዶች ምስጋና የምንቸርበትም ነው፡፡

ሳምንቱን አስመልክቶም ‹ዲፕሎማሲያችን ለብሔራዊ ጥቅማችን› በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው የፓናል ውይይት የትላንትን የታሪክ ዳራ ከመጥቀስ አንስቶ አሁን እስካለንበትና ነገ እስከምንደርስበት ያለውን የዲፕሎማሲ ሂደት የዳሰሰ ውይይት ተካሄዷል፡፡ በዚህ ውይይት ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ‹የትውልድ፣ የትምህርትና የእውቀት ሽግግርን ለመሙላት በዲፕሎማሲው ዘርፍ ጠንካራ ስራ እየተሰራ› እንደሆነ በንግግራቸው መመስከር ችለዋል። የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጉዞ ኢትዮጵያን በመሩ በሁሉም መሪዎች ብርቱ ጥረት የቀጠለ መሆኑን በማስታወስ እንደሀገር በበረታ ዲፕሎማሲ የበረታ ለውጥ እንደሚመጣም አመላክተዋል፡፡

ሌላኛው የዚህ ፓናል ውይይት ተሳታፊ በመሆን በመካከለኛው ዘመን ላይ የነበረውን የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ንቃት በጥናታዊ ጽሁፋቸው ያሳዩት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካን የነጻነት እንቅስቃሴ በዲፕሎማሲ በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገች እና የአፍሪካ ሕብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምስረታ ላይም ደማቅ አሻራ እንዳሳረፈች ጠቅሰዋል፡፡ ከሰላምና ከተግባቦት አንጻር ሶስተኛ ወገን ሆኖ በመግባት የአሸማጋይነት ሚናዋንም ያተተው ጥናታዊ ጽሁፉ የኮርያን፣ የላይቤሪያን፣ የሶማሊያን፣ የኩባንና የሩዋንዳን በጎ አሻራ ጠቅሷል፡፡ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴን ጨምሮ አምባሳደር ቆንጅት ስነጊዮርጊስ የዚህ ፓናል ውይይት አንድ አካል ነበሩ፡፡

ለጀመርነውና ውጤት እያመጣንበት ላለው አሁናዊ የዲፕሎማሲ ሂደት መንገድ ጠራጊ አስተሳሰቦችንና ልምዶችን ይዘን ቀጣይ ግንኙነታችን የምናቀላጥፍበት እንደሚሆንም ተስፋ ተችሮታል። ኢትዮጵያን ገላጭ በሆኑ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችና በፓናል ውይይት የታጀበው አውደ ርዕይ ትላንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ከነገ በማስተሳሰር በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያስመዘገብነውንና እያስመዘገብን ያለውን ወደፊትም የምናስመዘግበውን እድልና ድል ቃኝቷል፣ በመቃኘት ላይም ይገኛል፡፡

በአንድ ገላጭ እውነት ብናስረው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት የኢትዮጵያ የእውቀት፣ የተግባቦት፣ የሰላም ወዳድነትና፣ የሰጥቶ መቀበል የታሪክ አሻራ ነው፡፡ እንደ አድዋ ሁሉ፣ እንደ ህዳሴ ግድባችን ሁሉ በታሪክ ውስጥ ከፍ ብሎ የሚነሳ የዛኛውና የዚኛው የመጪውም ትውልድ የኩራት ገድል ነው፡፡ ..ዲፕሎማሲ የአንድ ሀገርና ሕዝብ፣ የአንድ መንግስትና አስተዳደር የጥንካሬና የስልጣኔ መመዘኛ ነው፡፡ ዛሬም ይሁን ድሮ በዲፕሎማሲው ረገድ የደከሙ ሀገራት ምንም መፍጠር የማይችሉ እንደሆኑ መረጃ የሚሰጥ እውነታ ነው፡፡

የእኛ ታሪክ ግን እንዲህ አይደለም፡፡ በዛ ዓለም ብዙም ባልነቃችበት ዘመን ስለሀገርና ሕዝብ፣ ስለሰላምና ልማት ባህር ተሻግሮ ከዓለም ሀገራት ጋር ወዳጅነትን መፍጠር አሁን ላለው ትውልድ ኢትዮጵያዊነትን የሚገልጥ፣ ታሪክን የሚያስረዳ፣ ማንነትን የሚያወሳ የታላቅነት መስካሪ ነው፡፡ ዓለም ላይ በቀጣናዊ፣ በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ በዚህ ልክ የተጓዘ ሀገርና ሕዝብ የለም ካለም በጣት የሚቆጠር ነው፡፡ ይሄ ማለት ስልጣኔና ዘመናዊነትን ቀድመን ለመጀመራችን አንዱ ምስክር ነው፡፡

