ከእናንተ ውስጥ ለሀገሩ አምባሳደር የሆነው ማን ነው?

እነገብረየስ ገብረማሪያም ዛሬም በማምሻ ግሮሰሪ ጠረጴዛ ከበው ተቀምጠዋል፡፡ ዘውዴ መታፈሪያ ማማረሩን ተያይዞታል፡፡ ተሰማ መንግሥቴ እና ገብረየስ የዘውዴን ምሬት ከመቀላቀል ይልቅ በፅኑ እየተቃወሙት ነው፡፡ እርሱ ደግሞ ‹‹እኔ ኢትዮጵያን ሀገሬ ናት ለማለት እየተቸገርኩ ነው፡፡ ያልተነካ ግልግል ያውቃል፡፡ እናንተ የማትማረሩት ስላልጎደለባችሁ እና በደል ስላልደረሰባችሁ ነው›› ይላቸዋል፡፡ እነርሱ ደግሞ መማረር ልማድ ሆኖብህ እንጂ ተለይቶ ለአንተ ብቻ የጎደለብህ ነገር የለም፡፡ ደግሞም ምንም ቢመርህ ለሀገርህ ክፉ መመኘትም ሆነ ሀገርህን መካድ እና በገዛ ሀገርህ ላይ ማሟረት የለብህም እያሉት ነው፡፡

‹‹በእርግጥ የጠለቀ የማሰብ ችሎታ ከሌለን ሀገራችንን አንወድም፡፡ ለእያንዳንዱ ጉዳይ የማይገባውን ትኩረት እየሠጠን ሀገራችንን የምንጠላበት ምክንያት አድርገን እናስቀምጣለን፡፡›› በማለት ተሰማ ዘውዴን ለመገሰፅ ሞከረ፡፡

ዘውዴ በበኩሉ፤ ‹‹ሀገራችንን እንወዳለን ካልን ከልባችን መሆኑን ማሳየት እና ያንንም መተግበር አለብን። የእኛ ሀገር መውደድ ግን ከቃል ያለፈ፤ ከአንደበታችን የተረፈ አይደለም፡፡ ለእዚህ ማረጋገጫ ካስፈለገ፤ ጥሎ ማለፍ ሳያስፈልግ ለመጣል የምናባክነውን ገንዘብ እና የምናፈሰውን ደም ብቻ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሀገር ለእኔ ጋራ ሸንተረሩ ወይም መሬቱ አይደለም፡፡ ሀገር ለእኔ በዋናነት ሰው ነው፡፡ ሲል ምላሽ ሰጠ፡፡

ገብረየስ ደግሞ፤ ‹‹ምንም ቢሆን ለሀገር ከመሥራት እና በየትኛውም ዓለም የሀገር አምባሳደር ሆኖ ሀገርን ከማስተዋወቅ በተቃራኒው ቆሞ ሀገር ማዋረድ እና አገር መጥላት ትክክል አይደለም፡፡ ነገር ግን በየትኛውም መስክ ዕድል ቀንቶህም ሆነ በትጋትህ ቦታ ስታገኝ በእውነተኛ ስሜት ሕዝብን ማገልገል ይጠበቅብሃል፡፡ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ በተቃራኒው ይሆናል ይሔ ደግሞ ሰዎች ሀገራቸውን እንዲጠሉ ያስገድዳቸዋል፡፡

በተናጠል ውጤት ብናመጣ እንኳ በጋራ ከዛ በላይ ውጤት ማምጣት እንደምንችል አምነን ሌላውን ለማስጠጋት ከመሞከር እና በሀገር ደረጃ ውጤታማነትን ከማረጋገጥ ይልቅ ለራሳችን አጥር እንሠራለን፡፡ የቅንጦት እና የምቾት ኑሮን ከሀገር በላይ በማስቀደም ሀገር መካድ፤ ጠመንጃ በያዘ ጠላት ሳንሸነፍ ስኳር በያዘ የውጪ ጠላት ተጠልፈን ሀገራችንን እስከመሸጥ እንደርሳለን፡፡ በስኳር እየተታለሉ ሀገር እወዳለሁ ማለትም ውሸት ነው። እንደአንተም በአደባባይ ሀገር ለመጥላት መዳዳትም ፍፁም ነውር ነው፡፡›› ብሎ ብርጭቆውን አንስቶ የሚጠጣውን ተጎነጨ፡፡

