ከገና ባሻገር

ገና ወይም በዓለ ልደት አልያም ብርሀነ ልደት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ ታኅሣሥ 29፣ በየአራት ዓመቱ ደግሞ ታኅሣሥ 28 ቀን የሚከበር ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓል ነው። ገና እየሱስ ክርስቶስ የአዳምን ዘር ሁሉ ለማዳን ከሰማይ ሰማያት ወርዶ በመንፈስ ቅዱስ ከድንግል ማሪያም በበጎች ግርግም የተወለደበት ልደት የሚዘከርበት ዕለት ነው። ለዚህ ነው የበዓላት ሁሉ በዓል ተደርጎ የሚወሰደው። የገና ስረወ_ ቃል (መነሻ) የበዓሉ ሁሉ ንጉሥ ፣ ታላቅና ገናናነት ከሚገልጸው “ገናና” ከሚለው ቃል የሚመዘዝ ነው። እየሱስ ክርስቶስ በይሁዳ ቤተልሔም ሲወለደ ከነገሥታቱና ከመሳፍንቱ ከእነ ሔሮድሰ ተሰውሮ ለእረኞች ተገልጧል።

እረኞችም ከመልዓክት ጋር “ስብሀት ለእግዚአብሔር በሰማያት …” ሲሉ ለክብሩ ዘምረዋል። አዋቂዎቹ ሰብዓ ሰገሎች የከበረ ስጦታ ይዘው በቤተመንግሥት ሲፈልጉት በበጎች ግርግም ነበር የተገኘው። እነዚህ ተምሳሌቶች እየሱስ ክርስቶስ ራሱን ዝቅ አድርጎ በእግዚአብሔርና በሰው ልጅ መካከል ቆሞ የነበረውን የጥል ግድግዳ ለማፍረስ፤ እርቅን ሰላምን ለማውረድ መምጣቱን ያበስራል። ገናን ለ2015 ዓመታት ጊዜ ስናከብረው ፍቅሩንና ሰላሙን ልብ አላልነውም። አልኖርነውም። ገናን ከቅርጫው ከዳቦው፣ ከድግሱና ሸቀጥ ከመሰጣጣት ባሻገር የልደቱን አብይ አላማ አልኖርነውም። በተለይ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በሀገራችን የተከሰተው ቀውስ፣ ጭፍጨፋና የመረረ ጥላቻ ይሄን የሚያረጋግጥ ነው። እስኪ በብርሀነ ልደቱ መስኮት የሌሎችን ባህላዊ ወረቶቻችን cultural capital አኳኋንና አከራረም እንቃኝ።

በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚከበሩ መንፈሳዊና ባህላዊ ሁነቶች የተሸከሙትን ግዙፍ መልዕክቶችና አንድምታዎች አለፍ አለፍ ብለን እየተመልከትን ሂሳብ እናወራርድ። ፍቼ ጨምበለላ፣ ቡሔ ፣ ሻደይ ፣ አሸንዳ፣ ሶለል አይነ ዋሬ ፣ እንቁጣጣሽ ፣ መስቀል ፣ መስቀላዮ፣ አጋመ፣ ጊፋታ፣ ኢሬቻን ፣ ጋሮ፣ ቺሜሪ፣ ትንሳኤ፣ ወዘተ… በአንድም በሌላ በኩል በተለያዩ የሀገራችን ማኅበረሰቦች የሚከበሩ ሃይማኖታዊ ወይም ባህላዊ ክዋኔዎች ናቸው። ሁሉም ማለት ይቻላል ተስፋን ፣ ፍቅርን፣ ነፃነትን ፣ አብሮነትን ፣ አንድነትን ፣ ምስጋናን ፣ እርቅን ፣ ይቅርታን፣ እኩልነትን ፣ ወዘተረፈ… የሚያውጁ፣ የሚለፍፉና የሚሰብኩ ናቸው።

ግን በነቂስ ወጥተን ለዘመናት በየዓመቱ በአደባባይ የምናከብራቸው የምንዘክራቸውን ያህል በዕለት ተዕለት ኑሮአችን አንኖራቸውም። አንለማመዳቸውም፡፡ ይሁንና ከገጠሙን ቀውሶች ፣ ፈተናዎች መውጣት ማገገምና ማንሰራራት የቻልነው በቀሩን ሽርፍራፌ እንጥፍጣፌ በባህላዊ ንብረቶቻችን social capital መሆኑን ልብ ይላል። ባለፉት 27/50 ዓመታት ቀን ከሌት ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ እንደ ተሰበከው ልዩነት ፣ ጥላቻና ዘርኝነት ቢሆን ኑሮ እርስ በእርስ ተበላልተናል። ተጨራርሰናል። ለዚህ ነው መዳኛችን ፣ ማገገሚያችንና ማንሰራሪያችን የሆነውን ባህላዊ ወረት ወደ ሙላቱ መመለስ ለነገ የሚባል ጉዳይ የማይሆነው።

