ቅድመ– ታሪክ
ተማሪ ናት። ለነገው የትምህርት ውሎዋ እንደወትሮው ማልዳ መነሳት አለባት። ይህን ስታስብ ያደረችው ታዳጊ ጠዋት ከዕንቅልፏ እንደነቃች የእጅ ሰዓቷን ተመለከተች። ወደ ትምህርት ቤት የመሄጃ ጊዜዋ ደርሷል። ቁርሷን ቀማምሳ ቦርሳዋን በጀርባዋ አዝላ ልትወጣ ስትል አሻግራ የእናቷን መኝታ ቤት አየችው። እናቷ ከዕንቅልፏ አልተነሳችም። ለታዳጊዋ ይህ አጋጣሚ አዲስ አይደለም። ብዙውን ጊዜ ከእሷ ቀድማ መነሳትን ለምዳዋለች።
ልጅት ሁሌም ቢሆን ትምህርት ቤት ውላ ስትመለስ እናቷን ከቤት ታገኛታለች። የቀን ውሎዋን እየነገረቻት የነገ እቅዷን ታወጋታለች። ጊዜውን በጋራ አሳልፈውም ምሽት መኝታ ይለያቸዋል። እናትና ልጁ የሚኖሩበት ትልቅ ግቢ ሁሌም በዘበኛ ይጠበቃል። እስከዛሬም በርከት ያሉ ጥበቃዎች እየገቡ ወጥተዋል። እየወጡም ገብተዋል።
ታዳጊዋ የዛን ዕለት ማለዳ ወደ ትምህርት ቤት ሄዳ ስትማር ውላለች። በተለመደው ሰዓትም ወደ ቤቷ ተመልሳ እናቷን ልታገኝ ሽታለች። አሁን ከቀኑ አስር ሰዓት ሆኗል። ይህ ጊዜ ትምህርት ተጠናቆ ተማሪዎች ወደ የቤታቸው የሚመለሱበት ነው። ጠዋት ወደ ትምህርት ቤቷ ተጣድፋ የወጣችው ተማሪም ልክ እንደ ጓደኞችዋ የደብተር ቦርሳዋን በጀርባዋ አዝላ የመልስ ጉዞዋን ጀምራለች።
ከእኩዮችዋ እየተጫወተች፣እየቀ ደለችና እየሳቀች ወደ ሰፈሯ ስትቃረብ ባልንጀሮችዋን ልትሰናበት ቆም አለች። ሁሌም ቢሆን ከሌሎች ቀድመው ሰፈራቸው የሚደርሱ ጓደኛሞች የሚለያዩት በተለየ ፍቅር መሆኑ ተለምዷል። በጉዟቸው ላይ የሚያነሱት የትምህርት ጉዳይ ካለም መቋጫ ውል የሚያገኘው በስንብታቸው መዳረሻ ላይ ይሆናል።
ተማሪዋ አሁን ከጓደኞችዋ ርቃ የሰፈሯን አቅጣጫ ይዛለች። የግቢያቸውን በር አልፋ ወደ መሀል ስትዘልቅ ግን ዙሪያ ገባው በጭርታ ተቀበላት። እንዲህ አይነቱ ያልተለመደ ዝምታ ለእሷ አዲስ ነበር። በዚህ ሰዓት የሰው ድምጽም ሆነ ኮቴ መጥፋቱ ፍጹም አስገራሚ ሆኖባታል። ከእርምጃዋ ፈጠን እያለች ከትልቁ ቤት ሳሎን በር ላይ ደረሰች። በሩ ጥርቅም ብሎ ተዘግቷል። ለመክፈትም ሆነ ለማንኳኳት አልሞከረችም።
ታዳጊዋ በሁኔታው ተገርማለች። ይህ ግርምታዋም ድምጿን ከፍ አድርጋ እንድትጣራ እያስገደዳት ነው። ጊዜ አልፈጀችም። በድንጋጤ ተውጣ የእናቷን ስም ደጋግማ ተጣራች። «አቤት» ያላት የለም። ጥቂት ቆይታ ጥሪዋን ደጋገመችው። አዲስ ነገር አልሰማችም። የደብተር ቦርሳዋን ከጀርባዋ እንዳዘለች ግቢውን ዞረችው። የገዘፈው ዝምታ አፉን ከፍቶ የሚውጥ ያህል ተሰማት። ድንጋጤዋ አይሎ ውስጧን ፍርሀት ያዘው።
