ከጥሪው ባሻገር …

ለኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ የሕልውናቸው መሠረት ናት። እሷ ወድቃ እነርሱ አይቆሙም። እሷ እያዘነች እነሱ አይደሰቱምም። እሷን ረስተው እነርሱ አይታወሱም። እሷ ከሌለች የእነርሱ በሕይወት መቆየት ትርጉም አልባ ነው። የሚኖሩት በእሷ ተከብሮ መቆየት ውስጥ ነው። እሷ ሰላሟን አጥታ ሕሊናቸው አትረጋጋም፡፡ ኢትዮጵያ ጎድሎባት እነርሱ አይሞላላቸውም፡፡

እሷ ዝቅ ብላ እነርሱ አይገዝፉም፡፡ ያለ ኢትዮጵያ የሚበሉት አይጣፍጣቸውም፡፡ የሚጠጡት አያረካቸውም። ልባቸውን እንጂ ጀርባቸው አይሰጧትም፡፡ እድገቷን እንጂ ዝቅታዋን፣ ደስታዋን እንጂ ኀዘኗን፣ ክብራን እንጂ ውርደቷን ፈፅሞ አይመኙም፡፡

ሀገር ውስጥ እንዳለው ሁሉ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊም ከምንም በላይ የሀገራቸውን ፍቅር በልባቸው ይዘው የሚኳትንና በአካል ቢርቁም በመንፈስ ሁሌም ሀገራቸው ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ሀገራቸውን የሚወድ፣ ሀገራቸው ተሻሽላና አድጋ መመልከትን የሚፈልግ፣ ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትኖር ከልብ የሚመኙና ለዚያም የሚታገሉ ናቸው።

ይሁንና የኢትዮጵያ ሕዝብ ተለያይቶ እንዲያስብና ተግባብቶ እንዳይኖር ፅኑ ፍላጎት ያላቸው መንደርተኞች አሉ፡፡ የፍላጎታቸውም የሚመኙትን ሥልጣን ለመቆናጠጥ የሕዝብ ማሰቢያ ላይ የበላይነትና የበታችነት ወላፈን በመዝራት ስሜት በማነሳሳት ንዴት ማስታጠቅና እንዳሻቸው ሕዝቡን እየዘረፉ ሀብት ማከማቸት ነው።

በጎሳና በጎጥ ተደራጅተው በሀገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች ፀብ በመዝራት ጥላቻን በመስበክ ማበጣበጥና የሕዝቡን ሠላም የሚያደፈርሱ ዛሬም መንደራዊ ሹማምንቶች፣ የሀገሬውን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ዲያስፖራውንም ከእናት ሀገሩ ለማፋታት ሌት ተቀን የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ በተደጋጋሚ ታዝበናል፡፡

ይሁንና ዲያስፖራው የዙፋን ጥማታቸውን ለማርካት ፀብን እየዘሩ ጥላቻን እያጎረሱ በሚኖሩ መንደርተኞች እንቶ ፈንቶ ተረብሾ ጨለማ ውስጥ መዳከር ምርጫው እንዳልሆነ እያስመሰከረ ይገኛል። ከምክንያታዊነት ይልቅ ለስሜታዊነት የተጋለጡ ጥቂቶች እንዳሉ ሆነው አብዛኛው ዲያስፖራ አንድ ከማድረግ ይልቅ የሚነጣጥል፤ መሰብሰብን ትቶ የሚበትን፣ ከማዋሓድ ይልቅ የሚለያይ አስተሳሰብን ማራመድ ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌለው ጠንቅቆ በመረዳት ሀገሩን ከፈተና ወደ ልዕልና ከፍ ለማድረግ ከሁሉም በላይ በሀገር ባለቤትነት ስሜት እጅ ለእጅ በመያያዝ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡

በተለይ ከለውጡ ወዲህ ዲያስፖራው የለውጥና የሀገር ባለቤትነት ስሜቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ በመላው ዓለም የሚገኙ ዲያስፖራዎች ለእናት ሀገራችን ለኢትዮጵያ አናንስም፣ ባለን ሁሉ እንቆምላታለን ብለው ሲነሱም ታይተዋል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ላይ የተከፈቱ ሴራዎችን ለመቀልበስ ዓለም እውነቱን እንዲረዳ ድምፃቸውን በማሰማት ረገድ ታላቅ ገድልን መፈፀማቸው መቼም የማይዘነጋ ነው፡፡

ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኮች በመወከል የሀገራቸውን መብትና ጥቅም ከመከላከልና ከማስከበር ባለፈ በሀገር ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን ለማቃለል የሚችሉና በጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ናቸው፡፡ ሀገር ግጭት ውስጥ በቆየችባቸው ጊዜያት ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለተፈናቀሉ ወገኖች ለመደገፍና በተለይ ‹‹በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል›› ለተባለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ያደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ለዚህ ምስክር የሚሆን ነው፡፡

መንግሥትም ለዚህ የዲያስፖራው ሁለንተናዊ አስተዋፅዖ ክብርና አድናቆቱን ከመግለፅ ባለፈ ከጋራ ሀገር እድገት ከዲያስፖራው ጋር ይበልጥ ለመቀራረብ የተለያዩ ጥሪዎችን ሲያቀርብ መቆየቱም የሚታወስ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) በ2014 ዓ.ም “የአንድ ሚሊዮን ዲያስፖራ የሀገር ቤት ጥሪ” እና “ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሀገር ቤት ጥሪ” ማድረጋቸውን ተከትሎም በርካቶች ወደ ሀገሪቱ መምጣታቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡

የዚሁ ምዕራፍ ቀጣይ በሆነ መልኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታኅሣሥ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሁለተኛው ትውልድ ዲያስፖራ ወደ ሀገር ቤት እንደሚመጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። ይህ የሁለተኛው ትውልድ ዲያስፖራ ጥሪ ዲያስፖራው ሀገሩን በማወቅና ከማንነቱ ጋር በመተሳሰር በሀገሩ ጉዳይ ላይ እንዲሳተፍ የማድረግ ዓላማን ያነገበ የሁለተኛው ትውልድ ዲያስፖራ ጥሪ ዓላማ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው ተፈጥሮ ታሪክና ባሕል በማወቅ ከሕዝባቸው ጋር ያለውን ትስስር የማጠናከርና በቀጣይ በሀገራቸው ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የማድረግ ዓላማ ያለው ነው ።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ መሠረት “Back to your Origin” በሚል መሪ ሀሳብ የዲያስፖራ አባላቱ ከታኅሣሥ 20 ቀን 2016 እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም በሦስት ዙር ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ሥራውን የሚያስተባብር ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ የተለያዩ ሥራዎችን በመከናወን ላይ መሆናቸው ታውቃል፡፡

የመጀመሪያ ዙር ከታኅሣሥ 20 እስከ ጥር 20/2016 ዓ.ም. ድረስ የሚቆይ ሲሆን ‘Connect to your culture’ በሚል መሪ ሃሳብ ይከናወናል። በዚህ ሁነት ዲያስፖራዎቹ ባሕላቸውን እንዲያውቁና እንዲያስታውሱ የሚያስችላቸው መርሐ ግብሮች ተዘጋጅቷል፡፡

ሁለተኛው ዙር ደግሞ ‘Connect to your his­tory’ በሚል መሪ ሀሳብ በየካቲት ወር 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ጀምሮ እስከ ክረምት መግቢያ የሚካሄድ ነው። ይህ ዝግጅት የዲያስፖራ አባላቱ በባሕል፣ በቋንቋ እና በሃይማኖት ያሉ ታሪኮችን እንዲያውቁ ማስቻልን ግቡ አድርጓል።

ሦስተኛው ዙር ደግሞ ‘Leave your legacy’ በሚል ከ2016 ዓ.ም የክረምት መግቢያ ጀምሮ እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም ይከናወናል። በዚህኛው ዙር ሕጻናትን ማስተማር፣ ችግኝ መትከልና ሌሎች ሰፋፊ የበጎ ፈቃድ ተግባራት በማከናወን በሀገራቸው አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ማድረግን ዋንኛ ዓላማ አድርጓል።