ባህላዊ ወረታችን ለበጎ አላማ ሲውል ሀገርን ከጥፋት ከእልቂት እሳት እንደሚታደግ በጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች ተመልክተናል። የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች እሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ ለበቀል ተነስቶ የነበረውን የአርባ ምንጭና የአካባቢውን ወጣት ለምለም ሳር ይዘው ተንበርክከው በመለመን ቁጣውን አብርደው መልሰውታል። ይህን የሀገር ሽማግሌዎች ገድል በጥሞና ለተረዳው የአርባ ምንጩን እሳት ብቻ አይደለም ያጠፉት የአርባ ምንጩን ጥፋት ተከትሎ በመላ ሀገሪቱ ሊዛመት የነበረውን የበቀል ሰደድ እሳት ጭምር እንጂ። ቁጣ አብራጁ ይህ የጋሞ አባቶች ልመና (ጋሞ ወጋ) እየጠፋ ፣ ትኩረት እየተነፈገው ያለው ባህላዊ ወረታችን ተጠብቆ ለትውልድ ሲተላለፍ ሀገርን እንዴት ማዳን እንደሚችል ጥሩ ማሳያ ነው።

የጋሞ አባቶች ከአራት ዓመት በፊት ልዩ የበጎ ሰው ተሸላሚ መሆናቸው በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ ያለ አንዳንች ልዩነት ዳር እስከዳር አድናቆትን ተቀባይነትን ያተረፈው በዚህ እሳቤ ነው። ሕግን ለማስከበር ከምናደርገው ጅምር ጥረት ባልተናነሰ በየአካባቢው እንደ ጋሞ ወጋ ዓይነት የሽምግልና ፣ የእርቅ ባህላዊ ካፒታሎቻችንን ላይም መሥራት ይጠበቅብናል። ከዚህ መሳ ለመሳ የአክራሪነት አዝማሚያ ፣ እኩይ አስተሳሰብ እንዲገታ ብሎም ተሸንፎ ከሰላምና ከእርቅ መንገድ ገለል፣ ዘወር እንዲል ድልብ የሆኑ የባህላዊ ንብረቶቻችን ወረቶች የማይተካ ሚና አላቸው።

ሁሉም ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ባህላዊ ወረቶች ባለፀጋ ስለሆኑ የየራሳቸውን መዋጮ ማበርከትና ወደ ሥራ መግባት ይጠበቅባቸዋል። በየአካባቢያችን፣ በየቀዬአችን የምናንፀው፣ የምናቀነቅነው ከባቢያዊ ብሔርተኝነት ወደ አክራሪነት፣ ፅንፈኝነት የሚያንደረድር ወደ ገደል አፋፍ የሚገፋ ስለሆነ እነዚህን ባህላዊ ወረቶች በመጠቀም መግታት ያስፈልጋል። የዜጎች ማንነት እሴት እንደተከበረ ወደ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት የሚያደርሰንን ቀና መንገድ በቅንነት መቀላቀል ፣ መያያዝ ይገባል።

ይህ ሀገራዊ ብሔርተኝነትም ከገደቡ ፣ ከውሃ ልኩ እንዳያልፍ ጥንቃቄ ማድረጉ እንዳለ ሆኖ። አይደለም ዘውጌአዊ ፣ ወንዜአዊ ብሔርተኝነት ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት በአግባቡ ካልተያዘ ፤ የጎረቤቱን የሚጎመጅ፣ የሚመኝ ፣ የሚመቀኝ ሆኖ የመውጣት አደጋ ስላለው በብልሀት ፣ በማስተዋል ሊቀነቀን ይገባል ። በዛድባሬ ይመራ የነበረው “የታላቋ ሶማሊያ” አክራሪ ብሔርተኝነት ለዚህ ጥሩ አብነት ነው፡፡ የናዚው አዶልፍ ሒትለር የአርዓያም ዘር ልፋፌ ነቢብ በዓለማችን ላይ ያስከተለው እልቂትና ቀውስም አይዘነጋም።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ጥንታዊ መሆኗን የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ። ከ3000 እሰከ 8000 ዓመት የሚደርስ ታሪክ ባለጸጋ እንደሆነች ይታመናል። ጥንታዊነቷ የዳበረ ሀገረ መንግሥት ባለቤት አድርጓታል። የደለቡ ባህላዊ ወረቶች መናኸሪያም ናት። ባህል፣ ባህላዊ ንብረትስ ምንድን ነው የሚለውን ለመግባቢያ ያህል እንመለከታለን። ባህል ሁሉንም የሚያስማማ የሚያግባባ ወጥ የሆነ ትርጉም ብያኔ ባይኖረውም የአንድ ማኅብረሰብ ወይም ሕዝብ ዕምነት፣ ልማድ ፣ ወግ በኪነ ጥበብ እና በሥነ ጥበብ ተዳውሮ፣ ድርና ማግ ሆኖ ፣ ተሸምኖ፣ ተንሰላስሎ የመገኘት ፣ የመገለጥ ዥጉርጉር ሕብራዊ ደማቅ ቀለም ነው።

