የሕዝብ ግንኙነት ሠራተኞች ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል

የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አንድ ተቋም ለትርፍ የተቋቋመ ይሁን አገልግሎት መስጠትን መነሻ ያድረገ ፣ ተቋሙ ከሕዝቡና ከተገልጋዩ ማሕበረሰብ ጋር ያለውን ግንኙነት ሚዛን ለመጠበቅና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የግድ አስፈላጊ ነው።

በሳን ጆሴ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ማቲው ካቦት Mathew Cabot የሕዝብ ግንኙነት ሥራ የሁለት ወገን ተግባቦት (two-way communication) መርህ ላይ የተመሠረተና ለመልካም ገፅታ ግንባታ፣ የተቋሙን ስምና ክብር ለማጉላት፣ ለግንዛቤ ፈጠራ፣ ለማስተማር፣ የሕዝብ አመኔታን መፍጠር፣ አገልግሎትንና ጥሩ ሥራን ማስተዋወቅ፣ ተደራሹን የማነሳሳት ሥራ ለመሥራት መነሻ መርህ እንዳለው ይገልፃሉ።

ሕዝብ ግንኙነት የሁለት ወገን ተግባቦት መርህን መሠረት ያደረገ እንደመሆኑም ራስን ከመሸጥ ባለፈ ከሕዝቡ ወይም ከተገልጋዩ ሃሳብ በመውሰድና አስተያየት በመቀበል አገልግሎት ለማሻሻል አቅም ይፈጥራል።

በሀገራችን አንዳንድ ተቋሞች ከሌሎች በበለጠ መልኩ እየደከሙና እየሠሩ ሥራቸው ስለማይገለፅ በሕዝብ ወይም በተገልጋዩ ማሕበረሰብ በኩል ያላቸው ተቀባይነት ሲያድግ አይታይም። ወይም እየሠሩ ምንም መሥራት እንደማይችሉ ሲቆጠሩ ይታያል።

አንዳንድ ተቋማት ደግሞ የወርና የዓመት የሥራ ግምገማ ሪፖርት ከማስተላለፍ በዘለለ ያሉበትን ቁመና እየሰጡ ያሉትን አገልግሎት በሚያሳይ ደረጃ ሲሠሩ አይታይም። የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ብቁ በሆነ ባለሙያ መመራት አለበት። አንዳንድ ተቋማት በድካማቸው በሥራቸው ልክ እንዳይገለጹና መልካም ሥራቸውና ለሕዝብ እየሠጡት ያሉት አገልግሎት ከሥራ እንዳይቆጠር ያደረገው ደረጃውን የጠበቀ ሥራ በብቁ ባለሙያ አለመሥራታቸው ነው። ይህ ምስል የአብዛኞቹ የሀገራችን ተቃማት ነፀብራቅ ነው።

በአሁኑ ወቅት መረጃ በሰው ልጅ የእለት ተለት ኑሮ ውስጥ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። ከእለቱ የአየር ሁኔታ እስከ ሀገራዊ ጉዳዮች ድረስ ማህበረሰቡ ባለበት አካባቢና ሀገር ምን እየተካሄደ እንደሆነ ማወቅ የሚችለው ሚዲያዎች በሚሰጡት መረጃ ነው። የሚዲያ ተቋማት ወደ ማህበረሰቡ የሚያደርሱትን መረጃ ከሚያገኙባቸው የተለያዩ ምንጮች መካከል የሕዝብ ግንኙነት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።

ሚዲያዎች አንድ ተቋም ምን እየሠራ እንደሆነ ፤ ሥራዎቹም በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ መረጃ ከሚያገኙባቸው መንገዶች መካከል የተቋማቱ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ተጠቃሽ ናቸው። የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችም መረጃዎችን በፍጥነትና በጥራት ለመገናኛ ብዙኃን የመስጠት ትልቅ ሙያዊ ኃላፊነትም ግዴታም አለባቸው ።

በእርግጥ ለብዙዎች የሕዝብ ግንኙነት ዋናው ዓላማ የተቋምን ገፅታ መገንባት ነው። የተቋሙን ስኬታማነት አስጠብቆ ለማስኬድ ሙያዊና ስትራቴጂያዊ ስልቶችን ቀይሶ በተገልጋዩ ዘንድ በጎ እይታ በተቋሙ ላይ እንዲኖረው ማስቻል ነው። ይህ በአብዛኛውን በቢዝነስ ተቋማት ጎልቶ የሚታይ ነው።

ይህ ሙያዊ አገልግሎት ከፍ ባለ መልኩ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት በማሳለጥ ሂደት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከዚህ ከፍያለ እንደሚሆን ይታመናል። በተለይም በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ባለ ማህበረሰብ ውስት የሚኖረው ፋይዳ ከፍ ያለ ነው።

አንድ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያም በመንግሣት እና በሕዝብ መካከል እንደድልድይ ሆኖ በማገልገል መልካም ግንኙነት የመፍጠር ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል። የመንግሥትን ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ለሕዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ የማሳወቅ ኃላፊነትም አለበት።

ለዚህ ዓላማውም የሕትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎችን ጨምሮ ዘመኑ ያፈራቸውን ዲጅታል የሚዲያ አመራጮች ይጠቀማል። በተለይም ከተቋሙ የበላይ አመራሮች ጋር የጠበቀ ግንኙነት በመፍጠር በእቅድ ተደግፎ አስፈላጊውን ወቅታዊ መረጃዎች፤ በጥራትና በፍጥነት ለሚመለከታቸው አካላት እንዲደርስ የማድረግ ከፍ ያለ ኃላፊነት አለበት።

