በጎ ተስፋ ይዞ የመጣው ስምምነት

ሪቻርድ ፓንክረስት ጥንታዊ ነጋዴዎች በጉዞ ማስታወሻቸው ያሰፈሯቸውን ጥንታዊ ፅሁፎች በመሰብሰብ ‹‹ኢትዮጵያ ከቀይ ባህርና ከህንድ ውቅያኖስ ማዶ›› በሚል ርዕስ ፅሁፍ አስነብበው ነበር:: በዚህ ፅሁፋቸው ከአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ መካከለኛው ዘመን ድረስ ህንድና ኢትዮጵያ በቀይ ባህርና በህንድ ውቅያኖስ በኩል ጠንካራ የንግድ ልውውጥ ያደርጉ እንደነበር አስፍረዋል::

በኤደን ባህረ ሰላጤ በኩልም ኢትዮጵያ ጠንካራ የንግድ ልውውጥ ታደርግ እንደነበር ፤አንድሬ ያኩሳል የተባለ ጥንታዊ የቬነስ ነጋዴ ያሰፈረውን ማስታወሻም አጣቅሰው ጽፈዋል ፤ ጸሀፊው በየመን ጠረፍ ላይ የምትገኘውን የኤደን ወደብ ዋንኛው የአረቢያና የኢትዮጵያ ወደብ ሲል በጽሁፊ ማስፈሩንም እንዲሁ ::

ሀገረ ኢትዮጵያና የባህር በር ታሪክ ሲነሳ የኋልዮሽ ሺህ ዘመናትን ሊሻገር ይችላል:: በየመንግስታቱ የይገባኛል መብት ሲነሳበት ሙግትና ድርድር አበቅ የለሽ እልህ አስጨራሽ ግንኙነት ሲደረግበት :: ከደርግ መንግስት በኋላ ግን ሀገሪቱ ያላት የባህር በር መብት ተቋርጦ ከርሟል:: የዜጎች ቁጭትም እያደር ሲባባስ ነው የመጣው::

ባለፉት ሶስት አስርት አመታትም የጅቡቲን ወደብ በመጠቀሟ ለወጪና ገቢ ንግድ በየአመቱ በርካታ ገንዘቦችን ለጅቡቲ ፈሰስ አድርጋለች:: አሁን ያለውን አመታዊ ክፍያ እንኳ ብንመለከት ከ164 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል:: ይህ ደግሞ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ምን ያህል ተፅእኖ እያሳደረ መሆኑን መረዳት ይቻላል::

የባህር በር አልባነት የወለደው የዜጎች ቁጭት ከዚህ በፊት ታላቅ ከነበርን አሁንም ታላቅ መሆን እንችላለን የሚል መንፈስን ያዘለ ነው:: ኢትዮጵያ ከሱዳን አንስቶ እስከ ታንዛኒያ ድረስ ያሉትን ወደቦች መጠቀም የምትችልባቸው በርካታ አማራጮች አሏት:: ከከበቧት ሀገራት ጋር ተወያይታ፣ተነጋግራ ሰጥቶ በመቀበል መርህ የባህር በር ታገኝ ዘንድ ቀጠናዊ ውይይት እንደሚያሻ ግልፅ አድርጋለች::

የባህር በር ጥያቄዋን በድርድር በሰጥቶ መቀበል እና በሰላማዊ አማራጭ የዲፕሎማሲ ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቃለች:: የኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚ መሆን ከራስ ጥቅም አልፎ ለቀጠናው ሀገራት ዘላቂ ሰላምና የጋራ ተጠቃሚነት የላቀ አስተዋፅኦ አለው፡