ዘውዴ ገብረየስን ከተል ብሎ ‹‹ሰዎች ለጊዜው ባለሥልጣን፣ ገንዘብ ያላቸው ወይም ቀልጣፋ እና ጉልበት ያላቸው ሆነው ሁሉን ማድረግ ይችሉ ይሆናል። ገንዘብ እና ጉልበት የሌለውን ዕድሜው የገፉ ሰውን ዝቅ አድርገው ሊያዩ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ እጅግ ያስቀይማል፡፡ እኔ እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች ተበራክተው፤ አቅመ ደካማ ሆኜ እየተገፋሁ ስኖር፤ ሰዎችን ያሰቃየ ዋጋ መክፈል ያለበት ሰው ዋጋ ሳይከፍል እንዲሁ ዘመናት ሲቆጠሩ ሀገሬን ላለመውደድ እና ኢትዮጵያን እንደሀገሬ ላለመቀበል ባናንገራግር እንደጥፋተኛ መቆጠር አለብኝ ብዬ አላምንም፡፡›› ብሎ ሀገርን አለመውደድ ወይም ሀገርን አለመቀበል እንደጥፋት መታየት የለበትም ሲል ለመሞገት ሞከረ፡፡

ገብረየስ፤ ‹‹ ድፍረትን ማብዛት በምንም መልኩ ስኬታማ ለመሆን ምቹ ሁኔታን አይፈጥርም፡፡ ምንም እንኳ ሀገርን እንደሚወዱ እና እንደሚያከብሩ ቢናገሩም ራሳቸውን ቅድሚያ ሀገራቸውን ሁለተኛ የሚያደርጉ፤ ደፍረው ብዙኃንን እየገፉ የሚያሰቃዩ ሊኖሩ ይችላሉ። ይህም በማኅበረሰብ ደረጃ በሁሉም ነገር የመቀዝቀዝ እና የመሰላቸት ስሜት ሊፈጥር ይችላል፡፡ እኔም በተመሳሳይ መልኩ የመሰላቸት አዝማሚያ ውስጥ ያለሁ ይመስለኛል፡፡ ይህ ቢሆንም ግን የትም ብሔድ ‹የሀገሬ አምባሳደር ነኝ፡፡› ብዬ ስለማምን ሀገሬን በተመለከተ የምናገረውም ሆነ የምሠራው ሀገሬን በሚጠቅም መልኩ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡›› አለ፡፡

ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹ በጣም የሚገርመው ልማዳችን መጥፎው መጥፎው ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ከማሞገስ ይልቅ ማንኳሰስን እንመርጣለን፡፡ መርምሮ መድኃኒት ሰጥቶ አክሞ ከሚያድነው ይልቅ፤ ተኩሶ የሚገድለውን እናሞካሻለን፡፡ ራሳችንን ስናይ እንኳ ውበታችንን ሳይሆን የጎደለብንን እያየን እንሸማቀቃለን።›› ብሎ ፊቱን ወደ ዘውዴ በማዞር፤ ‹‹በቅርብ ዓመታት ውስጥ የጎደለብህ ቢኖርም ያገኘኸውም በጣም ብዙ ነገር አለ። አንተ ግን ከምሬት አርፈኽ አታውቅም፡፡ ከመማረር ይልቅ መልካም መልካሙን እያየህ ያንንም እያሰብክ እና እየተናገርክ መቆየት ይሻልኃል፡፡ የዛን ጊዜ በሒደት ብዙ መልካም ነገር ሊመጣ ይችላል፡፡ ውጪ ሀገር እየኖሩ ኢትዮጵያን ከማገዝ እና ሀገራቸውን ከማስተዋወቅ ይልቅ፤ በተቃራኒው ሀገር የሚያጠፋ ተግባር እንደሚፈፅሙ ሰዎች መሆን የለብህም፡፡›› አለው፡፡

