የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት

‹ከአፍሪካ መዲናነት እስከ ዓለም መድረክ› በሚል መሪ ሀሳብ ከጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ ጥር 24 ድረስ በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀው የኢትዮጵያ የዲፕሊማሲ ሳምንት ኢግዚቢሽን ሀገራችንን ለውጪው ማህበረሰብ ከመግለጥና ቀጣይ የተግባቦት አቅጣጫዎችን ከመትለም አኳያ ላቅ ያለ ፋይዳ ያለው ነው።

ለሀያ ሁለት ቀናት ያክል ክፍት ሆኖ የሚቆየው አውደ ርዕይ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ሶስት አንኳር አላማዎችን እንዳነገበ ይነገራል። የመጀመሪያው ላለፉት በርካታ ዓመታት ያለፍንበትን የግንኙነት ሂደት የሚቃኝ ነው። ይሄ ማለት ከየት ተነስተን የት እንደደረስን፣ ባለፈው ጊዜ በነበረን የውጪ ሀገራት ግንኙነት ያተረፍነውን እንደ ውጤት የሚቀበል ኪሳራችንን ደግሞ እንደተግዳሮት የሚያጤን ነው። በመቀጠል አሁን ያለንበትን የዲፕሎማሲ ሂደት የሚገመግም ሆኖ እናገኘዋለን።

ሁለተኛው በአሁኑ ወቅት ከውጪ ሀገራት ጋር ያለን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ግንኙነት ምን እንደሚመስል፣ ትርፍና ኪሳራውን የምንገመግምበት ነው። ሶስተኛው ፤መጪውን በመቃኘት የምንደርስበትን የሚመለከት ነው። እኚህ የትናንት የዛሬና የነገ የዲፕሎማሲ ሂደቶች አሁን ባለችውና ወደፊት በምትፈጠረው ሀገራችን ላይ ያለውን አዎንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖ በአንክሮ እንድናይ እድል የሚሰጥ አውደ ርዕይ ነው።

የዲፕሎማሲ ሳምንቱ የሀገሪቱን ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የስኬት አቅጣጫ በማሳየት ብርቱ ፋይዳ እንደሚኖረው ይታመናል። በተግባቦቱ ዘርፍ የነበረንንና ያለንን ወደፊትም የሚኖረንን የሰጥቶ መቀበል ጉርብትና ጨምሮ ካለፈው መማርን በማካተት አዲስ ንቃትን እንደሚፈጥር ሰሞኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳምንቱን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ጠቁሟል።

የነበሩ ስኬቶችን እና ተግዳሮቶችን ነቅሶ በማውጣት ለቀጣዩ ግስጋሴ መንገድ የሚጠርግ እንደሚሆንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ቡርቱካን አያኖ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት ቃለ መጠይቅ አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከራሷ አልፎ ለጥቁር ህዝቦች ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል› ያሉት ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ናቸው።

ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ስሟን በወርቅ ቀለም ከጻፈችባቸው አጋጣሚዎች ውስጥ የዲፕሎማሲው ዘርፍ አንዱ ነው። ከራሳችን አልፈን ለሌሎች በተረፈ የተግባቦት ሂደት ውስጥ አልፈን ሀገር እንዳጸናን ብዙ መረጃዎች አሉ። ከነበረን የመደማመጥ ልምድና የሉአላዊነት መሻት ለመላው ጥቁር ህዝብ የነጻነት ችቦን ያበራን፣ አለም ባልሰለጠነችበት ዘመን በዲፕሎማሲው ወንዝ ተሻግረን ከሀያላኖች ጋር ለተግባቦት የተቀመጥን መሆናችን ለየትኛውም ማህበረሰብ የሚተረክ ጉዳይ አይደለም። ይሄ ስም ዛሬም ቀጥሎ ለትላልቅ ዓለም አቀፍ እድሎች መልስ ሲሰጥ እያየን ነው።

በስልጣኔና ቀድሞ በመንቃት ከአፍሪካ አልፎ ዓለምን ያነቃ የዝማኔና የእውቀት ባላባቶች ነበርን። ለዚህ ምስክር የሚሆኑን ከምሥራቅ አፍሪካ ኢጋድን፣ ከአፍሪካ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን፣ ከዓለም ደግሞ ሌግ ኦፍ ኔሽንን ጨምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን መስራች አባል ሀገራት መሆናችን ነው። የቅርብ ጊዜዎቹን እናስታውስ ካልን ደግሞ እንደብሪክስ ያሉ በጎ አጋጣሚዎችን መጥቀስ እንችላለን፡