በአሁን ወቅትም ጥሪውን ተቀብለው በመላው ዓለም የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል፡፡ በመግባትም ላይ ናቸው፡፡ ከኤርፖርት አንስቶ ለዲያስፖራው ጥሩ አቀባበልና መስተንግዶ እየተደረገና እየተሰጠ ስለመሆኑም ተመልክተናል፡፡

ወቅቱ የበዓል ሰሞን ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ከፍተኛ የቱሪስት ፍስት የሚስተዋልበት እንደመሆኑም በተለይ ዲያስፖራው የሚሳተፍባቸው የተለያዩ ፓኬጆችና መስተጋብሮች ተመቻችተዋል። እነዚህ ሁነቶቹም ዲያስፖራው ሀገሩ፣ እምነት፣ ባሕሉን ይበልጥ እንዲያውቅ፣ እንዲወድና እንዲያጣጥም ከማድረግ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ አበርክቷቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በተለይ የቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ይታመናል፡፡

እንደሚታወቀው፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኢትዮጵያ መንግሥት የቱሪዝም ዘርፉ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ለማድረግ የመዳረሻ ስፍራዎች በማልማት፣ በማስተዋወቅ፣ ጎብኚዎችን በመሳብና አዳዲስ መዳረሻዎችን በመፍጠር ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ብርቱ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

የሀገሪቱን የቱሪስት መዳረሻነት ለማሳደግ እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባራት መካከል የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ይገኝበታል። በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ቀደም ሲል ትኩረት ያልተሰጣቸው ቦታዎችን በመምረጥም የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ነው፡፡ በዚህም ትኩረት ተነፍጎት የቆየው የሀገሪቷን የተፈጥሮ ቱሪዝም ሀብት የማልማት ሥራ በጎርጎራ፣ በኮይሻና በወንጪ አካባቢዎች በመከናወን ላይ ይገኛል።

የእነዚህ እና ሌሎች ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ታዲያ የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ አቅም ይበልጥ በማጎልበት ከዘርፉ የሚገኘውንም ጥቅም ከፍ ለማድረግ ሁለንተናዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑ የሚያከራክር አይሆንም፡፡ ወደ ሀገሩ ለመጣው ዲያስፖራ ማኅበረሰብ ተጨማሪ የጉብኝት አማራጭ እንደሚሆኑም አይጠራጥርም፡፡

ይሁንና የአገሪቱ የቱሪዝም ተስፋ እንዲሰምር የመዳረሻ ስፍራዎች በማልማት፣ በማስተዋወቅ፣ ጎብኚዎችን በመሳብና አዳዲስ መዳረሻዎችን ከመፍጠር ባሻገር የዘርፉን እንቅስቃሴ ሠላማዊ መንገድ ላይ ማራመድ የግድ እንደሚል መዘንጋት አያስፈልግም። የዲያስፖራውን ጥሪውን ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት በመትመሙ ምክንያት ዓይናቸውን የሚቀላ አይጠፉም በዚህ ረገድም ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረግ ይገባል፡፡

ኢትዮጵያም ይህን ወርቃማ እድል በአግባቡ ልትጠቀምበት ይገባል፡፡ የዲያስፖራውን አቅም በአግባቡ ለመጠቀም ትኩረት የሚሹና ቀደም ሲል ግልፅ ድክመት ሆነው የሚስተዋሉ ጉዳዮችን በመለየት ለመፍትሔው አስቀድሞ መሥራት የግድ ነው፡፡

ከሁሉ በላይ ዲያስፖራው ገንዘቡን፣ ዕውቀቱንና ልምዱን አቀናጅቶ ሀገሩን የሚደግፍበት መደላድል እንዲፈጠር፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከወትሮው በተለይ ተገቢውን ክብካቤና ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይም አገልግሎት አሰጣጣቸውን ይበልጥ ማቀላጠፍ ይጠበቅባቸዋል።

