ከሀብት መመዝበሪያነት፣ ወደ ሀብት ማፍሪያነት

ለሀገር ልማት የሚበጁ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የመንግሥትና የሕዝብ ቁርጠኝነት፣ የተፈጥሮና የመሳሰሉት ሀብቶች፣ የተማረ የሰው ኃይል፣ ገንዘብ፣ በዋናነት አስፈላጊ በመሆን ሊጠቀሱ ይችላሉ። እነዚህ የልማት ግብዓቶች አንዱ ለአንዱ ወሳኝ ቢሆኑም፣ ሁሉንም ግን ያለ ገንዘብ ማሰብ ይከብዳል።

የቱንም ያህል የተፈጥሮ ሀብት ቢኖር፣ ያለ በቂ ገንዘብ ልማት ውስጥ ዘሎ አይገባም። የቱንም ያህል የተማረ የሰው ኃይል ቢኖር፣ የቱንም ያህል የሕዝብና መንግሥት ቁርጠኝነት ቢኖር ያለ ገንዘብ ሊታሰብ የሚችል ልማት አይኖርም። የመልማት ፍላጎትና የማልማት አቅም እየተጤነ ወደ ልማት የሚገባውም ለእዚህ ነው።

ኢትዮጵያም ከሀገር ውስጥ ከተለያዩ ምንጮች መሰብሰብ በምትችለው ሀብት፣ ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ካደጉት ወዳጅ ሀገሮች ልታገኛቸው በምትችላቸው ብድርና እርዳታዎች እንዲሁም ሕዝቧን አስተባብራ ልታገኝ በምትችለው ሀብት ልክ ነው ማልማት ውስጥ ስትገባ የቆየችው። እነዚህ የልማቱ ምቹ እድሎች ተደርገው ሲወሰዱ ቆይተዋል። በልማቱ ምቹ ሁኔታዎቹ ብቻ አይደለም ታሳቢ ተደርገው ሲታዩ የነበሩት፣ ስጋቶችና መፍትሔዎቻቸውም ጭምር ናቸው።

ሀገሪቱ የበርካታ እምቅ ሀብቶች ባለጸጋ ናት። በግብርናው፣ በቱሪዝሙ፣ በማዕድኑ፣ በውሃ ሀብቱ ወዘተ እምቅ ሀብት ሞልቷታል። ይህ ሀብት በእምቅ ሀብትነት መኖሩ ምቹ ሁኔታ ከሚባሉት መካከል ሊጠቀስ ይችላል። ሀብቱ ብቻውን ግን የልማት ፋይናንስ ሲሆን አልተመለከትንም፤ በኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ለማለት ነው። የከብት ሀብታችንን እየቆጠርን፣ የውሃ ሀብታችንን እየጠቀስን፣ ምቹ የአየር ንብረትና ለም አፈር ያለን መሆኑን እየጠቀስን ከመኖር የዘለለ ያፈራነው ሀብት ብዙም አለመኖሩም ይህንኑ ያመለክታል።

እርግጥ ነው እነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች ለልማቱ ዋስትና ሊሆኑ ይችላሉ። በአንዳንድ ሀገሮች እንደ ነዳጅ ያሉት የተፈጥሮ ሀብቶችን የውጭ ኩባንያዎች የሚያለሙት ይህ ሀብት ሲወጣ ለተወሰኑ ዓመታት አብዛኛውን እጅ ለመውሰድ የሚያስችላቸውን ስምምነት እያደረጉ ነው ይባላል።

ይህ ሁኔታ በሀገራችን መሬት ያላቸው የእኩል እንደሚያሳርሱት አይነት ማለት ሊሆን ይችላል። ድርጅትን እንደ ማከራየት አይነት ማለትም ሊሆን ይችላል። ወደፊት የሚሆነውን ባላውቅም፣ እኛ በውጭ ኩባንያዎች እንደ ነዳጅ ያሉ ተፈጥሮ ሀብቶችን በሆነ እጅ ለተወሰነ ጊዜ ለማልማት የሰጠነው ኩባንያ ያለ አይመስለኝም።