እነዚህ ወንዝ ተሻጋሪ እድሎች በሌላ በምንም የመጡ ሳይሆኑ ከሌላው ዓለም ጋር በነበረን የመነጋገርና የመወዳጀት ከፍ ሲልም አብሮ የማደግ ተሳትፎ የመጡ ናቸው። የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንትም ይሄን እውነታ የሚዘክር፣ እውቅና የሚሰጥና የሚያበረታታ መድረክ ነው።

ከአፍሪካም ሆነ ከዓለም ግንባር ቀደም ገናና ስም ይዘን በነጻነትና በሉአላዊነት የምንጠራው ለመነጋገር ባለን ልምድና ይሁንታ መሆኑ ብዙም አጠያያቂ አይሆንም። የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ታሪክ ስናጠና ብዙ ዓመታትን ወደ ኋላ መሄድ ግድ ይለናል። ይሄ የታሪክ ትርክት በበጎ የምንነሳበት አንዱ ገድላችን ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተመሰረተ ጀምሮ ባሉት ጊዜአት ውስጥ እንኳን መቶ አስራ ስድስት (116) ስኬታማ የዲፕሎማሲ ዓመታትን አሳልፈናል። ይህ ትልቅ ስኬት ነው። ይህን ያህል ዓመት ውጤታማ የሆነ ዲፕሎማሲን መከወንና ከዓለም ሀገራት ጋር ሁለንታዊ ወዳጅነትን የፈጠረ ሀገር ማግኘት ቀላል አይደለም። ባለፉት አመታት በውጤታማነት የመጣንባቸው ቀጣናዊ፣ አፍሪካዊና ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ ሂደቶች ከእድልና ድላቸው በተጨማሪ ኢትዮጵያዊ ማንነትን የሚናገሩ ሀገራዊ በጎ አሻራዎች ናቸው።

እነዚህ ሂደቶች እንደሀገር የጨመሩልን መልካም ስም እንዳለ ሆኖ በተጨማሪም የአፍሪካ ቁንጮ አድርገውን ሰንብተዋል። የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ፣ አፍሪካዊ ችግሮች ላይ ያተኮሩ ወዘተ የመሳሰሉ አፍሪካን ወክለን በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የተሳተፍንባቸው ታላላቅ ኃላፊነቶች የዚህ ዲፕሎማሲ ውጤት አንዱ ማሳያ ነው።

በአፍሪካ ደረጃም በርካታ አዳዲስ ለውጦችን ማንሳት ይቻላል። በጸጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ተወካይ እንዲኖራት ለአፍሪካውያን ድምጽ በመሆን እስከመሟገት የደረሰ፣ ለምንም ነገር ሀያላኑን ደጅ የምንጠናበትን ልምድ ያስቀረ ‹ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ› በሚል አዲስ እና ተራማጅ አስተሳሰብ አዲስ ትውልድና አዲስ አህጉር የፈጠርንበት ክስተት ማንሳት ይቻላል። አስታራቂና ሸምጋይ ሆነን የገባንባቸው አፍሪካዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ከዚህ ጎን የሚጠቀሱ የተሰሚነት ድሎቻችን ናቸው።

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት እንደስሙ ስለኢትዮጵያ የሚወራበት የሚነገርበትና የሚሰማበት ሳምንት ነው። አሳታፊና መረጃ ሰጪ መሆኑ ደግሞ ለየት ያደርገዋል። የተለያዩ ምሁራንን፣ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች እና ጥሪ የተደረገላቸውን የሁለተኛ ትውልድ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን የጋበዘው መድረኩ በእውቀትና በመረጃ በሳይንሳዊ ትንታኔም ዳብሮ ቀጣይ ሂደቶችን እንደሚያስተካክል ይጠበቃል። አውደ ርእዩ ከወሬ ባለፈ ግልጽና ተጨባጭ በሆነ መልኩ እውነታውን ለሕዝብም ሆነ ለመላው ዓለም ከማስረዳት አኳያ የማይናቅ ሚና ይኖረዋል።

እንደሀገር በዲፕሎማሲው ዘርፍ መልስ የሚፈልጉ ትላልቅ ጉዳዮች አሉን። በቀጣይም ለሰነቅናቸውና ልንደርስባቸው ላቀድናቸው ግቦች በእውቀትና ልምድ የተደገፈ መሰል የግንኙነት መርሆች ያስፈልጉናል።