በደስታ ፣ በሀዘን ፣ በሥራ ፣ በሃይማኖት፣ በትምህርት ፣ ወዘተ… የሕይወት አንጓዎች ይገለጻል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የተዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ባህልን፦ የኅብረተሰብ የአኗኗር ዘዴ ፣ ወግ ፣ ልማድ ፣ እምነት ፣ … ። በማለት ሲተረጉመው። የደስታ ተክለ ወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት በበኩሉ ባህል፦ ልማድ፣ ደንብ ሲል ይፈታዋል፡፡

ባህላዊ ንብረት ( cultural capital ) የሚለው ሀረግ ፔሬ ቦርዴው በተባለ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ የተነሳ የሥነ ኅብረተሰብ ተመራማሪ እንደተፈጠረ የተለያዩ የዘርፉ ድርሳናት ያትታሉ። ባህላዊ ንብረት በማኅበረሰብ ውስጥ ያለን ተቀባይነት ቦታ ከፍ ለማድረግ ዕውቀትን ፣ ፀባይና ክህሎትን የማሳደግ የማካበት ሂደት ነው። ባህላዊ ንብረት በግለሰብ፣ በማኅበረሰብ ከፍ ሲልም በሕዝብ በሀገር ይሰላል። የበለፀገ ባህላዊ ንብረት ያካበተ ግለሰብ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ከፍ እንደሚያደርገው ሁሉ ያደገ የለማ ባህላዊ ንብረት ያለው ማኅበረሰብ ሕዝብ በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍ ያለ ተቀባይነት ይኖረዋል።

ባህል ማለትም የኅብረተሰብ የአኗኗር ዘዴ ፣ ወግ፣ ልማድ ፣ እምነት ፣ ወዘተ… በሂደት በዕውቀትና በክህሎት እየበለፀገ ፣ እየዳበረ ሲሄድ ለሀገር ሰላም፣ አንድነት ከፍ ሲልም እድገት የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። በተቃራኒው ባህል በዕውቀት ፣ በክህሎት ካልበለፀገ አይደለም ለሀገር ሰላምና ዕድገት መዋል ይቅርና የማኅበረሰቡን እሴቶች ጠብቆ ማቆየት ካለማስቻሉ ባሻገር የዕለት ተዕለት ችግሮችን እንኳ መፍታት የሚሳነው ይሆናል። ባህላዊ ንብረት እንደ ኢኮኖሚያዊ ንብረት ማለትም ገንዘብ በአግባቡ ኢንቨስት ተደርጎ ሰላምን ፣ ፍቅርን ፣ እርቅን፣ መነጋገርን ፣ መቀባበልን ፣ መከባበርን ፣ መተባበርን፣ አንድነትን ፣ ወዘተ . እውን ማድረግ ካልተቻለ እንደባከነ እንደከሰረ ሊቆጠር ይችላል።

ሀገርን ሕዝብን ከግጭት ፣ ከቀውስ፣ ከመፈናቀል፣ ከመጠራጠር ፣ ከጥላቻ ፣ ከበቀል ፣ ወዘተ . መታደግ አልቻለማ። እስኪ ለአንድ አፍታ ባህሎቻችንን እምነቶቻችንን ወይም ባህላዊ ንብረቶቻችንን ከዚህ አኳይ እንመዝናቸው። ባክነዋል ወይስ በአግባቡ ሥራ ላይ ውለዋል ! ? አሁን ከምንገኝበት ሀገራዊ ቁመና አንጻር ባክነዋል ቢባል የሚያስኬድ ይሆናል። ታዲያ እነዚህን ባህላዊ ንብረቶቻችንን እንደ ጦር ዕቃ ለብሶ እንደ ጥሩር ደፍቶ መውጣት መግባት ፣ መመላለስ ለምን ተሳነን !? መልሱ ቀላል ነው። ላይ ላዩን እንከውናቸዋለን እንጂ አንኖራቸውም። በቃል እናነበንባቸዋለን እንጂ በልባችን አላተምናቸውም።