የተፈጥሮ ሀብቶቻችንንም ሆነ ሌሎች ሀብቶቻችንን ላለማልማታችን ምክንያቶቹ ብዙ ሊሆኑ ቢችሉም፣ አንዱ ምክንያት ሆኖ የሚጠቀሰው በቂ ገንዘብ አለመኖር ነው። እነዚህን የተፈጥሮና የመሳሰሉትን ሀብቶች ለማልማት እርሾ በመሆን የሚያገለግል በቂ ገንዘብ ያስፈልጋል። ከዚህ በሚገኘው ገንዘብ አንዱን ባንዱ እንዲሉ ደግሞ ሌላውን ማልማት ይቻላል። በመሆኑም ለእኛ ሀገር ልማት ገንዘብ ወሳኙ ግብዓት ነው።

ይህን ሀብት ማግኘት ላይ ሀገሪቱ ብዙ ጥረት አድርጋለች፤ እያደረገችም ትገኛለች። በግብር መሰብሰቡ፣ ከውጭ ብድርና እርዳታ በማፈላለጉ፣ ዜጎች በልማቱ በስፋት እንዲሠማሩ በማድረጉ ላይ ሠርታለች። በዚህም ለውጦች እንዳሉ ይታወቃል፤ የዓባይ ግድብን ያህል በዓለምም በአፍሪካም ተጠቃሽ ፕሮጀክት ማልማት የተቻለው በሕዝብና በመንግሥት ሀብት መሆኑ ለእዚህ አንድ ሁነኛ ማሳያ ነው።

እንደ ሀገር ያለው የልማት ፍላጎት ከፍተኛ ቢሆንም፣ ለእዚህ የሚሆነው ሀብት ውስን በመሆኑ ሳቢያ የተወሰነውን ጥያቄ ለመመለስ ሲሠራ ቆይቷል። ለእዚህ ምክንያቶቹ ለልማትና ለመሳሰሉት ሊውል የሚችለው ሀብት ማግኛ ከሆኑት መንገዶች መካከል አንዱ የሆነው የግብር አሰባሰብ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ደካማ የሚባል ነበር። ኢኮኖሚው የሚያመነጨው ገቢ እየተሰበሰበ ስላለመሆኑ መንግሥትም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም ሲያሳስቡ ቆይተዋል።

ለውጭ ገበያ የሚቀርቡት አብዛኛዎቹ ሸቀጦቻችን ዛሬም የግብርና ምርቶች ናቸው። እርግጥ ነው እንደ ወርቅ ያሉት ማዕድናት ለውጭ ገበያ ሲቀርቡ ኖረዋል፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አልባሳትና የኤሌክትሪክ ኃይል ለውጭ ገበያ እየቀረቡ ናቸው። ከእነዚህ የሚገኘው ሀብት ብዙ ሊያግዝ ቢችልም፣ በቂ የሚባል ግን አይደለም።

የውጭ ብድርና ርዳታ ሌላው የልማቱ ፋይናንስ ነው። በእነዚህም መንገዶች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የኃይል ማምንጫዎች ተገንብተዋል። ይህን ብድርና ርዳታ የሚዘውሩ ሀገሮችና ተቋማት በሚፈጥሩት ጫና ብድርና ርዳታው በሚፈለገው ልክና ጊዜ ለሀገሪቱ የማይደርስበት ሁኔታ እንደመኖሩ፣ አስተማማኝ የልማት አቅም ተደርጎ ሊያዝ አይችልም።

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወቅት እነዚህ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ በፈጠሩት ጫና ኢትዮጵያ እነዚህን ጥቅሞች እንዳታገኝ መደረጓ ይታወቃል። በእዚህ ዓይነቱ ሁኔታ የቅርብ ጊዜው ከፋ እንጂ አበዳሪ እና ለጋሽ ተቋማትና ሀገሮች በሀገሪቱ ላይ በሚፈጥሩት ጫናዎች የተነሳ በውጭ ብድርና እርዳታ ግኝት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ሲያሳርፉ ቆይተዋል።

