እንቁው ዲፕሎማትአምባሳደር ከተማ ይፍሩ

እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ተቋማት ሀገርን አኅጉርን ሲሸከሙ፤ እንደ አምባሳደር ከተማ ይፍሩ ያሉ የሀገር ባለውለታዎች ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርንና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አይነትን ተቋም ተሸክመው የዛን ጊዜውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የዛሬውን አፍሪካ ኅብረት አዋልደዋል።

በኢትዮጵያ የዘመናዊ ዲፕሎማሲ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነው የዲፕሎማሲ ዓውደ ርዕይ ባለፈው ዓርብ ጥር 3 ቀን 2016 ዓ.ም በሳይንስ ሙዚየም ሲከፈት ከሩቅ ጎልተው ከሚታዩት ዲፕሎማቶች ግንባር ቀደሙ ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ ናቸው። እኔም በዚህ የዲፕሎማሲ ሰሞናት ጉምቱውን ዲፕሎማትና ሀቀኛ ፓን አፍሪካኒስት እንዲህ ልዘክራቸው፣ ላስተዋውቃቸው፣ ላከብራቸውና ላወድሳቸው፤ መኅልዬ መኅልዬ ዘ ከተማ ይፍሩ” አልሁ።

በፊውዳሉ ሥርዓት ሹመት ከብቃት ይልቅ በዘር በሚሰጥበት ወቅት ስሟ ብዙ ከማትታወቀው የሐረርጌ ግዛቷ ጋራ ሙለታ ከደሃ ገበሬዎች ቤተሰብ የተገኙትና በ30ዎቹ ዕድሜ የነበሩት ወጣት ከተማ ይፍሩ የሀገሪቷ የውጭ ጉዳይ ግንኙነት አድራጊ፣ ፈጣሪ እንዲሁም የአፄ ኃይለሥላሴ ዋና ልዩ አማካሪ (ቺፍ ኦፍ ስታፍ) ይሆናሉ ብሎ ያለመ አልነበረም።

ነገር ግን የማይታሰበው እውን ሆኖ ከተማ ከዚህም አልፎ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ላይ አሻራቸውን ማሳረፍ ችለዋል። የታሪክ መዛግብትም ሆነ በቅርብ የሚያውቋቸው ተራማጅ ብለው የሚጠሯቸው ከተማ ኢትዮጵያ ቅኝ ባለመገዛቷ ከአህጉሩ የተለየችና ኢትዮጵያውያንም ልዩ ነን የሚል እሳቤ በአብዛኛው ዘንድ ቢንሸራሸርም ለሳቸው ግን የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ከሌሎች አፍሪካውያን የተለየ አይደለም። መተባበር ካለባትም ከአፍሪካውያን ጋር ነው የሚል ቁርጠኛ አቋም ነበራቸው።

ገና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያሉ ሊግ ኦፍ ኔሽን ኢትዮጵያን አንቅሮ የተፋበት ሁኔታ ቁጭት እንደፈጠረባቸው በአሁኑ ሰዓት የሕይወት ታሪካቸውን “ከተማ ይፍሩ፤ የሰላም የዕድገት እና የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ” በሚል ርዕስ ጽፎ ለሕትመት ያበቃው ልጃቸው መኮንን ከተማ ይናገራል። የጥቁር ሕዝቦች ነፃነት ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ በጣሊያን ስትወረር አባል የሆነችበት የሊግ ኦፍ ኔሽን ይተባበረኛል የሚል እምነት ነበራት። ነገር ግን ያልተጠበቀው ሆኖ አፄ ኃይለሥላሴ ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት በመዘባበት፣ በጩኸትና በፉጨት ንግግራቸው ተቋረጠ።