ቆይታው ሲቀጥል ስጋቷም እየጨመረ ሄደ። ሁሌም በዚህ ሰዓት ከቤት የማታጣት እናቷ ድምጽ ናፈቃት። ድንገት ድምጿን የምታሰማት ቢመስላት አይኖችዋ በጉጉት ተንከራተቱ። ጥቂት ቆይታ ከነበረችበት ፈጥና ተነሳች። ፈጣኑ እርምጃዋም ወደ ዘበኛው ቤት አደረሳት። ከበሩ ጀርባ እንደቆመች ዘበኛውን በስሙ ደጋግማ ጠራችው። የራሷን ድምጽ መልሳ ከመስማት በቀር ያገኘችው ምላሽ አልነበረም።
ፈራ ተባ እያለች ገርበብ ያለውን በር ገፋ አድርጋ ውስጡን ቃኘችው። የፈራችው አልቀረም። ዘበኛውም በስፍራው የለም። ሁኔታውን ይበልጥ ለማጣራት ወደ ውስጥ የዘለቀችው ተማሪ የዘበኛው ሙሉ ጓዝ በስፍራው ያለመኖሩን ስታውቅ ውስጧ በድንጋጤ ራደ። ወዲያው ልቧ በፍጥነት ሲመታ ታወቃት።
ታዳጊዋ እንደምንም ተረጋግታ የእጅ ስልኳን ከቦርሳዋ አወጣች። ቁጥሮቹን ነካክታም ወደ እናቷ ሞባይል መደወል ጀመረች። በዝምታ የቆየው መስመር ጥቂት ቆይቶ ስልኩ ጥሪ እንደማይቀበል አሳወቃት። ደግማ ደጋግማ ሞከረችው። ከቀድሞ ምላሹ በቀር አዲስ ነገር አልነበረውም። የስልኩ ጉዳይ ተስፋ ቢያስቆርጣት ወደ ነበረችበት ተመልሳ አረፍ አለች። አይኖችዋ ደጁን ከማየት፣ ልቧም እናቷን ከማሰብ አልቦዘኑም።
ምሽቱ እየገፋ ሰዓቱ እየነጎደ ነው። ጨለማው ለአይን ያዝ ማድረግ ሲጀምር ደግሞ የልጅቷ ፍርሀት ማየል ያዘ። ባልተለመደ ሁኔታ እናቷን በር አዘግቶ ከቤት ያራቃት ምክንያት አልገባትም። በሀሳብ ስትናውዝ የቆየችው ታዳጊ እንደመጨረሻ አማራጭ አንድ እድል ለመሞከር የእጅ ስልኳን አነሳች። በሚቀርቧትና በየዘመዶቿ ዘንድ እየደወለች የእናቷን መገኛ ጠየቀች። ሁሉም እንዳላይዋት አረጋግጠው ሲመልሱላት ጭንቀቷ ይባስ ጨመረ።
ተስፋ የለሹ መጠበቅ አሁንም ያለምንም መፍትሄ ቀጥሏል። የምሽቱ መግፋት ደግሞ ትንሿን ልጅ በነበረችበት የሚያቆያት አልሆነም። በሌላ ክፍል ገብታ ለማደር የፈራችው ታዳጊ ጎረቤት ዘንድ ሄዳ አመሸች። አዳሯን በዛው አድርጋም ጠዋት ወደ እናቷ ሞባይል ደወለች። ትላንት የተዘጋው ስልክ ዛሬ ድንገት መጥራቱ ድንጋጤና ደስታን ፈጠረባት። ቀጥሎ ያለውን ድምጽ ለመስማትም ተጣደፈች።