በብዙ ፈተና የሚገኘውን ሀብት ታሳቢ በማድረግ ሀገሪቱ የአስርና የአምስት ዓመት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ አዘጋጅታ በርካታ ፕሮጀክቶች ቀርጻ ወደ ትግበራ ገብታ እንደነበርም ይታወቃል። የታየው ለውጥ ግን ብዙም አልሆነም። ከተወሰኑት በስተቀር አብዛኛዎቹ መክነዋል፤ ቆመው ቀርተዋል። ለምን ብሎ መጠየቅ ጥሩ ነው።

ያ ዘመን በሀገራችን ከፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ ብዙ ድክመት የታየበት ዘመን ነበር፤ የዚያ ዘመን የፕሮጀክቶች በሽታ በርካታ ፕሮጀክቶች እንዳይሆኑ አርጓል። የሀገሪቱን የስኳር ችግር ይቀርፋሉ ተብለው በርካታ የስኳር ፕሮጀክቶች ተጀምረው እንደነበር ይታወሳል። የሀገር ውስጥ ፍጆታን ከመሸፈን አልፈው ስኳር ለውጭ ገበያ የሚቀርብበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ብዙ የተባለላቸው ቢሆንም፣ ዛሬ እጃችን ላይ የገባ ነገር የለም።

ፕሮጀክቶቹ የሀገር ውስጥ የስኳር ፍጆታን ሊመለሱና ለውጭ ገበያ ስኳር ሊያቀርቡ ቀርቶ ራሳቸውን የማያድኑ የእንጨት ምንቸት ሆነው ቀርተዋል። የዚህች ድሃ ሀገርና ሕዝብ ሀብት የተንዳሆ ስኳር ልማትን በሚል አሸዋ ውስጥ ቀርቷል፤ ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ ገቡ ከተባሉት የስኳር ፕሮጀክቶች ስኳር ብልጭ ብሎ ድርግም ከማለቱ ውጪ የታየ የሀገር ችግር የሚፈታ ምርት አልታየም። እየተሰማ ያለው ሀገሪቱ ስኳር ከውጪ እያስገባች መሆኑ ነው።

በያዩ የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት በሚል ስም የሀገር ሀብት መቀመቅ ገብቷል። አሁንም ድረስ የሚጨናበሱ የመስኖ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ይታወቃል። የዚያ ዘመኑ ዘረፋ ዜጎች ከአፋቸው ክፍለው ለዓባይ ግድብ ግንባታ ያዋጡትንም አልማረም። ከፕሮጀክቶቹ ፍሬውን ማጣጣም የተቻለው በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨቱ በኩል በተያዙ ፕሮጀክቶች ናቸው።

እነሱም ውጤታማ መሆን የቻሉት በለውጡ መንግሥት ቁርጠኛ አመራር ነው። የዓባይ ግድብ ግንባታ የለውጡ መንግሥት ባይደርስለት ኖሮ እጣ ፈንታው ከፍ ብለን ከጠቀስናቸው ፕሮጀክቶች መካከል ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም። የለውጡ መንግሥት ለእዚህ ፕሮጀክት በነፍስ ደርሶለትና እስትንፋስ ዘርቶበት ዛሬ ለደረሰበት ታላቅ ምዕራፍ አብቅቶታል።

የእዚያ ዘመን የግንባታ መጓተት ችግር ሀገሪቱን ግንባታ የሚጓተትባት ሀገር አርጓት ቀርቷል። ችግሩ ቀደም ባሉት ዓመታት በተነቃቃ ሁኔታ ውስጥ የነበረውን የግንባታውን ኢንዱስትሪ ስም ጭምር ሰብሮታል። ትላልቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች ያሏቸው ተቋማት /መንግሥትን ጨምሮ/ በሀገሪቱ የግንባታ ተቋራጮች ላይ እምነት እንዳያድርባቸው አርጓል።