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አቅጣጫ ከመተለም ባለፈ ራሳችንን ለተቀረው ዓለም የምንገልጥበት መድረክ ነው፡፡ ወቅትና ጊዜ ተቆርጦለት ቀጣይነት ባለው መልኩ ቢካሄድ ደግሞ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው የሚሆነው፡፡ የአፍሪካ የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቶች ነን፡፡ በአፍሪካ ቀንድና በአህጉሪቱ በምንም የማይደበዝዝ ደማቅ ስም አለን። በዓለም አቀፍ ደረጃም ከኢትዮጵያዊነት ጋር አብሮ የሚነሳ የታሪክ፣ የነጻነትና የሉአላዊነት ምኩራብ ነን፡፡ ላሉብን አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ጫናዎች እንደመመከቻ ሆኖ የሚያገለግለን ደግሞ የዳበረና በእውቀትና በልምድ የሚመራ የዲፕሎማሲ ተጽዕኖ ፈጣሪነታችን ነው፡፡

ከአባቶቻችን በወረስነው ሰላም ወዳድ ፖለቲካ፣ ሰላም ወዳድ ጉርብትና እና የአብሮ መልማት መስተጋብር የቀጠናውን ሰላም አስጠብቀን አፍሪካን የዋጀና ዓለምን ያስደነቀ የለውጥና የእድገት ባለቤቶች እንደምንሆን ጅማሬዎቻችን መስካሪዎች ናቸው። አንድ ሀገር በቀጠናውም ሆኖ ወንዝ ተሻጋሪ በሆነ የእርስ በርስ ጉርብትናዋ ጥሩ ስም ከሌላት ብዙ ነገሮቿ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚገቡ ናቸው፡፡ አይደለም ብዙ ነገሮቿ ቀርቶ አንድ ሁለት ጉዳይዋ ጥያቄ የሚያስነሳ ሀገር ራሷን መለስ ብላ እንድታይ የማንቂያ ደውል ነው፡፡ ከዚህ የተነሳም ዲፕሎማሲ የለውጥ፣ የእድገትና የዘርፈ ብዙ መስኮች መነሻ አውድ ነው፡፡

ተለዋዋጭ በሆነ ዓለም ውስጥ ነን፡፡ አሁን ግዜው የዲፕሎማሲ ነው፡፡ የነበሩንን ገልጠን ያሉንን አጥብቀን ለመጪው አዲስ ሂደት ራሳችንን ማዘጋጀት በአጽንኦት ልናየው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ እንደሀገር የጀመርናቸው ትላልቅ ልማቶች አሉ፡፡ ወደፊትም ልንሰራቸው ያሰብናቸው ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። እኚህ ሕዝባዊ ጸጋዎች ፍሬ አፍርተው ሀገርና ሕዝብ እንዲጠቅሙ መልካም ወዳጅነት የማይናቅ ሚና አለው፡፡

ዲፕሎማሲን በአንድ ሁነኛ ሀገራዊ ልማድ እንግለጸው ብንል..በቡና አጣጭ ጎረቤት ልንወክለው እንችላለን፡፡ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ቡና አጣጫ ጎረቤቶች አሉን፡፡ እነዚያ ጎረቤቶቻችን በሰላሙም በችግሩም ጊዜ አብረውን የቆሙ ናቸው፡፡ ለምንም ነገር አለውለህ የምንባባላቸው ናቸው፡፡ ከነዚህ ጎረቤቶቻችን ውስጥ ከአንዱ ጋር ተኮራርፈን ቡናችንን ለብቻ ስንጠጣና ቡናቸውን ለብቻ ሲጠጡ የሚኖረው ማሕበራዊ ክስረትን መረዳት ይቻላል፡፡ ይሄ ክዋኔ ወደቀጠናዊ ወደ አህጉራዊ እና ወደዓለም አቀፋዊም እውነታ ከፍ ሲል ነባራዊውን ዲፕሎማሲ ይወክላል። ከኢኮኖሚ፣ ከፖለቲካ፣ ከማሕበራዊ አኳያ ንጻሬውንም መረዳት ይቻላል፡፡

በሁሉም መስክ ወዳጅነት በሁሉም መስክት ትርፋማነት ነው፡፡ በሁሉም መስክ ጠላትነት በሁሉም መስክ ኪሳራ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከሌላው ጋር እንዴት መኖር እንዳለብን የምናውቅ እና መቶ ዓመታትን ያስቆጠረ የጉርብትና ታሪክ ያለን ነን፡፡ ታሪካችን በአብሮ መልማት፣ በአብሮ ማደግና የማንንም ሳንነካ እንዲሁም ማንም የእኛን እንዲነካብን ሳንፈቅድ የሆነ ነው፡፡ ትርጉም ያለውና ውሀ የሚያነሳው ዲፖሎማሲ ደግሞ እንዲህ ያለው ዲፕሎማሲ ነው፡፡ አሁንም በዚህ ጥንተ እውነት ታሪካችን ላይ ሳንገዳገድ በጽናት በመራመድ ኢትዮጵያን ከፍ የማደረጉ ኃላፊነት ተጥሎብናል፡፡