በተለይም ዲያስፖራው በሚወዳት ሀገሩ መዋዕለ ንዋዩን ፈሰስ ለማድረግ በሚፈልግበት ጊዜ እንቅፋቶች ሳይገጥሙት፣ በተቀላጠፈ መልኩ ለሚጠይቀው ጥያቄና ለሚፈልገውም ምቹ አማራጭና ከባቢን ፈጣን ምላሽ መስጠት ተገቢ ነው፡፡

ዲያስፖራው ኢትዮጵያ ውስጥ መሠረቱ የማይነቃነቅ አሻራ እንዲያሳርፉ በሀገሪቱ ምን አይነት አቅምና አማራጭ አለ የሚለው ታሳቢ ባደረገ መልኩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ ረገድ ሰፊ ሥራዎችን መሥራትም ግድ ይላል፡፡ የኢንቨስትመንት ፎረም ማካሄድ ይገባል፡፡

ከዚህ ባሻገር ልዩ ትኩረት ሊሠጠው የሚገባ የቤት ሥራም አለ፡፡ ይህም የጥቁር ገበያ ነው። መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ወደ ኢትዮጵያ በመደበኛ መልክ እየገባ ያለው ገንዘብ በጣም በዝቅተኛ መጠን ነው። ከአንድ ሦስተኛው የማይበልጥ ነው፡፡ የዚህ አንደኛ እና ዋነኛ ምክንያት ጥቁር ገበያ ወይንም ብላክ ማርኬት ነው፡፡

ኢትዮጵያም ጥቁሩን ሰንሰለት መበጠስ አለመቻሏ የዲያስፖራ ልጆችን አቅም መጠቀም ከልክሏታል። ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ገቢ አሳጥቷታል። ለአብነት ከግብፅና ከናይጄሪያ ገቢ አንፃር ብንመለከተው አንድ አራተኛ እንኳን አይሞላም። ሀገሪቱ ጥቁሩን ሰንሰለት መበጠስ ብትችል እስከ 12 ቢሊየን ዶላር ማግኘት እንደሚቻላትም ጥናቶች ይመሰክራሉ፡፡፡

በእርግጥ ይህ ችግር በተለያዩ መድረኮች ይነሳል። ይሁንና መፍትሔ በመስጠት ረገድ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ማከናውን የአጭርና የረጅም ጊዜ መፍትሔ ማስቀመጥም የግድ ይላል፡፡ በተለይም ከአጭር ጊዜ አንፃር ዲያስፖራውም ሆነ ባንኮች ከባድ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይሰማኛል፡፡

እንደሚታወቀው በርካታ ሀገራት የተቀየሩት ለእድገት የበቁት ዲያስፖራዎቻቸው በከፈሉት ዋጋ ነው፡፡ በመሆኑም ዲያስፖራው በተለይ በአሁን ወቅት ዋጋ በመክፈል ገበያው እስኪረጋጋ ልዩነቱን በመተው በባለቤትነት፣ በኃላፊነት፣ ዋጋ በመክፈልና ‹‹ለሀገሬ ነው የማደርገው›› በሚል ስሜት በመደበኛው መንገድ ብቻ ገንዘቡን መላክ ይኖርበታል፡፡

የፋይናንስ ተቋማትም ዲያስፖራው ገንዘብ በሚልክበት ወቅት በአነስተኛ የአገልግሎት ክፍያ አማራጭን ማስተዋወቅና የመላኪያው ወጪ የሚጋሩበት ሁኔታ ማሰብ እንዲሁም በመደበኛ መልኩ የሚልኩ ዲያስፖራዎችን ማበረታታት ፍቱን አማራጭ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው ነው። ሽልማት መስጠትና የእውቅና መርሐ ግብሮችን ማዘጋጀት የግድ ይላል። ይህ በማድረግ ተጨማሪ የውጭ ምንዛበ ማግኘት ይችላል፡፡ ከረጅም ጊዜ መፍትሔነት አንፃር ጥቁር እና ነጭ የሚባል ገበያ ስለማጥፋት መሥራት ተገቢ ይሆናል፡፡ ከጥሪው ባሻገር እነዚህ ዐበይት ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ጥር 4/2016

Recommended For You