ውልደቱን ስናስብ

 ከኢየሱስ ክርስቶስ የመወለድ ዓላማው ጋር ከሚጣጣሙ መልካም ቃሎች መካከል ‹ፍቅር ተወለደ› የሚለው ሁነኛ ገላጭ ቃል ይመስለኛል:: እንዴትም ብናስብ ልደትና ትንሳኤውን ከዚህ ለይተን ማየት አንችልም:: ግን ኢየሱስ ለምን ተወለደ? ለዛውም በከብቶች በረት. . ?::

ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው በሰው ልጆች ፍቅር አስገዳጅነት ነው:: ይህም ማለት ሞትን በፍቅር ሊሽር፣ ጥላቻን በእርቅ፣ መለያየትን በወንድማማችነት ሊቀይር ነው:: እናንተ በፈጣሪ አምሳል የተፈጠራችሁ የክርስቶስ ቤተ መቅደሶች እንጂ በዘርና በጥላቻ መንፈስ ተፈጥሮአዊ ቤተመቅደሳችሁን እንድታረክሱ አይደለም ሊለን ነው::

ደም አታፍሱ ፣ በመለያየትና በመራራቅ ተፈጥሮአዊ ማንነታችሁን አታቆሽሹ ሊለን ነው:: እንደ አንድ አማኝ ክርስቲያን ይሄ እውነት በብዙዎቻችን ዘንድ የታመነ እውነት ሆኖ በልባችን ውስጥ እንዳለ ይሰማኛል ::

በእየሱስ መወለድ በኩል ለሰው ልጅ ሁሉ ሰላም ሆኗል:: ዳግም እንዳንጣላ፣ ዳግመኛ እንዳንክድ፣ በወንድማማቾች መካከል ጠብና መገፋፋት እንዳይኖር በልደቱ መስክሮ በትንሳኤው አረጋግጦልናል:: አማኝ ነን የምንል ሁሉ ከዚህ የሥርዓት አውድ ስር ሆነን ስለሌሎች የምናስብበት ጊዜ ሊሆን ይገባል::

አሁን ባለው የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ የኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደዚች ምድር መምጣት ዋጋ ያለው ሲሆን አይታይም:: በአማኝነቱ የሚታወቀው ሕዝብ በፈጣሪ ፊት ነውር የሆነን ድርጊት በመፈጸም የልደቱን ትርጉም እየሳተ ይገኛል::

እግዚአብሄርን የሚያውቁ ልቦች የመጀመሪያ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው ፍቅር ነው:: ይሄን እውነታ ታላቁ መጽሀፍ ቅዱስ በቆሮንቶስ መልዕክቱ ‹እግዚአብሄር ፍቅር ነው፣ ፍቅር የሌለው እግዚአብሄርን አያውቅም፣ እግዚአብሄር ፍቅር ነውና› ሲል ይነግረናል::

ፍቅር በሆነ አምላክ፣ ፍቅር በሆነ ሃሳብና ጥበብ ሰው ሆነናል ታዲያ ጥላቻችን፣ መለያየታችን ከየት መጣ? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ልደቱን ካለማወቅ እና ከልደቱ በኋላ ያለውን የምድር ላይ የሰላሳ ሶስት ዓመት የፍቅር ስብከት ካለመረዳትና ብሎም በመስቀል ላይ የዋለልንን ውለታ ከመዘንጋት የመጣ ነው::

እንደእውነቱ ከሆነ መቼም ከፍለን በማንጨርሰው የፈጣሪ ውለታ ውስጥ ነን:: ውለታው በፍቅርና በይቅርታ፣ በትህትናና በወንድማማችነት የሚከፈል እንደሆነ ቢገባንም ይህን ለማድረግ ስንበረታ ግን አንታይም:: ሌሎችን በማሳደድ፣ ለሌሎች ውድቀት መንስኤ በመሆንና በእርስ በርስ መገፋፋት ውስጥ ማንም በማይችለው መጨካከን ውስጥ ነን:: ታዲያ በዚህ ከፈጣሪ በራቀ ሰውነት እንዴት ነው ውለታውን የምንከፍለው?።

ሉዓላዊነቱን ትቶ ክብር ለሰጠን ጌታ፣ ሰው አምላክ አምላክ ሰው በሆነ ጥበብ ከዝቅታችን ከፍ ላደረገን አምላክ ሌላ የምንሰጠው ባይኖር እንዴት መዋደድ ያቅተናል:: እኛ እኮ ወንድማማቾች ነን.. ብዙ ታሪክ ያጋመደን፣ እልፍ ሥርዓት ያስተሳሰረን የባህልና የወግ ድብልቆች ስለምን ፍቅር የሌለው ልብን መረጥን? የልደቱ ሚስጢር ይሄ ነው:: ፍቅር ከሌለን እግዚአብሄርን አናውቀውም:: በየዓመቱ ፍቅር ተወለደ ብለን ቤታችንን በአበባና በውዳሴ አሽሞንሙነን ብናከብረው ትርጉም የለውም::