ይሄ እንዲሆን እንደ ‹የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት› ን የመሳሰሉ አስተማሪና አወያይ፣ አንቂና አበረታች መድረኮች ያስፈልጉናል። ሕዝብን ከመንግሥት ጋር መንግሥትንም ከሕዝብ ጋር የሚያቆራኙ ውህደት ፈጣሪ መድረኮች ለቀጣይ ስኬቶቻችን የአንበሳውን ድርሻ ወሳኝ ናቸው።

እንዳሳለፍነው ረጅም እና ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ጉዞ በዚህ ረገድ ብዙ ተሰርቷል ለማለት አያስደፍርም። ይሄ እንደድክመት ተወስዶ በቀጣይ እርማት የሚወሰድበት የቤት ስራችን ነው። በሀገራት የእርስ በእርስ ጉርብትና መቶ ዓመታትን የተሻገረ ሀገር እንደብሄራዊ ድል ታሪኩን ሊዘክርና ሊያከብር ይገባል። አልተጠቀምንበትም እንጂ ኢትዮጵያን ከሚገልጡና ከሚያስተዋውቁ ታሪክ ነጋሪ ሁነቶች ውስጥ የዲፕሎማሲ ታሪካችን አንዱ መሆን የሚችል ነበር።

ውጤታማ ዲፕሎማሲን መተግበር ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግና የጀርባ አጥንት ነው። በዲፕሎማሲ ያልበረታና ያልጎበዘ ሀገር በምንም ሊበረታ አይችልም። አሸናፊ ሆኖ መውጣት አይቻልም። እኛ ደግሞ ከመበርታትም አልፈን ማንም በሌለው የረጅም ታሪክ ውስጥ የምንጠራ አሸናፊዎች ነን።

ስልጣኔ ካልነበረበት ከዛ የደብዳቤና የመልዕክተኛ ዘመን ጀምሮ ሀገራችን ከውጪው ማህበረሰብ ጋር ስለሰላም፣ ስለልማት፣ ስለፖለቲካ፣ ስለግዛት አንድነት፣ ስለሉአላዊነት ትመክር ነበር። ይሄ ገናና ተግባርን ስምና ዛሬ ላይ ተሀድሶ አቅጣጫዎቻችንን ጠራጊ እንዲሆን ማድረግ የእኛ ፈንታ ነው።

‹የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት› ለዚህ እውነታ መልስ ሰጪ ነው። አውደ ርዕዩም መጪውን የሚያስቃኝ ከምንም በላይ ደግሞ ለቀጣይ ሂደቶቻችን አጽንኦት የሚሰጥ ነው። ከአዲስ ግንኙነት አኳያ የነበሩብንን አስተካክለን በአዲስ ሀይል እንድንነሳ ሙያዊ እገዛ የሚሰጠን ነው። ቀጣይነት ቢኖረውና በአፍሪካና በዓለም ሀገራት ዘንድ የነበረንን የእርስ በርስ ግንኙነት እንደምስክር ተጠቅመን ለቀጣይ ድሎቻችን እንደመወጣጫ ብንጠቀመው የተሻለ እድልን የሚፈጥር ነው።

‹ከአፍሪካ መዲናነት እስከ ዓለም መድረክ› የሚለው መሪ ሃሳብ ካሳለፍነው የዲፕሎማሲ ሂደት አንጻር በትክክልም ኢትዮጵያን የሚመጥን ሃሳብ ነው። ከአፍሪካ ተነስተን ዓለም አቀፋዊነትን የዋጀንበት የእርስ በርስ ግንኙነት አለን። እኚህ ታሪካዊ እርምጃዎቻችን እንደሀገር ዛሬ ላይ ለተፈጠሩብን ጫናዎችና መድሎዎች ምናልባትም እንደመፍትሄ ሆነው ሊጠቅሙን የሚችሉ ናቸው።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለአስር ለራቀ ዓመታት በብዙ የዲፕሎማሲ ሂደት ውስጥ ያለፈ ነው። ሰሞነኛው የባህር በር ጥያቄና መልስም የውጤታማ ዲፕሎማሲ አንዱ ማሳያ ነው። ይህን ስምምነቱን ተከትሎ በአንዳንድ ሀገራት ዘንድ የተፈጠሩ ብዥታዎችም በተመሳሳይ በዲፕሎማሲያዊ አካሄድ እንደሚጠሩ እርግጥ ነው።