በሌለው አቅም አለው ተብሎ በተቋራጭነት እንዲኮፈስ የተደረገው ሜቴክ መሪዎችና ፕሮጀክቶቹን በባለቤትነት ፣ በተቆጣጣሪነት ወዘተ ሲመሩ የነበሩ አካላትና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው በታቀደ አግባብ የፕሮጀክቶቹን ሀብት ፈንጭተውበታል። ሜቴክ ሀገሪቱን እዳ አስታቅፎ ቢጠፋም መሪዎቹ በአንድም ይሁን በሌላ ሀብት አካብተውበታል። በዚህ የተነሳ ፕሮጀክቶቹ አንድ እርምጃ ሳይጓዙ የተመደበው በጀት እያለቀ ተጨማሪ በጀት ሲጠየቅባቸው ኖረዋል።

በፕሮጀክቶች ላይ የተፈጸመው ጥፋት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ንቃቃት እስከ መሆን ደርሷል። በንቃቃቱ ውስጥ ጥቂት የማይባሉ የውጭ የግንባታ ተቋራጮች የገቡበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ኩባንያዎቹ ለምን ወደ ሀገሪቱ መጡ አላልኩም፤ መግባት ያለባቸው የኛዎቹ አቅም በማጣታቸው ሳቢያ ሲሆን ግን ያማል። የውጭ ኩባንያዎች መምጣትን በሚገባ መጠቀም ከተቻለ ለእውቀትና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ስለመሆኑ የመንግሥትም እምነት ነው፤ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ተዋንያንም እምነት እንደሚሆን አስባለሁ።

በፕሮጀክቶች ላይ የደረሰው ስብራት ጥሎት ያለፈው ጠባሳ የግንባታ ኢንዱስትሪውን ክፉኛ ጎድቶታል፤ የሀገሪቱ የግንባታ ተቋራጮች መንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሲያስብ ላወዳድራቸው ቢል እንኳ ተወዳድረው የሚያልፉ አይነት አይደሉም እየተባሉ ነው። በኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ላይ ያ ሁሉ ችግር የተፈጠረው ለፕሮጀክቶች የተመደበውን ሀብት ለመቀራመት የተሠማሩ አካላት በፈጸሙት ሙስና ነው።

ሀገሪቱ ለፕሮጀክቶቹ የሚያስፈልገውን ሀብት መድባ ወደ ትግበራ ገብታ ባለችበት ሁኔታ ፕሮጀክቶች ችግር ውስጥ የገቡት ለፕሮጀክቶች በሚያስፈልግ የሀብት እጦት ሳይሆን በሀብት መዝባሪዎች ሳቢያ ነው። ሀገሪቱ ምንም እንኳ ለልማት የምታውለው በቂ ሀብት ሳይኖራት፣ የልማቱን አስፈላጊነት ግምት ውስጥ በማስገባት ከዚህም ከዚያም ብላ የመደበችው ሀብት ነው ለእዚህ የተዳረገው። ፕሮጀክቶቹ እንዳይጠናቀቁ ያደረገው የሀብት አለመመደብ ሳይሆን የገንዘብ ቀበኞቹ በመክፋታቸው ነው።

በአንጻሩ ከለውጡ ወዲህ የሚገነቡ በርካታ የመንግሥት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሲጠናቀቁና ወደ አገልግሎት ሲሸጋገሩ እየተመለከትን ነው። ይህ ብቻ አይደለም አንዳንድ ከለውጡ በፊት የተጀመሩና ሲጓተቱ የቆዩ ፕሮጀክቶችም የዚህ እድል ተቋዳሽ እንዲሆኑ ተደርገዋል።

ይህን መመልከት በራሱ አንድ ለውጥ ነው። መንግሥት ግንባታቸው የተጓተተ እንደ ዓባይ ግድብ ያሉትን ፕሮጀክቶች ችግር በማጥናትና መፍትሔ በማስቀመጥ ያከናወናቸው ተግባሮች እንዲሁም በራሱ አቅዶ በመጀመር ያጠናቀቀቸውና እያጠናቀቃቸው የሚገኙ ፕሮጀክቶች ፕሮጀክትን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ማሳያ ተደርገው ብቻ የሚወሰዱ አይደሉም፤ ለግንባታ መጓተት ምክንያት ከሆኑት መካከል የሚጠቀሰውና ይህን ተከትሎ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ለገባው የግንባታው ኢንዱስትሪ እስትንፋስ እፍ የተባለባቸው ናቸው ማለትም ያሰኛል።