ይህ ሁኔታ ታዳጊው ከተማን ከማስከፋት አልፎ ለተጨቆኑ ሕዝቦች እንዲቆም፤ ለፍትሕና ለእኩልነት እንዲታገል መሠረት እንደሆነው የቅርብ ጓደኞቻቸው ምስክር ናቸው። በአንድ ወቅት የቀድሞው የጣሊያንና ጂቡቲ አምባሳደር ዶ/ር ፍትጉ ታደሰ ስለ ከተማ ተጠይቀው ሲመልሱ በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ የአፍሪካውያን ሁኔታ ስለሚያሳስባቸውም “እኛ ነፃነት አግኝተን፤ እነርሱ በባርነት ቀንበር እንዴት ይሰቃያሉ” የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው ብለዋል።

ለዚያም ነበር ኢትዮጵያ ከጣሊያን ጋር በነበራት ትግል የረዳቻት እንግሊዝን እንኳ ለመተቸት ቅንጣት ወደ ኋላ ያላሉት። እንግሊዝ በአፓርታይድ ጭቆና ስር ለነበረችው ደቡብ አፍሪካ የጦር መሣሪያ መሸጧንም በከፍተኛ ሁኔታ ተችተዋል። ከመተቸት ባለፈም ነፃ ያልወጡ የአፍሪካ ሀገራት ነፃ እንዲወጡ ከፍተኛ ርብርብና ለነፃ አውጭዎቿም ድጋፍ አድርገዋል።

ከዚህም ውስጥ የሚጠቀሰው ለማንዴላ በኢትዮጵያ ፓስፖርት እንዲዘዋወሩ ማድረጋቸው ነው። ማንዴላ በአፓርታይድ መንግሥት በቁጥጥር ስር ሲውሉ የከተማ ፎቶ በኪሳቸው ውስጥ እንደተገኘ የከተማ ልጅ መኮንን ይናገራል። ፎቶው ላይ ለነፃነት ታጋዩ የሚል ጽሑፍ የነበረበት ሲሆን ፎቶው በማንዴላ እስር ወቅት እንደ ማስረጃ ሰነድ ቀርቦ እንደነበር በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ ቪትዝ ዩኒቨርሲቲ ሙዚየም በማስረጃነት ተቀምጧል።

1950ዎቹ ለአፍሪካውያን የተለየ ተስፋ ይዘው የመጡ ዓመታት ነበሩ። ወቅቱ የቅኝ ግዛት፣ የጭቆና እና የባርነት ቀንበር በመሰባበር የነፃነት ጎሕ መቅደድ የጀመረበት ነበር ሲል ቢቢሲ ያስታውሳል። በዛን ጊዜም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከዚህ ቀደም ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ወጣቱ ፓን አፍሪካኒስት ከተማ የአፍሪካ አህጉራዊ ድርጅት መፈጠር አለበት የሚል ንግግር አደረጉ።

ነፃ በወጡት አፍሪካ ሀገራት መካከል አህጉራዊ ትብብርና ኅብረት የመፍጠር ፍላጎት ቢኖርም፤ ነፃ የወጡ ሀገራት ተዋሕደው አፍሪካ አንድ ልትሆን ይገባል የሚል እሳቤዎችም የጎሉበት ጊዜ ነበር። በአንድ ወገን ዋናና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ሀገራቱ በፍጥነት ተዋሕደው አፍሪካ አንድ ልትሆን ይገባል የሚለው የካዛብላንካ ቡድን፤ እንዲሁም አንድ ከመሆን በፊት ሌሎች ትብብሮች ሊቀድሙ ይገባል የሚለው የሞኖሮቪያ ቡድኖች ነበሩ።

ኢትዮጵያም በወቅቱ የሞኖሮቪያን ቡድን ተቀላቅላ ነበር። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከተማ ኢትዮጵያ ሁለቱን አንጃዎች የማስማማት ሥራ መሥራት እንዳለባት ለንጉሡ አጥብቀው ተናገሩ። ምንም እንኳን በወቅቱ ወግ አጥባቂ የነበሩት ሹማምንቱና መኳንንቱ “እንምከርበት” የሚል ሀሳብ ቢያነሱም አፄ ኃይለሥላሴ ግን “ታምንበታለህ” የሚል ጥያቄ ብቻ እንዳቀረቡላቸውና ሂደቱን ብቻ እንዲያሳውቃቸው እንደነገሩት መኮንን ይናገራል።