ሀገራት ባላቸው የቆዳ ስፋት መጠን ከተለያዩ ሀገራት ጋር ይዋሰናሉ:: በዚህም ምክንያት በባህር በር አጠቃቀም ረገድ የተለያዩ ስምምነቶችን በመፈፀም የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ስራንም ይተገብራሉ:: አንዳንድ ሀገራት ደግሞ ልዩነታቸውን በውይይት መፍታት ባለመቻላቸው ምክንያት ለጦርነት ሲዳረጉ ይስተዋላል:: እ.ኤ.አ በ1879 ቦሊቪያ እና ፔሩ በጋራ ሆነው ከቺሊ ጋር ያደረጉት ‹‹ዋር ኦፍ ፓስፊክ›› የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው ጦርነት ተጠቃሽ ነው::

ክስተቱ ከግጭት ይልቅ ስምምነት አማራጭ የሌለው ተመራጭ መፍትሄ መሆኑን ታይቶበታል::በአለማችን ከሚገኙ ሀገራት መካከል 169ኙ አለም አቀፍ የባህር ስምምነትን ተፈራርመዋል:: ሀገራችን ኢትዮጵያም የዚሁ አካል ናት:: ኢትዮጵያ ከሰላሳ አመታት በኋላ ያጣችውን የባህር በር ተጠቃሚነት ጥያቄዋ አሁን ላይ ዋንኛ አጀንዳ አድርጋ ይዘዋለች:: ጥያቄዋም በጎ ምላሽ ማግኘት ጀምሯል::

የባህር በር ለአንድ ሀገር ምጣኔ ሀብታዊ እድገትና ስትራቴጂያዊ ጥቅሙ የጎላ መሆኑ ይታወቃል:: በአለማችን የሚገኙና የባህር በር ባለቤት የሆኑ ሀገራት በየአመቱ ከዘርፉ በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብትን ከኪራይ ገቢ ያገኛሉ ። በተቃራኒው የባህር በር ያላቸው ሀገራት ወደ ሀገራቸው ለሚያስገቡትና ለሚያስወጡት ሸቀጦቻችው ምንም አይነት ክፍያ ባለመክፈላቸው በቢሊዮን የሚቆጠር ወጪ ያድናሉ::

አሁን ላይ ኢትዮጵያ በበርካታ መሰረተ ልማቶቿ በመገንባት ፤ ለከአካባቢው ሀገራት ጋር ሁለንተናዊ ትብብርና የልማት ትስስር እየፈጠረች ነው:: የባህር በር ጥያቄዋም የዚህ አብሮ የመልማት ጉዳይአካል ነው:: የሀገሪቷ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲም ቢሆን መልካም ጉርብትናን፣ የጋራ ተጠቃሚነትን፣ አጋርነትንና ትብብርን መሰረት ያደረገ ነው::

በአለም አቀፉ የሀገራት ግንኙነት ውስጥ ትልቅ ስፍራ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ዋናው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ነው:: ኢኮኖሚያዊ ፣ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ የሚባሉት ዘርፎች እንዳሉ ሆነው ዲፕሎማሲው ግን ሁሉንም የማስተሳሰርና የማጣመር ሀይል አለው::

ወታደራዊ ጡንቻ ከዲፕሎማሲያዊ ውጤት ውጪ ሌሎችን ከማስፈራራትና በሌሎች ከመጠላት የዘለለ ውጤት የለውም:: የኢኮኖሚ የበላይነትም ከዲፕሎማሲ ውጪ የራሱን ምቾት ከመስጠት ተሻግሮ በሌሎች ዘንድ ከበሬታንና ተፈላጊነትን አያመጣም:: ዲፕሎማሲ ግን እነዚህን ወደራሱ በፍቅር የመሳብ ሀይል ይኖረዋል::

ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ያላት ከበሬታ ለብዙ ድሎች እያበቃት ነው:: ለጊዜው ሌሎቹን አቆይተን ባሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያ ከሱማሌ ላንድ ጋር ያደረገችው የወደብ ስምምነት ትልቅ የዲፕሎማሲ ትግል ውጤት ነው:: ዲፕሎማሲ ዝምብሎ ከሰማይ የሚወርድ ሳይሆን የብዙ ድሎች ውጤት ነው::

