ነገዎቻችንን ብሩህ ለ ማድረግ እንመካከር !

ዛሬ ላይ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ምን ትሻለህ ተብሎ ቢጠየቅ፤የሀገሬን ሰላም ከማለት ውጪ ሌላ ምላሽ ያለው አይመስለኝም፡፡ ”ከሌለህ የለህም” የሚለው አባባልም፤ከምንም በላይ ሰላምን ይገልጸዋል፡፡ እዚህች ምድር ላይ ምንም ነገር ባይኖረን ሰላምና ጤና ካለን የቱንም የምንፈልገውን ነገር ለማድረግም ሆነ ለማግኘት እንችላለን፡፡እኚህ ከሌሉ ግን የሌለንን ነገር ለማግኘት ይቅርና ያለንንም ነገር መጨበጥ ሊያቅትን ይችላል፡፡

ዝንጀሮ እንኳን “በመጀመሪያ የመቀመጫዬን” ማለቷ ነገሩ ቢገባት ነው፡፡ ከሁሉም ጉዳዮቻችን በላይ ለነገ ብለን ማሳደር የሌለብን የመቀመጫችንን እና የሰላማችንን ጉዳይ ነው፡፡ የሰላማችንን ጉዳይ ለነገ ብለን በይደር ካቆየነው መሽቶ በነጋ ቁጥር ነገን የማየት ህልማችን አስተማማኝ አይሆንም፡፡

እንደ ሀገር ዱካው የጠፋብንን ሰላም ለማግኘት፤የመንግሥትና የሕዝብ ጥምረት የሆነ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ችግሮቻችንን በውይይትና ተቀራርቦ በመነጋጋር ፈትተን ወደ ቀደመው ሰላማችን እንድንመለስ የሚያደርጉ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡ ነገር ግን በተግባር ስንቶቻችን ተቀብለን እየሠራንበት ይሆን? ሰላማችን እንዲመለስ ግላዊም ሆነ ቡድናዊ አስተዋጿችንን እንዴት ለማበርከት ተዘጋጅተን ይሆን? ጉዳዩን ጀመርነው እንጂ ገና አላጠናቀቅነውምና ሁላችንም ወደ ሰላም ያደርሳሉ በተባሉ መንገዶች ላይ ለመራመድ እንዘጋጅ፡፡

ከጠመንጃ አፈሙዝ የምናገኘው የጥይት ባሩድና ሞት ብቻ ነው፡፡ እስከዛሬም ዓለም ባላት ታሪክ፤በጠመንጃ አፈሙዝ የጸና ሰላም አይተንም ሆነ ሰምተን አናውቅም፡፡ ሳይንስ በደረሰበት ጥበብም እሳት በእሳት ጠፍቶ አያውቅም፡፡ ታዲያ በኛ የሚጀምር ከመሰለን ተሳስተናል፡፡

ጠመንጃ አንግበን ሰላምን ፍለጋ ብንኳትን ከቶም አናገኘውም ፤ እንዲህ አይነቱ የአዳኝና የታዳኝ ጨዋታ ምናልባት ውጤት ያመጣል ቢባል እንኳን ዘለቄታ አይኖረውም፡፡ ዓለም ላይ የብዙ ሰዎችን እልቂት ያስከተሉና የንብረት ውድመት ያደረሱ በርካታ ጦርነቶች ተካሂደዋል፤ አብዛኛዎቹ የተቋጩት በንግግር ነው፡፡ እኛስ…ካለፉት ምን እንማር? የትኛው መንገድ ይሻለናል? ስንል፤ያለን ብቸኛው አማራጭ፤ በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የቀረበውን የሰላም ጥሪ እውን ማድረግ ነው። ይህ ሊያመልጠን የማይገባ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።፡