ሁለቱም ቡድኖች ስብሰባቸው ላይ እንዲገኙ ጥሪ ሲያቀርቡ ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ በማሰብ አጀንዳቸውን ይዘው ሄዱ። የሚኒስትሩ ዋነኛ አጀንዳ የነበረው ከ20 በላይ አባላት የነበሩትን የሞኖሮቪያን ቡድንና ስድስት ብቻ አባላት የነበሩትን የካዛብላንካን አንጃ አሳምኖ አዲስ አበባ ጉባኤ ማካሄድ ነበር።

ኢትዮጵያ ሁለቱን ቡድኖች አንድ ላይ ለማምጣት የመሪነት ቦታውን በመያዝ የሞኖሮቪያን ቡድን ስብሰባ ለመሳተፍ አቶ ከተማ ወደ ሌጎስ አመሩ። አመራሮቹን አዲስ አበባ በሚካሄደው ጉባኤ እንዲመጡ፤ በኋላም ንጉሡንም አሳምነው ለመሪዎቹ ምስጋና እንዲያቀርቡ ያደረጉ ሲሆን ንጉሡም “ እኛ ከሞኖሮቪያም ሆነ ከካዛብላንካ አይደለንም። ከአፍሪካ ጋር ነን የሚል” ታሪካዊ ንግግራቸውን አደረጉ።

በተለይም በወቅቱ የሀሳቡ አመንጪና ከረር ያለ አቋም የነበራቸውን የጋናውን መሪ የነንክሩማህን ቡድን ማምጣት ቀላል እንዳልነበር ከተማ ይናገሩ እንደነበር ልጃቸው መኮንን ይገልፃል። በተለይም ጉዳዩን አወዛጋቢ ያደረገው በወቅቱ የሞኖሮቪያ አባል የነበሩት የቶጎው መሪ መገደል ያኛውን ቡድን መወንጀልና ሁኔታዎችም መካረር ጀመሩ። ነገሮችንም ለማለሳለስ ብዙ ጥረት ተደረገ።

ከዚህም ውስጥ ሌላኛውን የካዛብላንካ ቡድን አባል የነበሩትንም የጊኒውን መሪ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬንም ወደ አስመራ በመጋበዝ ከንጉሡ ጋር እንዲነጋገሩ ተደረገ። ኢትዮጵያና ጊኒ በመከፋፈል

 አያምኑም የሚል መግለጫም በጋራ አወጡ። መሪዎቹን አስማምቶ ማምጣት በጣም የከበደ ሥራ እንደነበር የሚናገረው መኮንን በብዙ አጋጣሚዎችም አባቱ ከተማ የዲፕሎማሲ ክህሎታቸውን በመጠቀም ነገሮችን እንዳሳኩ ያስታውሳል።

ከተማ በየሀገራቱ ሲዞሩ “ወደ ሀገሬ ምንም ሳልይዝ አልሄድም፤ ንጉሡ አያስገቡኝም” የሚሉ ማባበያዎችን ይጠቀሙ እንደነበር የሚናገረው መኮንን፤ ከተማ የቱኒዚያውን ፕሬዚዳንት ያግባቡበትን መንገድ ለይቶ ይጠቅሳል። ፕሬዚዳንቱ የሁለቱ ቡድኖች የጋራ አቋም ሳይኖር እንዴት አንድ ላይ እንሰበሰባለን የሚል የእምቢታ ምላሽ ሲሰጧቸው በምላሹም “አፄ ኃይለሥላሴ ያለርስዎ ይህ ስብሰባ አይካሄድም” እንዳሏቸው ይናገራል።