ስልኩ ጥቂት ከጠራ በኋላ «ሀሎ፣ሀሎ…» የሚልና የተጣደፈ ድምጽ ለጆሮዋ ደረሰ። እናቷ አልነበረችም። ከወዲያኛው ጫፍ የሚሰማት ጎርናና የወንድ ድምጽ ነበር። ዘበኛው መሆኑን የጠረጠረችው ልጅ እናቷ የት እንደምትገኝ እየተንቀጠቀጠች ጠየቀችው። ሰውዬው «ሀዋሳ፣ ሀዋሳ ነን»ከማለቱ ስልኩ ጥርቅም ብሎ ተዘጋ። ቀጥሎ የነበረው ተደጋጋሚ ሙከራ የተሳካ አልነበረም።
ይህ በሆነ ጥቂት አፍታ ታዳጊዋ ከፖሊስ ጣቢያ ደጃፍ ደረሰች። ወደ ውስጥ ዘልቃም ከትላንት እስከዛሬ ያጋጠማትን ሁሉ አስረዳች። የእናትን የሞባይል ቁጥር የተቀበለው ፖሊስ ደጋግሞ ወደ ስልኩ ደወለ። ከሙከራዎች በኋላ የተነሳው የሴትዬዋ ስልክ ዘበኛ ነው ከተባለው ሰው ጋር አገናኘው። ዘበኛው ለተጠየቀው ሁሉ ፈጣን ምላሹን ሰጠ። የሴትዬዋ አለርጂክ በመነሳቱ ድንገት ወደ ሀዋሳ መሄዳቸውንም በእርጋታ ተናገረ።
ፖሊስ ጥያቄውን ቀጠለ። የት ስፍራና በምን ሁኔታ እንደሚገኙም ጠየቀ። ዘበኛው ሴትዬዋ ለህመሟ ሲባል በህክምና እየታሸች መሆኗንና፣ ልጇን «አይዞሽ» ብሎ እንዲያበረታት መታዘዙን አሳወቀ። እሱም እየተመለሰ መሆኑን ሲናገርም በተለየ መተማመን ሆነ። ይህን ምላሽ ከፖሊስ አንደበት የሰማችው ታዳጊ በድንጋጤ ተረበሸች። እናቷ ባልተለመደ ሁኔታ ድንገትሀዋሳ ትገኛለች መባሉን አላመነችም።
አንድ ቀን ያስቆጠረው ጊዜ የእናቷን ድምጽ እንደሰወረ ሁለተኛው ቀን አጋማሽ ላይ ደርሷል። የዛሬውን ምሽት በጭንቀት መድገም ያልፈለገችው ታዳጊ ፖሊሶችን ይዛ ቤቱን ለመቃኘት ወስናለች። አሁንም የእናቷን በድንገት ከቤት መራቅና ከዘበኛው የደረሳትን መልዕክት ፈጽሞ አልተቀበለችውም።
ህዳር 30 ቀን 2002 ዓ.ም
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ከታዳጊዋ ተማሪ የደረሰውን ጥቆማ ተቀብሎ ሸገር መናፈሻ ፊት ለፊት ከሚገኘው መኖሪያ ሲደርስ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ሆኖ ነበር። በልጅቷ መሪነት ወደ ቤቱ አቅጣጫ ያመሩት አባላት ዙሪያ ገባውን ከቃኙ በኋላ በቤቱ ላይ ፍተሻና ምርመራ ለማካሄድ አስበዋል። ምክክራቸውን እንደጨረሱም የመኝታ ቤቱ መስኮት ቢሰበር እንደሚሻል ወስነዋል።
አሁን የመኝታ ክፍሉ መስኮት በፖሊስ አባላቱ ቅንጅት እየተሰበረ ነው። ፖሊሶቹ ወደ ውስጥ ለመዝለቅ የሚያስችላቸውን በቂ መግቢያ አግኝተዋል። ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃቸው ውሉን አልሳተም። ጆሯቸውን ጣል አድርገው እያዳመጡ ነው። ላይና ታች የሚቃብዙት አይኖቻቸው አዲስ ነገር ፍለጋ ይዘዋል። ከተዘጋው በርና መስኮት ጀርባ የሚሰማ ድምጽ የለም።