በተደጋጋሚ መመልከት እንደተቻለው፤ ከለውጡ ወዲህ መንግሥት የያዛቸው ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እየተጠናቀቁ ይገኛሉ። የዓባይ ግድብም ከዚያ የውድቀት አፋፍ ወጥቶ መብራት መሆን መጀመሩ፤ የኢንዱስትሪዎችን የኃይል ፍላጎት ጥያቄ ለመመለስም እያገዘ መሆኑ ለእዚህ በአብነት ሊጠቀስ ይችላል። አምና ኃይል ወደ ማመንጨት ከተሸጋገሩት ሁለት የኃይል ማመንጫዎች በተጨማሪ አምስት ማመንጫዎች ዘንድሮ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ይጠበቃል። ይህ ሁሉ የሆነው የለውጡ መንግሥት ፕሮጀክቱን ከወድቀት ለመታደግ ባደረገው ርብርብ ነው።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተባባሪነት ተገንብተው ወደ ሥራ ከገቡ ዓመታት ያስቆጠሩት የገበታ ለሸገሮቹ አንድነት፣ ወዳጅነት እንዲሁም እንጦጦ ፓርኮች በምን አይነት ፍጥነት ተገንብተው ወደ ሥራ እንደገቡና ለቱሪዝሙ ዘርፍ መነቃቃት ጉልህ አስተዋፅዖ እያበረከቱ መሆናቸው ይታወቃል።

በገበታ ለሀገር ከተጀመሩ ፕሮጀክቶች የኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነው በዳውሮ ዞን የተገነባው የሀላላ ኬላ ሪዞርት ተመርቆ ወደ ሥራ ገብቷል፤ በቅርቡ ደግሞ የዚሁ የኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነው የዳና ሎጅ ግንባታ ተጠናቆ ተመርቋል። የወንጪ ደንዲ የኤኮ ቱሪዝም ፕሮጀክትም እንዲሁ በቅርቡ እንደሚመረቅ ይጠበቃል። የጎርጎራ ፕሮጀክትም ግንባታው እየተካሄደ ይገኛል። ሌሎች በርካታ ተመሳሳይ ስምንት ፕሮጀክቶችን በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት በተለያዩ ክልሎች ለመገንባት ታቅዶ የአንዳንዶቹም ሥራ ተጀምሯል።

በአዲስ አበባ ከተማም በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል፤ የሳር ቤት ጎፋ ማዞሪያ ጎተራ መንገድ ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳል። የቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ፕሮጀክት ከፋይናንስ አቅራቢው የውጭ ድርጅት ጋር ፋይናንስ አለማቅረብ ጋር በተያያዘ መጓተት ታይቶበት ቢቆይም፣ የከተማ አስተዳደሩ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የመንገዱን ግንባታ ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ማድረስ ተችሏል። የመንገዱ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ሳይጠበቅ አገልግሎት እንዲሰጥም ነው የተደረገው፤ በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይም እንዲሁ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት መጠናቀቅ ብቻ ሳይሆን በፍጥነት አገልግሎት እንዲጀምሩ ሲደረጉም እየተመለከትን ነው።

የመስቀል አደባባይ፣ የአብርኆት ቤተመጽሐፍት፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ የአንድነት ፓርክ የተሽከርካሪ ማቆሚያ፣ የግብርና ምርቶች ግብይት ማዕከላትና የመሳሰሉትና ሌሎች ግንባታቸው እየተካሄደ የሚገኝ በርካታ ፕሮጀክቶችም እንዲሁ ከዚሁ አኳያ የሚታዩ ናቸው። ፕሮጀክቶቹ ዘመናዊ፣ የከተማዋን ገጽታ በእጅጉ ሊገነቡ የሚችሉ፣ በግንባታ ወቅትና አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ያስቻሉም ናቸው። በመሬት አጠቃቀም በኩልም እንዲሁ በምድር ውስጥ በርካታ ተሽከርካሪዎችን ማቆም የሚችሉ ግንባታዎች ናቸው።