ዘውዴ ተሰማን በትዝብት አስተያየት እየተመለከተው፤ ‹‹የምፈልገውን ያህል እንኳ ባገኝ ኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህ ሁሉ መከራ እና ችግሮች ተከማችተው እንዴት አልማረርም?›› ሲል ተሰማን ጠየቀው፡፡ ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ችግር መኖሩ የሚካድ አይደለም፡፡ የኑሮ ውድነት፤ ግጭት፤ ሥራ አጥነት የመሳሰሉት ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡ ነገር ግን እያራገቡ እና እያቀጣጠሉ ችግሩ እንዲሰፋ ከመሞከር ይልቅ፤ ስለሰላም መመካከር እና ችግሮች የሚፈቱበትን ሁኔታ መነጋገር ይሻላል፡፡ ያለበለዚያ ከውጪም ከውስጥም ያለነው ስለሀገራችን መጥፎ መጥፎውን ብቻ እያየን የምናዝን፤ ካየነው በላይ እያጋነንን የምናወራ ከሆነ ዞሮ ዞሮ ተጎጂዎቹ ሁላችንም ነን፡፡

ምሬትን የሚያመጡ ነገሮችም እየተቀጣጠሉ የበለጠ እየሰፉ ይሔዳሉ፡፡ አንዳንዴ እንደውም ሀገራችንን የባሰ ችግር ውስጥ የምንከታት እራሳችን እንሆናለን። ስለሀገራችን በጎ ነገር ከማሰብ እና ከመናገር ይልቅ፤ መልካም ገፅታዋን እያዩ እየተደሰቱ ከማስተዋወቅ ይልቅ በተቃራኒው ሀገራችን ውስጥ የሌለውን ችግር እየጨማመርን መከራውን ቆልለን ካወራነው ሀገር ወዳድ ሳንሆን ሀገር የምንጠላ ግብዞች ነን ማለት ይቻላል፡፡›› ሲል ሁሌም ቢሆን መጥፎ መጥፎውን ማየት እና ያዩትንም አጋንኖ ማስተጋባት ሀገር ወዳድነት ሳይሆን አገር ጠልነት መሆኑን አስረዳ፡፡

ዘውዴ ተቆጣ፤ ‹‹እንዴት እንዲህ ትላለህ? አይንህ እያየ የተፈጠረውን እንዳልተፈጠረ አላየሁም ስለጉዳዩም አልናገርም ብለህ ራስህን ታታልላለህ? ይሔ መቼም ቢሆን ተቀባይነት የሌለው አስተሳሰብ ነው።›› አለና የቀዳውን ቢራ ተጎነጨ፡፡ ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹ያለውን ችግር መካድ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ነገር ግን መጥፎውን ብቻ ሳይሆን ጥሩውንም እዩ፤ ሁልጊዜ መጥፎውን እያያችሁ ከምታንቋሽሹ ደጉንም እያያችሁ አሞካሹ። እያልን ነው፡፡ አንተ እና አንዳንዶች ግን ሁልጊዜም ከመጥፎ ወይም ከተሠራ ስሕተት ውጭ ጥሩ እና የተሠራ መልካም ተግባር አይታያችሁም፡፡ ይሄ ደግሞ እናንተን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ሀገርንም ይጎዳል፡፡›› ሲል ሃሳቡን ገለፀ፡፡

ዘውዴ ከመብረድ ይልቅ ይበልጥ ቁጣው አየለ። ‹‹እናንተ ስትል እነማንን አካተህ ነው? አልገባኝም›› ሲል ተሰማ ላይ አይኑን እያፈጠጠ፡፡ ተሰማ ፈገግ ብሎ፤ ‹‹እናንተማ ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጪ እየኖራችሁ ከእኛ በላይ ኢትዮጵያዊ የለም ብላችሁ የምትፎክሩ የተለየን ኢትዮጵያዊ ነን ባዮቹ፤ በተግባር ግን ኢትዮጵያን የማትወዱ፤ አንድ ሰው ሲሞት እልፍ አለቀ እያላችሁ የሞት ዜናንን የምታራግቡ እናንተ ናችሁ። ኢትዮጵያ ግድብ ስትገነባ የምትቃወሙ፤ የባሕር በር ስታገኝ አይናችሁ ደም የሚለብሰውን ማለቴ ነው፡፡

አንዳንዴ ለሀገራችሁ አምባሳደር መሆን ሲገባችሁ በሰው ሀገር ሆናችሁ ሳይቀር የሀገራችሁን ስም በውሸት የምታጠፉ፤ ሠላም እያለ ሠላም የለም እያላችሁ ቱሪስት የኢትዮጵያን ምድር እንዳይረግጥ የምታስፈራሩ…›› ብሎ ሊቀጥል ሲል ሃሳቡን ሳይጨርስ ዘውዴ ከመቀመጫው ተነሳ፡፡