ክፍሉ በድንገት ከመከፈቱ ወደ አፍንጫ የደረሰው መጥፎ ሽታ ለፖሊሶቹ ክፉ የሚባል ምልክት ነበር። ጥቂት አለፍ ከማለታቸው የተመለከቱት እውነት ደግሞ አባላቱን ከቆሙበት እልፍ የሚያስብላቸው አልሆነም። በአንድ ሰፊ አልጋ ላይ ጋቢ ተሸፍኖ የተጋደመው በድን አካል በሁሉም አይኖች ውስጥ አስደንጋጭ ምስሉን ከስቷል።
አሁን የፖሊሶቹ እይታ በዚህ ክፍል ውስጥ የሰው ህይወት መጥፋቱን አረጋግጠዋል። በስፍራው የተገኘው ዱላ የወይዘሮዋን ህይወት ለማጥፋት አጋዥ ስለመሆኑም ተጠርጥሯል። ከፍተኛ ድብደባ የደረሰበት የሟች አካል ላይ የደረቀ ደም መገኘቱ ድርጊቱ በጭካኔ ስለመፈጸሙ አመላካች ነበር። በስፍራው የሚታየው የዕቃዎች መተራመስና መዝረክረክም ከወንጀል ድርጊቱ በኋላ ዝርፊያ ስለመፈጸሙ የሚጠቁም ሆኗል።
ጉዳዩን በጥልቀት ለመመርመር ተጨማሪ ሀይል ያስፈለጋቸው አባላት የተፈጸመውን ወንጀል በቴክኒካዊ ማሳያ ለማረጋገጥ ሙያዊ እገዛ ጠይቀዋል። ከዚህ ሁሉ ድርጊት በስተጀርባ ግን በወይዘሮዋ ላይ የግድያ ወንጀሉን ማን ፈጸመው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ፖሊስ የምርመራ ቡድን በማዋቀር የክትትል ስራውን የጀመረው ሳይውል ሳያድር ነበር።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ የወንጀል ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ ያዋቀረው ቡድን ምርመራውን ከአካባቢው ማስረጃዎች ጀምሯል። ወይዘሮ ወርቅነሽ አበበ ሲኖሩበት ነበር በተባለው ሰፊ ግቢ በጥበቃ ተቀጥሮ የሚሰራው ግለሰብ ድንገት የመሰወር እውነታም የፖሊሶችን ጥርጣሬ አጠንክሯል። በምርመራው የተገኘው ውጤት ከግድያው በኋላ ዝርፊያ መፈጸሙን በማረጋገጡም የክትትል ቡድን አባላቱ በየአቅጣጫው ተሰማርተው ማነፍነፍ ጀምረዋል።
በምርመራ መዝገብ ቁጥር 337/02 የተከፈተው የፖሊስ መዝገብ በየቀኑ የሚገኙትን አዳዲስ መረጃዎች ያሰፍራል። በመርማሪ ሳጂን መረሳ ሀይሉ የሚመራው ቡድንም በግለሰቡ ላይ የሚያስፈልጉ ማስረጃዎችን ለማጠናከር የቀን ከሌት አሰሳውን ቀጥሏል።
