ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች የውድድር ዓመቱን በስኬት ጀምረዋል

በአዲሱ የአትሌቲክስ የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ሳምንት በመላው ዓለም በርካታ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ተከናውነዋል። በተለያዩ ርቀቶች በተደረጉት በእነዚህ ውድድሮች ላይም እንደተለመደው በርካታ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ተካፍለው ውጤታማ መሆን ችለዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ የቻይናው የዚመን ማራቶን ሲሆን፤ በሁለቱም ጾታዎች አሸናፊ በመሆን ውጤታማ ጅማሬን አስመዝግበዋል።

የዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ ከሰጣቸው ዋናዎቹ የማራቶን ሩጫዎች መካከል አንዱ እና በዓመቱ የመጀመሪያው በሆነው በዚህ ውድድር ሁለተኛው ፈጣን ሰዓትም ተመዝግቧል። የሩጫው አሸናፊ የሆነው ኢትዮጵያዊው አትሌት አሰፋ ቦኪ ፈታኝ በነበረው ውድድር ተፎካካሪዎቹን በጥቂት ሰከንዶች ብቻ በመቅደምም ነው ባለ ድል የሆነው።

አትሌቱ የገባበት ሰዓት 2:06:46 ሲሆን፤ እአአ በ2015 በኬንያዊው አትሌት ከተመዘገበው የቦታው ክብረወሰን 27 ሰከንዶችን ብቻ የዘገየ ነው። ሁለተኛ ደረጃን የያዘው ኬንያዊ አትሌት ፍሊክስ ኪርዋ 2:06:52 የሆነ ሰዓት ሲያስመዘግብ፤ ሞሮኳዊው ኦትማን ኤል ጎምሪ ደግሞ 2:07:18 በሆነ ሰዓት ሶስተኛ ሆኗል። በዚህ ውድድር ተሳታፊ የነበሩት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አዳነ ከበደ እና አለነ መኮንን በበኩላቸው አራተኛና አምስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

በሴቶች መካከል በተደረገው ውድድር ደግሞ በግማሽ ማራቶን የምትታወቀው አትሌት በቀለች ጉደታ አሸናፊ ልትሆን ችላለች። የ26 ዓመቷ አትሌት ርቀቱን 2:22:54 በሆነ ሰዓት ስትሸፍን የግሏን ፈጣን ሰዓትም አሻሽላለች። ሁለት ደቂቃዎችን ዘግይታ የገባችው ሞሮኳዊቷ ፋጢማ ኢዛህራ ሁለተኛ፤ እንዲሁም ቻይናዊቷ ዣንግ ዴሹን ደግሞ ሶስተኛ ሆነዋል። ሌሎቹ ኢትዮጵያዊያን አያና ሙሊሳ እና ጉልሜ ጫላ ደግሞ አራተኛ እና ስድስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

በሳምንቱ መጨረሻ ከተካሄዱ የማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ የዱባይ ማራቶን ነው። ለዓመታት የዱባይ ማራቶንን በበላይነት ማጠናቀቅ የቻሉት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ደግሞ ዘንድሮም እንደተለመደው ተከታትለው በመግባት በአሸናፊነት መፈጸም ችለዋል። በውድድሩ ታሪክ የላቀ የማሸነፍ ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አይበገሬነት በሁለቱም ጾታ የተረጋገጠ ሲሆን፤ በተለይ በሴቶች በኩል የቦታውን ክብረወሰን በመሰበሩ በሁለቱም ጾታዎች የፈጣን ሰዓት ባለቤቶች ኢትዮጵያዊያን ሆነው ሊመዘገቡ ችለዋል።

ሜዳማ በሆነ ስፍራ የሚካሄደው የዱባይ ማራቶን ፈጣን ከሆኑ የጎዳና ሩጫዎች መካከል አንዱ በመሆኑ በአትሌቶች በእጅጉ ተመራጭ መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም ታዋቂ እና ጀማሪ አትሌቶች በዚህ ውድድር በስፋት ተሳታፊዎች ናቸው። በአዲሱ የፈረንጆቹ ዓመት የመጀመሪያ ሳምንት በተካሄደው በዚህ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው አትሌት ትዕግስት ከተማ 2:16:07 ሰዓት በመግባት ነው የርቀቱን ክብረወሰን ከኬንያዊቷ አትሌት ሩት ቸህፕጌቲች እጅ ልትረከብ የቻለችው።

ኬንያዊቷ አትሌት እአአ በ2019 ውድድሩን 2:17:08 በሆነ ሰዓት በመሸፈኗ የፈጣን ሰዓት ባለቤት ብትሰኝም፣ ከአንድ ደቂቃ በላይ ፈጥና በገባችው 25 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ብልጫ ተወስዶባታል። ትዕግስት በዚህ ሰዓት በማራቶን ታሪክ ስምንተኛዋ ፈጣን ሴት ሯጭ ስትሰኝ የ80ሺ ዶላር ተሸላሚም ሆናለች። አምና በዚህ ውድድር ሁለተኛ የወጣችውና በበርካታ ማራቶኖች ተሳትፎዋ የምትታወቀው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሩቲ አጋ ዘንድሮም ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። አትሌቷ ከትዕግስት በሁለት ደቂቃዎችም ነው ዘግይታ የገባችው። በዚህ ውድድር ዘንድሮም ለሁለተኛ ጊዜ አሸናፊ ትሆናለች የሚል ቅድመ-ግምት ያገኘችው አትሌት ደራ ዲዳ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች። እስከ 12ኛ ያለው ስፍራም ከሁለት የሌላ ሃገር አትሌቶች ጣልቃ ገብነት በቀር በኢትዮጵያዊያን የተያዘ ሆኗል።

በተመሳሳይ በወንዶች በኩልም ኢትዮጵያዊያኑ ተከታትለው በመግባት የበላይነቱን ሲቆጣጠሩ አትሌት አዲሱ ጎበና የሃገሩን ልጆች በማስከተል አሸናፊ ሊሆን ችሏል። በጠንካራ ፉክክር መታጀቡን የሚያመለክተው ውድድሩ እጅግ ተቀራራቢ የሆነ ሰዓት የተመዘገበበት ሲሆን፤ 2:05:01 የሆነው ሰዓት አትሌቱን ባለድል ሊያደርገው ችሏል። በ19 ሰከንዶች ብቻ የተቀደመው አትሌት ለሚ ዱሜቻ ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ፤ ደጀኔ መገርሳ ደግሞ በ41 ሰከንዶች ዘግይቶ ሶስተኛ ሆኗል። በርካታ ቁጥር ያላቸው ሌሎች ኢትዮጵያዊያንም ተከታትለው በመግባት የውድድሩን ፍጹም የሆነ የበላይነት ተቆጣጥረዋል።

ከሳምንት በፊት በስፔን በተካሄደ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ላይ አሸናፊ የነበረው ወጣት አትሌት በሪሁ አረጋዊ በድጋሚ ሌላኛው የዙር ውድድር ላይም አሸናፊ በመሆን ድሉን ማጣጣም ችሏል። በስፔን እየተካሄደ በሚገኘውና በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ በተሰጠው የሃገር አቋራጭ ቱር ውድድር ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኘው አትሌቱ በጭቃማውና ፈታኝ በሆነው ውድድር ሳይረታ 30:34 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብም ነው አሸናፊ የሆነው።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2016

Recommended For You