ሀሳቡ ከማንም ይምጣ ከማን ሕዝባዊ ቅርጽ እንዲኖረው በማድረግ መድኃኒት ማድረጉ የኛ ድርሻ ነው፡፡ በተቋሙ ላይ ሕዝባዊ አጀንዳዎችን በመጫን ሕዝባዊ ማድረጉ በእጃችን ነው፡፡ የምክክር ኮሚሽኑ የተቋቋመበት ሒደትም ሆነ ዓላማ፤እንደ መንግሥታዊ ተቋም አይደለም። ተቋሙም የሚያስረዳው ይህንኑ ነው፡፡ የምንፈልገው ሰላምና ሰላም ብቻ እስከሆነ ድረስ ለጉዳዩ ዕድል ሰጥተን ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

ሀገራዊው ምክክሩ በቀጣዩ የጥር ወር ላይ እንደሚጀምር የተነገረ ቢሆንም ቀደም ሲል በነበሩት ጊዜያት ግን በክልሎችና ከተሞች፤የቅድመ ምክክር ሥራዎች ሲካሔዱ መሰንበታቸው የማይዘነጋ ነው። ከምክክሩ አስቀድሞ ሲካሔድ የነበረው የቅድመ ምክክር ሒደቱ፤ከምንም በላይ እጅግ ወሳኙ ምዕራፍ እንደመሆኑ የእያንዳንዱ ግለሰብ አሻራ ሊያርፈበት ይገባል፡፡

ኮሚሽኑ በተቻለው አቅም ሁሉ ይዞ የተነሳው ዓላማ ስኬታማ እንዲሆን ብርቱ ሥራዎችን እየሠራ ቢሆንም፤ ጉዳዩ ሀገራዊ እንደመሆኑ አንድም ዜጋ እንኳን ከዚህ ሊጎድል አይገባም። ሁሉም ዜጋ ከራሱ አልፎ የመጪው ትውልድ ብሩህ ነገዎች በኮሚሽኑ ውጤታማ ሥራ ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑ ለአፍታም ቢሆን ሊዘነጋ አይገባም ።

ለዚህም ከሁሉም በላይ ጥያቄ አለኝ የሚለውም ሌላውም ዜጋ ስለሰላም አብዝቶ መሥራት ይጠበቅበታል። የምክክር ኮሚሽኑ የስኬት ሚዛን ከሚለካበት አንዱ መመዘኛ ይሄው እንደሆነ መገመት የሚከብድ አይደለም፡፡

ኮሚሽኑ ለውጥ አይመጣም በሚል አጉል የተዛባ አመለካከት እጃቸውን አጣምረው ከዳር የቆሙ አካላትም፤ ያለ ሙከራ ከሰማይ የሚዘንብ ለውጥ የለምና፤ ተስፋ አድርገው እጃቸውን የሰላም አሸንዳው ላይ መደቀን ይገባቸዋል፡፡ ምንም ሳንሠራ ሰላምን ከሰላም ቅርጫት ውስጥ ብንፈልግ እራሳችንን ማታለል ነው፡፡ ተስፋ አድርገን እንሳተፍ ፤ ድሮም እኮ አይሆንም ብዬ ነበር ለማለት እራሳችንን አናዘጋጅ ፡፡

ይህ ሳይሆን ቀርቶ በድፍን የፖለቲካ ኮብል ሕዝብና ሀገር ቢደማ፤ተጠያቂዎቹ ዛሬ ከሀገራዊ ምክክሩ የሸሸን እኛው እራሳችን መሆናችንን አንርሳ። የመጣንበት የፖለቲካ ድብብቆሽ ከድካም ውጪ ያተረፈልን ነገር እንደሌለ ካለፈው ታሪካችን ተምረናል።

የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ ልንሆን እንችላለን፤ ከየትኛውም ብሔር ልንወጣ እንችላለን፤ የራሳችን የሆነ የፖለቲካ አቋም ሊኖረንም ይችላል፤ እነዚህ ሁሉ ከሀገራዊ ምክክሩ ተሳታፊነት አያግዱንም። ሀገራዊ ምክክሩን ደግፎ ከዓላማው ጎን መቆም ማለት የመንግሥት ደጋፊ መሆን ማለት አይደለም፡፡ ሀገር በመንግሥት ሥር ብትሆንም፤ሀገር ማለት ግን መንግሥት ማለት አይደለም፡፡ ሀገር ከመንግሥት በላይ ነች።

ይህ ታላቅ ሀገራዊ ጉዳይ በስኬት እንዲጠናቀቀ ከኮሚሽኑ ምን ይጠበቃል? የመጀመሪያው ጉዳይ የምክክር ኮሚሽኑ ከሕዝብ ጋር ያለው ግንኙነት ጠንካራና ግልጽ መሆን አለበት፡፡ በምክክር ወቅት ሕዝብን ይወክላሉ ተብሎ የተመረጡ አካላት፤በትክክልም ሕዝብን የሚወክሉና ሕዝቡ እራሱ የመረጣቸው መሆን አለባቸው፡፡ ይህን አሳማኝ በሆነ መንገድ ማሳ የት አለበት፡፡

አስቀድሞ ከሕዝቡ አሜንታን ያላገኙ ከሆነ ለማጥራት የሚሞከሩ ነገሮች ይባሱኑ መልሶ ማደፍረሱ የማይቀር ነው፡፡ በእነዚህ ሁሉ መንገዶች አልፎ ኮሚሽኑ በሕዝብ ያለውን አመኔታ ከፍ ማድረግ አለበት፡፡ በጦርነት ላይ ያሉ አካባቢዎችን ለማሳተፍ የሚችልበትን እቅድ መንደፍ የግድ ይለዋል፤አሊያ ለፍቶ መና መቅረት ነው፡፡

በፖለቲካው ትኩሳትና ወላፈን እየተማገደ ያለው ከማንም በላይ ወጣቱ ክፍል እንደመሆኑ በዋናነት ትኩረቱን በእነርሱ ላይ በማድረግ ተሳታፊነታቸውን ማሳደግ አማራጭ የለውም። በአብዛኛው የግጭት መንስኤ እየሆኑ ያሉት የወሰንና የድንበር አስተዳደር ጉዳዮች፤ግንባር ቀደም ራስ ምታቶች ናቸውና ቅድሚያ በመስጠት አስቸኳይ መፍትሔዎችን ማፈላለጉ ነገሩን ቀለል ያደርገዋል፡፡

አሁን አሁን በሀገራችን ውስጥ የሚንጸባረቁ ዝብርቅርቅ ስሜቶች አሉ፤ እያንዳንዳችን ፍላጎታችንና አስተሳሰባችን የተለያየ ነው፡፡ ባለፉት ታሪኮቻችን ላይ ሳይቀር የሀሳብ ግጭት፣ የቋንቋ መደበላለቅ ይታይብናል፡፡ ሀገራዊ ምክክሩ የተራራቁ አስተሳሰቦችን ለማቀራረብ ይጠቅማል፤ የጥላቻ እና የቂም ግድግዳዎችን አፈራርሶ በሕዝቦች መካከል ጤናማ መስተጋብር እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ታዲያ ለዚህ ሁሉ ስኬት መብቃት የምንችለው ሁላችንም በቅን ልቦና ለሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት ይበጃል በምንለው መንገድ ጠጠር መወርወር የቻልን እንደሆን ነው፡፡ ለሰላም እጦት ምክንያት የሆኑትን ተነጋግረን ያልፈታናቸው ችግሮች የነገዎቹ ትውልዶች እና የነገዋ ኢትዮጵያ በአዲስ ምዕራፍ እንዲጓዙ ፊታችንን ወደ ሀገራዊ ምክክሩ አዙረን ሰላሟ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ልናስረክብ ግድ ይላል፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን  ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You