እውቅና ሊሰጠው የሚገባውየአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት!

 የኢትዮጵያ ግብርና ከጊዜ ወደ ጊዜ በአፈር ማዳበሪያ ላይ ጥገኛ እየሆነ መጥቷል:: አርሶ አደሩ በሰብል ልማት ላይ ማዳበሪያ የመጠቀሙ ጉዳይ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ መሬቱ ያለአፈር ማዳበሪያ አያበቅልም:: በዚህም የአርሶ አደሩ የግብርና ሥራ በአፈር ማዳበሪያ ላይ ጥገኛ እየሆነ መምጣቱ ይነገራል።

ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር ግብርናውን ማዘመንና የአፈር ማዳበሪያን በተገቢው ጊዜና ወቅት ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት አስፈላጊ ነው:: ማዳበሪያ በወቅቱና በሚፈለገው ልክ ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ካልተቻለ መሬቱ ጾም እንዳደረ የሚቆጠርበት ሁኔታ ተፈጥሯል::

‹encyclopedia of soil science› እንደሚያትተው፤ ማዳበሪያ ሰብሎች ለጥሩ እድገት የሚያስፈልጉትን ንጥረ ነገሮች ያቀርባል:: አፈሩ በአነስተኛ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ለረጅም ጊዜ የታረሰ ከሆነ፤ ማዳበሪያ መጠቀም ተጨማሪ እና የተሻለ ጥራት ያለው ምርት እንዲመረት ማረጋገጫ ነው::

የአፈር ማዳበሪያ መጠቀሙ አርሶ አደሮች አዲስ የእርሻ መሬት ፍለጋ የሚያደርጉትን ደን ምንጣሮ በመቀነስ ማዳበሪያን መጠቀም በአነስተኛ ቦታ ላይ ከፍተኛ ምርት እንዲገኝ ያደርጋል:: ይህ ሲሆን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ፈተና አይሆንም::

የግብርና ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ማዳበሪያ በቀጥታ የዕፅዋትን ዕድገት የሚያፋጥን የአፈር ውስጥ አልሚ ምግብ አቅርቦትን የሚጨምር ተፈጥሮአዊ ወይም ማዕድናዊ ንጥረ ነገር ነው:: ማዳበሪያን በሰብል እርሻ ወይም ማሳ ላይ በመጨመር ምርታማነትን ማሳደግ ይቻላል::

እንደ ዩክሬን፤ ሩሲያና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት አሁን ለደረሱበት የዕድገት ደረጃ ዋና መሠረታቸው ግብርናን በአግባቡ በመጠቀማቸው ነው:: ይህም የአፈር ማዳበሪያን በራሳቸው አቅም አምርተው ከራሳቸው አልፈውና ተርፈው ለአፍሪካ ሀገራት ከማቅረብ ባሻገር ስንዴም በርዳታ መልክ ይሰጣሉ::

ኢትዮጵያ የሀገራትን ተሞክሮ በመቀመር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ደፋ ቀና ማለት ከጀመረች ውላ አድራለች:: ለዚህ እንደማሳያ የሚሆነው የአፈር ማዳበሪያን በወቅቱ በማቅረብ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ማሳደግ ነው:: ባለፈው በጀት ዓመት ከተከሰተው የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ክፍተት ትምህርት በመውሰድ በ2016/2017 የምርት ዘመን በተገቢ ጊዜ ለማቅረብ ግብርና ሚኒስቴር በዕቅድ እየሠራ ይገኛል::

በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ከጊዜ ወደ ጊዜ አርሶ አደሩ ማዳበሪያ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ የምታስገባው የአፈር ማዳበሪያ መጠን ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ። የኢትዮጵያ አፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም በ1960ዎቹ ውስጥ 35ሺ ኩንታል የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ከ17 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ደርሷል።

በ2008/2009 የምርት ዘመን የኢትዮጵያ አፈር ማዳበሪያ ዓመታዊ ፍጆታ አምስት ሚሊዮን 800 ሺ ኩንታል ሲሆን፣ ከአምስት ዓመት በኋላ በ2013/14 የምርት ዘመን 17 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ተጠቅማለች። ባለፉት አምስት የምርት ዓመታት ኢትዮጵያ የተጠቀመችው ማዳበሪያ በየዓመቱ እያደገ መጥቶ በአምስት ዓመት ውስጥ ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ እድገት አሳይቷል።

የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ፍላጎት ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ መጥቷል:: ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለፈው 2015/2016 የምርት ዘመን ዩክሬንና ሩሲያ በገቡበት ግጭት ምክንያት የአፈር ማዳበሪያ ወቅቱን ጠብቆ ሀገር ውስጥ ባለመግባቱ እጥረት ተከስቶ ነበር:: አንዳንድ ወገኖች ጉዳዩን የፖለቲካ አጀንዳ ለማድረግ የሄዱበት መንገድ የሚታወስ ነው ::

‹ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ› እንዳይሆን መንግሥት ከባለፈው ስህተት ትምህርት በመውሰድ የ2016/17 የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ስርጭትን ቀድሞ አቅዶ እየሠራ ነው:: የግብርና ሚኒስቴር የባለፉት አምስት ወራትን የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ ከሳምንታት በፊት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው ለ2016/17 ምርት ዘመን 23 ሚሊዮን 383ሺ 910 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ አቅዶ እየሠራ ነው::

በመሆኑም በተፈቀደው የ930 ሚሊዮን ዶላር እና 71 ነጥብ 44 ቢሊዮን ብር 19 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ፈጽሞ ለማስገባት እየሠራ ነው:: ይህም ባለፈው ዓመት ከተገዛው 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል አንጻር ከፍተኛ ጭማሪ አለው::

እስከአሁን በድምሩ የ15 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ኤን ፒ ኤስ ዝርያ እና ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈፅሟል:: ወደ ሀገር ውስጥ እየተጓጓዘ ያለ የማዳበሪያ መጠን እስከ ታኅሣሥ ዘጠኝ ቀን 2016 ዓ.ም በድምሩ ከ380ሺ ሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ ደርሷል::

ጅቡቲ ከደረሰው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ እስከ ታኅሣሥ 9/2016 ዓ.ም ድረስ በድምሩ 255ሺ 206 ነጥብ 50 ሜትሪክ ቶን ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዟል:: በቀጣይ እስከ ጥር አጋማሽ ድረስ 262ሺ ሜትሪክ ቶን የጫኑ አራት መርከቦች ጅቡቲ ወደብ ይደርሳሉ:: ወደ ኅብረት ሥራ ማኅበራት የተጓጓዘ የአፈር ማዳበሪያ መጠን 63ሺ 825 ነጥብ 48 ሜትሪክ ቶን ነው:: ለመስኖ ልማት የሚውለው 20ሺ 639 ነጥብ 78 ሜትሪክ ቶን ለተጠቃሚው መሰራጨቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል::

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ባወጣው መረጃ ደግሞ ለ2016/17 የምርት ዘመን ከውጭ ከተገዛው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ እስከ ታኅሣሥ 20/2016 ዓ.ም ድረስ በዘጠኝ ዙሮች 4ሚሊዮን 380 ሺህ ኩንታል ጅቡቲ ወደብ ደርሷል::

ከዚህ ውስጥ 3 ሚሊዮን 618 ሺህ 212 ኩንታል ማዳበሪያ ከወደብ ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዞ በመሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበር አማካኝነት ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ ነው:: እስከ ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም በሦስት መርከቦች ተጨማሪ ሁለት ሚሊዮን 90 ሺህ ኩንታል ኤን ፒ ኤስ፣ ኤን ፒ ኤስ ቦሮን እና ዩሪያ ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ እንደሚደርስ የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል::

ወቅቱን የጠበቀ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ሲኖር የአርሶ አደሩን ምርታማነት ይጨምራል:: ስለሆነም የአፈር ማዳበሪያውን ማቅረብ ብቻ በቂ ባለመሆኑ ከፌዴራል እስከ ታችኛው የቀበሌ የኅብረት ሥራ ማኅበር ድረስ በተገቢው ሁኔታ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን መከታተል አስፈላጊ ነው::

ይህ ሲሆን ገበሬው ከቅሬታ ነጻ ከመሆኑም ባሻገር በአላስፈላጊ መንገድ ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እንዳይከሰት የሚረዳ መሆኑ ልክ እንደ አቅርቦቱ ሁሉ ከትትልና ቁጥጥሩም ሊጠናከር ይገባል:: በተጨማሪም ዓለም ተለዋዋጭ በሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ እንደመሆኑ መጠን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ዘላቂ የሆነ መፍትሔ እንዲሰጠው በራስ አቅም የሚመረትበትን ሁኔታ ማመቻቸት ተገቢ ነው::

በግርማ ሞገስ

አዲስ ዘመን ጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You