የፖሊስ የምርመራ ውጤት ከግለሰቧ መገደል በስተጀርባ ዝርፊያ መፈጸሙን ካረጋገጠ ወዲህ የጠፉ ንብረቶችን ለይቷል። የተለያየ ግራም ያላቸው ወርቆችና ጌጣጌጦች፣ የውስጥና የውጭ ሀገራት ገንዘቦች፣ የተለያዩ ሰነዶችና የቤት ካርታዎች፣ ካሜራዎችና የእጅ ስልኮችን ጨምሮ በሻንጣ የተዘጋጁ በርካታ አልባሳት ተዘርፈዋል።
በርሄ ግደይ በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ግለሰብ ለስራ ወደ አዲስ አበባ የመምጣቱ ምክንያት ተወልዶ ባደገበት አካባቢ በትምህርቱ መግፋት ባለመቻሉ ነበር። ከተማ መግባቱ ትምህርቱን ለመቀጠል ባይረዳውም ሰርቶ ለማደር ግን የሚበጀው ነበር። በአንድ ሆቴል በአስተናጋጅነት የጀመረው ስራ ከብዙዎች አስተዋውቆ እንግድነቱን አስረሳው። ያም ሆኖ ግን ከአሰሪዎቹ ጋር መስማማት አልቻለም። ጥቂት ሰርቶ ከእንጀራው ሊቆረረጥ ግድ ሆነ።
ቀናትን በስራ ፈትነት ያሳለፈው ወጣት በወይዘሮዋ ቤት በጥበቃ ተቀጥሮ ለመስራት ሲወስን በደመወዙና በኑሮው ደስተኛ መሆን ጀመረ። በስራው «አቤት፣ ወዴት» ብሎ የሚያድረው በርሄ ከወይዘሮዋና ከሴት ልጃቸው ጋር ለመግባባት ጊዜ አልፈጀበትም። ውሎ የሚያድርበት ማረፊያው ምቹ መሆኑና ኑሮው መደላደሉ ስራውን በአግባቡ እንዲከውን ምክንያት ሆኖታል።
ፖሊስ በአካባቢውና ወይዘሮዋን በሚቀርቡ ሰዎች ዙሪያ ባደረገው ጥልቅ ምርመራ የድርጊቱ ፈጻሚ ጥበቃው በርሄ ስለመሆኑ ገምቷል። የትውልድ ስፍራውን አጣርቶ ማግኘቱም ተጠርጣሪውን በእጁ ለማድረግ አንድ እርምጃ ሆኖለታል። ግለሰቡ ይገኝበታል በተባለው ስፍራ ለመድረስ ፍንጭ ተገኝቷል። ለዚህ ደግሞ ከትግራይ የፖሊስ አባላት ጋር የተቀናጀው የክትትል ቡድን በሰውዬው ላይ የተገኘውን ሙሉ መረጃ አጠናክሮ ሪፖርት መቀባበል ጀምሯል።
እልህ አስጨራሹ የክትትል ስራ አሁን ከአንድ ፍንጭ ላይ እየደረሰ ነው። በርሄ ከድርጊቱ መፈጸም ጥቂት ቀናት በኋላ ወደ ትውልድ አገሩ ለመጓዝ የመቀሌን መንገድ እንደጀመረ መረጃዎች ደርሰዋል። መድረሻውን ከእህቱ ቤት አድርጎ ወላጆቹን ለመጠየቅ ወደ ገጠር ሲንቀሳቀስም አንድ በልብስ የተሞላ ሻንጣ ይዞ እንደነበረ በጥቆማ ተረጋግጧል።።