በወቅቱ አፄ ኃይለሥላሴ የነበራቸው ቦታ ከፍተኛ ስለነበርም የቱኒዚያው ፕሬዚዳንት እሺ ብለው መጡ። ያ ታሪካዊ ስብሰባ ሊደረግም በቃ፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ተበሰረ። ነገር ግን ሒደቱ ቀላል አልነበረም። ሁለት የተለያዩ እሳቤዎችን ይዘው የመጡ ቡድኖችን አንድ ላይ መምጣት ቀላል አልነበረም፤ የተወሰኑ አለመግባባቶች ቢፈጠሩም የነበረው ድባብ በጣም የተለየ እንደነበር አቶ ከተማ ለልጃቸው ለመኮንን ነግረውታል። “እንዲህ አይነት ስሜት አፍሪካ ውስጥ ተፈጥሮ አያውቅም” ብለው አባቱ አጋጣሚውን ገልፀውለታል።

በመቀጠልም የአፍሪካ ፖሊሲዎችን ማርቀቅ፣ የድርጅቱ ፀሐፊ እንዲሁም ዋና ጽሕፈት ቤት የት ይሁኑ የሚሉ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ነበሩ። በከተማ አመራርነት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሁለቱን አንጃዎች ፖሊሲና ሌሎች ሀሳቦችን ጨምረው አቀረቡ፤ ፖሊሲዎቹ ላይ አንዳንድ አለመስማማቶች ቢፈጠሩም ሰነዱ ተፈረመ።

ከተማ ሥራቸው አላለቀም ለኢትዮጵያ የነበረው ጥሩ ስሜት እያለ ኢትዮጵያ የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት መቀመጫ ትሁን የሚል ሀሳብ አቀረቡ። በፍጥነት ከአመራሩ “አይቻልም” የሚል ምላሽ ተሰጣቸው። ምክንያቱ ደግሞ “ከተማ የራሱን ዝናና ስም እየገነባ ነው፤ “ብለው ንጉሡን የሚመክሩ ስለነበሩ እንደሆነ መኮንን ይናገራል። የተፈራው አልቀረም ትንሽ ቆይቶም ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሀገራት የድርጅቱ መቀመጫ ዳካር እንድትሆን መስማማታቸው ተሰማ።

ኢትዮጵያ ድርጅቱን ለመመሥረት ይህንን ያህል ለፍታ አመድ አፋሽ መሆኗ ንጉሡን አስደነገጣቸው። ከሴኔጋል ሌላም ናይጄሪያ ያላትን ትልቅነት ተጠቅማ እዚህ መሆን አለበት የሚል ክርክርም ጀምራ ነበር። የሃገራቱ እሰጣገባ ብቻ ሳይሆን “ኢትዮጵያን አትምረጡ” የሚል ቴሌግራም እየተሰራጨ እንደነበር የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለከተማ አሳዩዋቸው። “ኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ግጭት እያለ ሚኒስትሩ ያንን ማድረጋቸው ለአባቴ በሕይወቱ ሙሉ የሚያስደንቀው ጉዳይ ነበር። ቢጋጩም የሶማሊያ ድጋፏ ለኢትዮጵያ ነበር” ይላል ልጃቸው መኮንን።

በመቀጠልም ኢትዮጵያ እንድትመረጥ የማግባባቱ ሥራ /ዘመቻ/ ተጀመረ። በተለይም ለጊኒ እናንተ ኢትዮጵያን መቀመጫ ካደረጋችሁ የጸሐፊውን ቦታ እንሰጣችኋለን የሚል ሃሳብን እንዳቀረበ መኮንን ይናገራል። በመጨረሻም ከናይጄሪያ በስተቀር ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ እንድትሆን ሀገራቱ ድምፃቸውን ሰጡ። “ብዙዎች እንደሚሉት በአፄ ኃይለሥላሴ ምክንያት አይደለም አዲስ አበባ የተመረጠችው፤ ከብዙ ማግባባት፣ ክርክርና ፍጭቶች በኋላ ነው የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት አዲስ አበባ ሊሆን የቻለችው።”