ሀገራት ኢትዮጵያን አጋራቸው አድርገው ሲቀበሏ ስለምታስፈልጋቸው እና ስለምትጠቅማቸው ነው:: የድሮ ገናናነቷና ታሪኳ እንዳለ ሆኖ በተለይ የአሁኑ አያያዟን አስቀጥላ ወደፊት የምትደርስበት ደረጃን በመተንበይ ሀገራት እንደአንድ አጋር እንዲመለከቷት አድርጓቸዋል::

በተለይም ከሱማሌ ላንድ ጋር ያደረገችው የወደብ ስምምነት ትልቅ ጥቅም ይዞላት መጥቷል:: በየአመቱም 25 በመቶ በላይ ገቢዋን የምትገብርለት የወደብ ጉዳይ በዚሁ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍትሄ ማግኘት ጀምሯል ማለት ነው:: በሌላት የውጭ ምንዛሬ በየአመቱ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ ስትከፍል ቆይታለች:: ገንዘቧን ከፍላም ቢሆን መጉላላቶች አሉባት:: የገቢዋም ሆነ የወጪዋ ሚስጥር የማይጠበቅ ነው:: እነዚህ ሁሉ ስብራቷ ሆነው ቆይተዋል::

ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷ መፃኢ እድሏ በቀጠናው ላይ የሚወሰን መሆኑን ያሳየ ነው:: በቀጠናው ያለው ተለዋዋጭ የፖለቲካ የሀይል አሰላለፎችና ልዩ ልዩ ኩነቶች የሚከሰትበት በመሆኑ ብሄራዊ ፍላጎቷንና ጥቅሟ ላይ ተፅእኖ የሚያደርጉ ጉዳዮችን በቅርበት መከታተል እንድትችል ያደርጋታል:: ለወጪ ገቢ ንግዷ የተሳካ እድል ይፈጥራል:: ከምንም በላይ በአካባቢው ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የነበራትን ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚና መልሶ የሚያቀናጃት ይሆናል::

የጋራ ተጠቃሚነት ማዕቀፍ ውስጥ ያለፈው የኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚነት ጥያቄ ጉዞ ብዙ ነገሮች ተብለውበታል:: በተለይ የብዙ ህዝብ መኖሪያ ሆና ድንበሯ ከባህር ርቆ መቆለፉ ተጠቃሚነቷ ላይ ጫና ሲያሳድር ቆይቷል:: የባህር በር ተጠቃሚነት ጥያቄዋ ከህዝብ እና ከቆዳ ስፋት አንፃር ተገቢ ሆኖ የቆየ ነው:: አሁን ምላሽ ማግኘት መጀመሩ ከፖለቲካዊ እስከ ማህበራዊ ጉዞዋ በዛው ልክ የሚወስን ይሆናል::

በቀጠናው ያሉ ሀገራት የውስጥ የፖለቲካ ትኩሳቶች በሚፈጥሯቸው ኩነቶች አካባቢውን ወደ አለመረጋጋት እየወሰደ ባለበት በአሁኑ ሰአት፣ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በሌላው አለምም መሰል ግጭቶች በስፋት እየታዩ ባለበት ወቅት ከሱማሌ ላንድ መንግስት ጋር የተደረሰበት የመግባቢያ ስምምነት ለአካባቢው ዘላቂ ሰላምም የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ ነው ።

ይሄ ስምምነት ለሁለቱም ሀገራት፣ ለአካባቢው፣ ለአፍሪካና ለአለም ሁሉ የሚሰጠው ትርጉም ታላቅ ነው:: ሰላምን ከማስፈን ኢኮኖሚን ከማሳለጥ የህዝብ ለህዝብ ትብብርን ከማጎልበት አንፃር የሚታይ ለውጥን ያመጣል:: በተለይ ኢትዮጵያ ወታደራዊ ካምፕን መመስረት መቻሏ ጠንካራው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በቀጠናው የሚካሄዱ የሽብርና የባህር ላይ ውንብድና ድርጊትን እንዲከላከል ያስችለዋል:: ይህም ለአለም ሁሉ እረፍት ነው:: ለኢኮኖሚያዊ ውህደት መነሻ ሆኖ ቀስበቀስ አፍሪካ ለያዘችው ለ2063 አጀንዳ መሳካት ግንባር ቀደም ሚና ይኖረዋል::