የእነዚህ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቅ ግንባታ ሲጓተትባት ለቆየችው ኢትዮጵያ ግንባታ ተጀምሮ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። ግንባታ ፈጥኖ ተጠናቀቀ ማለት በግንባታ መጓተት ሳቢያ ተጨማሪ ሀብት እየተጠየቀባቸው ከፍተኛ በጀት የሚያስወጡ ፕሮጀክቶች እንዳይፈጠሩ ማድረግ ይቻላል ማለት ነው።

ከለውጡ ወዲህ ወደ ግንባታ ገብተው በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ትምህርት ለሚቀስማባቸው ጥሩ ትምህርት ቤቶች መሆን የሚችሉ ናቸው። በተለይ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ተዋንያን ይህን ትምህርት ቤት መቀላቀልና ዘርፉን ለመለወጥ መሥራት ይኖርባቸዋል። ከእነዚህ ግንባታዎች አንዳንዶቹ በሀገር ውስጥ ተመራጮች አንዳንዶቹ በውጭ ተቋራጮች ነው የተገነቡት። የተገነቡት ግን እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው።

የግንባታው ዓውድ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ ብሎ መጠየቅና የራስን አሰላለፍ ማስተካከል ከኮንስትራክሽን ዘርፉ ተዋንያን ይጠበቃል። ለእዚህ ደግሞ ጥናት ማድረግ፣ አቅማቸው የት ቦታ ላይ እንደሆነ መለየት፣ ከለውጡ ወዲህ ግንባታቸው የተጠናቀቀና ወደ ሥራ የገቡ እንዲሁም ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ ለመግባት የተቃረቡ ፕሮጀክቶች ተቋራጮችን አሠራር መቃኘት ይኖርባችኋል።

እስከ ለውጡ ድረስ ፕሮጀክቶች የሙሰኞች የሀብት ምንጭ ሆነው ቆይተዋል። የእነዚህ ሁሉ ፕሮጀክቶች ሀብት በተለያየ ደረጃ ባሉ ሙሰኞች ተዘርፏል። ፕሮጀክት ሲታሰብ መንግሥትና ሕዝብ የሚጠብቃቸው ስለመሆናቸው ሳይሆን፣ በፕሮጀክቶቹ ዙሪያ ያሉ ሌቦች ሀብታቸውን የሚቀራመቷቸው ተደርገው ሲታዩ ቆይተዋል።

ሀገሪቱ የቱንም ያህል ውስን ሀብት ቢኖራት፣ ለልማት ፕሮጀክቶቿ ትኩረት በመስጠት ሀብት ስትመድብ ኖራለች፤ ችግር ሆኖ የነበረው ይህን ሀብት በአግባቡ አለመጠቀም ላይ ነው። አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ይህን ለመለወጥ እየሠራ ነው፤ ለውጦችንም እያሳየ ይገኛል።

አሁን ነገሮች ተቀይረዋል። ፕሮጀክቶች የሙሰኞች የሠርግና ምላሽ መፈንጠዣዎች ሳይሆኑ የመንግሥትና ሕዝብ ጥያቄ መመለሻዎች መሆን ጀምረዋል። ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ ለፕሮጀክቶች የተመደበውን ሀብት በሚገባ ሥራ ላይ በመዋል ነው። ሌላው ለፕሮጀክቶች በጊዜ መጠናቀቅ ምክንያት ተብሎ መያዝ ያለበት የፕሮጀክቶች ባለቤቶች ፕሮጀክቶችን ነጋ ጠባ እየጎበኙ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ ያለበት ሁኔታ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና(ዶ/ር) ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፕሮጀክቶችን በመጎብኘትና በመከታተል ሊጠቀሱ የሚገባቸው ናቸው።

 ዘካርያስ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2016

Recommended For You