ተሰማ የዘውዴን ከመቀመጫው መነሳት ተከትሎ ወደ ላይ አየው፡፡ ዘውዴ ሰውነቱ እየተንቀጠቀጠ‹‹ እንከባበር እንደእዚህ የማለት መብት የለህም፡፡›› ሲል ገብረየስ የዘውዴን ትከሻውን ይዞ አስቀመጠው። አንገቱን አስረዝሞ ወደ ላይ ሲያየው የነበረው ተሰማም አይኑን እና አንገቱን ወደ ታች ሰበር አድርጎ፤ የተቀመጠውን ዘውዴን ማየት ጀመረ፡፡ ዘውዴ፤

‹‹አምባሳደር የሚሆነው የሀገሩ ዲፕሎማሲያዊ ተወካይ እንጂ ሀገር ውስጥ ቁጭ ብዬ የመንግሥት ተቀጣሪ ሆኜ በማይረባ ደሞዝ የማገለግለው እኔ ዘውዱ አምባሳደር አይደለሁም፡፡ መሆንም አልችልም፡፡›› አለ።

ተሰማ በበኩሉ ለዘውዴ፤ ‹‹ተረጋጋ እንዲህ በትንሹም በትልቁም መበሳጨት እድሜ ከማሳጠር ውጪ ትርፍ የለውም፡፡ ለነገሩ አንተም ሆንክ የትኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገራቸው እና በተላኩበት ሀገር መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር ከሚላኩት አምባሳደሮች በተጨማሪ ሁላችንም አምባሳደር መሆን እንዳለብን አይካድም፡፡›› ሲለው ዘውዴ ንዴቱ ትቶት መሳቅ ጀመረ። ‹‹በእርግጥ አምባሳደሮች በኢትዮጵያ እና በተላኩበት ሀገር መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር ከመሥራት በተጨማሪ በአካባቢያቸው ስላለው ማንኛውም የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ እድገት የሀገራቸውን መንግሥት አዘውትረው ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል። ይህንን እየሠሩ ነው? መልሱን ራሳቸው ይመልሱት። እኔ ግን እዚህም ኖርኩ እዛ ያልተሾምኩበትን እኔን አምባሳደር ነህ ብለህ እንደአምባሳደር ሥራ ማለት ለእኔ ከማሾፍ የተለየ አይደለም፡፡›› ሲል አምባሳደር ስላልሆነ የሀገሩ አምባሳደር ሆኖ የመሥራት ግዴታ እንደሌለበት እና ፍላጎት እንደሌለው አስረዳ፡፡

ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹አየህ ከእኛ በላይ ኢትዮጵያዊ የለም ትላላችሁ፡፡ በተቃራኒው ስለሀገራችሁ መናገር እና መሥራት አትፈልጉም፡፡ ሀገር ውስጥ እንደ አምባሳደር ላትታሰብ ትችላለህ፡፡ ወይም አምባሳደር ሆነህ እንድትሠራ ብዙ ግድ ላይሠጥህ ይችላል፡፡ ነገር ግን ሀገር የሚያዋርዱትን ልትገስፅ ይገባል፡፡ በውጭ ስትኖር ደግሞ የበለጠ ‹ስንቅህን በአህያ አመልህን በጉያ› እንደሚባለው ኢትዮጵያዊነት እንዳይዋረድ ገበናችንን መደበቅ ሲኖርብህ በተቃራኒው ገበናችንን በማውጣት ራስን ለውርደት መዳረግ ትክክል አይደለም፡፡ ነገር ግን በተደጋጋሚ ብዙዎች ይህን ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ አንተም ከሀገር ብትወጣ ያው ነህ፡፡

ሀገር መውደድ ሌላ፤ መንግሥት መጥላት ሌላ ሁለቱም የተለያዩ ናቸው፡፡ ነገር ግን የወቅቱን መንግሥት የጠሉ ሰዎች ለሀገራቸው አምባሳደር ከመሆን ይልቅ በተቃራኒው መንግሥት ይወርዳል ብለው ሕዝብ እንዲተላለቅ የሚሠሩት ሥራ እና የሚያስተላልፉት መልዕክት እጅግ ያሳፍራል፡፡ አንዳንዶች በማኅበራዊ የትስስር ገፅ የሀገር ምስጢርን አሳልፈው እስከመግለፅ ይደርሳሉ፡፡ አሁን አሁንማ አንድ የመንግሥት አካል ለሀገር የሚጠቅም ዜና ሲያበስር ማጥላላትን እንደመልካም ሥራ ወስደውታል፡፡