ኢትዮጵያ በምትገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ነገሮች በሚፈለገው መልኩ ሲሆኑ አልተመለከትንም:: በቀሪው አለም አካባቢው የሚታወሰው ባለመረጋጋትና ሰላም ማጣት ውስጥ መሆኑ የአደባባይ ሚስጢር ነው:: እናም አሁን ኢትዮጵያ በዚህ ደረጃ የምታደርገው ቀጠናዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት የባህር በር ስምምነት ድርሻ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም::

በጋራ መግባባት ውስጥ ተጠቃሚነት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል:: በሀገራት መካካል የሚደረግ ስምምነት በዛው ልክ ቀጣይ የሚኖርን ቀጠናዊ አንድምታ መወሰኑ የሚካድ አይሆንም:: ሁለቱ አካላት ያደረጉት ስምምነት የሚገኙበትን አካባቢ ስምን መለወጥ ላይ አቅሙ ከፍ ያለ ይሆናል::

የአፍሪካ ቀንድ ሲባል የሚታወቀው በግጭት ነው:: በቀጠናው ሀገራት ተሳስረው ተጣምረው፣ ዘላቂ ሰላምን፣ ዘላቂ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስምምነትን ማድረግ አልተለመደም:: የቀጠናው ሀገራት እርስ በርስ በመተሳሰር ለኢኮኖሚ እድገት የበቁትን ሀገራት ተሞክሮ ሲወስዱ አይታይም::

ነገር ግን የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የብዙ የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤቶች ናቸው:: የአፍሪካም ሆነ የአለም ጂኦፖለቲክስ እየተቀየረ የሚሄደው በመሆኑ የሚያዋጣው አብሮ በጋራ መስራት መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል:: ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር ያደረገችው የመግባቢያ ስምምነት እንደተሞክሮ የሚወሰድ ነው:: ከዚህ በኋላ በቀጠናው ትስስርን ማጠናከሪያ ማሳያ ነው::

40 በመቶ ቀጠናዊ የቆዳ ሽፋንና 80 በመቶ የህዝብ ብዛት ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የምትወከልበት ቁጥራዊ ሀቅ ነው:: ከእሷ ጋር የሚደረጉ ስምምነቶች ትርፋቸው በዚህ አካባቢ ላሉ ሀገራትም ሲሆን ነው የቆየው::አሁን የተደረገው የወደብ ስምምነት ጥቅም በሂደት የሁሉም መሆኑ አይቀርም::

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሁሉንም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሚስብ አቅም ያለው ነው :: ይሄን የመሳብ በጎ አስተዋፅኦ /ፑል ፋክተሩን/ ማንም ሊያስቆመው አይችልም:: ስምምነት በወታደራዊ ፣ በመረጃና በመሰል ጉዳዮች ሌሎች የአካባቢው ሀገራትን በማገዝ ትብብር እንዲጠናከር ሊያደርግ እንደሚችልም ይታመናል :: ከህም ባለፈ ሀገራቱ ለጋራ እድገት በተለያ ዘርፎች አብረው የሚሰሩበትን አዲስ የትብብር ምእራፍ የሚከፍት ነው ::

በቀጣይም የአካባቢው ሀገራት ፤በመተማመንና በጋራ ተጠቃሚነት ከኢትዮጵያ ጋር ሊኖራቸው የሚችለው የትብበር ግንኙነት የቀጠናው ሀገራት ህዝብ ሁሉ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ::ለዚህም ነው ኢትዮጵያ የሰጥቶ መቀበል መርህን በመከተል ሀገራት በራሳቸው ብቻ ሳይሆን አብሮ በሚደረግ ተሳትፎ ተጠቃሚነታችንን እናረጋግጥ ስትል የቆየችው::

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ጥር 1/2016

Recommended For You