ወደ ዋናው ሃሳቤ ስመለስ፤ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሚዲያ ተቋማት በጠየቋቸው ጊዜ መረጃ የመስጠት ወይም መረጃውን ከሚሰጠው አካል ጋር የማገናኘት ኃላፊነት እንዳለባቸው በዚህ ጽሁፍ የማሳውቀው አዲስ እውነታ አይደለም፤ የነበረና ያለ ነው። ትልቅ ጥያቄ እየሆነ የመጣው ግን በአሁኑ ወቅት ይህንን ኃላፊነታቸው አውቀው በአግባቡ ለሚዲያ ተቋማት መረጃ የሚሠጡ የተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ምን ያህል ናቸው የሚለው ነው።

በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ የሆኑት ዶክተር እንዳለ ኃይሌ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ በ2015 በጀት ዓመት ብቻ የመረጃ ነፃነት የሚመለከቱ 141 አቤቱታዎች ለተቋሙ መቅረቡንና እነዚህ አቤቱታዎች የመገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ ለተለያዩ የምርምር ሥራዎች መረጃ ጠይቀው በተከለከሉ ግለሰቦች የቀረቡ ጥያቄዎች መሆናቸውን ተናግረው ነበር።

የመረጃ ነፃነት መብት አዋጁ በሚፈቅደው ልክ ተግባራዊ እየተደረገ እንዳልሆነ እና ይህንን ባለማድረጋቸው ከበርካታ የመገናኛ ብዙኃን ቅሬታ ለተቋሙ እንደሚቀርብ ገልፀው፤ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት በእጃቸው ያለውን መረጃ የመገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ ለሚጠይቋቸው ዜጎች መስጠት እንዳለባቸው አዋጁ፤ የመረጃ ነፃነት አዋጁ እንደሚያስገድድም አስረድተዋል።

“የመረጃ ነፃነት አዋጁ የመገናኛ ብዙኃን መረጃ በጠየቁ በ10 ቀናት ውስጥ፤ እንዲሁም ማንኛውም ዜጋ በ30 ቀን ውስጥ የጠየቁትን መረጃ የማግኘት መብት እንዳላቸው ያስቀምጣል። ሆኖም ለመገናኛ ብዙኃን የተቀመጠው የአስር ቀን ገደብ መረጃን በወቅቱ ወደ ማሕበረሰቡ እንዳያደርሱ የሚያደርግ ነው። ይህንን መሠረት አድርገን አዋጁ በራሱ ክፍተት እንዳለበት በመመርመር እንዲሻሻል ሃሳብ አቅርበናል” ብለው ነበር።

የመረጃው ባለቤት የተጠየቀውን መረጃ በአግባቡና በሚፈለገው ጊዜ መስጠት ካልቻለ ለሀሰተኛ መረጃ መበራከትና በማህበረሰቡ ዘንድ ለሚፈጠር ብዥታ ዋና ምክንያት ይሆናል። የሚዲያ ተቋማት የተቋቋሙበት አንዱ ዓላማ ለማህበረሰቡ ትክክለኛ እና የጠራ መረጃ ለመስጠት ነው። በመሆኑም ይህንን ለማድረግና ማህበረሰቡን ከሀሰተኛ መረጃ ለመከላከል ትክክለኛውን መረጃ ለማወቅና ለሕዝብ ለማድረስ መረጃን በጠየቁበት በወቅት በፍጥነት ማግኘት አለባቸው።

ይህ ደግሞ መገናኛ ብዙኃኑን በቀጥታ ከተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ጋር የሚገናኝ ነው። እነሱ የሚፈለገውን መረጃ አግባብ ባለው መንገድ በኃላፊነት መንገድ በፍጥነትና በጥራት መስጠት ካልቻሉ ነገሩ “ላም አለኝ በሰማይ” አይነት እንደሚሆን ለመገመት የሚከብድ አይደለም።

በችግሩ ዙሪያ ሁሉንም የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በአንድ ላይ መውቀስ አይቻልም። ሥራቸውን አውቀው በኃላፊነት ስሜት የሚሠሩ በርካታ ባለሙያዎች አሉ። በተለይም ጊዜው ያበረከተውን የቴክኖሎጂ ውጤት በመጠቀም እንቅስቃሴ የሚያደርጉ፣ የዕለት ውሏቸውን፣ አስፈላጊ ውሳኔዎችን በተመለከተ መረጃውን በተገቢው መንገድና ፍጥነት የሚያስተላልፉ ተቋማትም አሉ።

ይሁንና ከዚህ በተቃራኒ አንዳንድ ባለሙያዎች መረጃን ለሚዲያ ተቋማት ለመስጠት ሲበዛ ዳተኛ ሆነው ይታያዩ። ይህን ተከትሎም በርካታ መረጃዎች ሕዝብ ጋር ሳይደርሱ ይቀራሉ። የመረጃ መዛነፎችም ያጋጥማሉ።

መረጃን በመደበቅና ለሚዲያዎች በሮች ዝግ እንዲሆኑ ማድረግ መንግሥት እየሠራ ያለውን ሥራ እና ያለበትን ደረጃ ሕዝብ እንዳያውቅ ስለሚያደርግ ሊታሰብበት ይገባል። በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ጠንካራ ለማድረግና በየጊዜው የደረሰበትን ደረጃ በቀላሉ ለሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ለማድረስ ያለው ተመራጭ መንገድ ለሚዲያዎች በር መክፈትና አስፈላጊውን መረጃ መስጠት ነው።

የሕዝብ ግንኙነት ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመተግበር በተለይ ጎበዝ የተባሉት የመጡበትን መንገድና የገጠማቸው እንቅፋቶች እንዲሁም የተሻገሩበትን ዘዴ በአግባቡ መቃኘትና የልምድ ልውውጥ ማድረግም ይኖርባቸዋል።

ቲሻ ልዑል

አዲስ ዘመን ጥር 7/2016

Recommended For You