ቻይናዊ በፍፁም ቻይናን የሚያዋርድ ንግግር አይናገርም፡፡ ሀገር ለማዋረድ አይዳዳውም፡፡ ቢገፋም፤ ቢጨቆንም ችግሩን ዋጥ አድርጎ ችግር የሚፈታበትን መላ ይመታል፡፡ ሲሆን ሲሆን ሀገሩን የሚጠቅም ቴክኖሎጂም ሆነ መረጃ ሰርቆ ለሀገሩ ሕዝብ ኑሮ መሻሻል እና ዕድገት ሚናውን ይወጣል፡፡ አንድ አሜሪካዊ አሜሪካንን ያስቀድማል እንጂ ሌላውን ሀገር አስቀድሞ አሜሪካንን አዋርዶ አይናገርም፡፡

ለአገር መስዋዕት መሆን ቢያቅተን እንኳ እንዴት የሀገራችን ጠላት እንሆናለን? ይህንን በብዙ መልኩ አየዋለሁ፡፡ የትም ብንሔድ መጨረሻችን ሀገራችን ናት። ሀገራችን ብትከበር ለእኛም ክብራችን ነው። ለቱሪዝም የሚመች ሥራ ሲሠራ የቱሪዝሙን ዘርፍ ዕድገት ከማስተጋባት ይልቅ፤ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የተሠራውን ሰበብ እየፈለጉ ማጥላላትን ሙያ አድርገው የወሰዱ ብዙ ናቸው፡፡›› ብሎ አንዳንዶች የሚፈፅሙት ተግባር ፍፁም አንድ ሀገሩን ከሚወድ ሰው የሚጠበቅ አለመሆኑን አስረዳ፡፡

ገብረየስም በበኩሉ፤ ‹‹ አዎ! እኛ ኢትዮጵያውያኖች ሀገራችንን የምንወደው በምላስ እንጂ በተግባር አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በየማኅበራዊ የትስስር ገፅ የምናሳየው ስለሀገራችን ሕዝብ መልካም ባሕል እና እሴት ሳይሆን ሀገር ውስጥ ስላለው ግጭት አባብሰን ጎብኚ ደፍሮ ሀገር ውስጥ እንዳይመጣ የሚያደርግ ነው። ሐቁን ከመግለፅ ይልቅ ውሸት ላይ እንጠመዳለን።

በአጠቃላይ ጊዜ ወስደው የውሸት ሃሳብ ቀርፀው ኢትዮጵያን ለማጥላላት የሚደክሙ እና ኢትዮጵያዊ ነን ብለው የሚናገሩ ሰዎች መኖራቸውን ማሰብ እጅግ አድካሚ ነው፡፡ አንገትን ደፍቶ በድህነት መኖር እንዲቀጥል፤ ኢትዮጵያ ዘላለሟን በልመና እና በርዳታ ላይ ተንጠልጥላ እንድትዋኝ የሚፈልጉ ስለመኖራቸው መካድ አይቻልም፡፡ ለእኔ እነዚህ ፍፁም ኢትዮጵያዊ አይደሉም፡፡ ስለዚህ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ስለሀገሩ መልካም መልካሙን ያውራ፤ መልካም መልካሙን ያስተዋውቅ ይህ ሲሆን ሀገር ያድጋል፤ ሀገራችንን የፈለግንበት ደረጃ ላይ ማድረስ እንችላለን፡፡ ከድህነት ተላቀን የበለፀገች ሀገር እናደርጋታለን፡፡ ምሬት እና ውሸት ተሸክመን ያንንም ለሌሎች እያሻገርን ከቀጠልን ሀገራችንን እንቀብራታለን፡፡ ሀገር ተቀብራ የሚተርፍ ኢትዮጵያዊ አይኖርም፡፡ ሁሉም ይቀበራል፡፡›› ሲል ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ከመማረር ይልቅ ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ይሥራ ሲል ሃሳቡን ገልፆ የጠጡበትን ለመክፈል እጁን ወደ ኪሱ ከተተ፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን  ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You