ዲሞክራሲ መቻቻልና መከባበርን የሚጠይቅ ነው፡፡ ያለፉ የዲፕሎማሲ ስርዐቶቻችን ደግሞ በዚህ እውነት ውስጥ ያለፉ ስለመሆናቸው ካገኘነውና ለሌሎች ከሰጠነው ክብርና ሰላም መረዳት እንችላለን። የራስን ክብርና ሉአላዊነት በማስነካትና የሌሎችን ክብርና ሉአላዊነት በመድፈር ውስጥ የሰጥቶ መቀበል መርህ የለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት የተገኘው በፍትህና በእኩልነት ውስጥ በተከፈለ ጽኑ ተጋድሎ ነው። አንገታችንን ቀና አድርገን የተራመድንባቸው የነጻነትና የወዳጅነት ዳናዎች ማንንም ሳንነካና ማንም እንዲነካን ባለመፍቀድ ውስጥ ነው፡፡

ቀጠናዊ ዲፕሎማሲ ከአፍሪካ አዘልሎ አለምቀፋዊነትን የሚቸር ነው፡፡ ዙሪያችንን ተመልክተን ሁሉንም አይነት የተግባቦት አማራጮች ተጠቅመን ሀገራችንን ነጻ የምናወጣበት፣ ከውጪው ማህበረሰብ ጋር በሁሉም አቀፍ ዘርፍ የምንተባበርበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ በዲፕሎማሲ ያሸነፈ ሀገር በምንም አይሸነፍም፡፡ በዚህ ዘመን ላይ የኃይልና የብርታት የለውጥም መለኪያዎች ተደርገው ከተቀመጡት ውስጥ የዲፕሎማሲ ክህሎት አንዱ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ተወዳሽ ስም ከማትረፍ ጎን ለጎን ተወዳሽ ስራዎችንም ሰርተናል፡፡

ከሀገራችን የዲፕሎማሲ ፍሬዎች መካከል ታላቁ የሕዳሴ ግድብ፣ የባህር በር፣ የብሪክስ አባልነት የሚጠቀሱ ናቸው። እንደ ኢጋድና ተመድ፣ እንደ አፍሪካ ሕብረትና ሊግ ኦፍ ኔሽን የመሳሰሉ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሳረፍናቸው አሻራዎቻችን በድምቀት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በቀጣይም የዚህ ሂደት አንድ አካል የሆኑ ቀጠናዊና ባህር ተሻጋሪ ትልሞች አሉን፡፡ እንደ ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት ዓላማና እቅድ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ክፍተቶቻችንን ሞልተን በአዲስ ኃይል በችግሮቻችን ላይ የምንነሳበት የአዲስ ምዕራፍ ግስጋሴ እንደሚሆን ታምኖበት እየተሰራ ነው። ካለፈው ተምረን መጪውን ብሩህ የምናደርግበት የስኬታማ ዲፕሎማሲ አቅጣጫዎችቻችንን አበልፅገን የምናስቀጥልበት ነው፡፡

ከእርስ በዕርስ መደጋገፍ ባለፈ ዲፕሎማሲ የዘመናዊነት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ አሁን ላይ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ውጤት ማምጣት ብዙም ላይገርም ይችላል ምክንያቱም ጊዜው ለዚህ ነገር ምቹና ተስማሚ ስለሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከሌላው ሀገርና ሕዝብ ጋር በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሀሳብ ልውውጥ የጀመሩበት ያ ዘመን እንደዚህኛው ዘመን ለምንም ነገር ምቹ አልነበረም፡፡ በዛ ምቹ ባልሆነ ዘመን ላይ ሁኔታዎችን ምቹ አድርጎ ከዓለም ሀገራት ጋር ወዳጅነትን መፍጠር ቀድሞ መንቃት ከመባል ሌላ ምንም ሊባል አይችልም፡፡

እንዲህ አይነት የሀገርና ሕዝብ፤ የትውልድና የአስተዳደር ንቃቶች አሁን ላለችው ደማቅ ዓለም መሰረት የጣሉ ነበሩ፡፡ ሌላው ከዚህ ጋር አብሮ ሊነሳ የሚችለው ውይይትና ተግባቦትን ያስቀደመ በአብሮ ማደግ ዲፕሎማሲያዊ አረዳድ የዳበረ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ እኚህ የታሪክ ሁነቶች ዛሬ ላይ ዳብረው በብዙ ዘርፍ ውጤታማ አድርገውናል፡፡ ያላንዳች መጠራጠር ነገም ይቀጥላሉ፡፡

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን  ጥር 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You