ሌላው በጌታ መወለድ ቀን ልናውቀው የሚገባን ታላቁ ቁም ነገር የክብር ስፍራን ትቶ በከብቶች በረት የመወለዱን ሚስጢር ነው:: ታላቁ ጌታ ቤተመንግሥትንና ታላላቅ የክብር ቦታዎች ሲገቡት የማይረባውንና በዝቅታ የተሞላውን የከብቶች በረት መርጧል:: በመኳንቶችና በመሳፍንቶች በብዙ አጋፋሪዎች ፊት ምናልባትም በታላላቅ አዋጆች በኩል ሊወለድ ይችል ነበር::

እርሱ ግን ያን አላደረገም:: በዳዊት ከተማ ለሕዝብና ቤት ቆጠራ በመጡ እንግዶች በተሞላ ቤት ውስጥ ማረፊያ አልነበረም:: በሃይሉ ሁሉንም ማድረግ እየቻለ ሃይል እንደሌለው ሆነ:: በመጨረሻም በከብቶች በረት በእንስሳቶች መሀል ተወለደ:: ለምን ስንል የምናገኘው መልስ ትህትና የሚለውን ነው::

የፈጣሪ ተቀዳሚ ባህሪ ከሆኑ ቀዳማይ እውነቶች ውስጥ አንዱ ትህትና ነው:: በጸሎተ ሀሙስ እለት የደቀመዛሙርቱን እግር ሲያጥብ፣ በሆሳዕና ቀን በአህያ ውርንጭላ ተሳፍሮ ሲሄድ እናውቃለን:: ይሄ ሁሉ ትህትናን ሊነግረንና ሊያስተምረን ነው:: ሰው ከፍቅርና ከትህትና ጋር እስካልቆመ ድረስ ምንም እንደሆነ ሊነግረን በታላቅ ጌትነቱ ውስጥ ዝቅታን መርጦ ተወለደ::

እኛ የእሱ የእጅ ሥራዎች ነን:: አምሳሉ ነው ሰው ያረገን:: ሃሳቡ ነው የፈጠረን:: አባታችን በጌትነት ትህትናን ከመረጠ እኛ የማንረባው ልጆቹ ስለምን በመገፋፋትና በጥላቻ ቆምን? ገና ወይም የጌታ መወለድ አሁን ባለው የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ሊገለጥ የሚገባው እንዲህ ባለው ጥያቄና መልስ ውስጥ ነው:: ፍቅር ተወለደ ብለን ስንናገር ዝም ብሎ መሆን የለበትም:: የመወለዱን ዓላማ ወደሕይወታችን አስገብተን ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም በመኖር መግለጥ አለብን::

ዓለምን ለመፍጠር ከተጠበበው ጥበብ ሁሉ እኛን ለማዳን የተጠበበው ጥበብ እንደሚልቅ የኃይማኖት ሊቃውንቶች ይናገራሉ:: የዓለም አፈጣጠር በራሱ ከሰው የማሰብ እና የመረዳት አቅም በላይ የሆነ ነገር ነው:: እኛን ለማዳን የተጠበበው ጥበብ ከዚህ እውነት ሲልቅ የተከፈለልን መስዋዕት ምን ያክል እንደሆነ ማሰቡ አይከብድም::

ለሞተልን ደግሞም ሞትን አሸንፎ በአብ ቀኝ ላለው ጌታ የተመቸን ልንሆን ይገባል:: ደም እያፈሰስን፣ ከወንድሞቻችን ጋር ሆድና ጀርባ ሆነን ገናን ብናከብረው፣ ትንሳኤውን ብንዘክረው ትርጉም የለውም::

በአጭሩ የገና በዓል የሞተልንን ጌታ በግብር፣ በሃሳብ የምንመስልበት የእርቅና የተሀድሶ በዓል ነው:: በአንድነትና በፍቅር በይቅርታም የምንተቃቀፍበት የይቅር ለእግዜር ሰሞን ነው:: በአጠቃላይ ከቂም የምንሽርበት፣ ከጥላቻ የምንጸዳበት በአዲስ መንፈስ ወደ ነገ የምናገድምበት የመሻገር በዓላችን ነው::

ቴልጌልቴልፌልሶር (ኩሻዊው ባለዘውድ)

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You