በርሄ መቀሌ ገብቶ እንደቆየ ከእህቱ ጋር ወላጆቹን ጠይቆ ተመልሷል። በእጆቹ የሚገኙትን የውጭ ሀገራት ገንዘቦች ለመዘርዘርም ላይ ታች ሲል ታይቷል። ከሁለት ኪሎ በላይ የሚመዝነውን ወርቅ አውጥቶ ለመሸጥ ግን ድፍረት አልነበረውም። በአንድ ጣቱ ላይ አጥልቆት የቆየውን ቀለበት ለመሸጥ ከአስራ አንድ ሺህ ብር በላይ ተጠይቆ ተስማምቷል። ቀለበቱን የሚገዙት ወርቅ ቤቶች ግን ያለደረሰኝ መውሰድ ያለመፈለጋቸው በእጁ ላይ እንዲቆይ ምክንያት ሆኗል።
በርሄ እህቱ በእጁ ላይ ስለሚገኙት ውድ ንብረቶች ስትጠይቀው የጣት ቀለበቱን ከአሰሪው በስጦታ እንዳገኘውና ሌሎቹ ዕቃዎች ግን የግሉ ስለመሆናቸው ነግሯታል። ይህ አይነቱ መረጃ ደግሞ እግር በእግር ለሚከታተሉት ፖሊሶች ታላቅ ዋጋ ነበረው። ፖሊስ ካረፈበት መኖሪያ ድንገት ደርሶ በቁጥጥር ስር ሲያውለው እህቱ ስለ ወንድሟ ያየችውን ሁሉ ለመናገር ወደ ኋላ አላለችም።
አሁን በርሄ በአዲስ አበባ ፖሊሶች ታጅቦ ለሚቀርብለት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠትም ዝግጁ ሆኗል። ለፖሊስ ምርመራ ሲዘጋጅ የተጠየቀውን በሙሉ ለመመለስና የሆነውን ሁሉ ለማስረዳት ፈቃደኛ ሆኖ ነበር። ከዓመታት በፊት አዲስ አበባ የመጣው ወጣት ወይዘሮ ወርቅነሽ መኖሪያ ቤት በጥበቃ ሲቀጠር አላማና ግቡ ገንዘብ አግኝቶ ለመለወጥ እንደነበር ይናገራል።
ሶስት ወራትን በግቢው ሲቆይም ወይዘሮዋ ያዘዙትን ሁሉ ለመፈጸም ወደ ኋላ ብሎ አያውቅም። በርሄ ወንጀሉ በተፈጸመበት ቀን ማለዳ በወይዘሮዋ ጥሪ ቀርቦለት ቡና ወደሚፈላበት ክፍል መዝለቁን ያስታውሳል። ከስፍራው እንደደረሰ ልብስ እንዲያጥብ በመታዘዙ እሱን ለመፈጸም ሲዘጋጅ እንደነበርም ይናገራል።
በርሄ ልብሱን ማጠብ እንደያዘ እሱን አቋርጦ የእንጀራ ምጣዱን እንዲለኩስ ትዕዛዝ ደረሰው። ሶኬቱን ማስጠጋት እንደጀመረ ደግሞ ወይዘሮዋ በያዙት ወፍራም ዱላ ወገቡ ላይ አሳረፉበትና ቤቱን ማጽዳት እንዲቀጥል ነገሩት። ትዕዛዙን ሰምቶ ሳይጨርስ በፍጥነት እንዲንበረከክና ልብስ የሞላውን ሻንጣ ተሸክሞ ቁጭ ብድግ እንዲል በዱላ አጣደፉት።
በርሄ እንደሚለው ባረፈበት የዱላ ጫና አፍና አፍንጫው ክፉኛ ተጎዳ። በድጋሚ የደረሰበትን ስንዘራም የሚያልፈው አልሆነም። ራሱን ለማዳን ባደረገው ሙከራ ሀይለ ቃልና ጸያፍ ስድብን አስተናገደ። ይህኔ ውስጡ በንዴት ተንተከተከ። የሚሆነውን መቋቋም አቅቶትም ከወይዘሮዋ እጆች ላይ ቆመጡን ነጥቆ አናታቸውና ማጅራታቸው ላይ አሳረፈው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 24/2011
መልካምስራ አፈወርቅ