ባልንጀራህን ፣ ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ የሚሉ አብርሃማዊ እምነቶችን ማለትም ክርስትናን ፣ እስልምናንና አይሁድን እየተከተልን እንዴት በጥል ግድግዳ ተለያየን !? በአንድ አምላክ በዋቄ ፈና እያመንን ኢሬቻን በየዓመቱ እያከበርን እየከወን ይቅር መባባል ለምን ተሳነን !? መልሱን ለማግኘት ሚስጥሩን ለማወቅ ሞራ ማስገለጥ ወይም ኮከብ ማስቆጠር አያሻም። መልሱ ቀላል ነው። እሱም ባህላዊ ንብረቶቻችንን በሳጥን ቆልፈን እንደ ክት ልብስ በየዓመቱ በዓል ለማክበር ስለምናወጣቸው ነው። አናከብራቸዋለንን እንጂ አልከበርንባቸውም። ሥራ ላይ ስላላወልናቸው (ኢንቨስት) ስላላደረግናቸው ነው። ሀገራዊ ሰላምና አንድነት እውን ለማድረግ የተቆለፈባቸውን ባህላዊ ንብረቶች ከሳጥን አውጥቶ እያንዳንዱን ዜጋ በፍጥነት ማልበስን ይጠይቃል፡፡

እንደ ገና ስጦታ

ባህላዊ ወረታችን ቱባነቱን እንደጠበቀ ማደግ ዘመንና ትውልድ መዋጀት ይጠበቅበታል። አዎ! የትውልዱንና የዘመኑን ህፀፅ የሚያርም ለምፅ የሚያነጻ፣ የሚዋጅ መሆን አለበት። ዘረኝነትን ፣ ጥላቻን ፣ ቂም በቀልን ፣ ደባን ፣ መከፋፈልን ፣ ወዘተ . መቤዥ ፣ መዋጀት አለበት። ባህላዊ ንብረታችንን ይበልጥ በማጎልበት ፣ በማልማትና በማስፋት ለመጻኢ እድላችን ፣ ለነገ ተስፋችን ፣ ለእርቅ ፣ ለሰላም ፣ ለአንድነት ፣ ለሁለንተናዊ ብልፅግና ፣ ወዘተረፈ ልናውለው ይገባል።

ስኬቶቻችንን የምናወድስበት ፣ ፈተናዎቻችንን የምንሻገርበት ነገአችንን የምንተልምበት ጭምር አድርጎ ስለመጠቀም አብክረን ማሰብ ያስፈልጋል። የፍቅር ፣ የእርቅ ፣ የሰላም ፣ የአብሮነት ፣ የማካፈል ፣ የመተባበር ፣ የመተጋገዝ ፣ የመረዳዳት ፣ የምስጋና፣ ወዘተረፈ . ባህሎች፣ ልማዶች ፣ ዕምነቶች ፣ ሃይማኖቶች ከፍ ሲልም ድምር ባህላዊ ንብረቶች ባለቤት እንዲሁም የጥንታዊት ሀገር ባለቤት ሆነን አንድነትን በመከፋፈል ከሰዋን ፣ ፍቅር ከጎደለን፣ እርቅ ከገፋን ፣ ሰላም ከራቀን ፣ አብሮነትን በቀዬአዊነት ከተካን ፣ ማካፈልን በስስት ከቀየርን፣ መተባበርን በመለያየት ከለወጥን ፣ ምስጋናን በእርግማን ከተካን ፣ ወዘተረፈ . ምኑን ሙሉኡ ሆነው !?።

ባለፉት አራት ዓመታት ያለፍንባቸው ሀገራዊ ውጣ ውረዶች ፣ አሳፋሪ ድርጊቶች እውነት የእነዚህ ሁሉ መንፈሳዊና ባህላዊ ፀጋዎች ባለቤት ስለመሆናችን የሚመሰክሩ ናቸው !? በመሀላችን እየጎነቆለ ያለ ጥላቻ ፣ ቂም በቀል ፣ ልዩነት ፣ ጎሰኝነት ፣ ወዘተረፈ በአብነት ስንመለከት የደለበ ባህላዊ ወረቶች ባለቤት ካለው ሕዝብና ታሪክ የሚጠበቅ አይደለም። ስለዚህ ብርሀነ ልደቱን ከብርሀነ ልደቱ ባሻገር ሌሎች ባህላዊ ወረቶቻችንም በዕለት ተዕለት ኑሮአችን ልንኖራቸው ልንገልጣቸው ይገባል ።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You