ለዘመናት በተለያዩ መድረኮች ላይ ኢትዮጵያን የወከሉት አቶ ከተማ የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት በተለያዩ ኃላፊነት አገልግለዋል። የትምህርት ጉዟቸው ሀ ብሎ የተጀመረው ኬንያ ነበር። ምክንያቱም ጣሊያን ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር በሰባት ዓመታቸው ወደ ጅቡቲ ለመሰደድ ተገደዱ።

ትንሽ ጊዜ ጅቡቲ ቆይተውም ጉዟቸውን ከአጎታቸው ጋር ወደ ኬንያ አደረጉ። በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር በነበረችው ኬንያም ስደተኞች ከሀገሬው ተማሪ ጋር አብሮ መማር ስለማይቻል ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች ተብሎ በተከፈተውና በቢትወደድ ዘውዴ ገብረ ሕይወት ኃላፊነት በሚመራው ትምህርት ቤት ትምህርት ጀመሩ። ኢትዮጵያ ነፃነቷን ስትቀዳጅ ደግሞ ወደ ጋራ ሙለታ ተመለሱ።

ያኔም ትምህርታቸውን የመቀጠል ፅኑ ፍላጎት እንደነበራቸው መኮንን ይናገራል። ለዚህ ደግሞ የአጋጣሚ በር ተከፈተላቸው። ንጉሡ የተለያዩ አካባቢዎችን በሚጎበኙበት ወቅት ጋራ ሙለታን ሲጎበኙ በአካባቢው ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆች አሉ ምን ይደረግ? ብለው ሲጠየቁ አዲስ አበባ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምጣት እንደሚችሉ ምላሽ ተሰጣቸው። መኮንን እንደሚናገረው አዲስ አበባ ሄደው ወዲያው ትምህርት ቤት የሚገቡ መስሏቸው የነበረ ቢሆንም ሲደርሱ አናስገባም የሚል ምላሽ ተሰጣቸው። የሚያድሩበትም ሆነ የሚበሉት አልነበራቸውም፤ በጊዜው “ሰው ለሰው አዛኝ በመሆኑ” ይላል በአካባቢው የነበሩ ወታደሮች መጠጊያ ሆኗቸው። ሥራም እየሠሩ ትንሽ ከቆዩ በኋላ ነገሩ በወቅቱ የጦር ሠራዊት ኃላፊ ለነበሩት ጄኔራል መርዕድ መንገሻ በመነገሩ በሳቸው ምክንያት ትምህርታቸውን ሊጀምር እንደቻሉ ይናገራል።

የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የመኳንንትና የሹማምንት ልጆች በመሆናቸው ከፍተኛ ልዩነት ይታይበት የነበረ ሲሆን አባቱ የነገሩትንም መኮንን እንዲህ ያስታውሰዋል። “ንጉሡ በየጊዜው እየመጡ ተማሪዎቹን ይጎበኛሉ። መምህሩም ስም በሚጠራበት ወቅት ከስማቸው ፊት ደጃዝማች፣ ልዑል እንዲሁም ሌሎች ሹመቶች ነበሩ። ጃንሆይም ልጆቹ በእኩልነትና ያለምንም ተፅዕኖ ትምህርታቸውን እንዲማሩ ቅጥያው እንዲሰረዝ አዘዙ” ይላል።

በመቀጠልም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ሚቺጋን ሆፕ ኮሌጅ ፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ለማጥናት ያቀኑ ሲሆን፤ የማስተርስ ዲግሪያቸውንም በቦስተን ዩኒቨርስቲ በተመሳሳይ ትምህርት ተመርቀዋል። አሜሪካ ሲደርሱ ከፍተኛ ዘረኝነት ያጋጠማቸው ሲሆን፤ “ውሾችና ጥቁሮች አይፈቀድም” የሚሉ መልዕክቶች እንዲሁም የነበረው የዘረኝነት ሁኔታ አፍሪካዊነታቸውን ብቻ ሳይሆን የፓን አፍሪካዊነት ፅንሰ ሀሳባቸውንም በከፍተኛ ሁኔታ ያሳደገው ነገር እንደሆነ መኮንን ይናገራል። ምንም እንኳን የፒኤችዲ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ቢጠየቁም ቤተሰቤን እረዳለሁ ብለው ተመለሱ። ከዚያም ሀገራቸውን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነትና በተለያዩ ኃላፊነቶች አገለገሉ።

ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከዙፋናቸው ተወግደው ዓመታት ካለፉ በኋላ አምባሳደር ከተማ « … የአፍሪካ የመጀመሪያዎቹ መሪዎች ትልቁ ችግር … በእኛም ላይ ደረሰ፡፡ መሪዎች በሥልጣን ላይ በሚቆዩበት ጊዜ ተተኪውን ሥርዓትና ሰው ሳያዘጋጁ ጊዜው ይደርስና ሀገራቱ ስጋት ላይ ይወድቃሉ፡፡ የዴሞክራሲን መርሆች መከተል ሲቻል፣ ሥልጣን የሰፊው ሕዝብ መሆኑ ሲታወቅና ሕዝብም መብቶቹን እያወቀ ሲሄድ ነው ወደ ሌላ መንግሥት በጤና መዛወር የምንችለው…» ብለው ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ንጉሠ ነገሥቱ የአምባሳደር ከተማን ምክር ከመስማት ይልቅ አምባሳደር ከተማን ከውጭ ጉዳይ ወደ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ቱሪዝም ሚኒስትርነት አዛወሯቸው። አምባሳደር ከተማ የገመቱት አልቀረም … ከደብዳቤው ሦስት ዓመታት በኋላ የ1966ቱ አብዮት መጥቶ ንጉሠ ነገሥቱን በላቸው፡፡

ወታደራዊው መንግሥት ሥልጣን ሲይዝ አምባሳደር ከተማ ታሰሩ፡፡ ከስምንት ዓመታት እስራት በኋላ ተፈቱ፡፡ ከዚያም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር፣ የአፍሪካ ቀጣና ልዩ አማካሪና ተወካይ ሆነው አገልግለዋል፡፡ አምባሳደር ከተማ በ1952 ዓ.ም ከወይዘሮ ራሔል ስነ ጊዮርጊስ ጋር ጋብቻ መስርተው አራት ልጆችን አፍርተዋል።

ወይዘሮ ራሔል ስለባለቤታቸው ባሕርይ ሲናገሩ ‹‹ … ከሁሉም ሰው መግባባት የሚያስችል ተፈጥሮ ያለው ሰው ነበር …›› ይላሉ፡፡ ልጃቸው አቶ መኮንን ከተማ ይፍሩ በበኩሉ ‹‹ … አባቴ የነበረበትን ማንነቱን አይረሳም፡፡ በሰው እኩልነት ያምናል …›› ብሏል፡፡አምባሳደር ከተማ እጅግ ደማቅ ለሆኑት አኩሪ ተግባሮቻቸው የኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ አገራትን (የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የሶቪየት ኅብረት፣ የኢጣሊያ፣ የዩጎዝላቪያ፣ የሴኔጋል፣ የኬንያ፣ የናይጀሪያ፣ የጋና፣ የዛየር፣ የግብፅ፣ የብራዚል፣ የሜክሲኮ፣ የካናዳ፣ የጃፓን የኢንዶኔዥያ …) ኒሻኖችን ተሸልመዋል፡፡

አንጋፋ ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገራት ዲፕሎማቶችም ስለአምባሳደር ከተማ አስደናቂ ተግባራት በተደጋጋሚ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። «… ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴና አቶ ከተማ ይፍሩ በሁለቱ ጎራ ተሰልፈው የነበሩ መሪዎችን በማግባባት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እውን እንዲሆን አድርገዋል …» የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ

«… አቶ ከተማ ይፍሩን ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ታሪክ መለየት አይቻልም፡፡ በጣም ብዙ ደክመዋል። የአፍሪካ መሪዎች በጃንሆይ ሰብሳቢነት ሲሰባሰቡ ጀምሮ መሪዎችን በማነጋገርና በማግባባት ከፍተኛ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ የሞኖሮቪያና የካዛብላንካ ቡድኖች ተፈጥረው የሃሳብ ልዩነት በነበረበት ወቅት አምባሳደር ከተማ በየሀገራቱ እየዞሩ ከመከፋፈል ይልቅ አንድነት እንደሚሻልና የቡድኖቹን ሃሳቦች በውይይት መፍታት እንደሚቻል ያስረዱ ነበር፡፡

በጣም ወደ ግራ ያዘነበሉ የአፍሪካ መሪዎችንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን በማግባባት ያበረከቱት አስተዋፅዖ እጅግ ከፍተኛ ነበር ።» አንጋፋው ጋዜጠኛ፣ የታሪክ ጸሐፊና ዲፕሎማት አምባሳደር ዘውዴ ረታ«… አምባሳደር ከተማ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ «ብሔራዊ ጥቅምን ያስከበረና ገለልተኛ የሆነ» እንዲሆን ብዙ ጥረት አድርገዋል … ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መካከል የአፍሪካ የነፃነት ታጋዮችን በመደገፍና ወደ ነፃነት የሚያደርሱ መንገዶችን በማመቻቸት እንደአምባሳደር ከተማ ይፍሩ ታላላቅ ተግባራትን ያከናወነ ሰው የለም …» የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትርና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አያሌው ማንደፍሮ፤ አምባሳደር ከተማ ጥር 6 ቀን 1986 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

በኑዛዜያቸውም የሚከተለውን መልዕክት አስቀምጠው አልፈዋል …«በራሴ በኩል አገሬን በንጹሕ ልቦና አቅሜና የጊዜው ሁኔታ በሚፈቅደው መጠን ከማገልገል በስተቀር የፈፀምኩት ወይም ያደረስኩት አንዳችም በደል ያለመኖሩን ስለማምንና ስለማውቅ ምንጊዜም ቢሆን ሕሊናዬ ፍጹም ንጹሕ ነው። የፈፀምኩት በደል ቢኖር ከተራ ገበሬ ቤተሰብ ተወልጄ በችሎታዬና በድካሜ ተወዳድሬ በቁጥር አነስተኛ በሆኑ ክፍሎች በሞኖፖል ተይዞ ለነበረው ከፍተኛ የሥራ ቦታ ራሴን ብቁ አድርጌ መገኘቴ ብቻ ነው፡፡

የእኔ ወንጀል ኢትዮጵያ ሀገሬ በሰጠችኝ ዕድል ተጠቅሜ የእኔ ብጤ፣ ከድሃ ቤተሰብ የሚወለድ ዕድሉ ከተሰጠው ከማንም የማያንስ መሆኑን በሥራ ማስመስከሬ ብቻ ነው፡፡ ሥራ ላይ በነበርኩበት ዘመን በተለይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበርኩበት ጊዜ የፈጸምኳቸው ሥራዎች በተለይ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረትና ዋናው መሥሪያ ቤት አዲስ አበባ ላይ እንዲሆን ያደረግሁት ለኔ ምንጊዜም የሚያንጸባርቅና ሐውልት ስለሆነ ለባለቤቴንም ለልጆቼም የሚያኮራቸው ነው፡፡»

ከኢትዮጵያ አልፈው ለአፍሪካ ጭምር ኩራትና ባለውለታ ለሆኑት ለአምባሳደር ከተማ ይፍሩ ስም መታወሻ የሚሆን ተግባር ኢትዮጵያ ውስጥ አለመከናወኑ ብዙዎችን አስገርሟል፤ አሳዝኗልም ይሉናል፤ “ከተማ ይፍሩ – የተዘነጋው ታላቁ የአፍሪካ ኅብረት ኩራትና ባለውለታ!!!” በሚል ርዕስ ከአራት ዓመት በፊት “አዲስ ዘመን”ጋዜጣ ላይ ያስነበቡን አንተነህ ቸሬ የተባሉ ጸሐፊ፡፡

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን)

fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ጥር 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You