ዲፕሎማሲ የሚለውን ቃል በአንድ ሌላ ቃል ብንተካው ‹ሰላማዊ ግንኙነት› የሚል ሆኖ እናገኛዋለን። የቃሉ ትርጓሜ በየትኛውም ሀገራዊ አውድ ውስጥ ጣልቃ የሚገባ ነው። ያለሰላማዊ ግንኙነት ልማትና እድገት የማይታሰብ ነው። ፖለቲካና ኢኮኖሚ፣ ሉአላዊነትና ራስገዝነት ዋጋ አይኖራቸውም። በአጠቃላይ ከህልውና ጉዳይ ጋር አስተሳስረን ልናየው የሚገባ እውነታ ነው። ዓለም ወደ አንድ መንደር እየመጣች ባለችበት በዚህ ዘመን አይደለም በቀደመው ዘመን የዲፕሎማሲ ዋጋ ምን ያክል እንደነበር አይተናል።

ከዚህ በመነሳት ለጉዳዩ አጽንኦት ሰጥተን ወደፊት መንቀሳቀሱ ዋጋ ያለው ይሆናል። ለጀመርናቸውም ሆኑ ወደፊት ለምንጀምራቸው ድህነት ማለፊያ የትንሳኤ ትልሞች ‹ከሌላው ጋር እንዴት መኖር እና እንዴት መወዳጀት› የሚሉት ጽንሰ ሀሳቦች ገዢ ሀቆች ሆነው ከፊት ይመጣሉ። በዚህ ረገድ የተሳካልን ሕዝቦች ነን። እድሎቻችንን ግን ከዚህም በላይ ልንጠቀምባቸው ይገባል።

አንድ ሀገር ከሌላው ዓለም ጋር ከምትተሳሰርበትና ጥቅሟን ከምታስከብርባቸው መንገዶች ውስጥ ቀዳሚው የዲፕሎማሲ አካሄድ ነው ስንል ራሱን የቻለ ህግና ሥርዓት አለው እያልን ነው። ይህ ህግና ሥርዓት ነው የራስ ጥቅምን ሳያስነኩ ሰጥቶ መቀበል የሚለውን መርህ እውነት የሚያደርገው። ጥቅምን በማስነካት ውስጥ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የለም። እስከዛሬ ጥቅማችንን አላስነካንም ወደፊትም አናስነካም።

ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ራስን ለሌሎች መግለጥና ሌሎችን ወደ ራስ ማቅረብ ከሚለው አገላለጽ ጋር ተጣጥሞ መሄድ የሚችል ነው። በዚህ ረገድ ሀገራችን ኢትዮጵያ እድለኛ ሀገር ናት ማለት ይቻላል። ዘመናትን ያስቆጠረ የመልካም ተግባቦት ስም ባለቤት ናት። ከአፍሪካ ቀድማ ከዓለም ሀገራት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተሳካለት ግንኙነት አድርጋለች። በሌሎች ዘርፎች ላይም ወዳጅነትን በመፍጠር ሰላም መር በሆነ እንቅስቃሴ ራሷን ጠቅማ ሌሎችን ስትጠቅም የኖረችበትን መቶ ዓመታትን ያስቆጠረ የዲፕሎማሲ ዝማኔ ማንሳት ይቻላል።

የአሁኑ የዲፕሎማሲ ሳምንትም የሄድንበትን ረጅም የተግባቦት ሂደት የሚያስቃኝ ቀጣይ አቅጣጫዎቻችንንም የሚጠቁም የኢትዮጵያ የንቃትና የብርታት ጉባኤ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ ውጪ በእንዴትም ብንገልጸው አቻ ትርጉም አናገኝለትም።

የነበሩንን ማስታወስ ያሉንን አጥብቀን እንድንይዝ እድል የሚሰጠን ነው። የነበሩንን መግለጥና ለተቀረው ዓለም ማሳየት ቀጣይ ተግዳሮቶቻችንን የሚቀንስ ለትውልዱም ተስፋን የሚሰጥ አካሄድ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት በብዙ ረገድ ዋጋ ያለው እንደሆነ መመስከር ይቻላል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሰል ሀገራዊ ዳናዎችን የሚገልጡ፣ ገጽታ የሚገነቡ የሩቅና የቅርብ ሁነቶችን ወደ ሕዝብ የሚያቀርብበትን መድረክ በቀጣይም ይበልጥ አጠናክሮ ሊቀጥልበት ይገባል።

አሁን ላይም ትጋታችንን ለሀገራችን አውለን፣ ክፍተቶቻችንን በመሙላት በዳግም በጎ ስም ታሪክ የምናድስበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። መጪው ጊዜም በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በሰላም ፈጣሪነትና በልምድ ልውውጥ ዘርፍ በዲፕሎማሲው ልቀን ሀገራችንን ከነበረችበት እንፉቅቅ የምናራምድበት እንዲሆን ትጋት ያስፈልገዋል።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ጥር 3/2016

Recommended For You